አሜሪካ ለሩስያ የፖለቲካ ተቀናቃኝ ናት።
የአሜሪካ ርዕዮተ ዓለም ከሩስያ ርዕዮተ ዓለም የተለየ ነው።
በአሜሪካ፤ ከሀገሪቱ የግለሰብ የሃሳብ የነፃነት የተነሳ፤ ከሀገራቸው ይልቅ ራሳቸውን የሚያስቀድሙ ሰዎችም በመንግሥት መዋቅርም ይሁን በንድግ ተግባሩ ውስጥ በኃላፊነት የሚገኙ አሉ። ይህ የግል አመለካከታቸው፣ የራሳቸው ከመሆኑም በላይ፤ በማንም ግለሰብ፤ የበላይ አለቃቸውም ሆነ ለነሱ ተጠያቂ በሆኑ ግለሰቦች ዘንድ፤ አያስገምታቸውም። በአንጻሩ፤ እንደሩስይ ባሉ የአምባገነኖችን የበላይነት በሚያመቻቹና በሚያሞግሱ ሀገራት፤ (ይህ አብዛኛውን በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ያጠቃልላል። የኢትዮጵያውን የትግሬዎች ወገንተኛ ወራሪ ቡድንንም ይጨምራል።) ነዋሪዎቹ፤ ግለስብ ግለሰብነቱን አጥቶ፤ በገዥዎቹ ፍላጎት የሚተረጎም ማንነትን እንዲቀበሉ ስለሚገደዱ፤ የገዥዎቻቸው አገልጋዮች ናቸው ማለት ይቻላል። ከዚህ የተነሳ፤ ለገንዘብ ሊያድሩ የሚችሉ ግለሰቦች በየትኛውም ሀገር ያሉ ቢሆኑም፤ እንደሩስያ ያሉት ሀገሮች በኃላፊነት የሚያስቀምጧቸውን አበጥረው ተገዥ የሚሆኑትን የሚያወጡ ሲሆን፤ እንደ አሜሪካ ያሉት፤ ክፍትነታቸው ለብዙኀኑ ባደባባይ ያን የግል አመለካከታቸውን ለማወጅ አመቺ ነው።
እንግዲህ በመካከላቸው ባለው ልዩነትና ውድድር የተነሳ፤ አሜሪካና ሩስያ፤ በየትኛውም መስክ ቢሆን፤ ፉክክራቸው ቅድሚያ ይይዛል። ለዚህም፤ ሩስያ፤ በመንግሥት ደረጃ አሜሪካን ለማዳከምና የራሳቸውን ጥቅም ለማስቀደም፤ ሌት ተቀን ይሠራሉ። አሜሪካ ይሄን አታደርግም ማለት አይደለም። ነገር ግን፤ አሜሪካ የበላይነት አለኝ የሚል እብሪት ስላላት፤ “እኔ የምለው ሁልጊዜም ተቀባይነት አለው!” በሚል ጋቢ ተጎናፅፋ፤ “ዓለምን የምመራው እኔ ነኝ፤ ሩስያ ደካማ ናት!” በሚል፤ በሩስያ ላይ ዕቀባ መጣልና የመሳሰሉትን በቦታው አስቀምጣለች። በተወሰን ደረጃም አብረው የሚሰለፉላት ምአንግሥታት አሉዋት። በዚህ የፖለቲካ ጨዋታ መካከል ነው የሩስያን ጣልቃ ገብነት የምናየው።
ሩስያ፤ በአሜሪካ መንግሥት የሚደረገውን ውሳኔ ማወቅ ብቻ አይደለም፤ ከቻለች፤ በውሳኔ አሰጣጡ ላይ እጇን ማስገባት ትፈልጋለች። ማን የጠላቱን እንቅስቃሴ ማወቅ የማይፈልግ አለ? በየሀገሩስ ያሉት ኤምባሲዎች ዋናው ሥራቸው ምን ሆኖ ነው! ሩስያ ግን የሞትና የሽረት ጉዳይ አድርጋ ነው የያዘችው። አያስገርምም። ዓለም መተሳሰርና መተባበር ለእያንዳንዱ ሀገር የሥልጣኔ ግስጋሴና የቴክኖሎጂው እድገት ወሳኝ በሆነበት ወቅት፤ ከህዝቡ ነፃነት ይልቅ የራሳቸውን በሥልጣን መሰንበት የሚያስቀድሙ ሀገሮች፤ ተገደውም ሆነ ወደው ለብቻ መቀመጣቸው፤ አስጊ ነው። ሰሜን ኮሪያ፣ ኤርትራ፣ ሶሪያ፣ ይአትግሬዎቹ ገዥ ቡድን የነገሠባት ኢትዮጵያ፣ የዚህ ባለቤቶች ናቸው። እናም ያንን ሚዛን መድፊያ የግድ ማቀድ፤ ለሩስያ ግድ ሆኖባታል። ታዲያ የሩስያን መሯሯጥ የሚረዳ አካል ደግሞ፤ በአሜሪካ ውስጥ ይገኛል። ይሄም፤ በአሜሪካ ያሉ የራሳቸውን ጥቅም ከሀገራቸው ጥቅም አስበልጠው የሚገኙ ግለሰቦች ናቸው። እንደነዚህ ያሉ ግለሰቦች፤ ለገንዘብ ሲሉ፤ በሰላይነት፣ በተቀጣሪነት እናም መሳሪያ በመሆን ተገዝተው ለሩስያ የሚያገለግሉ ናቸው። ለግልሰብ ጥቅማቸው የሚንሰፈሰፉ ሰዎች በግል አይኖሩም። በጎናቸው መሰሎቻቸውን ይኮለኩላሉ። እናም የብርታታቸው ምሰሶዎች፤ ሌሎች እንደነሱ ያሉ የግል ጥቅም አሳዳጆች ናቸው።
ከግለሰብ ጥቅም አንጻር፤ ግለሰብ ዶናልድ ትራምፕ፤ ራሳቸውን ወዳድ፤ ማንንም ረጋግጠው ወደ ላይ ለመውጣት ቅንጣት የማይሰቀጥጣቸው ናቸው። እናም፤ ማንም በሚፈልጉት መንገድ ወደሚፈልጉት ቦታ ለመሄድ እንቅፋት የሚሆንባቸውን፤ ከሰይጣንም ጋር አብረው ለማጥቃት፤ ወደኋላ አይሉም። ይህ የሩስያ ጉጉትና የትራምፓ ራስ ወዳድነት፤ ባንድ ላይ ተጋጥመው መገኘታቸው ነው፤ ለዚህ አሁን ላለንበት የሩስያ ጣልቃ ገብነት መሠረቱ።
የሩስያ አሜሪካን የመቦርቦር ጥረት አዲስ አይደለም። እስከዛሬም ስታደርገው የነበረ ነው። የትራምፕም ጥቅሙን ማሳደድና የሀገሩን ጥቅም ወደ ትቢያ መጣል አዲስ አይደለም። የነበረ ነው። ምንም ታክስ አለመክፈሉ ብቻ ሳይሆን፤ አሁንም የታክስ መዝገቡን አላሳይም እንዳለ በእብሪት መቀመጡ፤ ምስክር ነው። በዚህ ስሌት፤ የቀድሞዋ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ የነበሩትን ሄለሪ ክሊተንን ለማቸነፍና ፕሬዘዳንት ለመሆን፤ ከሩስያ ጋር ለማበር ፈላጊ ሆኖ ቢገኝ፤ ሩስያም አደገኛ ይሆኑብኛል ያላቸውን የአሜሪካን የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ኃላፊዎን ሄለሪ ክሊንተንን ለማስወገድና እንደ ፈረስ እጋልበዋለሁ ብለው የተመኙትን ዶናልድ ትራምፕን ለፕሬዘዳንትነት ለማብቃት፤ ሁለቱም ተጠቃሚዎች የሚሆኑበት አጋጣሚ ነበር። እናም ሌት ተቀን ሠሩበት። በሂደቱም ዶናልድ ትራምፕ ተመረጠ።
ውሎ አድሮ ግን፤ የአሜሪካ ልዩ የሆነ መንግሥታዊ አወቃቀር፣ አሰራርና በውስጡ የተሰገሰጉ ሀገር ወዳዶች፤ “ዝም ብለን አናይም!” በማለት፤ ውስጥ ውስጡን ሚስጢር በማውጣት፤ ይሄው እንዲጋለጥ አደረጉት።
ከዚህ የምናነበው፤ በታጋዩ ወገናችን ውስጥ የሚካሄደውን ክስተት ነው። በውጥረት ላይ ያለው የትግሬዎች ገዥ ቡድን፤ በውስጥና በውጪ ያለበትን ሕዝባዊ ተቃውሞ ለመከላከል፤ በሀገር ውስጥ፤ ፍጹም አረመኔያዊ በሆነ መንገድ፤ ትክክለኛ ያልሆኑ ሕጎችን በማውጣት፣ አላግባብ ሰዎችን አጋፎ በማሰር፣ ሕጉን አጣሞ ፍርድ በመሥጠት፤ የለ ርህራሄ ሕዝቡን እያሰቃየ ነው። በውጪ ያለውን ተቃውሞ ደግሞ፤ ከፍተኛ ወጪ በማፍሰስ፤ የትግል አንድነት እንዳይፈጠር፣ ሆድ አደሮችን ሰግሰጎ በማስገባት፤ ትግሉ ባለበት እንዲቆም አድርጎታል። ምንም እንኳን ከመቼውም የከፋ ሥርዓት በሀገራችን ቢሰፍንም፤ ምንም እንኳን ብዙኀኑ በዚህ በትግሬዎች ገዥ ቡድን ተጠቂ ቢሆንም፤ ምንም እንኳን ታጋዩ ብዙ ቢሆንም፤ አንድነት ከመቼውም በላይ ርቆ ሄዷል። የትግል አንድነት ቀርቶ፤ ተቀራርቦ የመነጋገር ዕድሉ እንዳይሆን ሆኗል። የትግሬዎቹ ገዥ ቡድን ሊኮራ ይገባዋል። ምንም እንኳን ሙሉ በሙሉ ይህ የተደረገው በትግሬዎቹ ገዥ ቡድን የገንዘብ ፍሰትና የግለሰቦች ሆዳምነት ብቻ ነው ባይባልም፤ በአንድነት የመታገሉን ሁኔታ ያደቀቀው፤ በአብላጫው፤ የዚሁ ተወጣሪ ቡድን ጭንቀትና የሆዳሞች ስግብግብነት መሆኑን መካድ አይቻልም። በርግጥ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ፉክክሩና፤ እኔ ብቻ ነኝ ትክክለኛ ባይነቱ ሚና አለው። ሌላም ተጨማሪ፤ ለዚህ ጸሐፊ ያልታየው ሁኔታ ሊኖር ይችላል። ባጠቃላይ ከሩስያ ጣልቃ ገብነት የሚታየው ይህ ነው።
አንዱዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ
eske.meche@yahoo.com
አርብ፣ መጋቢት ፳፪ ቀን፣ ፳፲፱ ዓመተ ምህረት (03/31/2017)
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Mes says
አቶ አንዳለም ተፈራ በ CNN ፕሮፓጋንዳ አይምሮአቸው ዞሯል መሰለኝ ፣ ፑቲን ራሺያን ከዲክታይተሮች የነጭ አሽከሮች ጋር እንድ ማደወረጋቸው ፍፅም ስህተት ነው ፣ ምእራባውያን የቀድሞው ሶቪየት ተሸንፎ ፈረሰ ብለው እራሳቸውን እንዳሸናፊ ቆጠሩ: እውነታው ግን ሶቪየት ህብረት bankrupt ሆነ ታዲያ ምእራቡ የቀድሞውን የአለም ሰላም ስምምነቶች ከቀድሞ ሶቪየት ጋር የነበራቸውን መሻር ብቻ አይደለም በናቶ ጦር ሩሲያን መክበብ ጀመሩ ፣የማይፈልጉትን መንግሥታት አይ ሲስን በመጠቀም መንግስትን ግልበጣ ጀመሩ ፣ አለምን ከፍተኛ ወደ ኒኒኩለር ጦር አስጊነት ቀየሩት ፣ታዲያ ይህን በመቃወምና የአገርዋን ከበባ ለመቋቋም የምትወስደው ሩሲያ ከወያኔ ጋር ትመሳሰላለች ፣ አቶ አንዱአለም እዛው በአገራችን ፖለቲካ ቢቆዩ ይሻላል እንጂ ኢንተርናሽናል ትንሽ ተዘርባብቆባቸዋል ፣ ሩሲያ ናፖሊዮንን ያሸነፈች ሂትለርን ትምህርት የሰጠች ናት ፣ ሩሲያ ጦርነት መጀመር ሳይሆን ጦርነትን መጨረሽ ግን የተካነች ናተወና ፣ ጀግናን ህዝብና መሪዎችን ከኢትዮጵያ ሹምባሽ መሪዎች ጋር አንድ ማድረግ አለማወቅ ብቻ ሳይሆን አሳፋሪ አባባል ነው ።
የዜኑ ሰው says
ምናልባትም አቶ አንዱአላም ተፈራ በምእራብያኑ ሚዲያ በሚሰሙት ፕሮፖጋንዳ ሳይሸወዱ አይቀሩም መሠለኝ …..እንጂማ ይሄንን እንቶ ፈንቶ የሆነ ፁሁፍ ባላቀረቡ ነበር፡፡
የቀድሞዋን ሶቭዬት ህብረት ከታላቅነቷ አውርደው እና በታትነዋት አቅመ ቢስ ያደረጓትን እንደነ ሚካኤል ጎርባጆቭ እና ዬልሲን ያሉ የአሜሪካን ተላላኪና ባንዳ መሪዎችን ከወያኔ ጋር ማመሳሰል ሲገባ የተናቀችው ራሺያን ከወደቀችበት አንስቶ: ከአቅመ ቢስነት ወደ ሀያልነት ከፍ አድርጎ ወደ ቀድሞዎ ገናናነቷ የመለሳትን ጀግናና ሀገር ወዳድ መሪ የሆነውን ፑቲንንና መንግስታቸውን ከትግራዩ ወያኔ ጋር ማወዳደር ለተናጋሪው ይቅርና ለሠሚውም ይሰቀጥጣል፡፡ ይመስለኛል አቶ አንዱአለም አሁን ስላለው የራሺያ መንግስትም ሆነ ስለ ፑቲን የሚያውቁት አንዳችም ነገር የለም