አንድ የኢህአዴግ ካድሬ፣ ቤት ለመከራየት ወደ አንዲት ወይዘሮ መኖርያ ይሄዳል። ስፍራው እንደደረሰ ሌላ ተከራይም ከወይዘሮዋ ቤት ብቅ እንዳለ አስተዋለ። ሌላኛው ተከራይ ሰይጣን ነበር። ሁለቱ ተከራዮች ሰርቪስ ቤቱን ለመያዝ እንደ ጨረታ ብጤ ጀመሩ። ሰይጣኑ 400 ሲጠራ፣ ካድሬው ግን 500 ሊሰጥ ተስማማ። በመጨረሻ፣ ወይዘሮዋ ቤቱን ለሰይጣኑ በትንሽ ዋጋ ማከራየቱን መረጡ። የወይዘሮዋ ውሳኔ እንግዳ ነገር ነበር። ለሰይጣን፣ ለዚያውም በትንሽ ዋጋ ቤታቸውን ለመስጠት የወሰኑበትን ምክንያት ሲጠየቁ፤ “ሰይጣኑ አልወጣ እንኳን ቢል በጸበል ይለቃል። ካድሬው ገብቶ ቤቴን አልለቅም ቢለኝ ምን ላደርግ ነው?” ነበር ያሉት ወይዘሮዋ። ከፍ ባለ ገንዘብ ለኢህአዴጉ ሰርቪስ ቤታቸውን ቢያከራዩት ኖሮ ባጭር ጊዜ ዋናውን ቤታቸውን ለቀው የመውጣት ክፉ እድል ይገጥማቸው ነበር።
ዶ/ር መረራ ጉዲና ባለፈው ሳምንት ዘ ሄግ ላይ ስለ ወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ ሲነግሩን ጣል ያደረጓት ቀልድ ናት። የዚህች ቀልድ የፖለቲካ እንድምታ ቀላል አይደለም። መልእክትዋ ሲጠቃለል የኢትዮጵያን ህዝብ እየለቀቀ መሆኑን ትነግረናለች። እየከፋ የመጣው የኑሮውና የፖለቲካ ሁኔታ የህዝቡን አእምሮ ብቻ አይደለም እየነካው ያለው። ህዝቡ እየተገፋ ሃገርሩን ለቆ እንዲሰደድ እየተገደደም ይገኛል። በተለይ ደግሞ ሃገሪቱ በድህነት ያስተማረቻቸው ምሁሮችዋንና ባለሞያዎችዋን እንደዋዛ እያጣች ከመጣች እነሆ ሁለት አስርተ-ዓመታት ተቆጠሩ።
እለተ ሰኞ የካቲት 10፣ 2006 ዓ.ም.።
የአለም ዜና ርዕስ ሁሉ ትኩረት የጣለው በኢትዮጵያዊው ፓይለት ጉዳይ ላይ ነበር። እንደዚህ አይነት ክስተት ሲፈጸም አዲስ አይደለም። ግን ይኽኛው ልዩ ነው። ይዘቱ ለየት ይበል እንጂ በ1998 (እ.ኤ.አ.) ዩዋን ቢን በተባለ ቻይናዊ ፓይለት ከተፈጸመው ድርጊት ጋር ይመሳሰላል። የ30 አመቱ ወጣት የበረራ ቁጥር CA905 የሆነውን የቻይና አውሮፕላን በመያዝ የታይላንድን የአየር ጠረፍ ሰብሮ ገባ። የ27 አመት እድሜ ያላት ሚስቱን ይዞ ታይዋን ላይ ያረፈው ፓይለት ለዚያ አደገኛ ውሳኔ የሰጠው ምክንያት የኢኮኖሚ ችግር ነበር። የደረጃ እድገት፣ የደሞዝ ጭማሪ፣ የመሳሰሉ ከራስ ወዳድነት ያላለፉ ጥያቄዎች በማንሳት የፓይለቱ የራሱን ክብር ዝቅ አደረገው።
በ1995 (እ.ኤ.አ.) ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ በግዳጅ ከአውስትራልያ ወደሃገሩ እንዲመለስ ተደረገ። ኢትዮጵያዊ ግን የኦሎምፒክ አየር መንገድ ንብረት የሆነውን ጀት ግሪክ ላይ ለመጥለፍ በመሞከሩ የአለምን ዜና ርእስ ሆኖ ነበር። ጋዜጠኛው የፕላስቲክ ቢላዋ የበረራ አስተናጋጅዋ አንገት ላይ በመደገን ወደ ሀገሩ እንዳይላክ ጥያቄ አቀረበ። በመጨረሻም ኢትዮጵያዊ ወገን ባደረገው ርብርብ የዚህ ወጣት አላማ ተሳካለት።
የሃይለመድህን አበራን ጉዳይ ለየት የሚያደርገው ለዚህ ከባድ ውሳኔ የሰጠው ምክንያት ነው። የግል ሳይሆን የሃገር፣ የራስ ሳይሆን የወገን ጉዳይ። ረዳት ፓይለቱን እብድ ያሰኘውም ይኸው ነገር ይመስለኛል። ሃይለመድህን የ40 ሺህ ብር ደሞዝተኛ ነው። በኑሮው ምንም የጎደለበት ነገር የለም። ከመካከለኛው ኢትዮጵያዊ ዜጋ በላይ ይኖራል። የስደት ጥማት እንኳን ቢኖርበት ለመሰደድ በዚህ ሁኔታ አውሮፕላን ማገት እንደማይኖርበት ጠንቅቆ ያውቃል። ለዓለም ህዝብ ማስተላለፍ የሚፈልገው አንድ መልእክት ነበር። “ሜይዴይ … ሜይዴይ … የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር ላይ ነው!”
ተልእኮው በሚገባ ተሳክቷል።
ሰኞ ማለዳ የመስርያ ቤታችን የውይይት ርእስ የነበረው ጄኔቭ ላይ ሳይታሰብ ያረፈው ቦይንግ 767 ጉዳይ ነበር። የረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራ ታሪካዊ ውሳኔ የስራ ባልደረቦቼን ከሁለት ጫፍ ከፍሎ ለረጅም ውይይት ጋብዟቸውዋል። አንደኛው ወገን ፓይለቱ ያደረገው ጠለፋ ነው ብሎ ሲከራከር፤ ሌላኛው ወገን ደግሞ ድርጊቱ እንደጠለፋ መታየት የለበትም ይላል። የሁለቱን ወገን ክርክር እየሰማሁ ምንም ሳልተነፍስ ለረጅም ግዜ ቆየሁ። አእምሮዬ ግን አንድ ነገር ላይ ተጠምዶ ነበር። ክስተቱ ለፖለቲካ ደንታ የሌላቸውን እነዚህ ነጮች ማነጋገር መቻሉ እጅግ ደንቆኛል። “ወጣቱ ፓይለት ምን ያህል በደል ቢበዛበት ይሆን ለዚህ ካባድ ውሳኔ የበቃው?” የሚለው ጥያቄ በብዙዎች አእምሮ ይመላለስ የነበረ ጉዳይ ነው። አብዛኞቹ ስለ ኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ሁኔታ በደንብ እንዲረዱ ማድረጉም አልቀረም። ጅብ በቀደደው ውሻ ይገባል’ ነውና ሁሉንም ነገር ለማስረዳት አሁን በጣም ቀላል ሆነ።
ሃይለመድህን አበራ ‘እብድ ነው’ የሚሉም አልጠፉም፤ ልክ እንደ አፈቀላጤው ሬድዋን። ለነጮቹ ነገሩ እንግዳ መሆኑ አልቀረም። ፓይለት ሆኖ፣ ጥሩ ኑሮ እየኖረ፣ ቤት – ንብረቱን፤ የሚወዳት ሃገሩንና ቤተሰቡን ትቶ ለእስራት፣ ለስደትና ለእንግልት ራስን ማዘጋጀት እብደት ነው ሊባል ይችላል።
በኢትዮጵያ ተመክሮም የፓይለት ሞያ ያስከብራል። በሃገራችን የፓይለቶች የኑሮ ደረጃ አንደኛውን ረድፍ ይይዛል። ይህንን የመሰለ ህይወት ጥሎ የስደትን ኑሮ መምረጥ የሚያስችል ውሳኔ ላይ መድረስ ደግሞ እብድ ቢያስብል የሚደንቅ አይደለም። የሚገርመው የስርዓቱ ካድሬዎች ይህንን አባባል መደጋገማቸው ነው። ከራሳቸውም አልፈው የፓይለቱ ቤተሰቦችን በማስፈራራት ይህንን እንዲመሰክሩ ሲያደርጉ ይታያል። ወትሮውን በእብዶች መሃል አንድ ጤነኛ ሰው ካለ፣ እሱ እብድ ነው። እነሱ በሰብአዊ መብት ላይ ሲቀልዱ በዚያ የማይተባበራቸው ሁሉ እብድ ነው። ለህሊናው ሳይሆን ለመኖር ሲል ሰብአዊ መብቱ ላይ የማደራደር ሁሉ ሽብርተኛ – አልያም የአእምሮ በሽተኛ ነው።
እብድ ሰው ያንን ግዙፍ አውሮፕላን በስርዓት አብርሮ፤ በስርዓት ካሳረፈ፤ በኢትዮጵያ ፓይለት ለመሆን የቅጥር መስፈርቱ እብድ መሆን ነው። ግና በአውሮፕላኑ የነበሩ 202 ተሳፋሪዎችን ምን እንደተፈጠረ እንኳን ሳያውቁት ጄኔቭ ላይ ማረፋቸው ብቻ እነሱ የሚሉት ይጻረራል። ሃይለመድህን ዋናውን ፓይለት በሃይል አላስገደደውም። ተሳፋሪዎች እንዳይረበሹም ስለድርጊቱ አንዳች ነገር አልተነፈሰም።
ለባለስልጣናቱ ጥያቄ አለኝ። የሃይለመድህን እብድ መሆኑን እያወቁ ለምን ፓይለት አድርገው ቀጠሩት? የእሱ እብድ መሆኑ ለባለስልጣኖቹ እንዴት አሁን ታያቸው?
ያም ታባለ ይህ – የካቲት 10፣ 2006 ዓ.ም. በስዊስ ላይ የተፈጠረው ነገር “ከሺ ቃላት… ” እንደሚሉት አይነት ነው። አንዲት ትንሽ ድርጊት የአለምን ህዝብ ከጫፍ እስከጫፍ አነጋገረች። ሃይለመድህን በአንዲት ቅጽበት እና በአንዲት ቃል ብቻ ላለፉት 20 አመታት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ይፈጸም የነበረውን ግፍ ሁሉ ለአለም አሳወቀ። ይህንን ለማድረግ ግን ራሱን መስዋዕት ማድረግ ነበረበት። ወጣቱ ሊደርስ የሚችልበትን ነገር ሁሉ አስቀድሞ ያውቀዋል። ከሃገር አመራረጥ ጀምሮ የወሰዳቸው እርምጃዎች በሙሉ የተጠኑ እና በጥንቃቄ የተደረጉ መሆናቸውን ሂደቱ ራሱ ይመሰክራል።
ወጣቱ ፓይለት ሃገሩን ይወዳል። የልጅነት ህልሙን እውን ያደረገበትን የፓይለትነት ሙያም ያከብራል። ለኢትዮጵያ አየር መንገድም የተለየ ክብር አለው። ራስ ወዳድ ቢሆን ኖሮ ፓይለት ሁሉ እንደሚኖረው በሃገሩ እየሰራ መኖር ይችላል። እንደ እብደት ያስቆጠረበት የዚህ ውሳኔ ምክንያቱ ግን ለህሊናው ብቻ ተገዥ መሆኑ ነው። ለሱ ቅርብ የሆኑትም ይህንኑ መስክረዋል።
በሃገራችን ሰርቶ የመኖር ዋስትና በአንባገነኖች እጅ ላይ ወድቋል። በነጻነት የመስራት፣ በነጻነት የመናገር፣ በነጻነት ሃሳብን የመግለጽ ወዘተ ዋስትና ሳይኖር የመኖር ትርጉሙ ምንድነው? ሰው ያለ ነጻነት ምንድነው? ለመኖርማ እንስሳትም እየበሉ ይተኛሉ እየተነሱም ይበላሉ – ከዛ ይተኛሉ። ከእንስሳ የሚለየን ነጻነታችን መሰለኝ። ያለ ነጻነት ህይወት ትርጉም የለውም።
በኢትዮጵያ 80 ሚሊየን ህዝብ ያለ ነጻነት ይኖራል። ሃይለመድህን በአንዲት ቅጽበት የዚህ ሁሉ ህዝብ ድምጽ ሆነ። የ80 ሚሊየን ህዝብ ድምጽ ሆኖ በራሱ ላይ መፍረድ መቻል ደግሞ እብደት ሳይሆን ጀግንነት ነው። አንድ ሰው እንዴት መኖር እንዳለበት፣ ምን መናገር እንዳለበት … ወዘተ ሲወሰንት ለአንባገነኖች ብቻ ሳይሆን ለራሱ ህሊናም ባርያ ይሆናል። በተለይ የራስ መተማመን እና የሙያው የተካነ ሰው ተገዥ የሚሆነው ለህሊናው ብቻ ነው። እንዲህ አይነቱ ሰው መብቱን ለድርድር አቅርቦ ራሱን በባርነት አያስገዛም። በመብቱ ላይ የሚደራደር ካለ ህሊናውን የሸጠ ሰው ብቻ ነው። ነጻነት የሚገዛ ውይንም የሚሸጥ ነገር አይደለም። ነጻነትን ሊገዛው የሚችለው ህሊናችን ብቻ ነው። ያለ እራሳችን መልካም ፈቃድ ደግሞ ማንም ሃይል ነጻነታችንን ሊደፍር አይቻለውም። ሰዎች በአካል ሊታሰሩ ይችሉ ይሆናል። የሰውን ህሊና ግን ማንም ሃይል ሊያስረው አይችልም። ኔልሰን ማንዴላ ለ27 አመታት ሲታሰር ህሊናው ነጻ ነበር። በአንጻሩ አሳሪዎቹ ነጮች የአካል ሳይሆን የህሊናቸው እስረኞች ነበሩ።
ሃይለመድህን የህዝብ ድምጽ በመሆን ከህሊናው ጋር የገጠመውን ሙግት ያሸነፈ ጀግና ነው። አላማው በውስጡ የቆሰለበትን የኢትዮጵያ ህዝብ ሰቆቃ ለአለም ለማሳወቅ ነበር። ይህ ባይሆን ኖሮ ችግር ውስጥ ያማያስገቡት ሌሎች ብዙ አማራጮች እና እድሎች ነበሩት። “ዘ ክርስቲያን ሳይንስ ሞኒተር” የተባለው ጋዜጣ የሃይለመድህንን ስደት መጠየቅ አስመልክቶ ባሰፈረው ዘገባ የኢህአዴግ ስርአት ብልሹነትና የሰብአዊ መብት ረገጣው መባባሱን በስፋት ዘግቧል። ሌሎች መገናኛ ብዙሃንም የሃገሪቱን ሁኔታ ትኩረት ሰጥተው እንዲመረምሩት አድርጓቸዋል።
ዶ/ር መረራ ጉዲና ሲነግሩን የኢህአዴግ እድገትና ትራንስፎርሜሽን ሃገሪቱን ወደ ጥርነፋ ፖለቲካ እና ቁምራ ኢኮኖሚ አሸጋግሯታል። ጥርነፋ እና ቁምራ አዲሶቹ ኢህአዲግኛ ቋንቋዎች ናቸው። ጥርነፋ ማለት አንድ ሰው አምስት ሰዎችን እየሰለለ በማገት ከገዥው ፓርቲ አሰራር እንዳያፈነግጥ የማሰርያ ዘዴ ነው። ማንነትን የሚፈታተነው ይህ አሰራር አየር መንገድን ጨምሮ በሁሉም መንግስታዊ ተቋማት ተግባራዊ እየሆነ መጥቷል።
ቁምራ ደግሞ ቁርስ፣ ምሳና ራት በአንድ ግዜ ማለት ነው። ነብሳቸውን ይመርና አቶ መለስ በአንድ ወቅት ሲጠየቁ የኢትዮጵያ ህዝብ ሶስቴ በልቶ እንዲኖር ነበር ህልማቸው። እነሆ ዛሬ 70 በመቶው የኢትዮጵያ ህዝብ ሶስቱንም የእለት ምግብ አንድ ግዜ በቁምራ እንዲያጠቃልል አበቁት። 10ሺህ የሚሆን የአዲስ አበባ ነዋሪ የሚተዳደረው ከቦሌ አየር መንገድ እና ከሆቴሎች የሚጣል ቆሼ እየበላ ነው። በአንጻሩ ደግሞ እነ ስብሃት ነጋ ለአንዲት ጠርሙስ ሉዊስ ኮኛክ 260፣ 000 (ሁለት ሞቶ ስልሳ ሺህ ብር) ያወጣሉ። የ100 ሺህ ብር መጋረጃ ያለው፤ የ60 ሚሊየን ብር መኖርያ ቤት ውስት በሚዋኙ እጅግ ጥቂቶች እና ቆሻሻ እየተመገቡ በሚኖሩ ብዙሃን ወገኖች መሃል ያለው ክፍተት ይህ ነው አይባልም። ይህንን የኑሮ ሚዛን መዛባት የሚቃወመውን ስም ያወጡለታል። ኢ-ፍትሃዊ የሆነውን ይህንን የሃብት ድልድል ለመቀበል ህሊናው የማይፈቅደውን ሁሉ “እብድ” የሚል ስም ይሰጡታል።
የ”እብዱ” ፓይለት ጉዳይ በህግ አይን ሲታይ ጠለፋ ሳይሆን እገታ ነው – የስዊዘርላንድ አቃቢ ሕግ እንደገለፀው። እገታ እና ጠለፋ እጅግ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ድርጊቱ ጠለፋ ቢባል ኖሮ ቅጣቱም የከፋ ይሆናል። እገታም ቢሆን በስዊስ ህግ ከ3 እስክ 20 አመት ሊያስቀጣ ይችላል። የዳኝነት ስልጣኑም ያለው አውሮፕላኑ በግዛቷ ያረፈበት የስዊዘርላንድ ፌዴራል መንግስት ላይ ነው። ለግዜው ሃይለመድህን አበራን አግኝቶ ማነጋገር ስለማይቻል ወጣቱን ያቆሰለው ጉዳይ ላይ ከዚህ የበለጠ ማለት አይቻልም። የአቃቤ-ህጉ ምርመራውን እንዳበቃ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣል። ያን ግዜ የበለጠ መረጃ ይኖራል።
ኢትዮጵያዊ ወገን በሙሉ፣ ራሱን አሳልፎ ለሰጠው ለዚህ ፓይለት ባገኘው መንገድ ሁሉ ድጋፉን መግለጽ ይጠበቅበታል።
melisew fantahun says
WHAT A REAL PATRIOT HE IS!!!!!!
melisew fantahun says
Long live ሃይለመድህን!!!
Tsedalu says
He is the voice of 80million people.