• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

ችግራችን አጼ ምኒልክ ከሆኑ እውነቱን ተነጋግረን እኛም አርፈን ሕዝባችንን አናሳርፍ

November 6, 2019 07:17 pm by Editor Leave a Comment

የኢትዮጵያ ፖለቲካ እጅግ ያሳስበኛል፤ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለሚረከቡን ልጆችና ልጆቻቸው ጭምር ሳስብ የሀገራችን ፖለቲካ እንዳልተፈጠረ ሰው ቢታሰብ ደስ ይለኛል፤ ምክንያቱም በመኖሩ የሚፈይደው ከሌለ፡ አለመኖሩ እጅግ የሚሻል ነውና:: ነገር ግን ወደንም ሆነ ሳንወድ ተፈጥሯልና ስለእርሱ (ስለፖለቲካችን) ማሰብ ግድ እንደሚልም አምኛለሁ።

በዚህ ዓለም ያሉ ምሁራን ፖለቲካ የአንድን ሰው ሕይወት የሚነካና ሰውም ከፖለቲካ ርቆ መኖር የማይችል ፍጡር ነው ይላሉ። እውነትም ፖለቲካ ብትርቀውም ተከትሎህ ባለህበት ይነካሃል፤ ብትቀርበውም ደግሞ የበለጠ ይነካሃል። በመሆኑም ምሁራን ያሉት ትክክል ነው ብየ ማሰብን ጀመርሁ። እንግዲያስ ፖለቲካ ዝም ብንለውም፣ ብንርቀውም፣ የማይለቀንና የማይተወን ከሆነ ስለ እርሱ መነጋገርና ማሰብ ግለሰባዊም ቡድናዊም ግዴታ ነው ማለት ነው፤ በዚህ ከተስማማን ኃሳቤን ልቀጥል፦

እንደ እኔ መረዳት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ስስታም ያቦካው ሊጥ ይመስል። ሁሌ እንጀራው እየሳሳ ሳያጠግበን ይኸው ዕድሜያችንን ሙሉ፡ ሲቦካ፣ ሲጋገር! ሲቦካ፣ ሲጋገር! አንዳንዱም በምጣዱ ላይ ሲቀር! ሁሌም ግን ለቁርስም፣ ለምሳም፣ ለራትም፣ የማይበቃ እየሆነ የሚታይ ነገር ነው እላለሁ።

የአቡኪዎች ምላስና ጩኸት ግን እንኳንስ እኛ ይቅርና አፍሪካ በሙሉ ከፖለቲካ እንጀራችን ጠግቦ የሚያድር ነው የሚመስለው፤ ነገር ግን ጠብ የሚል አንድም ነገር የለም። የሚገርመው ግን በሀገራችን ሁልጊዜ የፖለቲካ ዱቄት  ተፈጭቶ ይቦካል፣ ይጋገገራልም፤ ይሁን እንጂ አንድም የሚበላ ውጤት የለም!!! አንድ ጊዜ የአንድ ጣራ የነካ የእህል በረንዳ የነበራቸው ሰው ሁሌ ሲያማርሩ የሰማቸው ሰው ምን ሆነው ነው ጌታው እንዲህ የሚያማርሩት? ሲላቸው: እከምራለሁ፣ እሸጣለሁ፣ በመጨረሻ ግን ዕዳየን እንኳ ለመክፈል እያቃተኝ ነው አሉ:: ጠያቂም ምንድን ነው ምክንያቱ ቢላቸው? ሰላቢ ነው እንጂ! ሠርቼ፣ ሠርቼ፣ ከእጄ መቼ ላፍ እንደሚያደርገው አላውቅም አሉ፤ ይባላል።

ጎበዝ! ኧረ ጎበዛዝት ጭምር! የእኛን ሀገር ፖለቲካ ሰላቢ ወይም ቡዳ በልቶት ይሆን? የፖለቲካ ነጋዴዎቻችን ሁሌም የፖለቲካ ዱቄት ይከምራሉ። ማቡካት፣ መጋገር፣ ለቅምሻ የሚሆን እንጀራው ግን የለም። እኒያ የእህል በረንዳው ባለቤት እንዳሉት የፖለቲካ ሰላቢ ይኖር ይሆንን? ካለስ የፖለቲካ ሰላቢ የተባለው ማን ይሆን? ለነገሩ አቡክቶ የሚጋግረው ራሱ ሰላቢ ቢሆንስ? ብቻ የሀገራችን ፖለቲካ ችግር ላይ ለመሆኑ እንስማማለን፤ ዛሬ ለመነጋገር የፈለግሁት ፖለቲከኞቻችን የፖለቲካ ኃሳብ አላችው ወይ? በሚለው ሃሳብ ላይ ነው። ሁላችንም ይህን ጥያቄ ብንጠይቅ ጥሩ ነው። ይህ አነጋገሬ እንዲያው በደፈናው ደህና ፖለቲካኛ በሀገሪቱ ውስጥ የለም እያልሁ እንዳልሆነ ግምት ውስጥ ይግባልኝ።

አብዛኞች ግን እውነተኛ የፖለቲካ ኃሳብ ሳይሆን ያላቸው: የነበረም፣ ያልነበረም፣ ታሪክን የቋጠረ ልብና እሳቤ ነው ያላቸው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሻለሁ። ሁሉም ማለት ይቻላል፤ ያልነበሩበትና ያልነበረ ታሪክ ጭምር አላቸው፤ እናም የፓርቲያቸው መነሻ ምክንያት እራሱ ስልጡን የፖለቲካ አስተሳሰብ ሳይሆን፣ የፖለቲካ አስተሳሰብን ቀይሮ የያዘላቸው የኃላፊ ጊዜ ታሪክና ትርክት ነው። ይህ ነገር ፖለቲከኞች ስሜትን በመኮርኮር ተከታይና ለእስትንፋሳቸው መቆያ ጊዜን እንዲያገኙ ከመርዳት ያለፈ ርባና ያለው አይመስለኝም።

በእርግጥ አብዮታዊ ፖለቲካ መነሻው አስተሳሰብና እውቀት አይደለም። አብዮታዊ ፖለቲካ ሁልጊዜም መነሻውም ሆነ መጠሪያቸው፡ የሆነ ችግር ነው ብለው የሚያስቡት አልያም ቢሆን ብለው የሚያልሙት ችግር መሆኑ የታመነ ነው። የአንዳንዶችም ደግሞ ነው ተብሎ የተነገራቸው! አልያም እንዲህ ነበር ብለው የማይወዱን ውጫዊ የሆኑ ግለሰቦችና ታሪካዊ ጠላትነትን ያበቀሉ ሀገራት የሚፈጥሩትና በየትኛውም ማስረጃ አረጋግጠህ ልታወራው የማትችለውን ነገረ- ሊጥ አቡክተው እንጀራቸውን (ለደሃው የማይወጣና የማይበላ) ይጋግራሉ።

ምንም እንኳ አብዮታዊ ፖለቲካ በአብዛኛው ብሶት መሆኑን ባንክድም ሕዝብ ከተቀበለው፣ ወንበር ካገኘ፣ ጥያቄውም መልስ ካገኘ በኋላ ግን ዛሬም ብሶትና አብዮታዊ የዓመጽ መዝሙርን ማቀንቀንን ማቆምና ወደ እድገት ተራራ ለመውጣት የሚያስችል መሰላልን ማበጀት ካልቻለ በእርግጥም ፖለቲካው በሽታ ያለበት መሆኑን በድፍረት መናገር ይቻላል።

የተደረገና የነበረ ታሪክ እንኳ ቢሆን እንዲህ ዓይነቱ ፖለቲከኛነት የሕዝባቸውን ሕይወት ለመለወጥ እንዲያመች የሚያደርግ ሳይሆን አዲስ በደልና ሞት፣ ግጭትና ሁከት፣ እንዲያገኘው ተደርጎ በታሰበ ፍልስፍና የፖለቲካ ቢሮአቸውን ይከፍታሉ፤ ሕዝባቸው የሚፈልገውን ሳይሆን እነርሱ እንዲሆን የሚፈልጉትን ነገር ብቻ ያቦካሉ፣ ይጋግራሉ፤ ከምጣዱ የማይወጣውን ፍርፋሪም ባለበት ቢሆን በልተው የፓርቲው ጋጋሪና አቡኪ የመታወቂያ ስም ያወጣሉ።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በእውነት ምን እንዲሆን ነው የሚፈለገው? ምንስ ሊያደርጉለት ነው የሚወዱት?። ከ110 ያላነሱ እንጀራ ጋጋሪዎች (ፖርቲዎች) ከምጣድ የማይወጣ እንጀራ ለመጋገርና ለፍሬ የማይበቃ ሊጥን ነው የሚያቦኩለት? ይቅርታ! እዚህ ላይ ትንሽ ስለትናንት እንነጋገር የሚል ሃሳብ ተቀስቅሶብኝ ነው ይህን ያልኩት! በሁለት መንገድ እነሆ፦

እነዚህ የማይበላ እንጀራ፣ ከምጣዱም መውጣት ያቃተውን ቂጣ፣ አቡኪና ጋጋሪ ምክንያተ – ቡኬታቸውን ሀገር እንዲያውቀው ጸሐይ እንዲሞቀው ይገባል ብየ በማሰብ ነው።

ይኸ በአጭሩ እንኳ ከአያት ቅድመ አያቶቻችን ጀምሮ እስከ እኛና የእኛ ልጆች ድረስ ኑሮውንና ሕይውቱን ብናይ ለመጣላትም ሆነ ዱላ አንስቶ ለመመታታትና ብሎም ለመገዳደል አቅምም ፍላጎትም የሌለው ሕዝብ በመሆኑ፣ ለእርሱ የሚያስፈልገው ትምህርት፣ ሥልጣኔ፣ ብልጽግና አንድነትና እኩልነት መሆኑን በመረዳት ወደፊት መሄድ እንዲችል የአቡኪና የጋጋሪ (ፓርቲ) ብዛት መቀነስ እንዲቻል ነው።

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ ወደፊት መሄድ በሚገባው ትውልድና ወደ ኋላ ሄዶ ከ100 ዓመት በፊት በነበረ ነገር ልክ በሚያስቡ ትውልዶች መካከል የተወጠረ የፖለቲካ ገመድ ነው። ገሚሱ ዓለም ደረሰበት ወደሚባለው ሥልጣኔ እንሂድ ሲል፣ ገሚሱ በአጼ እገሌ፣ በዳጃች እገሌ፣ በፕሬዘዳንት እገሌና በጠቅላይ ሚንስትር እገሌ ላይ ቅጣትና ፍርድ ለመስጠት ፊቱን ከዓለም ስልጣኔ አዙሮ፣ ለሚያደርገውም ፍርድ የታሪካዊ ጠላቶቻችንን ሰነድ ያገላብጣል።

ይኸ ነገር መቋጫ ካልተበጀለት አሁን ላለነውም ሆን በተለይ ለልጆቻችን ብሩህ ዘመን ሲባል ነገን ለማይፈልጉና ዓለምን በእነርሱ ዕድሜና እውቀት ብቻ እየለኩ የሚኖሩ ሰዎቻችንን በቃችሁ ካልተባሉ እስከመቼስ ነው በመከራ ከበሮና በእልቂት ጡርንባ ነፍሳችንን እያባነን የምንኖረው? ብሎ መጠየቅና የጋራ መፍትሄ መውሰድ ልጆቹን ከሚወድ ጤናማ ወላጅ የሚጠበቅ ጉዳይ ነው እላለሁ።

ዛሬ ዓለም ወደ አንድ መንደርነት እየተለወጠች ነው በሚባልበት ጊዜ ላይ ሆና እኛ ግን ፊታችንን አዙረን ወደ ኋላ ስንሮጥ ላየን ለስልጡኑና ከልማታቸው፣ ከትምህርታቸውና፣ ከሥልጣኔያቸው ሲያርፉ የእኛን ኋላ ቀርነት ብቻ ሳይሆን ወደፊት ለመሄድ ያለመውደድ ጠባያችንን እያዩ መዝናኛቸው እንደሚያደርጉን መገንዘብ ነበረብን።

የሀገራችን ሰው ፊደል አያውቅ ይሆናል እንጂ እውቀትስ አለው። በተለይ አልተማረም የምንለው! ስለ ፖለቲካና ፖለቲከኞች በደንብ ያውቃል፤ ነገር አልጥመው ሲል፣ የሚሰማው (የሚያደምጠው) ነገር ውሸት ነው ብሎ ካመነ እንዲህ ይላል። አንተ ፖለቲከኛ! ፟ፖለቲካህን አትንፋብኝ! ይላል፤ አይገርምም አልተማረም የምንልው ራሱ የሀገራችን ፖለቲካና ፖለቲከኛ ውሸትና ውሸተነት እንዳለበት ተረድቷል ማለት ነው።

እናም ይኼ ነገር አንድ ቦታ ለይ መቆም አለበት ባይ ነኝ። ቴሌቭዥኖቻችን፣ ራድዮኖቻችን፣ ድሕረ ገጾችና፣ ጋዜጣና፣ መጽሔቶቻችን፣ በሙሉ ሰፊ ዘገባቸው ሀገርና ትውልድ ወደፊት እየሄዱ ሳይሆን በኃላፊ ጊዜ ታሪኮቻችው እሰጥ አገባ ላይ መሆናቸውን ነው። ዋናው ጉዳይ ደግሞ ያለፉ መንግስታትና የግዛት ዘመናቸው ነው። የሚገርመው ያለፉት መንግሥታትና የግዛት ፍልስፍናቸው ልክ አልነበረም የሚሉትም ሆነ ልክ ነበረ የሚሉትም ጭምር እነርሱ ራሳቸው እያደረጉ ያለው ነገር እንዲሁ ልክ አይደሉምና ልክ ናቸው በሚባል መንገድ ላይ መሆናቸው ነው፤ እናም ‘’ሳይቃጠል በቅጠል’’ እንዲሉ አንድ ነገር ይደረግ እላለሁ።

አጼ ቴዎድሮስ፣ አጼ ዮሐንስ፣ አጼ ሚኒሊክ፣ አጼ ኃይለ ስላሴ፣ ኮሎኔል መንግሥቱ፣ አቶ መለስ፣ አቶ ኃይለማርያም ሀገሪቱንና ሕዝቦቿን በነበሩበት ዘመን አስተዳድረዋል፤ እነዚህ ሰዎች በነበሩበት ዘመንና የፖለቲካ አስተሳሰብ የሕዝብ ብዛትና ዓለም አቀፋዊ አስተሳሰብ አስተዳድረውን አልፈዋል፤ የአንዳንዶች ሥራ ክፉቱ አመዝኖ ጎድቶን ይሆናል፤ አንዳንዶቹ መልካም ነገሮቻቸው አመዝነው ጠቅመውን ይሆናል፤ ግን ላይመለሱ አልፈዋል።

ብልህ፣ ስልጡን ሕዝብና፣ ፖለቲከኛ፣ ቢኖር መልካሞችን ነቅሶ! ክፉ ያልናቸውን ለይቶ የአሁኑን ሀገርና ሕዝብ ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ የፖለቲካ ምጣዱን በቅንነትና በታማኝነት ጉልቻዎች ላይ መጣድ ይገባችው ነበር ባይ ነኝ፤ ነገር ግን አሁንም አልታደልንም! ይኸው 50 (60) ዓመታትን በማቃሰት እና በምጥ አሳለፍን፤ ዮሐንስ ናቸው፣ ቴዎድሮስ ናቸው፣ ምኒልክ ናቸው፣ ኃይለ ስላሴ ናቸው፣ መንግሥቱ ናቸው፣ መለስ ናቸው፣ ችግራችን እያልን የወገዛና የውይይት አጀንዳ አድርገን የተጠቀሱት ሰዎች ወገን ያልናቸውን ጭምር በእነርሱ ዓይንና መልክ እየሳልን የቴዎድሮስ፣ የዮሐንስ፣ የሚኒልክ፣ የኃይለ ሥላሴ፣ የመንግሥቱ፣ የመለስ ዘሮች በሚል የመለያያ አጀንዳ እየተጠመድን ብቻ ሳይሆን ተጠላልፈን እየወደቅን ነው።

በተለይ አጼ ምኒልክ የተባሉትን መሪ በተመለከተ ከፍተኛ ክርክርና ሙግት ተከፍቶ ይኸው ወደፊት መሄድን ከልክሎን ዛሬ እንኳ የምኒልክ ስምም፣ ፎቶም፣ ታሪክና ምንም ነገር መስማት የሚቀፈውና ካልሰማ የሚያመው ትውልድ ፈጥረን የኢትዮጵያን እድገት አንድ እርምጃ ወደፊት ሁለት እርምጃ ደግሞ ወደኋላ እያደረግን እንደ አህያ ሥጋ “አልጋ ላይ ሲሉት መሬት’’ እየሆነ የዓለም መሳቂያና ለራሳችንም ልጆች ማፈሪያ የሆነ ፖለቲካችንን ተሸክመን ይኸው እስከ አሁን ድረስ በጫጫታ፣ በግርግርና በጥፋት ደመና ተከበን እንኖራለን።

ዛሬ መሆን አለበት ብየ የማስበውን ነገር የሀገሬ ሕዝብ በሙሉ ቢጋራኝ ደስ ይለኛል! በተለይ በአጼ ምኒልክ ጉዳይ ላይ! አንደኛው አንጃ አጼ ምኒልክ ሀገር ዘርፈዋል፣ ህዝብ ፈጅተዋል፣ መሬት ወርሰዋል፣ ቋንቋና ባሕል አጥፍተዋል፤ እንዲውም ቅኝ ግዛት አድርገውናል! ብሎ ጦር ሲመዝ፣ በሌላኛው በኩል ደግሞ የለም! አጼ ምኒልክ ሕዝብን ነጻ ያወጡ፣ ሀገርን ያስከበሩ፣ ቅኝ ገዢዎችን የመከቱ፣ እንዲውም ኢትዮጵያዊያንን ለሥልጣኔና ለዘመናዊነት እንዲነሳሱ ማድረግ የቻሉ፣ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካና ለጥቁር ሕዝቦች አለኝታ የሆኑ ናቸው ብሎ ይሟገታል።

ይኸ ርዕስ ፖለቲከኞቻችን ሊወድቁ ሲሉና አቡክተው የጋገሩትና የማይበላ እንጀራቸው ማረር ሲጀምር እንደ ዶፒን ሳብ የሚያደርጉት የማነቃቂያና የማበረታቻ ኪኒናቸው ነው፤ ብሔሮች ነጻ ከወጡ (ፖለቲከኞቻችን እንዳሉት) አሁን ወደ 30 ዓመት ገደማ ሆኗል፤ ምኒልክም ከ130 ዓመት በላይ ሆኗቸዋል ከምድሪቱ ከተለዩ፤ ግን ዛሬም በእኒህ ሰው ምክንያት ሰልፍና ጦርነት አለ፤ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የዚህ ንትርክ ማብቂያ እንዲኖረው ከተፈለገ በእውነት አንድ ነገር መደረግ አለበት እላለሁ፤ ሁላችንም በሰላም አብረን ለመኖር፦

1. ከሁለቱም (ከተቃዋሚና ከደጋፊ) ጎራ ምሁር ናቸው፣ ሊቅ ናቸው፣ አዋቂ ናቸው የሚሏቸውን ሰዎቻቸውን ይምረጡ፣

2. በተለይ በአጼ ምኒልክ ጉዳይላይ ይህ ነው የሚሉትን ቅሬታና ከበሬታ (ተቃውሞና ድጋፍ) በጽሁፍ ያዘጋጁ፣

3. ሀገር እየሰማው ሕዝብ እያዳመጠው በቴሌቪዥኖቻችን የቀጥታ ሥርጭት ፊት ለፊት ይከራከሩ፣

4. በክርክራቸው ጭብጥ ማስረጃ ላይ ሕዝብ ድምጽ ይስጥበትና የእነዚህ ጤናማ ያልሆኑ ፖለቲከኞች የማይበላ እንጀራ ይቋረጥ እላለሁ፤ በእኔ እምነት አጼው በትክክለኛ ጥናትና ማስረጃ ጠቀሜታቸውም ሆነ ጉዳታቸው ይገለጥ፣ እናም በዘመኑ የፖለቲካ ፍልስፍና፣ የማኅበረሰብ የአኗኗር ዘይቤ፣ ኢኮኖሚና ዓለም አቀፍ እሳቤ አንጻር ታይቶ ፍርድን ያግኙ፤ እኛም እንረፍ፤ የግጭትና የጥፋት እንጀራ ጋጋሪዎችም ድምጻቸው ይጥፋ፤ ምኒልክ ይሙት ብለው የሚምሉም ሆነ ምኒልክ ይጥፋ ብለው የሚርግሙትም በጋራ ጠረጴዛ ላይ እንያቸውና ከውጤቱ በመነሳት ወደፊት ብቻ እንድንሄድ ቢደረግ የተሻለ ነው እላለለሁ።

ይህን በሚገባ ባለመቋጨታችን የተነሳ ይኸው ዛሬ አዲስ ምኒልክ ፈጥረን ወደፊት መጋጨት የምንችለበትን አጅንዳ (የጦርነት ሜዳ) አግኝተናል፤ አቶ መለስ!!! አቶ መለስም ላይ እንዲሁ በምሁራን እውነተኛ ጥናትና ምርምር ተከራክረው ልማትና ጥፋታቸውን በመመዘን ጥፋታቸው እንዳይደገም ልማታቸው እንዲቀጥል ማደረግ አይገባም ትላላችሁ???

ዝም ብለን መለስ ይወደም! ወይም ጀግናው መለስ! እያልን አንድ ሀገር ለመምራትም ሆነ አብሮ ለመኖር ፈጽሞ የምንችል አይመስለኝም፤ በጀግኖቻችን አንስማማም፣ በጠላቶቻችን አንስማማም፣ በወዳጆቻችን አንስማማም፣ በወሰን አንስማም፣ በጥቅም አንስማማም፣ በአንደኛነት አንስማማም፣ አሁን አሁንማ በንግግር አንኳ አንስማማም ወዘተ….ይህ እንግዲህ ፖለቲከኞቻችን የፈጠሩልን ዳኛ አልባ የኳስ መጫወቻ ሜዳ መሆኑ ነው! ግርግርና መደባባት!!!

በእኔ እምነት ቀን ይቆረጥ፣ ሰው ይመረጥና በማንስማማባቸው ነገሮች እንደየ ቡድናችን፣ ምክንያታችን፣ መልሳችን፣ ማስረጃችን፣ በአደባባይ ይቅረብና የዉሾን ነገር ያነሳ …. ተባብለን ለግጭት ምክንያታችን ድንበር እናበጅለት? ይህ ካልሆነ ግን ፖለቲከኞቻችን ከተመቻቸው ነገሩን የተው መስለው የጎረበጣቸው ሲመስላቸው ጥንተ ነገርን እየጎተቱና እያጣቀሱ፡ ሶሪያን ፣ ሊቢያን፣ የመንን፣ እያነሱ ሰላማችንን መንሳታቸው አይቀሬ ነው።

አንዱ ተነስቶ እኔ ያልኩት ካልሆነ ይህች ሀገር ትበታተናለች፣ ትፈረካከሳለች፣ ትጠፋለች፣ ይለናል፤ ሌላው ተነስቶ እስከ አሁንም ያቆየናት እኛ በመሆናችንና በመኖራችን ነው ይለናል፤ ሌላኛው ብቅ ብሎ ደግሞ እንዳትፈርስ ብለን ነው እንጂ ራሳችንን ገንጥለን መኖር እንችላለለን! እያለም ልዩ የማስፈራሪያ ስብከት ይሰብከናል፤ ሌላው ደገሞ እርር ድብን በሉ እንጂ ኢትዮጵያ እንደሆነች በእግዚአብሔር እጅ ስለሆነች፣ እናንተ ትጠፋላችሁ እንጂ እርሷ እንደሆነች ለዘላለለም ትኖራለች ብሎ ይዘምራል፤ መቼ ነው አንድ ዓይነት ስብከትና መዝሙር ስለሀገራችን የሚኖረን? አጥብቄ እናፍቃለሁ!!!

ስለዚህ ወገኖቼ የምትፈቅዱና የምትወዱ ከሆነ በተለይ ስለ አጼ ምኒልክ ጉዳይ ርዕስ ተይዞ የሁለቱ ጎራ ተጨቃጫቂና አጨቃጫቂዎች፣ እንዲሁም ሌላ ሦስኛ ሃሳብ ያለው ካለ ተጨምሮ በቀትታ ሥርጭት ለሀገርና ለህዝብ ትንተናቸውን እንስማው? ያኔ ነገራችን ይለይለታል፤ በተለይ አንተ የመጪው ዘመን ዓለም ተረካቢና ኃለፊነቱ የወደቀብህ የዛሬው ወጣት ትውልድ? ለዚህ ነገር መቋጫ እንዲበጅለት ድምጽህን በስርዓት ጮክ አድርገህ አሰማ!!! ፖለቲከኞቻችን እስኪ ይቀመጡ፣ ይመዘኑ፣ ይፈተኑ፣ አጼ ምኒልክ ችግራችን ከሆኑ ለምን እውነቱ አይገለጥም? ትልቁ የክርስትና መጽሐፍስ “የማይገለጥ! የተከደነ፣ የማይታወቅም! የተሰወረ ምንም የለም” (ማቴዎስ 10:26)ይል የለም እንዴ?

እስከዚያው፡

ቸሩ በቸርነቱ ቸር ያሰንብተን!

ጌታቸው ምትኩ (መምህር) eunethiwot@gmail.com


“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Opinions Tagged With: Left Column

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • ሤራ አክሻፊው ጎንደር ለሦስተኛ ጊዜ ታሪክ ሠራ May 10, 2023 09:25 am
  • ማር በከፍተኛ ደረጃ የኮንትሮባንድ ሰለባ ሆኗል May 9, 2023 09:24 am
  • ኦነግ በኦሮሚያ ሪፈረንደም እንዲካሄድ መጠየቁ ለሰላም ንግግሩ ዕንቅፋት ሆነ May 4, 2023 01:12 am
  • መረጃ ቲቪ ያጋራው አሳሳች መረጃ May 2, 2023 12:37 pm
  • “ከፈጣሪ በታች መከላከያ የሁላችን ዋስ ጠበቃ ነው፤ ትልቅ ይቅርታ እንጠይቃለን” April 13, 2023 10:19 am
  • በትግራይ የ”ልጆቻችን የት ናቸው?” ጥያቄ እየተሰማ ነው April 13, 2023 08:56 am
  • በትህነግ የፈረሰው የአክሱም ኤርፖርት ያስከተለው ዘርፈብዙ ኪሣራ April 13, 2023 03:21 am
  • “የከተማው ነዋሪ በመሰላቸቱ ተፈናቃዮች ከፍተኛ የምግብ ችግር” ገጥሟቸዋል April 12, 2023 09:23 am
  • ከዕድሜ ልክ እስከ 20 ዓመት ቅጣት ተበይኖባቸዋል April 11, 2023 02:58 pm
  • የኡጋንዳ የክልሎች ሚኒስትር በቆርቆሮ ሌብነት ተጠርጥረው ታሰሩ April 10, 2023 03:59 pm
  • ታከለ ከተነሳ በኋላ የመዐድን ሌቦች እየተያዙ ነው April 6, 2023 02:53 pm
  • አገር ለማተራመስ ያለመ የምሁራን፣ የሚዲያ ባለቤቶችና አክቲቪስቶች ህቡዕ ቡድን ተያዘ April 4, 2023 10:07 am
  • በ10 ዓመት ውስጥ ከ44 ቢሊየን ዶላር በላይ ሸሽቷል April 4, 2023 09:26 am
  • አየር ጨብጦ አሁን ያለውን መንግሥት ከሥልጣን ልቀቁ አይሆንም March 29, 2023 09:47 am
  • ሦስት ትውልድ የበላ የሐሰት ትርክት! March 23, 2023 11:59 am
  • “ሽብርተኝነቱን ማንሳቱ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለማቋቋም ይረዳል” – ዶ/ር ጌዲዮን March 22, 2023 05:05 pm
  • አስነዋሪ ተግባር ሲፈጸምባቸው የነበሩ የምሽት ክለቦች ተዘጉ March 22, 2023 12:57 pm
  • ህወሓትን ከሽብርተኝነት እንዲሰረዝ የወሰናችሁ ሁሉ ተጠያቂዎች ናችሁ – ኢዜማ March 22, 2023 12:06 pm
  • የኡጋንዳ ፓርላማ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን በእስር የሚያስቀጣ ወንጀል የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ አጸደቀ March 22, 2023 12:44 am
  • በጌታቸው ምርጫ ማግስት በትግራይ ሕዝባዊ ዐመፅ ተጀመረ March 21, 2023 11:01 pm
  • በትግራይ ሥልጣንና ንጉሥ ፈጣሪነት ከአድዋ ወደ ራያ ተሻገረ March 19, 2023 03:45 am
  • ኤርሚያስ ከጌታቸው ረዳ ጋር ምሥጢራዊ የስልክ ግንኙነት ነበረው March 19, 2023 02:44 am
  • እየተገባደደ ያለው የምስራቅ አፍሪቃ የትራንስፖርት ኮሪደርና ለውጥ የናፈቃት ኤርትራ March 15, 2023 04:44 pm
  • በባዶ እግር በሮም አበበን ለመድገም March 15, 2023 01:40 pm

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2023 · Goolgule