ከዛሬ ሰማኒያ ዓመታት በፊት የነበሩት ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን እና እናቶቻችን፣ ከትግራይ እና ከኤርትራ ምድር በበቀሉ ባንዶች አጋዥነት በፋሽስት ጣሊያኖች ጦር ማይጨው ላይ ድል ሲመቱ «እሺ፣ አሜን፣ እንገዛለን» ብለው እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም። ራሣቸው ፋሽስቶችም እንዳመኑት፥ በተለይ በሰሜን ሸዋ፣ በጎጃም፣ በጎንደር፣ በወሎ፣ በጉራጌ፣ በጅባት እና ሜጫ እንዲሁም በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች የነበሩት አርበኞች በመረጧቸው የጎበዝ አለቆቻቸው እየተመሩ፣ ለአምሥት ዓመታት የፋሽስት ጣሊያንን ጦር ከእነ ባንዳ ግሣንግሱ መውጫ መግቢያ አሣጥተውታል። ከዚያም ከየካቲት 1933 ዓም ጀምረው ጀግኖች አርበኞቻችን ባደረጉት የተቀነባበረ የጥቃት ዘመቻ ልክ የዛሬ 75 ዓመት ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓም በቀዳማዊ ኃይለሥላሤ መሪነት በድል አድራጊነት ዋና ከተማችንን አዲስ አበባን ለመቆጣጠር በቅተዋል። ሆኖም ዛሬ ላይ ሆነን ስናየው ያ ሁሉ መስዋዕትነት ያስገኘልንን ብሔራዊ ክብር እና ልዕልና እንዲህ አሽቀንጥረን እንድንጥል ያደረገንን ምክንያት ለመገንዘብ ትልቅ እንቆቅልሽ ይሆንብናል።
የአምሥቱ ዓመት የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ በአገራችን በኢትዮጵያ ላይ ታላቅ የትውልድ ስብራትን ፈጥሮ አልፏል። ብዙ ጀግኖች አርበኞቻችን መሥዋዕት ሆነውብናል። በተቃራኒው ደግሞ ለፋሽስት ጣሊያኖች በባንዳነት ያገለገሉ አያሌ ከሃዲዎች ተፈልፍለዋል። በመሆኑም ፋሽስት ጣሊያኖች በጀግኖች አርበኞቻችን ከፍተኛ ተጋድሎ ከኢትዮጵያ ምድር ተጠራርገው ቢወጡም፣ እነርሱን በባንዳነት ሲያገለግሉ የነበሩት የእናት ጡት ነካሾች ግን ተንሠራፍተው ለመኖር በቅተዋል። ለዚህም የረዳቸው በተለይ ቀዳማዊ ኃይለሥላሤ ሥልጣናቸውን ለማደላደል ሲሉ በአገሪቱ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ አብዛኞቹን የጣሊያን ሎሌ ባንዶች በመሾማቸው ነው። በሚያሣፍር ሁኔታ ንጉሠ-ነገሥቱ ይባስ ብለው አርበኞችን እያደኑ በእሥር፣ አልፎም በግድያ ቀጧቸው። የአርበኞችን ቤተሰቦች አጎሣቆሉ። በተቃራኒው የባንዶች ልጆች በምርጥ ምርጥ የውጭ አገር ትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች እንዲማሩ አደረጉ። የተዘረጋውም ሥርዓተ-ትምህርት ተተኪውን ትውልድ ስለአገሩ እንዲያውቅ ሣይሆን የምዕራቡን ሥልጣኔ የበላይነት እንዲቀበል የሚሰብክ እንዲሆን ተደርጎ ተቀረጸ። የእነዚህ ድምር ውጤት አገሩን የማያውቅ፣ በኢትዮጵያዊ ማንነቱ የሚያፍር፣ ዐይቶት የማያውቀውን የውጭውን ዓለም የሚቀላውጥ መጢቃ ትውልድ ፈጠረ። ስለዚህ ዛሬ ላይ ሆነን ስናየው ጣሊያኖች በ1888 ዓም ዐድዋ ላይ ድል ሆነው ቢመለሱም፣ ከማይጨው ውጊያ በኋላ ግን የረዥም ጊዜ ዕቅዳቸውን እንዳሣኩ መገንዘብ ይቻላል።
ከፋሽስት ጣሊያን ወረራ በኋላ ዘመናዊ ትምህርት የቀመሰው ትውልድ፣ በወቅቱ እንደ ወረርሽኝ በመላው ዓለም በመሠራጨት ላይ የነበረው የኮሚኒስት ርዕዮተ-ዓለም ተከታይ ለመሆን ጣረ። «ያ ትውልድ» ለአገሩ ቀና ያሰበ መስሎት ጎትቶ ያመጣው ርዕዮተ-ዓለም ግን ከራሱ አልፎ የታላላቆቹን እና የታናናሾቹን ትውልዶች ቀርጥፈው የሚበሉ አምባገነን ሥርዓቶችን ፈጠረ። በዚህ ረገድ ወታደራዊው ደርግም ሆነ የትግሬ-ወያኔ ሥርዓቶች ምንጫቸው «የተማሪዎች እንቅስቃሴ» እየተባለ የሚጠራው ክስተት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በእርግጥ በአገራችን ላይ የደረሰውን እና አሁንም በመድረስ ላይ ያለውን መዓት ሁሉንም በዚያ ትውልድ የተሣሣተ የፖለቲካ አቅጣጫ ብቻ ማሳበብ ባይቻልም፣ ግዙፉን ድርሻ እንደሚወስድ ግን መጠራጠር አይገባም። ስለዚህ ዛሬ በኢትዮጵያዊነቱ የሚያፍር ትውልድ ቢፈጠር ሊደንቀን አይገባም፥ አባቱን አያውቅ፣ አያቱን ናፈቀ ተብሏልና።
ትውልድ በትውልድ ሲተካ በጎም ሆነ መጥፎ ነገሮች ይከሰታሉ። የአሁኑ ወጣት ትውልድ ያለፉት ትውልዶች ያከማቹት ጥሪት ውጤት ነው። ባንዳነት እንደ መሠልጠን እየተቆጠረ፣ በጥራዝ-ነጠቅነት ከውጪ «አዲስ መጣ» የተባለውን ርዕዮተ-ዓለም ስላነበነቡ ብቻ «አዋቂ» የሚያስብል ባህል እንዲስፋፋ እየተደረገ፣ ስለ አገር ታሪክ እና ስለ ሕዝብ ባህል ከማወቅ ይልቅ በምዕራቡ ዓለም የሚፈበረኩ ርካሽ የባህል ሸቀጦች ማራገፊያ መሆን የዘመናዊነት ምልክት ተደርጎ እየታየ፣ ዓለም በቴክኖሎጂ እየተመነደገ ሲሄድ የእኛ አገር ገዢዎች ሕዝብን በማስራብ እና በጅምላ በመፍጀት ከፍተኛ መዋዕለ-ንዋይ ሲያከማቹ እንድ ብልጠት እየተቆጠረ፣ ወዘተርፈ፤ ይህ አዲሱ ወጣት ትውልድ ከማን ያየውን እና የተማረውን የመልካም የዜግነት ምግባር እንዲያሣይ ይጠበቃል? ስለዚህ ከታሪክ ተወቃሽነት፣ ከትውልዱም ፈፅሞ መጥፋት እንድንድን በአንድነት ለትክክለኛው ኢትዮጵያዊ ማንነታችን ልዕልና እንነሣ!
ኢትዮጵያ በጀግኖች እና ቆራጥ ልጆቿ መስዋዕትነት ለዘለዓለም ፀንታ ትኖራለች!
Leave a Reply