ወደ ነበረው የአባቶቻችን ፍቅርና አብሮነት እንመልከት!
የትግሬ-ወያኔ የሚያራምደው ዘርን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ፣ የቋንቋ ልዩነት ያላቸውን ሰዎች ብቻ ሳይሆን፣ ከተለያዩ ነገዶች የተወለዱ እህታማቾች፣ ወንድማማቾች እና አንድ አካልና አምሳል የሆኑ ባልና ሚስቶችን እያለያየ እንደሆነ ባለፉት 26 ዓመታት የታዘብነው ጉዳይ ነው። ወያኔ ይህን ቋንቋን መሠረት ያደረገ የማለያየት ሥራ የሚሠራው ደግሞ፣ አንዳንድ የዋሆች እንደሚሉት ለነገዶችና ጎሣዎች ዕኩልነት አስቦ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያን የማፍረሻውና ለዘመናት ሲያልሙት የኖሩትን የትግራይ ረፐብሊክ ለመመሥረት አቋራጩና ቀላሉ መንገድ ይህ ሆኖ ስላገኙት ነው። «አባቶቻችን፣ ሁልህም ወደ ወገነህ ተጠጋ ቢባል፣ ዳዊት ወደ ቁርበት፣ አክንባሎ ወደ በረት ተጠጋ» ያሉት ኅይው ሆኖ፣ የተፋቀው፣ የለሰለሰው፣ በአያሌ ቀለሞች የተዋበው፣ ውብና መንፈሣዊ ሥዕሎች፣ ፊደሎች ያረፉበትን ከመደበኛው ቁርበት በብዙ መንገድ የሚለውና ማንነቱን በሌላ ዳዊት በሚል የተካው ቁርበትን ፍለጋ መሄድ፣ ከጭድ፣ ከገለባ፣ ከውኃና ከዋልካ አፈር ጋር ተለንቅጦ ማንነቱን በባዙ መልኩ የቀየረው አክናባሎ ወደ በረት ገብቶ አዛባና እበት ፍለጋ መውረዱ ለጤና እንዳልሆነ መገንዘብ አይገድም። ዳዊት ተመልሶ የቁርበትን ባሕሪይ ሊላበስ አይችልም። ቁርበት ግን ተዘፍዝፎ፣ ለፍቶና ታሽቶ ወደ ዳዊትነት የመለወጥ ዕድሉ ሠፊና የሚጠበቅም ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ፣ አክንባሎ የአዛባን ወይም እበትን ባሕሪይ ሊይዝ ከቶ አይቻለውም። እበት ወይም አዛባ ግን ከዋልካ አፈር፣ ጭድና ገላባ ጋር ተዋህዶ ወደ አክንባሎ የመለወጥ ዕድሉ የሠፋ ነው።
በተመሣሣይ ሁኔታ ላለፉት ሦስት ሺ ዘመናት በተፈጥሮ ሳቢና ገፊ ኃይሎች፣ በፍልሰት፣ በንግድ፣ በጦርነት፣ እና በጋብቻ ኢትዮጵያዊ ማንነትን የተላበሱ፣ የተዋለዱና የተዛመዱ ነገዶችን ወደ አንድ ነጠላ ነገድ ማንነት ለመመለስ አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን፣ የሚቻል አይደለም። ይህን ስንል በኃይል አስገድዶ አንዱን እንዲመርጥ ማድረግ አይቻልም እያልን አይደለም። በኃይል ማንነትን የማስለወጥ ተግባር ደግሞ ዘለቄታ ይኖረዋል የሚባል እንዳልሆነ ግልጽ ነው። በዘመነ ወያኔ ሰዎች ተገደው የወላጆቻቸውን የአንዱን ትተው የሌላውን በተለይም ጥቅም ይገኝበታል ያሉትን እየመረጡ እንደሆነ እያየን ነው። ይህ ግን ያ ሰው ኢትዮጵያዊ ማንነቱን ፈጽሞ አጥቶ የነጠላ ነገድ ማንነትን ተላበሰ ማለት አይቻልም። ልክ ዳዊት እበት ወይም አዛባ እንዳልሆነ ሁሉ፣ በኃይል ኢትዮጵያዊ ማንነቱን ወደ ነጠላ ነገድ ማንነት እንዲለውጥ የተገደደ ሰው፣ የነጠላው ማንነቱ ይዋሐዳዋል አይባልም። ድርብ የነበረው ማንነቱ ነጠላ እንደሆነ ይሰማዋል። የሰው ልጅ ፍላጎት ደግሞ ከነበረው የተሻለ እንጂ፣ ያነሰን አይመርጥም። በዛሬዋ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ነገዶች የተወለዱትን ኢትዮጵያውያን፣ ነገዳችሁ የአባታችሁ ነው ወይም የእናታችሁ ነው ተብለው አንዱን ወደውም ሆነ ተገደው ቢመርጡ፣ በውስጣቸው የአባታቸው ወይም የእናታቸው ዘርና ስሜት ፈጽሞ ሊጠፋው አይችልም። ይህም የነጠላ ነገዶች ማንነት በማምረት፣ በማከፋፈልና በመጠቀም ሂደት የወል ማንነቶችን በመላበስ ኢትዮጵያዊ ማንነትን የሚያጠናክሩ እንጂ፣ የነጠላውን ነገድ ማንነት እያጎሉ የሚሄዱ እንዳልሆነ የዓለም ማኅበረሰቦች ዕድገት ሂደት በሚገባ አሳይቷል።
ይህ ሂደት ወደፊትም ይቀጥላል። በመሆኑም ዛሬ ወያኔ በተራዘመ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በደስታ በመከራው፣ በሰላም በጦርነቱ፣ በሠፈራ በፍልሰቱ ተዋሕደውና ተለንቅጠው አንደ ዳዊቱ፣ እንደ አክንባሎው አንድ የወል ኢትዮጵያዊ ማንነትን የተላበሱ ሰዎችን ወደ አንድ ነጠላ ማንነት የኋሊት ለመመለስ የሚደረገው ጥረት ግብ፣ ኢትዮጵያን ማፍረስና የትግራይን ረፐብሊክ መመሥረት እንደሆነ መጠራጠር አይቻልም።
የትግሬ ወያኔ ኢትዮጵያን አፍርሶ፣ «ታላቋን የትግራይ ረፐብሊክ» ለመመሥረት ባለፉት አራት አሥርተ ዓመታት፣ ለምትገነጠለው ትግራይ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና ባሕላዊ መሠረት የሆኑ ሥራዎችን በኢትዮጵያ ሕዝብ አንጡራ ሀብት ገንባቷል። ትግራይን በኢንዱስትሪ የበለጸገች ለማድረግ የጨርቃጨር፣ የመድኃኒት፣ የብረታብረት፣ የስሚንቶ፣ የምግብ፣ ግዙፍ ፋብሪካዎችን ገንብቷል። በሁሉም አውራጃዎች፣ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ተከፍተዋል። ሁለት ታላላቅ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያዎች ተገንብተዋል። መቀሌን ከሱዳንና ከጂቡቴ የሚያገናኝ የባቡር ኃዲድ በመገንባት ላይ ይገኛል። በሁሉም ቀበሌዎች የአንደኛና የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተሠርተዋል። ሁሉም የትግራይ ቀበሌዎች ክረምት ከበጋ የሚያገናኙ አውራ ጎዳናዎች ተሠርተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው። ትግራይ ከማዕከላዊ መንግሥት ውጭ በቀጥታ ከተለያዩ መንግሥታት ጋር የውጭ ግንኙነት ያደርጋል። የአገሪቱ መከላከያ ኃይል ጠቅሎ ትግራይ እንዲገባ ተደርጓል። የአየር ኃይል ከደብረዘይት ነቅሎ መቀሌ ገብቷል። የአገሪቱ የመረጃ ማዕከል ከአዲስ አበባ ተነቅሎ መቀሌ ገብቷል። የአገሪቱ የቱሪስት መስብህ የሆኑ ቅርሶች በሙሉ ተለቅመው አክሱም ተወስደዋል። የዚህ ሁሉ ዝግጅት የመጨረሻ ግቡ ትግራይን ለመገንጠል መሆኑ ግልጽ ነው።
ወያኔ ትግራን ገንጥሎ ወደ ጉሬው ሲገባ፣ በሰላም ለመኖር እንደማይችል ያውቃል። ከመሐል ኢትዮጵያ የወሰደውን ወስዶ፣ ያወደመውን አውድሞ ትግራይ በሰላም እኖራለሁ ብሎ ያሰበው፣ በዘር ጠላትነት የፈረጀውን የዐማራ ነገድ ከሌሎች ነገዶች ጋር እሣትና ጭድ በማድረግ፣ እነርሱ እርስ በርሳቸው ሲተላለቁ ወያኔ የኔ የሚለውን በመደገፍ፣ ጠላቴ ያለውን ማጥቃት የሚለውን ስትራቴጂ በማራገብ መሆኑን አጢኗል። ለዚህም ባለፉት 26 የአገዛዝ ዘመኑ ዐማራውን ከሁሉም ነገዶች ጋር በማጋጨት ነጥለው እንዲመቱት አድርጓል። የዐማራውና የኦሮሞው ነገዶች በደም ጠላትነት እንዲተያዩ የመለያየት ሥራ ሠርቷል። በታሪክ ያልተፈጸመ ድርጊትን፣ የተስፋየ ገብረዐብ የምናብ ውጤት የሆነውን የ«ቡርቃ ዝምታ» ልብ ወለድ መጽሐፍ መሪ ተዋናያን የሆነውን «አኖሌን» በሀውልትነት እንዲቆም አድርጓል። በዚህም በሁሉም አየገሪቱ ክፍሎች በሚኖሩ ዐማራዎች ላይ የዘር ማጽዳትና የዘር ማጥፋት ወንጀል ተጠቂ እንዲሆኑ በመቀቀስ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ዐማራ ከምድረገጽ እንዲጠፋ አድርጓል።
ዐማራውን ከሌሎች ነገዶች ነጥሎ የማስመታቱ ተግባር ብቻውን ወያኔ ላቀደው የትግራይ ረፐብሊክ ምሥረታ ሊያዋጣው እንደማይችል ግንዛቤ ወስዷል። ከወሰዳቸው ግንዛቤዎች የሚከተሉት ይገኙበታል። የመጀመሪያው የምትገነጠለው ትግራይ ከጎረቤት አገሮች ጋር የሚያገናኛት ድንበር ማግኘትና ከመደበኛው የትግራይ ክፍለሀገር የተሻለ የተፈጥሮ ሀብት ያለው መሆን እንዳለበት ጊዜ ወስደውና አስበው ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸው አምነዋል። ለዚህም፣እኤአ በ1952 ስፔንሰር ትሪንግሀም የተሰኘው ፀረ-ኢትዮጵያ ጸሐፊ «Islam In Ethiopia» ሲል ባሳተመው መጽሐፍ የሰፈረውን ካርታ፣ በኋላም አረጋዊ በርሄ ለዶክትሬት ማሟያ ሥራው «A Political History of Tigray People’s Liberation Front(1975—1991)» ሲል ባሳተመው መጽሐፍ የሰፈረውን ካርታ፣ ማለትም ትግራይን ከአሶሳ ጋር የሚያገናኝ ካርታ ስለው በተለያዩ መንገዶች ሕዝቡን ማለማመድ እንዳለባቸው አምነው፣ ይህኑ ካርታ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የምትገነጠለው ትግራይ ምን እንደምትመስል ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሳዩ። ይህ እንግዲህ፣ «ሲሰድቡት ዝም ያለ፣ ቢመቱትም ያው ነው» የሚሉት የአባቶቻችን ቃል ሕያው ሆኖ፣ የትግሬ ወያኔዎች ምን ታመጣላችሁ በሚል ዕብሪት እኛ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ማዕካለዊ ሥልጣን ከሌለን፣ ሁልሽም የለሽም በሚል ትዕቢት ላለፉት 26 ዓመታት ሲያምታቱት የመጡትን ዕውነተኛ ማንነታቸውን በይፋ እንዲታወቅ ያደረጉበት የካርታ ሥራ ዝግጅትና የትግራይ መገንጠል አይቀሬነት ያሳዩበት አንዱ ነው።
ሌላው ምን ጊዜም የነርሱን የመገንጠል ዓላማ የሚቃወመው ኃይል ከየትም ሳይሆን፣ ከዐማራው እንደሚመጣ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ምክንያቱም ዐማራው በተፈጥሮ መልከዓምድራዊ ኩታገጠምነት የተነሳ ከትግሬ ጋር የተቆራኘ ነው። ከዚህ አልፎ ቋንቋቸው ከግዕዝ የሚቀዳ በመሆኑ ተቀራራቢ ነው። የሁለቱም ነገዶች በአብዛኛው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ነው። በዚህም የተነሳ መቀራረብ መኖሩን ስለሚረዱ፣ ይህ ቅርርብ እንዳይ ቀጥል ባለፉት 44 ኦመታት የማለያየቱን ሥራ ከመሥራታቸው ባሻገር፣ ጥቁር ደም አቃብተውታል። ይህም በሁለቱ ነገዶች መካከል የልዩነት ግንብ እንዲቆም አድርጓል። ይህ የልዩነት ግንብ በፍቅር ግንብ እንዳይፈርስ፣ የዐማራው ነገድ በብዛት በሚኖርባቸው ክፍለሀገሮች የሚገኙ የኦሮሞ፣ የአገውና የቅማንት ነገዶችን አደራጅተው ጃዝ በማለት ዐማራውን በግራ በቀኝ፣ ከፊት ከኋላ እንዲያጠቁት ሠፊ የማደራጀትና የመቀስቀስ ሥራዎች ሠርተዋል።
ከሁሉም በላይ በጎንደር ዐማራና ቅማንት ነገዶች መካከል ይህ ነው የሚባል ለመለያየትና ፊትና ጀርባ ሆኖ ለመቆም የሚያስችል ልዩነት መኖሩን የሁለቱም ነገድ ዕውነተኛ ሰዎች ባልተናገሩበት፣ ታሪካቸውም በማይመሰክርበት ሁኔታ ወያኔ ጥላቻን ግቶ ባሳደጋቸው የቅማንት ጥቂት ወጣቶች አማካኝነት የተራገበው ልዩነት ሁለቱን ነገዶች ደም ከማቃባት አልፎ በአንድ የጎንደር ክፍለሀገር ስም ለመኖር አንችልም በማለት የራሳቸው ክልል እንዲሰጣቸው ባደረጉት የወያኔ የተልዕኮ ሥራ፣ ይኸውና ቅማንትን ከጎናደር ዐማራ የሚለይ መሥመር እንዲሰመር ተደርጓል። በዚህም መሥመር መሠመር የተነሳ ከ63 ቀበሌዎች በላይ አዲስ ማንነትን ለመለማመድ ላለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ሲያለማምዱን ከቆዩ በኋላ፣ በወልቃይት ጠገዴ ማንነት ጥያቄ የተነሳው ሕዝባዊ እንቢተኝነት አድማሱን እያሰፋ ወደ ፊት በመገሥገሡ የተነሳ፣ ጭንቅ ውስጥ የገባው ወያኔ፣ የመገንጠል ዓላማውን ባሻው መልክ ሳያከናውን ጉርቦውን በመያዙ ምክንያት፣ሰሞኑን ከመነሻው ጥያቄ ያልቀረበባቸውን 12 ቀበሌዎች ወደ ቅማንት ክክል ለማስገባት ሕዝበ ውሣኔ እንዲሰጥ አደረገ። ውጤቱ ግን ወያኔ በሚፈልገው መልኩ ባለመጠናቀቁ፣ ቂም ቋጥሮ የሁለቱንም ነገድ ልጆች በተለመደው የጭካኔ ተግባሩ መግደሉንና ማሰሩን በይፋ ተያይዞታል። ወያኔ ቅምንትን ከጎንደር ዐማራ ለማፋታት የፈለገበት ዋና ዋና ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው።
- ወያኔ ከ1983 ዓም ጀምሮ በኃይል ወደ ራሱ ክልል ካጠቃለላቸው የወልቃይት ጠገዴ ወረዳዎች ጋር በማገናኘት፣ትግራይን በተፈጥሮ ሀብት ተጠቃሚ እና የሠፊ ግዛት ባለቤት ለማድረግ፣
- ከጎጃም አዊ ዞን ብሎ ከከለለው ዞን ጋር በማገናኘት ወደ ደቡብ አቅጣጫ ተስቦ፣ አሶሳ አውራጃ ጋር ትግራይን ለማገናኘት ላቀደው ዕቅዱ ተፈጻሚነትና የታላቋ ትግራይ ረፐብሊክ ምሥረታ ሠፊ መደላድል ለመፍጠር፣
- የዐማራ ክልል የተባለውን ከጎረቤት አገር ጋር ግንኙነት እንዳይፈጥር ለማድረግ፣
- የትግራይን ክልል ከሱዳን ጋር በሠፊው በማገናኘት የአገሪቱ የውኃ ሀብት እና የተፈጥሮ ደን ባለቤት ለመሆን፣
- ኢትዮጵያን በነገድ ከፋፍሎ ለማጥፋት ላቀደው ዓላማ ስኬት ማረጋገጫ የሌሎች ነገዶች ድጋፍ ለማግኘት፣
- በብአዴን የሚመራውን የዐማራ ክልል ተብየን አመራር በዐማራ ተቆርቋሪነት በመፈረጅ፣ ዕውነተኛ የዐማራ ልጆች የሆኑትን የብአዴን አመራር አባላት ከላይ እስከታች ያሉትን ነጥሎ በመምታት የትግራይ ረፐብሊክ ምሥረታን የማይቃወም የራሳቸው የሆነ አመራር ለመፍጠር፣
- የወያኔ ጥቅም አስከባሪ በቅማንት ክልል ተብየ ለማስቀመጥና የወያኔን ዓላማ ለማሳክት፣
- የወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄዎችንና የጎደር ሕዝብ እያሰማው ኢለውን የፍትሕ ጥያቄዎች ፈር ለማሳትና የትግራይን የመገልጠል ፍላጎት ለማሳካት፣
- ለዘመናት በአንድነት በኖሩት የዐማራና የቅማንት ተወላጆች ላይ ዘመን የማይሽረው የጠላትነት ስሜት ተክሎ ለመሄድና የጎንደርን ሕዝብ አንድነት ለመነጣጠል፤
- ዛሬ ቅማንት ማንነቱን አጎናጽፈነዋል፣ የራሱ ሰው ሆኗል በማለት ፕሮፓጋንዳ በመንዛት፣ ጥቂት የቅማንት ተወላጆችን ልብ በጥቅምና በተለያዩ ምክንያቶች ከሳቡና ከዐማራው ጋር ዓይንና ናጫ ከደረጉ በኋላ፣ልክ ኦነግን ከጨዋታ ውጭ እንዳደረጉት ሁሉ፣ እነዚህንም አውልቆ በመጣል፣ አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት እንዳለው፣ ነገ ጎንደር የቅማንት ነው በማለት ጎንደር ከተማን ጨምሮ ሰሜን ጎንደርን ወደ ትግራይ ለመጠቅለል ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቂያ መሆኑ ፣ እንደሆነ ልብ ልንል ይገባል።
ቅማንትን ከዐማራው የመነጠሉና ጎንደርን የመከፋፈሉ ዓላማ ግቦች ከዚህ በላይ በጥቅሉ የተጠቀሱት ናቸው። እነዚህ ደግሞ ቅማንቱ ቀርቶ ትግሬውን ይጠቅማሉ የሚባሉ አይደሉም። ቅማንቱም ሆነ ትግሬ የሚጠቀሙት በሠፊዋ ኢትዮጵያ አንድነት፣ በሁሉም ቦታዎች ተዘዋውረው ሢሠሩና ሲኖሩ እንጂ፣ እንደ ገበያ በሬ በተወሰነ ክልል ሲታጠሩ አይደለም። ሕዝብ ሠፊ ገበያና መዘዋወሪያ ቦታ ይሻል። ዛሬ የትግሬ ወያኔ እያለን ያለው ይህን ተዘዋውሮ የመሥራትና የመኖር መብታችን በነገድ ጉረኖ ውስጥ አስገብቶ ታሰሩ እያለን መሆኑን ስንቶቻችን ተገንዝበነው ይሆን?
ከሁሉም በላይ፣ በጎንደሬነታቸውና እና በማንነታቸው የሚመኩት የዐማራ እና የቅማንት ነገድ ልጆች ፣ ኅልውናቸውን አስጠብቀው፣ የኢትዮጵያን አንድነት ለማስከበር፣ ከምንጊዜውም በበለጠ አንድነታቸውንና የጥንቱን የአባቶቻቸውን የአብሮነት ስሜት በማዳበር ጎንደር የሚለው የክብርና የኩራት፣ የአንድነትና የመተሳሰብ መጠሪያ ስም ጠፍቶ በሌላ እንዲተካ ወያኔ እያደረገ ያለውን ታላቅ ሤራ ግብ አጢነው፣ ዐማራንና ቅማንትን የመከፋፈሉ ሥራ ዕውን እንዳይሆን ሊተጉ ይገባል። በየትኛውም መልኩ ቢሆን፣ አንዱን ነገድ ከፍ፣ ሌላውን ዝቅ ከሚያደርጉ የደካማ ሰዎች ዕይታ ወጥተን፣ ለትውልድ የሚሸጋገር የአብሮነትና የመቻቻል ስሜት በሕዝቡ አዕምሮ ውስጥ እንዲሰርጽ የሚያስችሉ ሥራዎችን ልንሠራ ይገባል። «በለስላሳው ምላሴ፣ ደንደሮ በላሁበት እንዳለችው፣ እንስሳ»፣ ወያኔ ካጠመደልን ክፉ የመበታተን ሥራ በድል አድራጊነት ልንወጣ የምችለው፣ እኛ ለዘመናት በአንድነት የኖርን ነገዶች፣ ክፉውን በክፉ በመመለስ ሳይሆን፣ ክፉውን በደግ፣ ጥላቻን በፍቅር፣ ጠብን በሰላም በመመለስ መሆን ይኖርበታል።
ስለሆነም የዐማራና የቅማንት ተወላጆች በሚኖሩባቸው የዓለም ክፍሎች በመቀራረብ፣ አሉ የሚባሉ ችግሮችን ወደ ፊት በማውጣት ችግሮቹን እንዴት መፍታት እንደሚቻል ሀሳብ ማመንጨት ይጠበቅባቸዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ፣ አገር ቤት ያሉት አባቶቻችን በችግሮቹ ዙሪያ መወያየት እንዲችሉ ከውጭ ያለነው ባሉት የመገናኛ መንገዶች ሁሉ በመጠቀም፣ ነገር ቆስቋሽና የወያኔ ተላላኪ የሆኑ ግለሰቦችን አደብ እንዲገዙ ማድረግ እንዲችሉ ማሳወቅና ማስተማር ለነገ የሚባል አይሆንም። በዐማራውና በቅማንቱ መጣላት የሚያተርፈው የትግሬ ወያኔ እንጂ፣ ዐማራው ወይም ቅማንቱ አለመሆኑን በተከታታይ ማስገንዘብ ቀለም ቀመስ እና አንድነትን ወደድ ከሆኑ፣የሁለቱም ነገድ ልጆች የሚጠበቅ ወቅቱ የጋረጠባቸው ጥያቄ መሆኑን አጢነው፣ ዕውቀት እና ትምህርት የችግር መፍቻ ቁልፍ መሆኑን በተጨባጭ ሊያሳዩ ይገባል።
ዐማራ ቅማንት ነው! ቅማንትም ዐማራ ነው!
በዐማራና በቅማንት መነጣጠል ጎንደር ታሪካዊ ሚናዋን እንዳታጣ በአንድነት እንቁም!
ዐኅኢድ
ማስታወቂያና ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply