አድዋ! በድልሽ የተገኘ ምስራች
ጊዜው ረዘመ ብሎ ሳይሰለች
ዕድሜው በዕድሜ ላይ እየጨመረ
ጀግኖችን እንደገና እያነሳ እየደመረ
ዛሬም በልጅ ልጅ ልጅ ልጅ ልጅ….ታሪክሽ ታውቀ
የድል ብስራትሽ በዓለም ዓለም ዓለም ዓለም….አንጸባረቀ
የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ሻማ
መሆንሽ ተወራ ሀገር ለሀገር ተሰማ
ይሄው ተከበረ መቶ አስራ ስምንተኛ ዓመት
ሁላችንም ደስ ይበለን በዚህ ብስራት
የአበው ተጋድሎ የጀግንነት ደም
ታሪኩ ተወሳ በከንቱ ፈሶ አልቀረም
የአባ ዳኘው መድፍ አሁንም አገሳ መልሶ
የጣይቱ ስም ተጠራ ተወደሰ አባ ነፍሶ
እንደገና አስተጋባ የአድዋ ድል
ገኖ ታየ ተደነቀ አባ መቻል
ሀብተ ጊዮርጊስ አባ መላ
ስራው በድጋሚ ጎላ።
አድዋ! በድልሽ የተገኘ ምስራች
ጊዜው ረዘመ ብሎ ሳይሰለች
ዕድሜው በዕድሜ ላይ እየጨመረ
ጀግኖችን እንደገና እያነሳ እየደመረ
ዛሬም በልጅ ልጅ ልጅ ልጅ ልጅ….ታሪክሽ ታውቀ
የድል ብስራትሽ በዓለም ዓለም ዓለም ዓለም….አንጸባረቀ
ራስ አሉላ አባ ነጋ
በከፈለው የደም ዋጋ
ስሙ ዛሬ ሲነሳ
የባልቻ የገበየሁ አብሮ ሲወሳ
እነ አባተ ቧ ያለው
እነ ቃኘው እነ ውቃው
ከተኙበት ቀና ብለው
መቃብሩን ፈነቃቅለው
የአድዋን ድል አበሰሩ
ጀግንነትን አስተማሩ
አድዋ! በድልሽ የተገኘ ምስራች
ጊዜው ረዘመ ብሎ ሳይሰለች
ዕድሜው በዕድሜ ላይ እየጨመረ
ጀግኖችን እንደገና እያነሳ እየደመረ
ዛሬም በልጅ ልጅ ልጅ ልጅ ልጅ….ታሪክሽ ታውቀ
የድል ብስራትሽ በዓለም ዓለም ዓለም ዓለም….አንጸባረቀ
የአበው ተጋድሎ ያፈሰሱት ደም
ተወሳ ተነገረ ከንቱ አልቀረም
የሚኒሊክ መድፍ አሁንም አገሳ መልሶ
የጣይቱ ስም ተጠራ ተወደሰ አባ ነፍሶ
ትውልዱም የአባቶቹን ድል በማደስ
የጀግንነት ስራቸውን እያነሳ በማውደስ
ለመጪውም ጊዜ እንዲሻገር
ኢትዮጵያ በታሪኳ እንድትከበር
የድርሻውን በተግባር አስመሰከረ
ይሄው የድል ቀኑን በአንድነት አከበረ
አድዋ! በድልሽ የተገኘ ምስራች
ጊዜው ረዘመ ብሎ ሳይሰለች
ዕድሜው በዕድሜ ላይ እየጨመረ
ጀግኖችን እንደገና እያነሳ እየደመረ
ዛሬም በልጅ ልጅ ልጅ ልጅ ልጅ….ታሪክሽ ታውቀ
የድል ብስራትሽ በዓለም ዓለም ዓለም ዓለም….አንጸባረቀ
የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ሻማ
መሆንሽ ተወራ ሀገር ለሀገር ተሰማ
ይሄው ተከበረ መቶ አስራ ስምንተኛ ዓመት
ሁላችንም ደስ ይበለን በዚህ ብስራት።
———————————
ማርች 30/2014 (መጋቢት 21/2006) ዓ.ም በስዊድን የዓድዋን 118 ኛ የድል በዓል ስናከብር የቀረበ።
Leave a Reply