ከአንድ ዓመት በፊት አንድ ህመምተኛ ለሚደረግለት ህክምና ደም የሚያስፈልገው ከሆነ፣ ቤተሰብ አሊያም ወዳጅ ዘመድ ምትክ ደም ሰጥቶለትና የሚያስፈልገው የደም አይነት ከደም ባንክ ወጥቶለት ይታከም ነበር፡፡
ይህ አሠራር ግን በርካቶች የሚያስፈልጋቸውን ደም በቀላሉ እንዳያገኙ የሚያደርግ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ቤተሰብ አሊያም የታካሚው የቅርብ ወዳጆችም ‹‹ደም ለግሱና ደማችሁ ተተክቶ ለታካሚው ሌላ ደም ይሰጠው›› የሚለውን ሐሳብ ሲሰሙ ሃሳቡን ይሸሻሉ፣ ከልገሳው ያፈገፍጋሉ እንዲሁም ይፈራሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ደማቸው ተወስዶ እምብዛም ጥቅም ላይ መዋል የማይችል ግለሰቦች በደላሎች አማካይነት በሽያጭ ደም ይለግሳሉ፡፡ ደም ባንክ የእነዚህን ሰዎች ደም በምትክ ወስዶ ከባንኩ ለታካሚዎች ደም ቢሰጥም፣ በሕገወጥ መንገድ ተሸጦ ገቢ የተደረገው ደም ከሞላ ጎደል ይወገድ እንደነበር ባንኩ ይገልጻል፡፡
ይሁንና የዛሬ ዓመት ገደማ ብሔራዊ ደም ባንክ በጀመረው አዲስ አሠራር መሠረት፣ በመንግሥት የሕክምና ተቋም የሚታከሙ ግለሰቦች የሚያስፈልጋቸው ደም አለምትክ እንዲሰጣቸው አድርጓል፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ በሕገወጥ መንገድ አላግባብ ደማቸውን የሚሸጡ ግለሰቦችን አስቀርቷል፡፡
‹‹የቤተሰብ ደም ተተክቶ ደም ይሰጥ በነበረበት ጊዜ ደላሎች ደም እየሸጡ ከአንድ ሺሕ እስከ ሁለት ሺሕ ብር ድረስ ይቀበሉ ነበር፡፡ ይህንን መረጃ እኛም ልክ እንደ ኅብረተሰቡ በወሬ ደረጃ ነበር የምንሰማው፡፡ ግለሰቦቹን ለመያዝ ከፖሊስ ጋር ተጣምረን ብንሠራም ሕገወጦቹን ማግኘት አልቻልንም ነበር፤›› ያሉት የብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶ/ር ዳንኤል ገብረ ሚካኤል፣ በአሥራ አንድ ወር የሥራ አፈጻጸም ጊዜ ውስጥ የበጎ ፈቃደኞች ደም ልገሳ ከመቼውም በላይ ጨምሮ ሕገወጦቹ ከጨዋታ ውጪ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
ምትክ ደም መስጠት ከመቅረቱ በፊት ከበጎ ፈቃደኞች በዓመት የሚሰበሰበው ደም 30 በመቶ አይሞላም ነበር፡፡ ዶክተር ዳንኤል እንደሚሉት ይህ ዛሬ ተቀይሯል፡፡ ምትክ ደምን የማስቀረት ሥራ ሙሉ በሙሉ በመሳካቱ ባለፉት 11 ወራት በነበረው አፈጻጸም በአገር አቀፍ ደረጃ ከበጎ ፈቃደኞች የተሰበሰበው የደም ብዛትም 68 በመቶ ደርሷል፡፡ ቀሪውንም 32 በመቶ ደም ከበጎ ፈቃደኞቹ ለመሰብሰብም ቀላል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ደም መለገስን በተመለከተ የማኅበረሰቡ አመለካከት እየተቀየረ እንደሆነ የመሰከሩት ዳይሬክተሩ፣ ከ120 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን በመስጠት ለውጥ ማምጣት እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ከመንግሥት ተቋማት፣ ከግል ተቋማት፣ ከጤና ተቋማት፣ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከኮሌጆች የተውጣጡ ናቸው፡፡
አገሪቷ በ350 እና በ450 ሚሊ ሊትር የሚለኩ 850 ሺሕ ከረጢት ደም በዓመት ያስፈልጋታል፡፡ ይሁንና እስከ ዛሬ ድረስ ማሳካት የተቻለው ከ85 እስከ 86 ሺሕ ከረጢት ብቻ ነው፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው የበጐ ፈቃደኞች አለመበራከት ነው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ 850 ሺሕ የደም ከረጢት ቢያስፈልግም ደምን በቋሚነት የሚለግሱ በጎ ፈቃደኞች ግን ሦስት ሺሕ ብቻ ናቸው፡፡ አንድ ሰው አንዴ ደም ከለገሰ በኋላ ድጋሚ መለገስ የሚችለው ከሦስት ወራት በኋላ ሲሆን አዲስ አበባ ብቻ በሥርዓቱ የሚስተናገዱ 50 ሺሕ በጐ ፈቃደኞች ያስፈልጓታል፡፡
ሌላው ምክንያት ደግሞ የ44 ዓመት ዕድሜ ያለው የደም ባንክ በስሩ ያሉት አጠቃላይ የደም ባንኮች ቁጥር 25 ብቻ መሆኑ ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ስምንት የሚሆኑት ሥራ የጀመሩት ገና ዘንድሮ መሆኑን ዶ/ር ዳንኤል ተናግረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የኅብረተሰቡ ደም የመለገስ ልምድ እየተሻሻለ ቢመጣም በከፍተኛ ደረጃ አለማደጉ ተግዳሮት እንደሆነ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
ባንኩ ከሚሰበስበው ደም ውስጥ ዘጠኝ በመቶ የሚሆነውን ያስወግዳል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ የሄፒታይተስ ቢ፣ የሄፒታይተስ ሲ፣ የኤችአይቪና በቂጢኝ ኢንፌክሽኖች አማካይነት እንደሆነ ዶ/ር ዳንኤል ተናግረዋል፡፡
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በተከበረው ‹‹የዓለም የደም ለጋሾች ቀን›› ላይ በአዲስ አበባ 1300፣ በባህርዳር 200፣ በመቀሌ 300፣ በድሬዳዋ 300 እንዲሁም በሌሎች ከተሞች ላይ ደም ከለጋሾች ተሰብስቧል፡፡ (ሪፖርተር)
Leave a Reply