• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

ማንነት (identity)

December 29, 2013 11:03 am by Editor 5 Comments

አዲሱ ዓመት መጣና ፤ ጎረቤቴን የሰፈሬን ልጅ

እንኳን አደረሽ ብላት ፤ መልካም ምኞቴን ሳውጅ

እኛን አያገባንi ብትለኝ ፤ እንዴት? ለምን? ብየ ጠየኳት

አታውቅም ? በእኛ ሃይማኖት ፤ ጃንዋሪ ላይ ነው አዲስ ዓመት

ብላ ብትለኝ ደንግጨ ፤ ሆኘ ቅርት የጨው ሀውልት

አየ አዲስ ዓመት እንቁጣጣሽ ፤ በምድሪቱ ሳይቀር ተበሳሪ

ተፈጥሮ አጅቦ የሚያመጣት ፤ በአበባ ልምላሜው ከባሪ

የእኛ አይደለሽም ተባልሽ ? እዚሁ በምድርሽ በቅሎ

ማዛሽ ማዛው ላይ እየናኘ ፤ ከአፈር አየርሽ ኮብልሎ

ምን ሳይሰማ እንዲሉ ፤ እንዲህም መቷላ ጉድ ፈጦ

መለያን ከስሩ ነቃቅሎ ፤ ልብን ከልብ ላይ ቆርጦ

አሁን ይህችን ልጅ እኅቴን ፤ ማን ናት ምን ብየስ ልጥራት

እነሱስ ሰባኪዎቿ ፤ ሰላዮቹ የቅኝ ግዛት

ማን ብለው ይሆን ትውልዷን ፤ የሷን ዜግነት የሚያውቁት

ኢትዮጵያዊት እንዳልላት ፤ የኔ አይደለም አለች እሴቱ

አውሮፓዊት እንዳልላት ፤ የቆዳ ቀለሟ ማሚቱ

መለስ ብየ ባጤናት ፤ ሁሉን ነገራችን ጥላለች

ከስሟ እስከ ባሕሏ ፤ ምዕራባዊ አድርጋለች

የቀረ ነገር ቢኖራት ፤ ያልተቻላት ልትለውጠው

ከልዩ የቆዳ ቀለሟ ፤ ኢትዮጵያዊነቷን ከሚያሳብቀው

እስከ ግርማዊያን ዓይኖቿ ፤ ካሜራ ሳይቀር ከሚፈራውIdentity

አካል ሰውተቷ ብቻ ነው ፤ የአምላክ ሥራ የሆነው

የሕዝቧን ማንነት ቅርስ ፤ የሀገሯን ሀብት ሁለመና

ታሪኬ ቅርሴ እሴቴ ፤ ካላለች ሰጥታ ዕውቅና

ማንነት መለያ ባሕሌ ፤ ብላ ካልጠበቀች ጀግና

እኮ በል ምን ታደርጋለች ፤ በእኛ ስም ደምና ቁመና

በእኛ ሰገነት መድረክ ላይ ፤ በአርያም ባለው ልዕልና ፡፡

ሃይማኖት ቢቀየር ቢለወጥ ፤ ምን ይሁን የፈቃድ ነውና

ሃይማኖት ቀየርኩ ተብሎ ፤ ማንነት መለወጥ ግና

ይሄ የእብደት ነው ወገኔ ፤ ፍጹም አይደለም የጤና

ሃይማኖት ማለት ለሁሉም ፤ ሲወዱ የሚቀበሉት

ሳይወዱ ደሞ የሚተውት ፤ ነው የማንነት ጉልላት

እንደ አያት ቅምቅማቶችህ ፤ ብትጠብቀው ደግ ነበረ

የማንነት ቅርስ አሻራህ ፤ በእሱ ነውና የታሰረ

ከአንተ ወደዚያ ሄደ እንጅ ፤ በመልከጼዴቅ በዮቶር

ከዚያ እኮ ወዲህ አልመጣም ፤ ሃይማኖት ጥበብ አሥተዳደር

ባለማወቅ ወይ በሌላ ፤ ያን ሃይማኖትህን ብትቀይር

ባሕል ቅርስ መለያን ግን ፤ እንድትጠብቅ  በፍቅር

ኢትዮጵያዊነትህ ግድ ይልሀል ፤ ዜጋ መሆንህ ለሀገር

ያያትህ አሻራ ነውና ፤ ይኖርበታል መከበር

ይሄ ነው እንግዲህ ማንነት ፤ የራስ መለያ ሀብት ስር

እንደዚህ አርገህ ካላመንክ ፤ ወጣ ባልክ ጊዜ ለሥራ

ምን ብለህ ልታወጋ ነው ? እኛ እኮ ብለህ ስታወራ

ፉክክሩ ሲያጋጥምህ ፤ የከኔ ታንሳለህ ፉከራ

መናቅ መገዳደር ሲጋፋህ ፤ ምንም እንደሌለህ ስትጠራ?

አንገትህን ልትደፋ ነው ? ምንም እንደሌለው ደሀ?

ባዶ እንደሆነ ሁሉ ? አንድ እንደሌለው ዘሀ ?

እንዲህ ያደረክ ጊዜ ፤ ልመሳሰል ብለህ ልጠጋ

የሞትከው ያን ጊዜ ነው ፤ ነፍስ የተለየችህ ከሥጋ

የሚንቀሳቀስ በድን ነህ ፤ ግዑዘ አካል ዲንጋ

አለሁ እንዳትል ሞተሀል ፤ በማንነት ቀውስ አደጋ

ለሆድህ ስትል ከካድካት ፤ ማንነትክን ከጣልክ ፈራርሳ

ሰብአዊ እሴት ከሌላቸው ፤ በምን ትለያለህ ከእንስሳ ?

በል እራስህን ታዘበው ፤ የሰውነትህን ደረጃ

የብስለትህን ርቀት ፤ በዕውቀት ሚዛን ፍረጃ

ጽናት ጥንካሬ የሌለው ፤ ሆነሀልና ሳር ሙጃ

ሰው ነው በሉኝ እንዳትለን ፤ ምን እንደሆንክም እንጃ

ኢትዮጵያዊነት ማለት ፤ በሽ የወረቀት አዋጅ

እንዲህ ሆንኩ እንዲህ ቢሉትም ፤ ለሥጋዊ ሕይዎት እንዲበጅ

የማይለወጥ ቀለም ነው ፤ ጥቁር ቀይዳማ ጠይም

በፍላት የሚንተከተክ  ፣ አካልህን የሞላው ደም

ፍቀህ የማታጠፋው ፤ ተፈስሶ የማይፈጸም

መቸም የማይለዩት ፤ የእግዚአብሔር ማኅተም

ቆዳየን ገፍፌ ልጣል ፤ ዐይኔንም ጓጉጨ ላውጣ

እንዲህ ሳያሰኛት እብደቷ ፤ ራሷን በአደጋ ሳትቀጣ

ባካቹህ ምከሩ አስተምሩ ፤ ምን ማለት እንደሆን ማንነት

በማንነት ቀውስ ስትናጥ ፤ ምንድን ነው ዝም ብሎ ማየት ?

ከመንጋው ጠፍቶ የሄደ ፤ ሌላ ለመሆን የከጀለ

የትም ቢሔድ ባይተዋር ነው ፤ ለብቻው የተነጠለ

ትርፉ ማበድ ብቻ ነው ፤ ከሁለት ሳይሆን የነሆለለ

ከቶም ተለይተሸ ላትለይ ፤ ሆነሽ ላትሆኝ ሌላ

ምንም አማራጭ የለሽም ፤ ድመቂ በራስሽ ገላ

ኩሪ በማንነትሽ ፤ አያዋጣሽም ኩብለላ

ሌላው የሌላ ነው እቴ ፤ የአንችው ብቻ ነው የአንቺ

ማንነት ክብርሽን ጠብቂ ፤ ወደሽ ያዠ እንጅ አታመንቺ

የምዕራቡ የእነሱ ነው ፤ የዓረቡም ደሞ የዓረብ

እንደጆንያ ስልቻ ፤ ማንም የራሱን ትብትብ

ለምን ጠቅጥቆ ይሙላብሽ ፤ የራስሽን አስጥሎ ጥበብ

አንችም በርትተሽ ብትሠሪ ፤ እንደነሱ ሁሉ ጠንክረሽ

መለያየት መገነጣጠል ፤ እርስ በርስ መቧጨቅ ትተሽ

እንኳንና ተሳክቶልሽ ፤ ሆነሽ ሀብታም ገናና

በድህነትሽ ላይ እንኳን ፤ በሰበረሽ ባሳጣሽ ዝና

በነባር ታሪክሽ ተማርኮ ፤ ስንቱ መጥቷል እየቀና

ኢትዮጵያዊ ነኝ እያለ ፤ ያለ ትውልዱ በልመና

አልሰማሽውም ማንዴላን ፤ ማርክስ ጋርቤይን ማልኮልምኤክስ

ቦብ ማርሌይን ሉተር ኪነግን ፤ ማን የቀረ አለ ከሚወደስ

ኢትዮጵያዊ መልኩን ሲባል ፤ ነብር ደሞ መዥጎርጎሩን

ይለውጥ ዘንድ ይቻላል ወይ ? ብሎ ሲጠይቅ የአምላክ ቃል

እኛን ነጥሎ ሲጠራ ፤ ምንን መናገሩ መስሎሻል ?

ነጩ ቢጫው ጥቁሩ ቀዩ ፤ የቆዳ ቀለሙንማ

ማንስ ቢሆን ለመለወጥ ፤ ይችላል እንዴ ስንሰማ ?

መልኩን መቀየር መለወጥ ፤ ማንም ሕዝብ ቢሆን ካልቻለ

ምን ማለቱ ነበር ታዲያ ? ኢትዮጵያዊ መልኩን ያለ ?

መልክ ያለው ማንነት ነው ፤ የራስ መለያ አሻራ

ኢትዮጵያዊ አይቻለውም ፤ ያንን ቀይሮ ሊሆን ተራ

አንዴ በመጻኢ ስደተኛ ፤ አንዴ በሲራራ ነጋዴ

አንዴ በሰላይ ሚሲዮን ፤ ተወስዶ አለቀ ክናዴ

ጣራ መሠረቴ ተናጋ ፤ ስለወዳደቀ አዕማዴ

ብላ ትጣራለች ኢትዮጵያ ፤ ልጆቸ ታደጉኝ ከጉዴ

ወገን ታጠቅ ለዘመቻ ፤ እንቢልታ መለከት ንፋ

ምርኮኛህን ለመመለስ ፤ አንተም ተማርከህ ሳትጠፋ

ይሄንን የሚያህል ነውር ፤ ለመነገር ደርሶ በይፋ

ምን ደርሶብሀል ወገኔ ? ከዚህ ኪሳራ የከፋ ?

ከዚህ ጦርነት የከበደ ? ጥይት ሳይጮህ ሳይሰማ

ወገንን ማርኮ ከሚያግዝ ፤ ሀገርህን ከሚያደር ባድማ ?

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

መስከረም 2000 ዓ.ም.

amsalugkidan@gmail.com

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Literature Tagged With: Right Column - Primary Sidebar

Reader Interactions

Comments

  1. kuku says

    December 31, 2013 04:06 pm at 4:06 pm

    እጅግ ድንቅ ነው ማንነታችንን መዘንጋት አያስፈልገንም የራሳችን የቀን አቆጣጠር ያላት በጀግኖችተከብራ የኖረች ቅኝ ግዛት ያልተገዛች ድንቅ ውብ አገር አለን የራሳችን ባህል የሚያኮራን ኩሩ ኢትዮጵያዊያን ነው የራስ ሁሌም የራስ ነው በራሳችን ዘመን አቆጣጠር እንኮራለን :: ማንነትን ፈልጎ ማግኝት መልካም ነው ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !

    Reply
  2. wey Gud says

    January 3, 2014 01:40 am at 1:40 am

    yetu new ye Egna yetebalew ?

    Andu ye emperor Julian ye zemen qimir aqotater new.
    Lelaw degmo ye Gregorian ye zemen aqotater new !!
    Tadia emperor Julian newot woyis Gregorious Ethiopiawi……………?!

    Wey Gud ………..jero yemaysemaw yele !

    Reply
    • ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው says

      January 12, 2014 07:37 am at 7:37 am

      ወዳጀ የገዛ ማንነትህን ከማጣጣልህ በፊት ስለማንነትህ በቂ ግንዛቤ ቢኖርህ መልካም አይመስልህም ? የጁሊያን የዘመን መቁጠሪያ ጁሊየስ ቄሳር(የሮም ንጉሥ) ከ 2052 ዓመታት በፊት ላይ የጀመረ ነው ፡፡ የጎርጎርዮሳዊያን (የግሪጎሪያን) የሚባለው ደግሞ በ365 ዓ.ም. ከ1641 ዓመታት በፊት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አባት የሆነው ጎርጎርዮስ አስቀድሞ ሲጠቀሙበት ከነበረው ከጁሊያኑ የዘመን መቁጠርያ ስሌት ላይ ከዓመቱ 11 ደቂቃ ከ14 ሰከንዶች በማንሣት አረምኩ ብሎ የቀመረው የዘመን አቆጣጠር ቀመር ነው ፡፡
      እነኝህን ሁለት የተለያዩ የመሰሉህን የዘመናት አቆጣጠር የመጀመሪያውን ማለትም ለሁለተኛው መሠረት የሆነውን የጁሊያኑን የዘመን አቆጣጠር የቀመረው በንጉሡ በጁሊየስ ቄሳር ትእዛዝ መሠረት ከግብፅ አሌክሳንድሪያ የሥነ-ከዋክብት ሊቃውንት አንዱ የነበረው ሶሲጂነስ ነው ፡፡ ለግብፃዊያኑ ደግሞ መሠረት የሆነው እኛ ኢትዮጵያዊያኑ ነን ፡፡ ይሄንንም የራሳቸው የግብፃዊያኑ የዘመን አቆጣጠር ሊቅ የሆነው አቡሻክር በስሙ በተሰየመው መጽሐፉ ላይ ጠቅሶታል ፡፡ የእኛ የዘመን አቆጣጠር ከአዳም ጀምሮ ሳይቋረጥ በትውፊት የመጣ ከ7506 ዓመታት በፊት ጀምሮ የነበረ ነው ፡፡ አመሰግናለሁ

      Reply
  3. ezra says

    January 5, 2014 05:32 pm at 5:32 pm

    በጣም የተዋበና የደም ሥርን ሁሉ የሚነዝር ግጥም ነው።
    እንዲህ ነው እንጅ ግጥም ፡
    ከልብ ጋር የሚገጣጠም።

    በጣም እናመሠግናል

    Reply
  4. Daniel michiel says

    January 23, 2014 12:20 pm at 12:20 pm

    Wede Maninetachinn yemimelsen denk akerareb new…….. TEBAREK

    Reply

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • የእምዬ ምኒልክ አዳራሽ October 30, 2023 10:27 am
  • የኢትዮጵያ መከላከያ መሥራች አጼ ምኒልክ መሆናቸውን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ተናገሩ October 26, 2023 01:30 pm
  • ጥቅምት 15 ለምን? October 26, 2023 01:29 am
  • “በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የሚፀና የድል ሠራዊት” October 26, 2023 12:57 am
  • “ውትድርና ሕይወቴ ነው” October 26, 2023 12:13 am
  • መከላከያ በሁሉም መስክ ኢትዮጵያን የሚመጥን ኃይል እየገነባ ነው October 20, 2023 05:07 pm
  • “ሁሉም ኢትዮጵያዊ ትምህርት ቤት እኩል ነው በችሎታው ነው እንጂ የሚመዘነው” ፕ/ር ብርሃኑ October 20, 2023 04:47 pm
  • 42 የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አመራሮች እና ሠራተኞች ታሰሩ October 18, 2023 04:29 pm
  • በተማሪዎች ፈተና ውጤት ለታየው ውድቀት ትምህርት ሚ/ር ኃላፊ መሆን አለበት ተባለ October 18, 2023 04:00 pm
  • ቀይ ባሕር እና ዓባይ “የኅልውና ጉዳይ ናቸው”፤ “መተንፈሻ ወደብ ያስፈልገናል” October 13, 2023 10:04 pm
  • ከ3,106 ትምህርት ቤቶች 1,328ቱ (44%) አንድም ተማሪ አላሳለፉም October 10, 2023 01:51 pm
  • “አቋጥሬ” በአማራ ክልል እያጫረሰ ነው፤ ” ኑሮውን መቋቋም አልቻልንም ” ነዋሪዎች October 10, 2023 09:07 am
  • እሸቴ አሸባሪ፤ ቲዲኤፍ/ትሕነግ “ሰማዕት” – የዘመናችን ጉድ! October 7, 2023 06:47 am
  • በወልቃይት 1.1ሚሊዮን ኩንታል ሰሊጥ ለመሰብሰብ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሠራተኛ ይፈለጋል September 27, 2023 10:42 am
  • በአማራ ክልል ሰላም ዕጦት ከ90.5 ቢሊዮን ብር በላይ ፕሮጀክቶች ቆመዋል September 27, 2023 08:41 am
  • ወርቁ አይተነው የሸሹት ከዝርፊያ፣ ውንብድናና ዕዳ ጋር በተያያዘ ነው September 21, 2023 02:38 pm
  • ወደ አማራ ክልል ሊተላለፍ የነበረ መሣሪያና ሰነድ ተያዘ September 19, 2023 04:35 pm
  • በትግራይ መርዶ በይፋ ሊታወጅ ነው September 19, 2023 04:22 pm
  • ጃርቶች ለምን ይጮኻሉ? September 19, 2023 04:37 am
  • “ዐቢይ ግድቡን ሸጦታል” ጌታቸው ረዳ September 11, 2023 10:18 am
  • አቶ አገኘሁ መረጃ አሳልፎ በመስጠት ዋጋ እንደሚከፍሉ ተሰማ September 10, 2023 06:52 pm
  • ለዋዜማ ሬዲዮ “ኢትዮጵያን ቋሚ የውሀ ባለ እዳ” ያደርጋል ያላችሁት ረቂቅ ሰነድ የታለ? September 10, 2023 01:58 am
  • ወደር የሌለው የኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ጀግና! ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ኃብተማርያም September 8, 2023 02:31 pm
  • የትግራይ መፍረስ በርዕሰ መስተዳደሩ አንደበት September 8, 2023 02:49 am

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2023 · Goolgule