የእግር ኳስ ጨዋታ ለኢትዮጵያዊያን ከረጅም ርቀት ሩጫ ውድደር ጋር ከፍተኛ ቦታ የያዘ ነው። በእድሜያችን ገፋ ላልነው፤ የነመንግሥቱ ወርቁ የኳስ ጥበብ፤ የኢታሎና ሊቻኖ . . . ኧረ ስንቱን በትዝታ ዓለም መጎብኘት ይቻላል። ብቻ ለሁሉም ያንን እንዳስታውስ ያደረገኝ፤ በዛሬው ዕለት ከቤቴ ተቀምጨ ያየሁት የኢትዮጵያ ቡድንና የዛምቢያ ቡድን ጨዋታ ነው። ቡድናችንን በሀገራችን ካለው ዘረኛ አገዛዝ ነፃ አውጥቶ ለብቻው ማየት መቻል ከባድ ነው። ነገር ግን አደረግነው። ስንደቅ ዓላማችንን እንኳ በመሐከሉ ላይ ያስቀመጠውን ጉድፍ ረሳነው። የዘረኛውን የስንደቅ ዓላማ ጉድፍ ለዚች ቀን ከሰንደቅ ዓላማችን ላይ ተሰቅሎ ሲውለበለብ ዝም ብለን ዓየን፤ ትኩረታችን በተጫዋቾቻችን ላይ ነበርና።
ከጎኔ ሆነው የባራክ ኦባማን የፕሬዘዳንትነት ምርጫ ስነ ሥርዓት እያዩ ሲጯጯሁብኝ፤ ኮምፒውተሬን ይዤ ክፍሉን ለቀቅኩላቸው። ለነገሩ እነሱን አማሁ እንጂ፤ እኔ እግሮቼን እንደ ተጫዋቾቹ ሳፈራግጥና አቀብለው እያልኩ ስጮህ፤ የበለጠ በጥባጭ ነበርኩ። በስድሳ ሰባተኛው ደቂቃ ላይ፤ አዳነ ግርማ ግብ ሲያስቆጥር፤ የቤቱን ጣራ አነቃነቅሁት። ያለሁበትን አላቋጠርኩትም። ዓይኖቼን ጨፍኜ ነበር። ከመቀመጫዬ መነሳቴ ትዝ ይለኛል፤ ተነስቼ ምን እንዳደረግኩ ግን አላስታውስም። ለአንድ ቀን፤ ባንድ ጊዜ፤ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪቃና እዚሁ ካለሁበት ሀገር፤ ከሶስቱም ቦታ ተገኘሁ። አንድም ሶስትም ሆንኩ። ከተጫዋቾቹ ጋር በሜዳው፣ ከተመልካቾቹ ጋር በስታዲየሙ፤ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ኢትዮጵያ ተገኘሁ። ዓይኖቼን ስገልጥ እንኳን ደስ አልህ የሚለኝና የምለው ፈለግሁ፤ አልተገኘም። ደስታዬን ግን ቅንጣት አልቀነሰብኝም። ተጫዋቾቹ የኢትዮጵያን ሕዝብ ነበር የወከሉት። ተጫዋቾቹ ኢትዮጵያን ነበር የወከሉት። ተጫዋቾቹ ለሀገራቸው ነበር የተጫወቱት። ተመልካቾቹ ለሀገራቸው ነበር የጮሁት።
የነገዋ ኢትዮጵያ ያማረች ትሆናለች። አሁን ያለንበት የፖለቲካ ሀቅ ውጥንቅጡ ብዙ፤ የደፈረሰና መያዣ መጨበጫ የሌለው ቢሆንም፤ በኢትዮጵያዊነት ላይ ምንም ብዥታ የለንም። ደስ ብሎኛል። ለወደፊት የምትመጣዋን ኢትዮጵያ እንዳይ ረድቶኛል።
ሰኞ ጥር ፲፬ ቀን ፳ ፻ ፭ ዓመተ ምህረት
(ፎቶ፡ በጸሐፊው የተላከ)
Oumer says
Egnam des blonal