ከ25 ዓመታት በላይ ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል ለመጓዝ እየጠበቁ ያሉ በተለየ ፈላሻ ሙራ ተብለው የሚጠሩት ቤተ እስኤላውያን ወደ “ቅድስት አገራቸው” እንዲመጡ የእስራኤል መንግሥት ወሰነ፡፡ እስኤል እንደገቡም የአይሁድ እምነትን በተመለከተ የተሃድሶ ትምህርት እንደሚሰጣቸው ተመልክቷል፡፡
በእስራኤል ያሉ እና ሌሎች ዓለምአቀፋዊ የዜና ምንጮች እንደዘገቡት የጠ/ሚ/ር ቢኒያም ኔታንያሁ መንግሥት ውሳኔውን ያስተላለፈው እሁድ ዕለት በሙሉ ድምጽ ነበር፡፡ ይህ የአሁኑ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት የዛሬ ሁለት ዓመት እስራኤል ምንም ዓይነት ዜጋዋ በኢትዮጵያ እንደሌለ ይፋ ነበር፡፡ “ዛሬ ጠቃሚ ውሳኔ አስተላልፈናል” በማለት የተናገሩት ኔታንያሁ ውሳኔው በእስራኤል እየኖሩ ከቤተሰቦቻቸው ለተለያዩት ኢትዮጵያውያን ተስፋ ሰጪና ጠቃሚ እንደሆነ በላኩት መግለጫ አመልክተዋል፡፡
ከዚህ በፊት እስራኤል “የተስፋዋ አገር ዜጎቿን” ከኢትዮጵያ ያስወጣች ሲሆን መጨረሻ ላይ የቀሩት በተለይ ፈላሻ ሙራ የሚባሉት በ18ኛውና በ19ኛው ክፍል ዘመናት ወደ ክርስትና እንዲቀየሩ የተደረጉት ናቸው፡፡ ፈላሻ ሙራ የሚለው ስም የአይሁድን ሕግጋት የማይከተልና በግድ ወይም በፈቃደኝነት ወደ ክርስትና የተቀየረ የሚወክል እንደሆነ Jewishpress.com ባወጣው ዜና ላይ ጠቁሟል፡፡
የኤርትራ ክፍለ ሃገርን ጨምሮ ከጎንደር የመጡት 9ሺህ አንድ መቶ የሚሆኑት አይሁድ ተብለው ስለማይጠሩ እስራኤል እንደደረሱ በአክራሪ የአይሁድ ዕምነት መምህራን የተሃድሶ ትምህርት እንዲሰጣቸው የተወሰነ መሆኑን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚ/ሩ ማስታወቃቸውን የዜና ዘገባዎቹ ጠቁመዋል፡፡ ከሚሰጧቸው ትምህርቶች መካከል የአይሁድ ሕግጋት እና የጽዮናዊነት እንቅስቃሴ ታሪክ ይገኝባቸዋል፡፡ ፈላሻ ሙራዎቹ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባና በጎንደር ይገኛሉ፡፡
ጠ/ሚ/ሩ ባወጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት እነዚህ “የመጨረሻ” የተባሉት ተጓዦች በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ወደ እስራኤል ይጓዛሉ፡፡ ለዚህ በርካታ ዓመታት ለፈጀ ውሳኔ ተግባራዊነት በአሁኑ ጊዜ የእስራኤል ሸንጎ አባል የሆኑት የኢትዮጵያ ዝርያ ያላቸው እንደራሴ አብርሃም ንጉሤ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳደረጉ በዜና ዘገባው ላይ ተመልክቷል፡፡ “ለአይሁድ ሕዝብ ይህ ታላቅ ቀን ነው” ያሉት እንደራሴው “ለሺዎች ዓመታት ኢትዮጵያውያን አይሁዶች ወደ እስራኤል ለመመለስ ሲጸልዩ ኖረዋል፤ ለዓስርተ ዓመታት ደግሞ ከቤተሰቦቻቸው ተለያይተው ሲጠብቁ ቆይተዋል፤ ዛሬ ጸሎታቸው ተሰምቷል” ብለዋል፡፡
መጽሓፍቅዱሳዊ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ኢየሱስ ክርስቶስ “ቤታችሁ የተፈታ ይሆናል” ካለ በኋላ በወቅቱ የሮም ጄኔራል የነበረው ቲቶስ (ታይተስ በኋላ አባቱን ተክቶ ቄሣር ሆኗል) ኢየሩሳሌምን ከብቦ ካሰጨነቃት በኋላ በ70ዓም ቤተመቅደሱን በማፍረስ ከተማዋን በሮም ቁጥጥር ሥር ካዋለ በኋላ የአይሁድ ሕዝብ “የእግዚአብሔር ምርጥነት” በይፋ አክትሞ ክርስትና ቦታውን ወስዷል በማለት አንዳንድ የሥነመለኮት ምሁራን ይከራከራሉ፡፡ በአይሁድ እምነት መሠረት መሲሕ ገና ይገለጣል ተብሎ ስለሚጠበቅ በምሁራኑ የሚቀርበው አስተያየት ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም፡፡
የዛሬ ሃያ ዓመት አካባቢ አስቀድመው ወደ እስራኤል የሄዱት ኢትዮጵያውያን እንደ ዜጋ የለገሱት ደም ኤችአይቪ/ኤይድስ ይኖርበታል በሚል ስጋት ለበርካታ ዓመታት ሲለግሱ የነበረው ደም ሲደፋ የቆየ መሆኑ ይፋ በተደረገበት ጊዜ ከፍተኛ ቁጣን በቤተ እስኤላውያኑ ዘንድ አስነስቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከዚያ በኋላ ሁኔታዎች ይስተካከላሉ የሚል ተስፋ የተሰጠ ቢሆንም ኢትዮጵያውያኑ ከሌሎች በተለየ በድሃ የአገሪቱ ከተሞች እንደሚሰፍሩ፤ አሰቃቂ የፖሊስ ግፍ እንደሚፈጸምባቸው፤ በዘር መድልዖ በደል እንደሚደርስባቸው በቅርብ ጊዜያት የተከሰቱት ዕውነታዎች ያስረዳሉ፡፡ ሆኖም የጠ/ሚ/ር ኔታኒያሁ መንግሥት ችግሮችን እንቀርፋለን፤ ሁኔታዎችን እናሻሽላለን በማለት በተደጋጋሚ ቃል ገብቷል፡፡
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
Leave a Reply