
በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን በሌሙና- ቢልቢሎ ወረዳ ሌሊት ላይ መኖሪያ ቤት የገባ አንድ ጅብ በሰውና በቤት እንስሳት ላይ ጉዳት ማድረሱን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ኢንስፔክተር ጎሳ አማን እንደገለጹት፥ ጅቡ በሰውና እንስሳት ላይ ጥቃት ያደረሰው በሌሙዲማና ሁላሃሳ የገጠር ቀበሌ ነው።
የካቲት 10 ቀን 2007 ከሌሊቱ 10 እስከ 11 ሰዓት በሁለት አርሶ አደሮች የእንስሳት በረትና መኖሪያ ግቢ በመግባት በሁለት አባወራና ስምንት የቤት እንስሳት ላይ ንክሻ መፈጸሙን ገልጸዋል።
አርሶ አደሮቹ የቤት እንስሳቱን ከጅቡ ለማስጣል በገጠሙት ግብ ግብ የተደናገጠው ጅብ ወደ ጭላሎ ተራራ ሊያመልጥ መቻሉን አስታውቀዋል።
ከአርሶ አደሮቹ መካከል አንደኛው ብልታቸው ላይ ሌላው አርሶ አደር ደግሞ በሆዳቸውና ሌላ አካላቸው ላይ በደረሰባቸው ጉዳት አሰላ ሆስፒታል ህክምና በመከታተል ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ከቤት እንስሳቱ መካከል አራቱ በደረሰባቸው ጉዳት ወዲያውኑ ሲሞቱ፥ ቀሪዎቹ ህክምና ተደርጎላቸው በማገገም ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
እንዲሁም በዚሁ የገጠር ሁላሃሳ ቀበሌ ትናንት ከምሽቱ ሁለት ሰአት አካባቢ አንድ ጅብ በአንድ አርሶ አደር መኖሪያ ግቢ በመግባት ተመሳሳይ ጉዳት ማድረሱን ኢንስፔክተር ጎሳ አማን ገልጸዋል።
በእንስሳቱ በረት ጅብ መግባቱን የሰሙት አርሶ አደር መሐመድ አማን ከበረት አባረው ሲያስወጡት መኖሪያ ቤት በመግባት በባለቤታቸው፣ የሁለት ወር ሕጻናን ጭምሮ በሦስት ልጆቻቸውና ሁለት ጎረቤቶቻቸው ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቀዋል።
አባወራው ጅቡን በስለትና ዱላ ደብድበው እንደገደሉት አስታውቀው፥ ከፍተኛና መካከለኛ ጉዳት የደረሰባቸው ስድሰቱ ሰዎች አሰላ ሆስፒታል ገብተው ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የአርሲ ዞን እንስሳት ሀብት ልማትና ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር አብዲ ዩሱፍ በሰጡት አስተያየት የዱር እንስሳት መጠለያ የሆነው ደን ከተመናመነ ወዲህ የዱር እንስሳት ወደ ሰዎች መኖሪያ አካባቢ የመምጣቱ ሁኔታ የተለመደ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል። [አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2007 (ኤፍ.ቢ.ሲ)]
Leave a Reply