በድርብ አኻዝ በከፍተኛ ፍጥነት ዕድገት ላይ ነች እየተባለ ሲደሰኮርባት በነበረችው አገር በቅርቡ ይፋ የተደረገ ጥናት እንደጠቆመው ሰላሣ ስድስት ሚሊየን የሚጠጉ ህፃናቶቿ ዘርፈብዙ በሆነ መልኩ ድሃ መሆናቸው ተነገረ። ይህም ማለት ህፃናቱ ለመኖር የሚያስፈልጓቸው መሠረታዊ አገልግሎቶችን እንኳን ማግኘት ብርቅ ሆኖባቸዋል ነው ጥናቱ ያለው።
በኢትዮጵያ ከ18 አመት በታች ከሆኑት ከ41 ሚሊየን ውስጥ 36 ሚሊዮኑ በድህነት ውስጥ እንዳሉ የስታቲስቲክ ኤጀንሲ እና ዩኒሴፍ ጥናት አስረድቷል።
ጥናቱ በተለያዩ ዘጠኝ ክፍሎች ተለይቷል። ድህነቱ በዕድገት፣ በምግብ፣ በጤና፣ በውሃ፣ በንፅህና እና በመጠለያ ሲሆን ሌሎቹ የድህነት መለኪያ መስፈርቶች ደግሞ ትምህርት፣ ከጤና ጋር በተያያዘ በቂ ዕውቀት፣ መረጃና ተሳትፎን የሚጨምር ነው ተብሏል።
በጥናቱ እንደተገለጸው 88 በመቶ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ18ዓመት በታች የሆኑት (36 ሚሊዮን) ልጆች ከዘጠኙ መለኪያዎች በተለይ በመጠለያና በንጽህና ጉዳይ ከፍተኛ ዕጥረት ያለባቸው እንደሆነ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ከኢትዮጵያ የጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ አንጻር በገጠር የሚኖሩት በከፍተኛ ሁኔታ የችግሩ ሰለባ መሆናቸውን ነው ጥናቱ የጠቆመው። ይህም ማለት በገጠር ከሚኖሩት 94 በመቶ የሚሆኑት ዘርፈብዙ በሆነው ድህነት የተጠቁ ሲሆን በከተሞች ግን ቁጥሩ 42 በመቶ ነው ተብሏል።
በክልል ደረጃ ከታየ በአዲስ አበባ ያለው የህጻናት ድህንት መጠን 18 በመቶ ሲሆን በአፋር፣ በአማራና በደቡብ ሕዝብ 91 በመቶ፣ በኦሮሚያና በሶማሊ 90 በመቶ ሲሆን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ደግሞ 89 በመቶ በዘገባው ተጠቅሷል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ሁሉም መሠረታዊ መሥፈርቶች የተሟሉላቸው ህጻናት ቁጥር 1 በመቶ መሆኑን ዘገባው አትቷል።
ይህንኑ የከፋ የህፃናቱን ድህነት ለመቀነስና መላ ለማለትም መንግስት የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና የሚመለከታቸውም በሙሉ ጉዳዩ በጣም ትኩረት የሚያስፈልገው እንደሆነ አውቀው በርትተው መሥራት እንዳለባቸው ጥናቱን ያወጣው ድርጅት አስረድቷል።
ጎልጉል፤ የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply