ቤን እባላለሁ። EthiopiaFirst የሚባል ለሕወሓት/ኢሕአዴግ ጭፍን ወገንተኛ ሆኖ የሚሠራ “የሚዲያ” ተቋም አለኝ። EthiopiaFirst የሚለው ያው ደርግ ‘ኢትዮጵያ ትቅደም’ እንዳለው ወይም ናዚዎች ‘ጀርመን ትቅደም’ እንዳሉት ሰው ማባበያ ስያሜ ነው። ኢትዮጵያ ፈርስት እያልኩ የምጠራውን የሚዲያ ተቋምን ተጠቅሜ ኢሕአዴግ የጠላውን ጠልቻለሁ፣ ኢሕአዴግ የወደደውን ወድጃለሁ። ለምሳሌ የዞን፱ ጦማርያን እና ጋዜጠኞች ሲታሰሩ “እሰይ! አገር ሊያተራምሱ ሲሉ ተያዙ” እያልኩ፣ እየማልኩ እና እየተገዘትኩ ፕሮግራም ሠርቼ ተመልካች ለማሳሳት ጥሬ ነበር።
በዜግነቴ ካናዳዊ ነኝ፤ ቢሆንም ግን ለውጭ ዜጎች የማይሰጠው ዕድል የሕወሓት/ኢሕአዴግ ወዳጅ ስለሆንኩ ተሰጥቶኝ አንዳንዴ በየወሩ የሚታተም «ኅብረ–ብዕር» የተባለ መጽሔት ባለቤትና አዘጋጅ ሆኛለሁ። በመጽሔቴ ላይ ‘አብይ ጉዳይ’ የሚባል አምድ አለኝ። አምዱ «…በተመረጠ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ትንታኔ፣ ማብራሪያ የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ በጉዳዩ ላይ በቂ ጥናት በማድረግ ወቅታዊ አብይ አጀንዳ ላይ በመመርኮዝ መረጃ የሚቀርብበት ነው»። በዚሁ መሠረት በዚህ ሳምንት (ቅፅ 02፣ ቁጥር 17) ላይ “አዲስ አበባ ስለምን ታወዛግባለች?” የሚል አብይ ጉዳይ ይዤ ወጥቻለሁ። ጽሑፉን ከየት እንዳመጣሁት ታቃላችሁ? እነዛ ‘ኢትዮጵያን ሊያተራምሱ ነበር ያልኳችሁ ጦማሪዎች (በመሀሪ መንግሥታችን ርሕራሄ አሁን ተፈተዋል፣) ከጦማሪዎቹ አንዱ – ዘላለም ክብረት የሚባለው፣ እሱ ጽፎት፣ ከZone9 ጦማር ላይ ሰርቄው ነው። በነገራችን ላይ ግማሹን ነው አሁን ያተምኩት። ግማሹ ደግሞ ለሚቀጥለው እትሜ ገፅ ማሟያ ይሆነኛል ብያለሁ።
በነገራችን ላይ መጽሔቴን ማንም አይገዛልኝም ግን ነፍ የመንግሥትና የግል መሥሪያ ቤቶች ማስታወቂያ ስለሚሰጡኝ ረብጣ እንደጉድ ነው የማፍሰው። የመንጌ ማለትም የመንግሥት ደጋፊ ነኛ! ካላመናችሁ እናንተም ሞክሩት።
ሰሞኑን ደግሞ ፩ኛ – ልክ እንደኔ የሕወሓት ጭፍን ደጋፊ ከሆኑ፣ ፪ኛ – በልባቸው ቢደግፉም/ቢቃወሙም፣ በጋዜጣቸው ገለልተኛ ለመምሰል ከሚሞክሩ፣ እንዲሁም ፫ኛ – ከሕወሓት ጋር የሚያጣላ እውነት ፈፅሞ ከማያቀርቡ ሚዲያ ባለቤቶች ጋር ሆኜ ***የሚዲያ ካውንስል*** በይፋ ላቋቁም ነው። ካውንስሏ ካሁኑ አትራፊ መሆኗ ስለታወቀ ምቀኛ በዝቶባታል። ለወትሮው “እነእከሌ ይታሰሩ” እያልን ስናወራ እና ስንጽፍ ያጨበጭቡልን የነበሩ “ጋዜጠኞች” የካውንስሉ ፕሬዚዳንትነትን ቦታ ሊቀሙኝ እየተስገበገቡ ነው። እኔም በቀላሉ አልፋታቸውም። በሆድ ቀልድ የለማ!
(ምንጭ: BefeQadu Z. Hailu ፌስቡክ ገጽ)
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply