
ከብር ኖት ለውጡ ጋር በተያያዘ በአማካኝ በቀን ከ16 ሺ 700 በላይ ሰዎች አዲስ የሒሳብ ደብተር እንደሚከፍቱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታወቀ። በየእለቱ በአማካኝ ከ351 ሚሊዮን ብር በላይ ወደ ንግድ ባንኩ ገቢ እንደሚሆን ገለጸ።
የባንኩ የኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ የአብስራ ከበደ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ የብር ኖቱ መቀየሩ በባንኮች የሚቆጠበውንም ሆነ የሚቀመጠውን ብር ሆነ የደንበኞችን ቁጥር ያሳድጋል።
ባንኩ ከ5ሺ ብር በላይ ለቅያሬ ይዘው የሚመጡ ሰዎች የቁጠባ ደብተር እንዲከፍቱ እያደረገ መሆኑን አመልክተው ፣ የቁጠባ ሒሳብ ደብተር የሚከፍቱ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን አስታውቀዋል።
በቀን በአማካኝ ከ16ሺህ 700 በላይ ሰዎች የቁጠባ ሒሳብ እንዲከፈቱ ጠቁመው ፣ የቁጠባ ሂሳቡ በየእለቱ ከ351 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንደሚሆን አስታውቀዋል። በቀጣይም የተገልጋዩ ቁጥር እንደሚጨምር ጠቁመዋል። ገንዘብን ቤት ማስቀመጥ በርካታ ችግሮችን ሊያስከትል እንደሚችል አመልክተው ፣ በባንኮች ማስቀመጥ ራስን ከመታደግ አይተናነስም ብለዋል።
ብሔራዊ ባንክ ውክልና የሰጣቸው 36 ገንዘብ አከፋፋይ ቅርንጫፎች እንዳሉም አስታውቀው፣ በነሱ በኩል ከ1600 በላይ ቅርንጫፎቹን ሊያዳርስ በሚችል መልኩ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። ገንዘብ የማዳረሱ ሥራ ከፍተኛ ጥንቃቄን እንደሚጠይቅ ተናግረው፣ ቅርንጫፎቹ ባሉበት ሁሉ በመድረስ ለመስራት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የብር ኖት ለውጡ በየቀኑ የሚከናወን በመሆኑ ምን ያህል ቅያሬ እንደተደረገ ለመግለጽ ልዩነቶች ይኖሩታል ያሉት አቶ የአብስራ፣ በዚህም ከሦስት ቀን በፊት በነበረ መረጃ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ16 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ከብሔራዊ ባንክ ተቀብሎ ለለገንዘብ አከፋፋይ ቅርንጫፎቹ እንዳስረከበ አስታውቀዋል። ቅርንጫፎቹም ትናንትን ጨምሮ የማከፋፈሉን ሥራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ አቶ የአብስራ ገለጻ፤ ህብረተሰቡ አዲሱን የብር ኖት መቀየሩ ብቻ በቂ አይደለም። ለውጡን ፈጽሞ ወደነበረበት አሰራርም መመለስ የለበትም። ደንበኞች የተለያዩ የቁጠባ ሒሳቦች በመኖራቸው ገንዘባቸውን በባንኮች በማስቀመጥ አገራቸውንም ሆነ ራሳቸውን ከአደጋ ሊጠብቁ ይገባል ብለዋል ።
በተለይም ገንዘብ በቤታቸው የሚያስቀምጡ ሰዎች ትልቅ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። በተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች ብዙ ንብረቶች እየጠፉና እየወደሙ ናቸው። ከዚያ በተጨማሪም ለዘረፋ የሚዳረጉበት ሁኔታም ሰፊ ነው። ለመጭበርበርም በር ይከፍታል። እነዚህንና መሰል ችግሮች እንዳይደርስባቸው ገንዘባቸውን በባንክ ማስቀመጡን ልምድ ሊያደርጉ እንደሚገባ አመልክተዋል::
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ1 ሺ 600 በላይ ቅርንጫፎች፤ ከ100 በላይ ንዑስ ቅርንጫፎችና ከ25 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች አሉት። ከ5 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ኤትኤም ካርድ፤ ከ 4 ነጥብ 25 በላይ ደግሞ የሞባይል ባንክና ከ3ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የሲቢኢ ብር ተጠቃሚዎች እንዳሉት ከባንኩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። (አዲስ ዘመን መስከረም 18/2013)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply