ከተወለድኩበት እለት ጀምሮ በቅጡ የማውቀው ጎጃሜነቴን ነበር። ከዚያ ልዩ የምጠራበት ስም እንዳለኝ የሰማሁት እያደር ነው። ሌላው ቀርቶ ኢትዮጵያዊ እንደምባል እንኳን የገባኝ ትምህርትቤት ገብቼ ሶስተኛ ወይም አራተኛ ክፍል ግድም ስደርስ ሳይሆን አይቀርም።
ከዚያም ሙት ወቃሽ እንዳልሆን ስማቸውን የማላነሳው ግን እጅግ የምወዳቸው ዖሮሞው የህብረት አስተማሪዬ የዛሬን አያድርገውና ኢትዮጵያ 14 ክፍለሀገሮች እንዳሏት ሲነግሩኝ ለካ ከጎጃም ሌላ ሀገር አለ ብዬ ደነቀኝ።
በኋላማ አማርኛ የማይናገር ወገን እንዳለኝ ሳስተውል ሆጃሜ ብቻ እንዳልሆንኩ በሚገባ መገንዘብ ጀመርኩ። ልባድርጉልኝ፣ እስካሁን ድረስ (አረ ምን እስከዛ ድረስ ብቻ እስከኋለኛው የስርአት ለውጥ ድረስ) አማራ ነህ ያለኝም፣ እኔም አማራ ነኝ ያልኩበት ጊዜ ትዝ አይለኝም። ብቻ በልጅነቴ አዋቂዎች ሲያወሩ (ያን ጊዜ ከአዋቂ ጋር እኩል ማውራት እንጂ አዋቂ ሲያወራ ማዳመጥ ይፈቀድ ነበርና) ከመካከላቸው አገር አውርቶ ለጨረሰው አንድ ጉዳይ እንግዳ የሆነ ሰው ሲያጋጥማቸው፥ ይህማ እስላም አማራው አውርቶ የጨረሰው ጉዳይ እኮ ነው፥ ሲሉ ትዝ ይለኛል። ከዛም አማራ ማለት ክርስቲያን ማለት እንጂ አማርኛ ተናጋሪ ማለት እንዳልሆነ ገብቶኝ አደግሁ። እዚህ ላይ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን ያስታውሷል። ፕሮፌሰሩ ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋር መከራከር ይቻል በነበረበት ጊዜ አማራ የሚባል ማንነት የለም ብለው መከራከራቸውን አስታውሳለሁ። እውነቱን ለመናገር እኔም ብሆን ዛሬም ስሜ የሚመስለኝ ሆጃሜነት እንጂ አማራነት አይደለም።
ዛሬ ግን ጨዋታው ተቀይሯል። እኔም ብሆን የኋላ ኋላ በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ የበረሃ የፖለቲካ መርሃግብር ላይ አማራ ስለሚባል ህዝብ በተለይ መስፈሩን፣ በደርግ ውድቀት ማግስት በየክልሉ አማራ የሚባል ህዝብ እየተለየ በጭካኔ መጨፍጨፉን፣ ከዚያም በኋላ በየጊዜው ይሄው ህዝብ ተለይቶ አንጡራ ሀብቱን በጉልበት እየተቀማ ከየክልሉ መባረሩን ስሰማ አማራ ሃይማኖት ሳይሆን ብሄር መሆኑ ገባኝ። ከዛም ሆጃሜነት መገኛዬ፣ አማራነት መጠሪያዬና ኢትዮጵያዊነት ጥላዬ መሆኑን አመንኩ።
የዛሬ መነሻዬ የብሄር ትንተና አይደለም። ስለሰሞነኛው ያማራ አርበኝነትና የብሄር አብዮተኝነትም ቢሆን ለጊዜው የምለው የለኝም። አማራ መደራጀት አለበት ወይስ የለበትም? በጎንደር በኩል ከመንግስት ጋር የሚዋጋው አማራ ነው ወይስ ግንቦት 7? በሚሉ የጅል ጥያቄዎችም ላይ ቢሆን የማጠፋው ጊዜ የለኝም። እነዚህ ጥያቄዎች ያላዋቂ ወይም የጅል ጥያቄዎች ናቸው የምልበትን ምክንያት ግን መጠቆም ሳይኖርብኝ አይቀርም። ምክንያቴን እነሆ።
ግቡ ህገወጥ እስካልሆነ ድረስ ወይም ለጥፋት አላማ እስካልታቀደ ድረስ ማንም ሰው ላመነበት አላማ መደራጀት መብት መሆኑ እየታወቀ አማራ ባማራነቱ ሊደራጅ አይገባም በሚል ዘራፍ ማለት በተለይ ስለሰባዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚያውቅ ሰው ተቃውሞውን ያላዋቂ ሊለው መብት ያለው ይመስለኛል። ይህም ብቻ አይደለም፤ አገር ምድሩ በየዘውጉ ተሸንሽኖ እኔ እኮ እገሌ እባላለሁ፣ እንቁልጭጫችሁ እያለ ባማራው ላይ ሲቀልድና አልፎም ሀገር እንደሌለው ካገር ውጣ ሲባል ለመሆኑ እኔ ማነኝ? ሀገሬስ የት ነው ብሎ መጠየቅ ነውር ነው ሲባል ያናድዳል። በሌላ በኩል ደግሞ መንግስትን የሚወጋው አማራ ነው ወይስ ግንቦት ሰባት የሚለውም ቢሆን ነጥብ ለማስቆጠር የሚደረግ ገና ያልተሰራ ታሪክ ለመሻማት የሚደረግ ልላኛው መንትያ የጅልና የስግብግቦች ጥያቄ ነው። አሁን ይህን ጉዳይ በቀጠሮ ትቼ የተነሳሁበትን ጉዳይ ልናገር።
እኔን ያሳሰበኝ አዲስ ያማራ መብት ተሟጋቾች ወይም አርበኞች መነሳት ጉዳይ አይደለም። ከንቅናቄው መጀመር በላይ እጅግ አሳሳቢው ጉዳይ የንቅናቄው መሪዎች ዲሲፕሊን ባማራው ህዝብ ጨዋነት፣ ሆደሰፊነትና ኩሩነት የደቀነው ግልፅ አደጋ ነው። ስጋቴን በሁለት ምሳሌዎች ላስረዳ፤ አንድ የእንቅስቃሴው መሪ የሰጡት ቃለመጠይቅና የቡድኖቹ እንደአሸን መፍላት።
ሰውየውን (ወጣቱን ልበል መሰለኝ) በስም ካልሆነ በአካል አግኝቸውም ሆነ በድምፅ ሰምቼው አላውቅም ነበር። ደራሲ፣ ያማራው ጠበቃ፣ አርበኛም ሲባል እሰማለሁ። ለነገሩ ከመሪነቱ ፅነፅሁፉ ያምርበት ነበር ያሉኝም ነበሩ። ብቻ መቼም ያላንድ ነገር ይህ ሁሉ መወድስ አይወርድለትም ብዬ እኔም አድንቄው ነበር።
በቅርቡ ለአንድ የሬዲዮ ጣቢያ ቃለመጠይቅ ሲሰጥ በሰማሁት ጊዜ ግን የፍቅር እስከመቃብሩ በዛብህ ቦጋለ ትዝ አለኝ። በዛብህ ከደብረወርቅ ከተማ ተነስቶ ወደዲማ ሲጓዝ ስመገናናው የዲማ ጊወርጊስ ደብር አነስተኛ መንደር ሆኖ ባገኘው ጊዜ፥ አይ ዲማ፣ ባላይህ ኖሮ እድሜዬን ሁሉ ሳከብርህ እኖር ነበር፥ እንዳለው ሁሉ እኔም ይህንኑ ወጣት ቃለመጠይቁን ሳልሰማ በተከታዮቹ ውዳሴ ሳከብረው ብኖር ይሻለኝ ነበር ማለቴ አልቀረም። ወጣቱ የሚናገረው በደም ፍላት ነው። የሚጠቀምባቸው ቃላት ያድማጭን ደም ያስቆጣሉ። አንዳንዶቹም ይዘገንናሉ። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን የወጣቱ ንግግር ባደኩበት ያማራ ባህል የማውቀው ጨዋነት የለውም። ባደኩበት ያማራ ባህል የ60ና የ70አመት አረጋውያን በመጀመሪያ ስማቸው ብቻ አይጠሩም። አንተ ወይም አንቺም አይባሉም። ተናጋሪው እነአቶ ሌንጮ ለታን፣ እነ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋንና ሌሎችንም የእድሜ ባለፀጎች ያለማንጠልጠያ ሲዘረጥጣቸው መስማት እጅግ ይዘገንን ነበር።
ያማራ ህዝብ ታላላቆቹን ቀርቶ ታናናሾቹን እንኳ አንቱ የሚልበት ጊዜ አለ። ያማራ ህዝብ አንደበቱ የተገራና ትህትና ያለው ነው። ጠላቱን እንኳን የሚያናግረው በጨዋ ቋንቋ ነው። አይባልግም።
ይህን ጨዋ ህዝብ ባደባባይ ወክሎ ለመናገር ጨዋነቱን መላበስ ያስፈልጋል። አማራን መወከል ከነክብሩ ነው። አማራ ሲሟገት እንኳን በጨዋነት ነው። በጨዋነቱም ይረታል። ለዚህም ነው ካነጋገር ይፈረዳል ካያያዝ ይቀደዳል ሲል ያንደበት ልእልናን የሚነግረን። ከዚህ አንፃር ከአዲሶቹ የአማራ ብሄርተኝነት መሪዎች መካከል አንዱ የሆነው የዚህ ወጣት ንግግር ግን ያማራ ጨዋነት፣ ሰው አክባሪነትና ትህትና አልነበረውም። በዚህም ምክንያት ባቀራረቡ የሚወክለውን ኩሩ ያማራ ህዝብ እውቅ እሴቶችን የወረሰ መሪ ሳይሆን በውዳሴ ከንቱ የነገሰ የእብሪትና ትእቢት ተናጋሪ አስመስሎታል። በዚህም ደንግጫለሁ።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ በየጊዜው የሚነሱ የእውቀት ሳይሆን የስሜትና የጉልበት መሪዎች ብዙ መከራ አድርሰውብናል። ዛሬም መዘዙ አለቀቀንም። እናም እኒህ አዲስ ያማራ ንቅናቄ መሪዎች በዚህ አያያዛቸው ባማራው ህዝብ ታሪክ፣ ባህልና ክብር ላይ የማይመለስ ጉዳት እንዳያደርሱ ስጋት አለኝ። ከጀግንነትና የማይናወጥ ሀገራዊ ፍቅር በቀር ሌላ አበሳ ለሌለበት መከረኛ ህዝብ መብትና ክብር መቆማቸው ሲያስመሰግናቸው አያያዛቸው ጠበኝነት፣ እብሪትና ግንፍልተኝነት ያየለበት ስለሚመስል አሳሳቢ ነው። የሚወክለን ካለ ስማችንን ብቻ ሳይሆን ጨዋነታችንን ጭምር መውረስ አለበት። በዚህ ላይ አጀንዳው በተነሳ ማግስት ትግሉ አንዲት ጋት እንኳን ሳይራመድና ስራው እፍኝ ሳይሞላ ድርጅቶቹ ደረብ አኻዝ ሊሞሉ መቃረባቸው ሲታከልበት አደጋውን የበለጠ ያገዝፈዋል። ጎበዝ መፋቀር ቢያቅተን እንዴት በስነስርአት መጣላት እንኳን ያቅተናል?!
ህሩይ ደምሴ (zobar2006@gmail.com)
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
አለም says
ውድ ህሩይ፣
የሚገርመው ይህ ያንተ የሕይወት ልምድ የአብዛኛው ወጣት ልምድ መሆኑ ነው። ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ ደብረ ብርሃን ወይም ጊንጪ ያለ የሚያስበው መንደርተኛነትን እንጂ ብሔረተኛነትን አይደለም። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሲገባ፣ በዘመቻና በሥራ ሲመደብ ያኔ ከየክፍለ ሃገሩ የመጣውን በማየት ከአገራችን ወርድና ስፋት ጋር ይተዋወቃል። ይህ እድል ያጋጠመው ጥቂቱን ክፍል ብቻ ነው። አብዛኛው አንተ በገለጽከው ሁኔታ የሚገኝ በመሆኑ ዛሬ ለሚያወናብዱ ሰለባ ሆኗል። መፍትሔው እንደ ጀመርከው መጻፍና መናገር ነው። በመነጋገር ውስጥ ዋሾው ይገለጣል። መንግሥት የመገናኛ መስመሮችን አጥብቆ የተቆጣጠረው ለዚሁ ነው። ራሱ መርጦ በፈጠረው እውነት ትውልዱን እያደነቆረ ይገኛል። ቁምነገሩ እውነቱን መግለጥ ላይ ነው እንጂ መንግሥትና ተቃዋሚዎቹ እንደሚያደርጉት ውሸት መዝራት ከሆነ ምን ፋይዳ ይኖረዋል? በርታበት።
Tadesse says
wed wndme,and Eritrawi yetsafew lechmer,le mefaker emanchel kehone,tekebabren menor endet yaktenal.
Tadesse says
wede amarigna tergume new yetsafkut.