እልህ መጋባት በመሠረቱ መጥፎ ጠባይ ነው፤ መጥፎ የሚሆንበትም ምክንያት ዓይንን ስለሚጨፍን፣ ጆሮን ስለሚያደነቁር፣ ልብን ስለሚያደነድን፣ አእምሮን ስለሚዛባ ነው፤ ይህንን ሁሉ የሚያስደርግ ጠባይ መጥፎ ካልተባለ ሌላ ምን ይባላል? በቤተሰብ ውስጥ በባልና ሚስት መሀከል እልህ ከገባ ትዳርን ማፍረሱ የማይቀር ነው፤ ባለሥልጣኖችም ከሕዝብ ጋር እልህ ከተጋቡ እንደልጅነታችን ጨዋታ ፈረሰ! ዳቦ ተቆረሰ! ማለት ነው፤ ክፉ እልህ መጥፎ ነው፤ አገር ያጠፋል፡፡
ፈረንጆች (አውሮፓውያን ነጮች ማለቴ ነው፤) ጥሩ እልህ አላቸው፤ ፍርሃታቸውን ለማሸነፍ እልህ ውስጥ ይገባሉ፤ የሙያ ብቃታቸውን ወደፍጹምነት ለማስጠጋት እልህ ይይዛቸዋል፤ በውድድር አንደኛ ለመውጣት እልህ ውስጥ ይገባሉ፤ … እልሃቸው አያስተኛቸውም፤ እልሃቸው እረፍት አይሰጣቸውም፤ እልሃቸው በርትተው እንዲሠሩ ይገፋፋቸዋል፤ በየጊዜው የሚፈጠሯቸውን የስፖርት ዓይነቶች ተመልከቱ፤ አብዛኛዎቹ ከፍርሃታቸው ጋር ለመጋፈጥና ፍርሃትን ከውስጣቸው ሙልጭ አድርገው ለማውጣት ሲሉ የሚያደርጓቸው የስፖርት ውድድሮች ናቸው፤ በሞተር ቢስክሊት (ድቅድቂት) በአሸዋ ላይ፣ በበረዶ ላይ፣ በመንገድ ላይ በጣራ ላይ፣ … ምን የማያደርጉት አለ!
የፈረንጆች ጥሩ እልህ የሚነዳው አካላቸውን ብቻ አይደለም፤ ልባቸውንም፣ መንፈሳቸውንም፣ አእምሮአቸውንም ነው፤ ብዙ ነገሮችን እንዲፈጥሩ የሚያደርጓቸው እነዚህ ጥሩ እልሆች ናቸው፤ በእውቀት ምርምር ችኮ-መንቻካ ሆነው ሰማዩን፣ መሬቱን፣ ዓየሩን፣ ባሕሩን እንዲጎረጉሩና እንዲያበጥሩ፣ የተፈጥሮንም ምሥጢር እንዲገልጡ የሚያደርጓቸው እነዚህ ጥሩ እልሆች ናቸው፤ ከዓመት ወደዓመት እየተሻሻሉና እየተራመዱ ዓለማትን በሙሉ በእውቀትም፣ በጉልበትም፣ በሀብትም እንዲቆጣጠሩ የሚያደርጋቸው ጥሩው፣ ችኮ-መንቻካው እልሃቸው ነው፡፡
እኛንም በኋላ-ቀርነት፣ በደሀነት፣ በደንቆሮነት፣ በደካማነት ጠፍሮ የያዘን መጥፎ እልሃችን ነው፤ ይህንን መጥፎ አልህ በተጨባጭ ለማየት በዛሬው ጊዜ በየትኛውም መንገድ ላይ የሚተላለፉትን ተሸከርካሪዎች ቆም ብሎ ማየት ይበቃል፤ የሁሉም ዓላማ — የወጣቱም፣ የሽማግሌውም፣ የወንዱም፣ የሴቷም፣ የግሉም የድርጅቱም፣ የፖሊሱም፣ የመከላከያውም፣ የታክሲውም … — ዓላማ ሌላው መኪና እንዲቆም ማድረግ ነው፤ የሁሉም ዓላማ ሌላውን ማቆም ከሆነ ማንም ወደፊት አይሄድም! የሁሉም ዓላማ አብሮ ተባብሮ መቆም ነው ማለት ነው፤ ችኮ-መንቻካ መጥፎ እልህ!
ሥልጣን ላይ በጉልበት የወጡ ሰዎችን ይህ መጥፎ እልህ ጠፍሮ ሲይዛቸው አገርን ጠፍረው ይይዛሉ፤ መስማትን ያቆማሉ፤ ላለመስማት እልህ ይይዛቸዋል፤ ማንም በጉልበት አያሸንፈንም የሚል እልህ ይይዛቸዋል፤ ማንንም ማታለል እንችላለን የሚል እልህ ይይዛቸዋል፤ እዚህ ላይ ችግር ይገጥማቸዋል፤ ከአንድ ቦታ በአንድ ኃይል እኛ አንታለልም የሚል እልህ ይገጥማቸውና ተዘጋግተው እንደቆሙት መኪናዎች ይቆማሉ!
ፕ/ር መስፍን ወልደ-ማርያም፤ ሰኔ/2008
(ምንጭ: Mesfin Wolde-Mariam Blog)
Yonas says
Thank you for a timely message that all need to heed; including both government and opposition groups. In the good old days a father’s advice is whole heartedly accepted and adhered too, I hope this will be the case in this instance. I myself after reading it am putting it into practice on day one, on my day to day activity.
God bless you and wish you a prosperous life and good health !!!
Respectfully;
Yonas Atle