
የኢትዮጵያ መካለከያ ሠራዊት ቅዳሜ በሰጠው መግለጫ በከሃዲው ጄነራል ምግበይ ይመራል የሚመራው “አርሚ 1” የተባለ ኃይል ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን በይፋ አሳወቀ።
መግለጫውን የሰጡት የመከላከያ ሚኒስቴር የሠራዊት ግንባታ ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ ሲሆኑ የኢትዮጵያ ሰራዊትን ግዳጅ አፈጻጸምና ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ህወሓት ህፃናትን አሰልፎ በአማራ ክልል ወረራ መፈፀሙን ያነሱት ሌ/ጄነራል ባጫ የቡድኑ ፍላጎት ኢትዮጵያ የምትባልን ሀገር መበታተን ነው ብለዋል።
ህወሓት ስልጠና ያልወሰዱ ህፃናትን ወደ ጦርነት በመማገድ ላይ ነው ሲሉም አክለዋል። የትግራይ ወጣቶችን ከተቻለ ሁለት ቀን አሰልጥኖ አንድ ጠመንጃ ለአምስት ሰጥቶ ወደግምባር ካስገቡ በኋላ መሪዎቹ ውጊያውን ስለሚያውቁ ተኩስ ሲበዛባቸው ወደኋላ የሚሸሹትን እንደሚገድል ነው የገለጹት።
ሌ/ጄነራሉ በመግለጫቸው፥ ህወሓት በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ወጣቶችን አሰልፎ በ4 አርሚ ራሱን በማደራጀት በአማራ ክልል የሚያደርገውን ወረራ እንደቀጠለ ጠቁመዋል።
በ4 አርሚዎች ካደራጃቸው ኃይሎች መካከል አንደኛው በጀነራል ምግበይ የሚመራ ሲሆን ይህ ኃይል አርሚ 1 ተብሎ የሚጠራ እንደሆነ አስረድተዋል።
ሌ/ጄነራል ባጫ፥ ይኸው ኃይል በሁመራ አካባቢ አደርቃይ እና ማይ ፀብሪ አካባቢ ደባርቅንና ዳባትን በመቁረጥ ጎንደርን በመያዝ ከዚያ በኋላ ሁመራን ነፃ ለማድረግ ቢንቀሳቀስም ሙሉ በሙሉ ተደምስሷል ብለዋል።
በ3 ክፍለ ጦሮች የተደራጀው ይህ የአሸባሪ ኃይል በእያንዳንዱ ክፍለ ጦር ስር ሶስት ኮሮችን ያቀፈ ሲሆን ሰሞኑን በተደረገ ውጊያ ከ5 ሺ 600 በላይ ሙት ከ2 ሺ 300 በላይ ደግሞ ቁስለኛ ሲሆኑ፣ 2 ሺ አባላቱ ተማርከው ቀሪዎቹም ተበታትነውበታል።
በዚህም ህወሓት ወደሱዳን ለመውጣት ያቀደው ሙከራ ሳይሳካለት ቀርቷል፥ ሙሉ በሙሉም ተዘግቶበታል ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በሜ/ጀነራል ዮሐንስ ወ/ጊዮርጊስ የሚመራ አርሚ 2 የተባለ ሃይል በጋሸና ከክምር ድንጋይ ጀምሮ በተደረገ ውጊያ ሁለቱ ክፍለጦሮች እንደተደመሰሱበት፤ በውጭ በብ/ጀነራል ፍስሃ የሚመራ እና የሰለጠነ አርሚ 3 የሚባል ኃይል በሽንፋ በኩል ከቅማንት ቅጥረኛ ቡድን ጋር በመተባባር ጥቃት ቢሰነዝርም ተደምስሷል የተረፈውም ወደመጣበት ተመልሷል ብለዋል።
“ይህ ሃይል በተለይ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ስራ ለማስተጓጎል ቢያስብም እቅዱ በጀግናው ሃይላችን ተደምስሷል” ብለዋል ሌ/ጄነራል ባጫ።
አሸባሪ ቡድኑ እየደረሰበት ያለው ኪሳራ በጣም ብዙ ነው ያሉት ጄነራል ባጫ በተለይ የትግራይ ወጣቶችን እያስጨረሰ መሆኑን ገልጸዋል።
ጦርነቱ በተደረገባችው አካባቢዎቸ በጣምመ አስቀያሚ የሆኑ ኢሰብአዊ ድርጊቶችንና የጁንታውን የአሸባሪነት ተግባርም አይተናል ብለዋል ሌ/ጀነራሉ።
በጦርነቱ የቆሰሉትን ለይቶ በተለይ ከባድ አደጋ የደረሰባቸውን ባሉበት ገድሎ እንደሚሸሽ የገለጹት ጀነራል ባጫ ደበሌ ይህም የቡድኑን ባሕርይ ያመላከተ ነው ብለዋል።
አሸባሪው ህወሓት በከፈተው አወደውጊያ ሁሉ ሽንፈት ቢያጋጥመውም ያሰለፋቸውን ህጻናት ጭምር ለመግደል ያልሳሳ አረመኔ መሆኑን ገልጸዋል።
እያንዳንዱ የትግራይ ወጣት ነፃ እናወጣሃለን በሚሉ የጁንታ ጥርቅም አመራሮች ግድያ ህይወቱ እየጠፋ መሆኑ አሳዛኝ ነው ብለዋል ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ። (ቲክቫህ፤ ኢብኮ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply