አቶ ፈቃደ ሸዋቀና የስደትን ነገር መነሻ አድርገው ስለ ብሔራዊ እርቅ የሰነዘሩት ሀሳብ ካለፈው የባሰ ጨለማ የሆነው የሀገራችን መጻኢ እድል አሳስቦ አስጨንቆአቸው ያቀረቡት በጎ ሀሳብ እንደመሆኑ አንብበን የምንተወው ወይንም ተግባራዊ ሊሆን የማይችል ብለን ልናናንቀው የሚገባ አይደለም፡፡ ርሳቸውም አንዳሉት ሁሉም የየበኩሉን ይበጃል የሚለውን ሀሳብ በመሰንዘር በመተላለቅ ሳይሆን በመታረቅ የምናተርፈበትንና ሀገራችንንም አድነን ለመጪው ትውልድ ልጆቿ በሰላምና በፍቅር የሚኖሩባት ዴሞክራሲያዊት ሀገር ለማቆየት ወደሚያስችለን እቅጣጫ ብናመራ ነው የሚበጀው፡፡ በዚህ መንፈስ እኔም እንዲህ ቢሆን እላለሁ፡፡
ወያኔ ስልጣኑን ለብቻው ካደረገ ግዜ ጀምሮ በተለያየ መንገድ የብሔራዊ እርቅ ጥያቄ የተነሳ ሲሆን የሀሳቡ አቀንቃኞች በሁለት ወገን መወገዛቸውን እናስታወሳለን፡፡ ወያኔ የደርግ ሥርዓት ወንጀለኞችን ከሕግ ተጠያቂነት እንዲያመልጡ ለማድረግ፤በምርጫ ሊያገኙት ያልቻሉትን ሥልጣን በአቋራጭ ለማግኘት ማን ከማ ተጣላና ወዘተ በማለት የብሐየራዊ እርቅ ጥያቄን ያልተገባ መልክ ሲሰጠው ፤አንዳንድ ተቀዋሚ ግለሰቦችና ፓርዎች ደግሞ ኢህአዴግ በትግል ማስወገድ እንጂ ከርሱ ጋር የምን ዕርቅ ነው፤ በመንገዳገድ ላይ ያለውን ወያኔ እድሜ ለማራዘም ነው ወዘተ ከማለት አልፈው የብሐየራዊ ዕርቅ ጥያቄ ማቅረብ የህዝብን የትግል ወኔ መስለብ ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ የሀሳቡ አራማጆችንም በተለመደው የፍረጃ ፖለቲካ “በወያኔ ደጋፊነት” እስከ መፈረጅ የደረሱም ነበሩ፡፡
በመንገዳገድ ላይ ነው የተባለው ወያኔ 24 ዓመታን በሥልጣን ቆይቶ መቶ በመቶ አሸነፍኩ ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ወደፊትም ሰላሳና አርባ ዓመታት አንደሚገዛን በድፍረትና በዕብሪት እየነገረን ነው፡፡ በመሆኑም አስገዳጅ ሁኔታ ካተፈጠረ በስተቀር ዛሬ ወያኔ ለብሔራዊ እርቅ ጥያቄ ጆሮ አይኖረውም፡፡
መጀመሪያ ከራሳችን እንታረቅ
በተቃውሞ ጎራ የተሰለፉ በውጪም በሀገር ቤትም የሚኖሩ ፓርቲዎች ብዙ ናቸው፡፡ በዓላማ ልዩነት ሳይሆን በመሪዎች አለመስማማት እየበዙ እየተባዙ የተፈጠሩ፤ ሆድና ጀርባ ሆነው የሚኖሩ፤ አንዱ ለሌላው እንቅፋት ሆነው የሚሰሩ፡፡ ወያኔን የልብ ልብ የሰጠውና ለእርቅ አሻፈረኝ እንዲል ያበቃው መቶ በመቶ አሸነፍኩ የሚልበት ደረጃ ላይም ያደረሰው አንዱና ዋና ምክንያት ይኼ የተቃውሞው ወገን ርስ በርስ በጠላትነት መቆሙ ይመስለኛል፡፡
የሀገራችን የፖለቲካ ጉዞ ለመለወጥ ጥረው ተጣጥረው መለያየት አንጂ አብሮ መዝለቅ ባሪው ባልሆነው ፖለቲካ ተሸንፈው የጻፉትን መተግባር ያልቻሉት ቅንጅቶች በምርጫ ማንፌስቶአቸው ስለ ብሔራዊ ዕርቅ አስፈላጊነት የገለጹት “በሐገሪቱ ታሪክ ውስጥ እንደ መጥፎ ገጽታ የሚታዩ የእርስ በእርስ ግጭቶችም ደም ያፋሰሱ ጦርነቶችና እልቂቶች በተለያዩ ምክንያቶች ተከስተዋል፡፡ በሀገራችን የሚመሰረተው ዴሞክራሲያዊ ሥርዐት በማይናወጥ ዴሞክራሲያዊ መሰረት መገንባት ላይ ካለበት የእስካሁኑ የጥላቻ የበቀልና ያለመተማመን ምዕራፍ ተዘግቶ ለተከታይ ትውልድ የሚዘልቅ አዲስ ምዕራፍ መከፈት ይኖርበታል፡፡ በመሆኑም እያንዳንዳችን ከራሳችን ፤ ሕዝብ ከሕዝብ መንግሥት ከሕዝብ የፖለቲካ ፓርቲ ከፖለቲካ ፓርቲ ለመግባባት የሚችሉበት ብሔራዊ ዕርቀ ሰላም ከሁሉ በፊት መቅድ አለበት ብሎ ቅንጅት ይምናል፡ በማለት ነበር፡፡ (ሰረዝ የተጨመረ) በእውነቱ ቅዱስ ሀሳብ ነበር፣ ግና ምን ይሆናል ለሀገር የተመኙትን ለራሳቸው ማድረግ ተስኖአቸው ተበታተኑ፡፡
የሀገራችን ሁኔታ እየባሰ አንጂ እየተሻለ የሚሄድ ባለመሆኑ ተለያየ ግዜ ተነስቶ ገቢራዊ መሆን ያልቻለው የእርቅ ጉዳይ ዛሬ አንደ አዲስ ቢነሳ ተገቢም ወቅታዊም ነው፡፡ ነገር ግን ወያኔ የዚህ አካል እንዲሆን ከማሰብ በፊት በቅንጅት ማንስቶ ተገልጾ አንደነበረው እርቅን ከራስ መጀመር ያስፈልጋል፡፡ ከራሳቸው ተጣልተው ፖለቲካውን የሚያብጡ፤ ተነጋሮ መግባባት ተከባብሮ መስራት እንዳይኖር የሚያበጣብጡ፤ በእድሜ ሰክነው ከግዜ ተምረው የማያርፉ ወይ የማይሸነፉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህን ለይቶ በሽታቸውን አውቆ በማውገዝ ሳይሆን በማገዝ ከራሳቸው ጋር እንዲታረቁ ማድረግ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ቢሳካ ቀጣዩ ሥራ በጣሙን እየቀለለ ይሄዳል፡፡ ከዛም ፓርቲዎች በየውስጣቸው እርቅ መፍጠር ፓርቲ ከፓርቲ እርቅ መፍጠርና በተባበረ ድምጽ በተጠናከረ ኃይል ወያኔን እርቅ መጠየቅ እምቢ ካለም ማንበርከክ፡፡
ይህን ለመፈጸም ባለፈ መጸጸትን በሚገልጽ ኁኔታ መቆጨትን ከራስ በላይ ሀገር ከግል ሥልጣን በላይ ሕዝብ ብሎ ማሰብን ይጠይቃል፡፡ ራስን ለሥልጣን ማብቃትን ወይንም የተመኙትን ጥቅም ማግኘትን፤ የያዙትንም ሙጥኝ ማለት ሳይሆን ሁሉም አሸናፊ ሆኖ ሀገርንና ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ ድል የሚያመጣውን ውጤት በጸጋ ለመቀበል ተዘጋጅቶ መስራትን ይሻል፡፡ትናንት ከቆሙበት ሆኖ ይህን ማሳካት አይቻልም፤፡ በትናት አስተሳሰብ የዘመኑን ጉዞ ማፋጠን አይቻልም፡፡ እናም የትናንቱ በግዜው ጥሩም ጥሩም ያልሆነ ውጤት አስገኝቷል፡፡ ከዛ በመማር መለወጥ አሰራን መቃኘት ያስፈልጋል፡፡
ትናንት ልንከውነው ይገባን የነበረን ይህን ተግባር ዛሬም መፈጸም ካቃተን የታሪክ ሂሳብ አወራረድን አላወቅንበትም ማት ማለት ነውና ቀሪ እድሜአችንን ከምንኖርባት ይልቅ ለልጆቻችን የምናቆያት ኢትዮጵያ እንዴትነት ያሳስባል፡፡
ሀሰን ዑመር አብደላ በሚል የብዕር ስም በጦቢያ መጽሄት እናውቃቸው የነበሩት ጸኃፊ በአንድ ጽሁፋቸው “የታሪክ ቁርሾ ቁስል ሰንበርና ስብራት አያት ለአባት አባት ደግሞ በውርስ አንዳልተወራረደ በውዝፍ ሂሳብ አንዱ ትውልድ ወደ ሌላው ትውልድ እያስተላለፈ የታሪክ ሂሳብ አወራረድን ዘዴ አላገኘነውም ማለት ነው” ብለው ነበር፡፡
የታሪክ ሂሳብ ማወራረጃው አንዱ መንገድና ዘዴ ብሐየራዊ ዕርቅ ይመስለኛል፡፡ስለሆነም የዛሬ መቆሚያችንን መሰረት የሚያናጉ፤ በመንገዳችንም ላይ ጋሬጣ በመሆን የሚያደናቅፉ፤የነገውን ተስፋችንን የሚያጨልሙ ወዘተ የትናንት ችግሮች የምላቸውን በብሔራዊ እርቅ ሂሳብ እናወራርድና ፋይሉ ይዘጋ፡ ይህን በማድረግም ሁሉ አሉታዊ ነገር በእኛ ይብቃ ብለን ለትውልድ መልካም ነገር እናቆይ፡፡
አቶ ፈቃደ ሀሰባቸው ገቢራዊ ሊሆን ስለሚችልበት መንገድ ሲያመላክቱ “የተጠቀሱት የመፍትሄ ሃሳቦች ከመንግስት ቅን ምላሽ የሚያገኙት ቀደም ሲል እንዳነሳሁት በቅንነት ወይም በበጎ ፈቃደኝነት ብቻ አይደለም። የፖለቲካ ተቃዋሚዎች መንግስት ላይ ከፍተኛ ግፊት የሚፈጥር ትግል ማድረግና ያቀረቡለትን የመግባቢያ ሀሳብ እንዲቀበል ከማስገደድ ያልተናነሰ ተጽዕኖ መፍጠር አለባቸው። ተቃዋሚዎች ልዩነታቸውን አጥብበው ባንድ ላይ መሰለፍ ቢችሉ ትልቅ የተጽዕኖ ሀይል ይፈጥራሉ። ለዚህ የሚሆን መሰረታዊ የመስማሚያ ሀሳብ ማፍለቅ አንድ ትልቅ ጊዜ የማይሰጠው ስራ አድርገው ሊያዩት የሚገባ ይመስለኛል። እንደውም ከቀዳሚዎቹ ነገሮች እንዱና ዋነኛው በተቃውሞው ጎራ የተሰለፉ የፖለቲካ ሀይሎች ያግድሞሽ ትግል ከማድረግ ወጥተው በእንድ ላይ የመሰለፋቸው ጉዳይ ነው” ብለዋል፡፡ በጣም ትክክል ናቸው፡፡ ትግል እንጂ ድል ማየት ያላስቻለን አብዩ ችግር ይህ ነው፡፡ ፖለቲከኞቹ አቶ ፈቃደ ያሉትን ለመፈጸም የሚችሉት አበው እንደሚሉት ሳል ይዞ ስርቆት ቂም ይዞ ጸሎት ስለማይሆን መጀመሪያ ከራሳቸው ጋር መታርቅ ቀጥሎ በየሚመሩት ፓርቲ ውስጥ እርቅ ማውረድ ካዛ ደግሞ በፓርቲዎች መካከል እርቅ መፍጠር ሲችሉ ነው፡፡
በአላማቸው ምንነት በአመሰራረታቸው እንዴትነት ለሀገር ባላቸው ራዕይ ምክንያት እርቁን የማይፈልጉ ሊኖሩ ይችላሉ፤ከመለያየት የሚያተርፉም ወደዚህ መንገድ ሊመጡ ፈቃደኛ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ግና ያለፈው የሚቆጫችሁ፣ መጪው ሁኔታ የሚያሳስባችሁ፣ ከምር ለሀገርና ለሕዝብ የምትጨነቁ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ፓርቲዎች የምትፈላለጉበት እርቅ ፈጥራችሁ የጋራ አጀንዳ ቀርጻችሁና ክንዳችሁን አጠንክራችሁ ወያኔ ጠፍቶ እንዳያጠፋን ለእርቅ የምታስገድዱበት ግዜ አሁን ይመስለኛል፡፡
የእኛ ተለያይቶ መቆም ከቀጠለ የወያኔ እብሪት እየጨመረ ከሄደ የሚከተለው ጥፋት የከፋ ይሆናል፡፡
abutam2006@gmail.com
Leave a Reply