ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ የዓለም የሰላም ኖቤል ሽልማታቸውን ሲቀበሉ ባደረጉት ንግግር ፕሬዚደንት ኢሣያያስ አፈወርቂ አወደሱ። «ይኽን ሽልማት የምቀበለው በኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ስም ነው። በተለይ ደግሞ ለሰላም ሲሉ ከፍተኛውን መስዋእትነት በከፈሉት ስም። በተመሳሳይ ሽልማቱን የምቀበለው በአጋሬና የሰላም ጓድ በኾኑት ፕሬዚደንት ኢሣያያስ አፈወርቂ ስም ነው» ብለዋል። ይኽ ንግግራቸውም ከታዳሚያን ሞቅ ያለጭብጨባ ታጅቧል። የፕሬዚደንት ኢሣያያስ አፈወርቂ «መልካም ፈቃድ፣ እምነት እና ቁርጠኝነት ለኹለት ዐስርተ-ዓመታት በሃገሮቻችን መካከል የዘለቀው መቆራረጥ እንዲያበቃ ወሳኝ ነበር።»
በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ጦርነቱ ሲከፈት ወጣት እንደነበሩ የተናገሩት ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ፦ በጦርነት አውድማ «ወንድም ወንድሙን ሲገድል» መመልከታቸውን ገልጠዋል። የጦርነት መራራ ገጽታን፤ የሰላምን ወሳኝነት አጉልተው ተናግረዋል። በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጦርነት የተነሳ ለኹለት ዐሥርተ-ዓመታት ተለያይተው የነበሩ ቤተሰቦች መገናኘታቸውን፤ «ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ እንደ አዲስ መጀመሩንም» ጠቅሰዋል። የአየር እና የቴሌኮሙኒኬሽን ግንኙነት በኹለቱ ሃገራት መጀመሩንም በንግግራቸው አሰምተዋል።
«በአኹኑ ወቅት ትኩረታችን የጋራ መሠረተ-ልማትን ማጎልበት ላይ ነው» ብለዋል። ይኽም የሃገራቱ የምጣኔ ሐብት ትልም መኾኑን አጽንዖት ሰጥተውበታል። ስለመደመር አስተሳሰባቸውም ለታዳሚያኑ ገለጣ አድርገዋል። በአማርኛም፦ «በሰላም እንድታድር ጎረቤትህ ሰላም ይደር» እንላለን ሲሉ ታዳሚያን በጭ ብጫባ አጅበዋቸዋል። አባባሉን በኦሮሚኛ ሲደግሙት ከአዳራሹ ዳግም ጭብጨባ ታጅበው ነበር። ይኽ አባባል አብዛኛው የአፍሪቃ ሃገራት የሚጋሩት መኾኑንም ጠቅሰዋል።ይኽ ምሳሌያዊ አባባል በቃጣናው ሃገራትን ትብብ ትብብርን ለማጠናከር መሪ ነው ብለዋል።
የአፍሪቃ ቀንድ የሰላም እና የብልጽግና ማዕከል ኾኖ በሌሎች አፍሪቃ ሃገራት በአብነትነት ሲወሰድ ማየት ትልማቸው እንደኾነ ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ፦ “ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች ፈትተናል፤ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የሚፈጸሙባቸው ማሰቃያዎችን ዘግተናል” ብለዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ “የታሰረ ጋዜጠኛ የለም” ሲሉም አክለዋል። “ለእውነተኛ መድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲ መሰረቱን አደላድለናል በቅርቡም ነጻ እና ፍትኃዊ ምርጫን እናካሂዳለን” የጽንፈኝነትን እና የከፋፋይነትን መንገድ ማስወገድ እንደሚገባም ተናግረዋል። በማጠቃለያቸውም በአፍሪቃ ቀንድ ሰላም እና ብልጽግናን ለማስፈን የ«መደመር» አስተሳሰባቸውን ዓለም አአፉ ማኅበረሰብ እንዲቀላቀል ጥሪ አስተላልፈዋል። «ሰላም ለሁላችን» ሲሉም በአማርኛ እና ኦሮሚኛ ተናግረው ረዘም ያለ ንግግራቸውን ቋጭተዋል።
(DW)
Leave a Reply