በወልቃይት ጠገዴ ሴቲት ሁመራ ከ1.1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ሰሊጥ ምርት የሚጠበቅ በመሆኑ ያንን ለመሰብሰብ አንድ ሚሊዮን የጉልበት ሠራተኛ እንደሚፈለግ ተገለጸ።
“ከየትኛውም የኢትዮጵያ ክልል አስተማማኝ ሰላም ያለው እዚህ ነው። ለሠራተኞች እንደ ቤተሰብ ዝግጅት አድርገናል። ኑ” ሲሉ የተሰሙት አምስት መቶና ሶስት መቶ ሄክታር ሰሊጥና ማሽላ ያመረቱ ባለሃብቶች ናቸው። የዞኑ ግብርና ቢሮ ኃላፊ እንዳሉት አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሃምሳ ሁለት ሺህ ኩንታል የሰሊጥ ምርት ስለሚጠበቅ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሠራተኛ ሃይል ያስፈልጋል።
የዞኑ አርባ በመቶ በሰሊጥ ምርት መሸፈኑን ያመለከቱት የዞኑ የግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ አወቀ መብራቱ “ሰሊጥ ሲሰበሰብ በቂ የሰው ኃይልና ጥንቃቄ ስለሚሻ ይህን ባገናዘበ መልኩ አጨዳ ለመጀመር ዝግጅት ተደርጓል” ብለዋል። ከዝግጅቱ መካከልም ሠራተኞችን መቀበል ነው። ከአጎራባች ዞኖች ጋር በጋር እየተሠራ እንደሆነም አመልክተዋል።
በአማራ ቴሌቪዥን ቀርበው የተናገሩት ባለሃብቶች ዞናቸው እጅግ ሰላማዊ በመሆኑ አጨዳ ለመጀመር ለሠራተኞች ማረፊያ፣ ቀለብ፣ ትራንስፖርትና መድሃኒት ማዘጋጀታቸውን አመልክተዋል። “ሰርተን፣ ጥሩ ምርት አግኝተን፣ ራሳችንን ጠቅመን፣ ለመንግሥት የሚጠብቅብንን ከፍለን አብረን መሻሻል አላማችን ነውና መጥታችሁ ሠርታችሁ እናንተም ተጠቀሙ። እንደ ቤተሰብ ለንቀበላችሁ ዝግጁ ነን” ሲሉ ጥሪያቸውን በሚዘናጠፈውና ታይቶ በማያለቅው ማሳ ውስጥ ሆነው ጥሪ አሰምተዋል።
2014 ዓ ም የምርት ዘመን በተመሳሳይ ለሠራተኞች ቅጥር ማስታወቂያ ሲነገር የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪና 360ዎች በመቀባበል “አትመዝገቡ፣ አትሂዱ፣ ወታደር አድርገው ሊማግዷችሁ ነው” በሚል በተደጋጋሚ ቅስቀሳ ማካሄዳቸው በወቅቱ ከፍተኛ ቅሬታ ያስነሳ፣ በታሪክም የማይረሳ ጠላትነት እንደሆነ ጠቅሰው አስተያየት ሲሰጡ እንደነበር ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ “ትህነግና ኢትዮ 360 በአማራ ክልል ሰብል እንዲወድም በቅንጅት እየሠሩ ነው” በሚል ርዕስ ባስነበበው ዘገባ ጠቁሞ ነበር።
አሁን ላይ የመንግሥት ተቃዋሚ ሚዲያ እየመራ ያለው ጌታቸው ሽፈራው በወቅቱ “ኢትዮ 360 በጦርነቱ ምክንያት መሬት ጦሙን አደረ ሲል ከርሞ፣ አሁን ለሰብል ስብሰባ የሠራተኛ ቅጥር ሲወጣ የህወሓትን አጀንዳ እያራገበ በህዝብ ላይ ሌላ ጦርነት ከፍቷል” በሚል ከትቦ ነበር። ጌታቸው ሽፈራው በራሱ የማህበራዊ ገጽ ሳይቀር ባሰራጨው ሰፊ አስተያየት 360ዎች “በአንድ ዞን ሚሊዮን የስራ እድል ሲፈጠር እንዲስተጓጎል እየሰሩ ነው። አርሶ አደር ሰብል እንዳይሰበስብ ቅስቀሳ ማድረግ በህዝብ ላይ ጦርነት መክፈት ነው። ሚሊዮን ወጣት ስራ እንዳይሰራ መቀስቀስ ወንጀል ነው። ያፈጠጠ የህዝብ ጠላትነት ነው” ሲል አክርሮ ማስረጃ በማስደገፍ ተቃውሞውን ገልጾ እንደነበር ይታወሳል።
ይህ ዘገባ እስከታተመ ድረስ በግልጽ የተሰማ የተቃውሞ ቅስቀሳ ባይኖርም “ጎንደር ዓይናቸውን በሰሊጥ መሬት ላይ በተከሉ፣ ለሃጫቸውን በቦሎቄ ፍሬ ላይ በሚያዝረበረቡ፣ ወልቃይትን እንደ ድሬደዋ መስተዳድር ራስ ገዝ አድርገው ከዐማራ ሊለዩ በሚታትሩ ተውሳኮች የታጠረች፣ የተመረዘች፣ ጎንደር አሜሪካ ተቀምጠው ሳይደክሙ የሸዋና የጎጃም፣ የወሎና የጎንደር ፋኖዎችን በፍርፋሪ ዶላር ከፋፍለው 4 ኪሎ ለመግባት ቋምጠው በተጎለቱ ድልብ የተማሩ መሃይሞች ተጠርንፋ ያለችና እነዚህ ሾተላዮች ሊወገዱላት የሚገባት ናት” ሲል ዘመድኩን በቀለ (ዘመዴ) በቴሌግራም ገጹ ስለጎንደር መያዝ መስማቱን ጠቅሶ ማረጋገጫ ሳይሰጥ ለተከታዮቹ ጽሁፍ አሰራጭቷል።
ይኸው የአማራ ትግልን ከሚመሩት ወገን የአንዱ ወገን እንደሆነ የሚገልጸው ዘመድኩን በቀለ ሰሞኑንን በተከታታይ “ጎንደር ባንዳ ሆነ” በሚል ሲጽፍና የጎንደርን ዝምታ ከሰሊጥ ጋር በማያያዝ ወልቃይት ራስ ገዝ እንድትሆን የሚደራደሩ ዓይነት አድርጎ በመሳል የጎንደርን ሕዝብ እጅግ ጸያፍ ቃላትን በመጠቀም በተለይ ፈጽሞ በማይታወቅበት በባንዳነት በመፈረጅ የስድብ ይዘት ያለው መረጃ ሲለቅ ነበር።
ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ የሰላም ቀጠና መሆኑንን ጠቅሰው ኮሎኔል ደመቀ ሲናገሩ “ከመከላከያ ጋር እጅ ለጅ ሆነን እየሰራን ነው” ማለታቸውን ተከትሎ ትችት ተሰንዝሮባቸው እንደነበር ይታወሳል። ከከፍተኛ ሰቆቃ እንደተላቀቁ የሚናገሩት የወልቃይት ጠገዴ ሲቲት ሁመራ ነዋሪዎች ራሳቸውን አደራጅተው በጥብቅ ስነስርዓት ሌትና ቀን አካባቢያቸውን እንደሚጠብቁ፣ መከላከያም ያለአንዳች ስጋት የራሱን ስራ እንደሚሰራ ኮሎኔሉን የጠቀሳቸው የጀርመን ድምጽ ከወራት በፊት ማስታወቁ አይዘነጋም።
በዞኑ ከአስራ ሁለት በላይ የተለያዩ አዝርዕቶች የሚበቅሉ ሲሆን በዘንድሮው ዓመት ከሰሊጥ በተጨማሪ ከፍተኛ የማሽላ ምርት እንደሚጠበቅ ሃላፊው አስታውቀዋል። ወልቃይት ጠገዴ ሴቲት ሁመራ በአማራ ክልል እጅግ ሰፊ፣ ምቹና ለም የሆነ መሬት ያካለለ አካባቢ ነው። (ethio12)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
አብይ አህመድ says
ምን ዓይነት ዘገባ ነው? ለአንድ ሚሊየን አንድ መቶ ሺህ ኩንታል አንድ ሚሊዮን ሠራተኛ ያስፈልጋል ስትሉ ቁጥር አታውቁም ወይስ ሚስጢሩ ሌላ ነው? ይገርማል?