
በአባቱ ወንበር ላይ ሳሎን ተቀምጦ
በባዶ ግድግዳ ተግ ብሎ አፋጦ
የፊቱን ሁኔታ እየለዋወጠ
ትካዜ ተጭኖት ቃላት እያማጠ
ዓይኑን አጨንቁሮ እየመረመረኝ
እንደዚህ እያለ አባቱን ነገረኝ
አባቴ…
አባባ ኤጭ! አለ ፊቱን አጨማዶ
ሁሉን ነገር ጠልቷል ውስጡ ሆኗል ባዶ
በምሬት ኮምትሯል …
በጥላቻ በግኗል …
አስሬ ኤጭ! ይላል
አባባ ኤጭ! አለ እንደገና ደግሞ
በሳሎኑ መሀል ተገትሮ ቆሞ
እንደገና ደግሞ ቁጭ አለ አንገት ደፋ
ካፍጫው አወጣ እምቅ አየር ተፋ
ኤጭ! አለ እንደገና ተነሳና ቆመ
ሽቅብ አንጋጠጠ ጣሪያው ላይ ቆዘመ
የአባባን ንዴት ይቺን አላውቃትም
ከወትሮው ተለየች ብዙ አልወደድኳትም
አባባ አሳዘነኝ አዝኜም ፈራሁት
ምን ሆንክ? አይባልም በንዲህ ያለ ንዴት
አባባ ዓይኑ ቀላ ስሩ ተገተረ
በአንድ ጊዜ አረጀ ሀያ ዓመት ጨመረ
እንደዛ ሆነብኝ
አባባ አሳዘነኝ
አዝኜ ዝም አልኩት
ከድሮው ጨምሬ ደርቤ ፈራሁት
አባባ ምን ነካው …?
እንዴት ልጠይቀው ?
ዓይን ዓይኑን እያየሁ
ብዙ ተቀመጥኩኝ በዝምታ ቆየሁ
ሲመሽ ወደ ማታ ልሄድ ተነሳሁኝ
ዝምታዬን ላፈርጥ ከቤቱ ወጣሁኝ
ዝምታን አፈረጥኩ …
አባባን ረሳሁ መልካም ቀኔን አደስኩ
ቢራን የፈጠረ – ይመቸው ተባለ
ተበላ ተጠጣ ጨዋታ ቀጠለ
በጨዋታ ፈካሁ
በቢራው ወረዛሁ
እስከ ፍጥርጥሩ ሁሉንም ረሳሁ
ቢራው አበቃና አልኮል ተጀመረ
አገር ቀውጢ ሆነች ለጉድ ተጨፈረ
እኩለ ለሊት ላይ መጠጥ እያገሳሁ
ዝምታን ደፍጥጨ ሁሉን እንደረሳሁ
ስካሬን አዝዬ እቤቴ ስመለስ
ከሳሎን ገብቼ መብራቱን ስለኩስ
አባባ ጉድ ሰራኝ ኤጭ! እንዳለ ሄዷል
የጠላትን ሕይወት ጥሏት ተሰናብቷል
አባቴን ጠየኩት
ምነው? አባባ አልኩት
በሕይወት ፈርቼ በሞቱ ደፈርኩት
እያለ አወራልኝ
አባቱን ነገረኝ
ሀዘኑ በረታ ጓደኛዬ ከፋው
አይኖቹ ወረዙ እንባ ፊቱን ሞላው
ምነው ባልወጣሁኝ ባልሄድኩኝ እያለ
አባቱን አስታውሶ በቁጭት ከሰለ
እንዴት አይዞህ ልበል ፍራት ፍራት አለኝ
መልኩ ተለወጠ አባቱን መሰለኝ
ኤጭ! አለ እንደ አባቱ ኤጭታውን ጠላሁ
አሳዘነኝ ጓዴ አዝኔ አይዞህ ፈራሁ
እንደገና ቆመ አጨማዶ ፊቱን
ይንጎራደድ ጀመር ዙርያውን የቤቱን
ልክ እንደነገረኝ
ልክ እንዳወራልኝ
በሁሉም ነገሩ አባቱን ቢመስለኝ
ትቼው መሄድ ፈራሁ – ማደሩም ቀፈፈኝ።
Leave a Reply