ይሄንን ጽሑፍ የጻፍኩት ታች አምና አሁን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ሆኘ እየመራሁ ነኝ የሚሉት አባ ማትያስ ለማወናበዱ እንዲመች እጣ መሆኑ ቀርቶ በይስሙላ ምርጫ ሐሙስ እንደተመረጡ ቅዳሜ በዕንቁ መጽሔት ላይ የወጣ ነው፡፡ በወቅቱ በጽሑፉ ላይ ሁለት ነገሮችን ተንብየ ነበር፡፡ አንደኛው ፓትርያርክ ተብለው የተመረጡት ሰው እንደ አባ ጳውሎስ ሁሉ ለቤተክርስቲያን ደኅንነትና ህልውና አደጋ እንደሚሆኑ የሚናገረው ሲሆን፡፡ ሌላው ደግሞ የሰይጣን ጆሮው ይደፈንና ከአንድ ዐሥርት ዓመታት በኋላ የክርስቲያኖች (የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ምእመናን) በመላዋ ሀገሪቱ የሚኖራቸው ብዛት እጅግ አሽቆልቁሎ ከአዲስ አበባ ሕዝብ ብዛት ያልበለጠ ይሆናል የሚል ነበር፡፡
በወቅቱ ይሄንን ትንበያየን አለቅጥ የተጋነነ አድርገው የቆጠሩት ብዙ ነበሩ፡፡ አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ በጥቂት ወራት ውስጥ አባ ማትያስን በተመለከተ ተናግሬው የነበረው ነገር እውን መሆኑን ሲያዩ ግን ምንኛ ትክክል እንደነበርኩ ለመገንዘብ ተገደዋል፡፡ በግሌ ነገሩ ሳይሆን ቀርቶ እኔ ውሸታም በተባልኩ ኖሮ ምንኛ ደስ ባለኝ ነበር፡፡ ትንበያዎቸ እውን መሆናቸውና እየሆነ መሆኑን ሕዝበ ክርስቲያኑ በቅጡ አለመገንዘቡ ቢያሳስበኝና ቢያስደነግጠኝም ይሄንን አሳዛኝና አስደንጋጭ አደጋ ካህናትና ምእመናን በቅጡ ያጤኑት ዘንድ እንዲሁም አስፈላጊውንና የሚጠበቅባቸውን ዋጋ ከፍለው ቤተክርስቲያንን (ሃይማኖትን) ይታደጉ ዘንድ ለማሳሰብ ሰሞኑን ወደ እናንተ የማደርሰው አንድ ጽሑፍ አለ ከዚያ በፊት ግን ግንዛቤው እንዲኖራቹህና እውስጡ ያሉት ጠቃሚ መረጃዎች እንዳያመልጣቹህ ያኔ የጻፍኩትን ጽሑፍ እንዳለ አቅርቤላቹሀለሁ፡፡ በሚቀጥለው ጊዜ አሁን ያለውን ሁኔታ እናወራለን ወደ ጽሑፉ፡-
የእርቅ ድርድሩ የአባ ጳውሎስ ሞትና ከዚያም የ”ፓትርያርክ” ሹመት ውዝግብ ጉዳይ ተዳፍነው የኖሩ ብዙ ጉዳዮችን ሸፍጦችንና የጥፋት የክህደት ድርጊቶችን ግልጽ እንዲታዩ እንዲወጡ አድርጓል፡፡ በዚህ ጣጣና ሽኩታ ውስጥ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የነበሩባትን ያሉባትንና የተጋረጡባትን አደጋዎች ማየት ችለናል፡፡ ይህ የቤተክርስቲያን ችግር ድንገት አሁን የተፈጠረ ሳሆን ሕወሀት ሥራዬ ብሎ ከረጅም ጊዜ ጅምሮ በተጠናከረ ዝግጅት እየሠራበት የመጣ ጉዳይ እንደሆነ አብዛኛው ሕዝበ ክርስቲያን የሚያውቀው ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ ምንም እንኳ ወደ ኋላ ቢተወውም ደርግም በነበረው ፀረ ሃይማኖት አቋም የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንም ቀላል የማይባል ጉዳትና ኪሳራ ደርሶባት አልፏል፡፡ ደርግን በተካው በወያኔ መንግሥት ደግሞ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከድጡ ወደ ማጡ ለመስጠም ግዴታ ሆኖባት ይሄው በከባድ ችግር ታንቃ እየተንፈራገጠች ትገኛለች፡፡ ይህ ችግር ብዙዎቹ እንደሚመስላቸው የዘር የደጋፊ ወይም የወገንተኝነት ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ በእርግጥ የዚህ ችግር ፈጣሪዎች ጉዳዩ የዘር ወይም የወገኝተኝነት ጉዳይ ብቻ እንደሆነ መስሎ እንዲታይ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ የዚህ ችግር ትክክለኛና የተደበቀው ገጽታ ግን በፍጹም ብቻ ይህ አይደለም፡፡ ይሄ ብቻ በነበረ ምንኛ በታደልን ነበር፡፡ ችግሩ የሚወደድና ቀላል ሆኖ ሳይሆን ከመጥፎው ከከባዱ ጥፋትና አደጋ ቀለል ያለውን ጥፍትና አደጋ ከመምረጥ አንጻር እና ከረጅም ዘመናት ጀምሮ ምን አልባትም ከሰው ልጅ ታሪክ ጋር ዘመድ ሆኖ አብሮ የኖረ የሰው ልጅ መገለጫ ወይም ችግር ስለሆነ እንጅ፡፡
ወያኔ ምንም አንኳ በእናታቸው በኩል ጎጃሜ ቢሆኑም አባ ጳውሎስን አስቀድሞ አጭቶ ቆይቶ ከወገኖቹ መርጦ እንዲሾሙ ማድረጉ ከቤተክርስቲያኗ ሕግና ቀኖና ውጭ መሆኑ ከፋ እንጅ የራሱን ወገን ማሾሙ በራሱ ብቻውን አስቀድሜ እንዳልኩት ይህ ሰው በመሆን ዘወትር የምንፈጽመው ጥፋትና ደካማ ጎናችን ነውና ምንም ባልነበር፡፡ ከወያኔ በፊት የነበረው ደርግም ምንም እንኳ ደርግ የአማራ መንግሥት ነው የሚባል ባይሆንምና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማርያምም እራሳቸው በአባታቸው ኦሮሞ በመሆናቸው ይሁንና ግን መንግሥታቸው የራሴ የሚላቸውን ሰው እንዲሾሙ አድርጓልና፡፡ ከዚያም በፊት በነገሥታቱም ዘመን ጳጳሳቱ የእኛ ወገን ባይሆኑም ማለትም ግብጻዊያን ቢሆኑም ነገሥታቱ እስከ ወደዷቸውና እነሱን እስከመሰሉ ጊዜ ድረስ እንጅ ተጻራሪ አቋም ይዘው በአንድም በሌላም ምክንያት እንዲሠሩ ዕድል የሰጡበት አጋጣሚ ብዙም አልነበረምና አዲስ ችግር ባለመሆኑ ወያኔም ይህንን ማድረጉ ምንም አልነበረም፡፡
ለየት ያለው ወያኔ የፈጠረው የሚከፋው ችግር ግን በዓይነቱ አዲስና እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ ይህ ችግር ቀድሞ ከነበሩት ነገሥታት ዘንድ በዐፄ ሱስኒዮስ ጊዜ የተከሰተና ቀላል የማይባል መሥዋዕትነት ቢያስከፍልም ችግሩ ወይም ስሕተቱ ወዲያውኑ ታርሟል፡፡ ይህ ችግር ምንድን ነው? ይህ ችግር ነገሥታቱና መሪዎቹ በመሰላቸውና ባመኑበት ግላዊ አቋምና አቅጣጫ ቤተክርስቲያንን ያለ ሕግጋቷ፣ዶግማዋና ቀኖናዋ ባጠቃላይ አስተምህሮዋ አቅጣጫዋን ለማሳት የማስገደድ ሙከራዎች ናቸው፡፡ ዐፄ ሱስኒዮስ በፖርቹጋሎች አሳሳችነት ይሄንን ለማድረግ ሲሞክሩ ከባድ መሥዋዕትነት በጠየቀ የሕዝቡ ዐመፅ እንዲከሽፍ ተደርጎ ነበር፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስም ያልነበረ ሥር ነቀል መንግሥታዊ ሥርዓት በመደንገጋቸው ካህናትንና ደብተሮችን ቢያስቆጣም እሳቸው እራሳቸው የቤተክህነትን ትምህርት የተማሩና በዲቁናም ያገለገሉ ስለነበሩ የካህናቱን አግባብ ያልሆነ ጥቅምና የሚበዛውን ጊዜያቸውን ሥራ ፈትተው መቀመጥ ስላልወደዱ በጉልበታቸውም አምራች ዜጎች እንዲሆኑ አስገደዱ እንጅ የቤተክርስቲያኗን አስተምህሮ ሕግና ሥርዓት በፍጹም አልነኩም፡፡
ወደ ደርግ አገዛዝ ስንመጣ ደግሞ በግብታዊነት ሳይገባው ከሀገሪቱ ማንነት፣ ሥልጣኔ፣ ታሪክ፣ ባሕል፣ ሰብእና፣ አስተሳሰብና እሴቶች በሙሉ ጋራ ፈጽሞ የማይጣጣም ጭፍንና የደነቆረ ባዕዳዊ የፖለቲካ (የእምነተ-አሥተዳደር) አስተሳሰብ ወይም ርዕዮተ ዓለም ይዞ አባሎቹን የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ እንዳይሆኑ እስከማድረግና እንደውም ሃይማኖትን እስከ ማጥፍት የደረሰ ዓላማ በማንገብ የገጠር አብያተክርስቲያናትን የገበሬ ማኅበር ጽ/ቤት የከተሞችን ደግሞ ሙዚየም (ቤተ-መዘክር) የማድረግ ከባድ የጥፋት ዓላማ ነበረው፡፡ ወደ ኋላ ግን የሚከተለው ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም ከመላው ዓለም እየደከመና እየኮሰመነ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ያንን የጥፋት ዓላማ ለማስፈጸም ይዞት የነበረውንም ቁርጠኝነትና ትጋት ለመተው ተገዷል፡፡ በዚህ ወቅት ነበር አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ የሆኑት፡፡ በእርግጥ አቡነ መርቆሬዎስ ከዚያም በፊት የደርግ ሰው የነበሩ ቢሆኑም ደርግ እንደነበረው ዓላማ ፓትርያርኩን በቤተክርስቲያን ላይ ጥፍት እንዲሠሩ ለማድረጉ ወይም ደግሞ እርሳቸው የደርግ ሰው ስለነበሩ የደርግን ዓለማ ለማስፈጸም ሲሉ በቤተክርስቲያን አስተምህሮ ከዶግማ እስከ ቀኖና ፈጸሙ የተባለ አንድም ጥሰት መቆነጻጸል ወይም ክህደት የለም ሲጠቀስ ሰምተንም አናውቅም፡፡ ከዚህ ይልቅ እንዲያውም አቡነ መርቆሬዎስ ከፕትርክናቸው በፊት ገና ቤተክርስቲያንን ወይም እግዚአብሔርን ለማገልገል ሲሉ ያደርጉት የነበረውን ለምሳሌ የክርስቲያኖች ቁጥር በተመናመነበት በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል በግራኝ መሐመድና በተለያዩ ምክንያቶች የጠፉና የፈረሱ አብያተ ክርስቲያናትን ምዕመናንን እያስተባበሩ ሲያሠሩና ሲያስገነቡ የደርግንም ድጋፍ በመጠየቅ ድጋፍ ያገኙም ነበር፡፡
ወደ ወያኔ ‹‹መንግሥት›› ስንመጣ ግን ነገሩ የተለየ ችግሩና ጉዳቱም ከባድ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በርዕዮተ ዓለም ደረጃ ወያኔ የሚከተለው ፖለቲካዊ (እምነተ-አሥተዳደራዊ) አስተሳሰብ ከደርግ የተለየ አይደለም፡፡ የምከተለው የመንግሥት አስተዳደር ዓላማዊ (secular) ነው ስለሚል አመራሮቹ ሃይማኖተኛ እንዲሆኑ አይፈቅድም፡፡ ወያኔ ይህ አሁን በቤተክርስቲያኗ ላይ እያደረገ ያለውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ዝግጅት ማድረግ የጀመረው ገና ከድሮው በረሀ እያለ ጀምሮ እንደነበረ የትግሉ አካልና አመራር የነበሩ ሰዎች በጻፏቸው የመመረቂያ ጽሑፎች፣ መጻሕፍትና በቃለ መጠይቆች ይናገራሉ፡፡ ወያኔ አባ ጳውሎስን ፓትርያርክ ሌሎች ታጋዮችንም ጳጳሳት ያደረገው 1984 ዓ.ምና ከዚያም በኋላ ሳይሆን ገና በረሀ እያለ ጀምሮ ነበር፡፡ እነኝህን ሰዎችንም ለዚህ ተልእኮ የበቁ ይሆኑ ዘንድ ለማደናገሪያ ወይም መስሎ ለመታየት የሚያስችላቸውን ትምህርት በየገዳማቱ በማስረግ እንዲያገኙ እንዳደረገ ይህን ሥራ የመሥራት ኃላፊነት የነበራቸው አመራሮች በጻፏቸው መጽሐፎቻቸው ገልጸዋል፡፡
እኔ እንኳን በሆነ አጋጣሚ ታሪካቸውን የማውቅላቸው ከእነኝህ ታጋዮች አንዱ በደርግ ጊዜ ለዓመታት በገነት ሆቴል ሆነው ሲሰልሉ የነበሩ ዛሬ ግን ጳጳስ የሆኑ ሰው አውቃለሁ፡፡ እነኝህ አመራሮች ከጻፏቸው መጻሕፍት እንደምንረዳው አባ ጳውሎስ ጳጳስ አድርገው ከሾሟቸው ከ40 በላይ ጳጳስት አብዛኞቹ ወያኔ በረሀ እያለ ለጵጵስና ያዘጋጃቸው ታጋዮች እንደነበሩ ታውቋል፡፡ እንደኔ እንደ እኔ አሁንም ቢሆን እነኝህ ግለሰቦች ለጵጵስናም ይሁን ለፕትርክና የሚያበቃውን መስፈርት የሚያሟሉና ለቅድስት ቤተክርስቲያን (ለእግዚአብሔር) ታማኝ አገልጋይ ቢሆኑ ኖሮ እንዲህ መደረጉ በራሱ ችግር ነው ብየ አላስብም፡፡ ምክንያቱም ሀገራችን ኢትዮጵያ ወይም ቤተክርስቲያን እንኳንና የገዛ ዜጎቿን ይቅርና የማናውቃቸውን ግብጻዊያን፣ ሶርያዊያንና ሮማዊያን ጳጳሳትንና አባቶችን ተቀብለን በእነርሱ መንፈሳዊ አገልግሎት ስንገለገል ኖረናልና፡፡ ሐዋርያዊ ተልእኮና አገልግሎት በዘርና በድንበር የሚገደብ ባለመሆኑ፡፡
ችግሩ የሚፈጠረው ግለሰቦቹ ታማኝነታቸው ለቤተክርስቲያን ሳይሆን ለድርጅታቸው ፣ ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለመንግሥታቸው፣ የቤተክርስቲያንን እነጀራ እየበሉ ግን የሚያገለግሉት እግዚአብሔርን ሳይሆን ድርጅታቸውን የሆነ እንደሆነ ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ የሆነው ነገርም ይሄው ነው፡፡ ወያኔ ለኢትዮጵያ ታሪክና ቅርስ የሚሰጠው ዋጋ ምን እንደሆነ ሁላችንም የምናውቀውና ግልጽ ነው፡፡ ምንም እንኳ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሀገሪቱ ያሉ ብሔረሰቦች ሁሉ ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ማንነት የየራሳቸው አስተዋጽኦ እንዳለበት የታወቀ ቢሆንም በወያኔ ዕይታ ግን 3 ሺህ ዓመታትን ያስቆጠረው ከቀዳማዊ ምኒልክ የሚጀምረው ሰሎሞናዊው ሥርወ መንግሥትና የዛሬ 4500 አካባቢ ጀምሮ 22 ነገሥታትን ካስተናገደ በኋላ በነገደ ዮቅጣን ተተክቶ እናቱ ሳባ (ማክዳ) የመጨረሻዋ በሆነችበት 52 ነገሥታት የነበሩበትን ሥርዎ መንግሥት የተቆጣጠረው፤ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ታሪክና ቅርስ የአንድ ዘር ብቻ ማለትም የአማራ ብቻ እንደሆነ አድርጎ ነው፡፡
ወያኔ ይህንን ጉዳይ ለወዳጆቹ የውጭ መንግሥታት አንጀት በሚበላ ገለጻ አጅቦ ጭምር በማቅረብ ዘለዓለም ዓለማችንን ስንጨቆን ስንረገጥ የነበር ነን እያለ ሲያባብልበትና ፈር የለቀቀና በመርሕ ሊገደብ ያልቻለ ድጋፍ ሲያገኝበት ቆይቷል፡፡ ከዚህ የተነሣ ወያኔ ስናውቀው ጊዜ ጀምሮ ለታሪካችንና ቅርሶቻችን ካለው ጥላቻ የተነሣ በሚገርምና በሚደንቅ ሁኔታ ህልውናቸውን ጨርሶ በመካድ የኢትዮጵያን ታሪክ በ100 ዓመታት ብቻ ገድቦት እንደነበር ይታወሳል፡፡ የታገሰ ከሚስቱ ይወልዳል እንዲሉ ምንም እንኳ አሁን ወደ መጨረሻ ወያኔ ተገዶ ለኢትዮጵያ ታሪክ የነበረውን የ100ዓመታት አስተሳሰቡን የቀየረውና ያስተካከለው ቢሆንም፡፡
ወያኔ በዚህ ጤነኛ ባልሆነ ከባድ ጥላቻ እንደተመረዘ እንደተሞላና እንደሰከረ ነበር ሥልጣን የተቆናጠጠው፡፡ ወያኔ በዚህ ጥላቻው ብቻም ሳይሆን ለራሳቸው ዓላማ ለእሱ ድጋፍ ይሰጡት ከነበሩት እኛን እንደ ታሪካዊ ጠላታቸው አድርገው ከሚቆጥሩን ከሀገራችን ጠላቶች የተሰጠው ተልእኮም በአጋጣሚ ከፍላጎቱም ጋር በመጣጣሙም ጭምር ነው፡፡ እናም ሥልጣን ከያዘበት ቀን ጀምሮ ወደ ፊት ሊሠራው አስቦት የነበረው ሥራ ሁሉ በዚህ በሽተኛና መርዘኛ አስተሳሰብ ማዕቀፍና መሠረትነት የተሰላና የተቀመረ ነበር፡፡ በመሆኑም ይህንን ከባድ ጥላቻ ያለበትን ታሪክና ቅርስ ስልታዊ መሆነ መንገድ ለማጥፍት ሲያስብ የዚህ ሁሉ ታሪክና ቅርስ ማኅደር የሆነችው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ዕይታው ውስጥ ጥልቅ አለች፡፡ ስለዚህ ይህንን የተወሳሰበ የጥፋት ሥራ በተሳካ መልኩ ለመሥራት ገና ከበረሀ ጀምሮ በአማካሪዎቹና ደጋፊዎቹ ጠላት ሀገራት እየታገዘ ዝግጅቱን ያጧጡፈው ያዘ፡፡ ወያኔ የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን የሚያያት የአንድ ዘር ጠበቃና የህልውና መዋቅር አድርጎ ነው፡፡ የወያኔ ባለሥልጣናት ይህንን እኩይ አስተሳሰብ የሚያንፀባርቁ የተለያዩ ንግግሮችን በአደባባይ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከፊደልና ቁጥር እስከ ዜማ፣ ከመድኃኒት ቅመማ እስከ ፍልስፍና ከዘመን አቆጣጠር፣ ቀመር እስከ ሥነ-ፈለክ (የዐበይተ-ከዋክብት ወይም የፕላኖቶችና የከዋክብት ጥናትና ምርምር)፣ ከአርበኝነት ነጻነታችን ተጠብቆ እንዲኖር እስከ ሀገር ፍቅር እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉ ከሀገራችንም አልፋ ለመላው ዓለም ያበረከተቻቸውን የማይተካ አስተዋጽኦ ሆን ተብሎ ለማየት ባለመፈለግ ልክ ለሀገር ተቆርቋሪ እንደሆኑና እንደሚያስቡ ሁሉ “ሊሠራ የማይወድ አይብላ” 2ኛ ተሰሎ. 3፤8-10 እያለች የፈጣሪን ቃል የምታስተጋባ ቤተክርስቲያንን በዓላትን በመጥቀስ ለዚህች ሀገር ድህነት ተጠያቂ ነች እያሉ በአደባባይ በመክሰስ ተደምጠዋል፡፡ የነፍጠኛ ሃይማኖት እያሰኙም ሲያዘልፏትና ሐዋርያዊ ተልእኮዋንም ሲያደናቅፉ ቆይተዋል፡፡
ለወያኔ ባለሥልጣናት ሥራ ማለት ቁፋሮ፣ጉልጓሎ፣አጨዳ፣ፈለጣ የመሳሰሉት ነገሮች ብቻ ናቸው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን አስተምህሮና አስተሳሰብ ግን ሥራ ማለት ቁፋሮ ጉልጓሎ ቆረጣና የመሳሰሉት ብቻ አይደሉም፡፡ ቤተክርስቲያን በጣም ውስን ቀናትን በዓል ብላ ከጉልበት ሥራዎች ነጻ እንዲሆኑ ብታደርግም በእነዚህ ቀናት ግን እንዲሠሩ የምታዛቸው ሥራዎች ደግሞ አሉ፡፡ ለምሳሌ የታመመ መጠየቅ፣ የተጣላ ማስታረቅ፣ የታሠረ መጎብኘት፣ ለአረጋያንና ለሕፃናት ባጠቃላይ ለቤተሰብ ጉዳይ ጊዜ መስጠት ወደ እግዚአብሔር ቤት በመሄድ ቃሉን መስማት መማር የመሳሰሉት ማኅበራዊ ክንውኖች ሁሉ በትዕዛዝ ጭምር እንዲሠሩ እንዲደረጉ ትኩረት እንዳይነፈጋቸው ትመክራለች ታስተምራለች ታስጠነቅቃለች፡፡
ቤተክርስቲያን ይህንን ሥርዓት ለምን እንደደነገገች ባለ አእምሮ የሆነ ሰው ሁሉ በሚገባ ይረዳዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ነው በዚህ አስከፊ ድህነት ውስጥ ሆነንም እንኳ ጠንካራ የሆነ የማኅበራዊ ሕይዎት ትስስር ሊኖረን የቻለው፡፡ የሚጎበኙን ምዕራባዊያንንም የሚገርማቸውም ጉዳይ ይሄ ነው፡፡ በዚህ አስከፊ የድህነት ዓይነት ውስጥ ሆነንም እንኳ እንዲህ ዓይነት ጠንካራ ማኅበራዊ ትስስር ይዘን ሲያዩ የማይታመንና ተአምር ሆኖባቸው ሲገረሙ ይስተዋላሉ፡፡ እነሱ ይህንን እሴት በሥነ ልቡና ሊቃውንት (psychologists) እና በሳይንሳዊ (በመጣቃዊ) የኅብረተሰብ ትምህርት (sociology) ባለሙያዎቻቸው ምክርና ትምህርት ሊያመጡት አልቻሉምና፡፡
የማንም ሀገር ሕዝብ ቢሆን የፈለገ ቢሆን ከዓመቱ 365ቱንም ቀናት ከወር 30ውንም ቀናት ከሳምን 7 ቱንም ቀናት በከባባድ የጉልበትና ተመሳሳይ ሥራዎች ላይ ማሳለፍ የሚችል ጨርሶ አይኖርም፡፡ ይህም ስለሆነ ነው ሁሉም ሀገራት በሳምንት ውስጥ ከ1-3 የሚሆኑ ቀናትን የዕረፍት ቀናት አድርገው የደነገጉት፡፡ ሕይወት ሥራ ብለን በምናስበው ነገር ብቻ አትቆምምና ሰው እንደመሆናችንም ልንሠራቸው የሚገቡ ነገሮች ደግሞ ብዙ አሉ፡፡ ሀገራችንን ያደኸያት ይህ ሳይሆን ቀጠሮ እንዳለው የራሱን ጊዜ እየጠበቀ ከውጭና ከውስጥ በሚፈጠር ቀውስ የሚከሰተው ጦርነት ነው፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ በረጅሙ ታሪኳ ከአንዱ ጦርነት ወደ ሌላው ጦርነት አንድትገባ ስትገደድ በአማካኝ ከ10 ዓመታት የበለጠ የሰላም ጊዜ ኖሩት አያውቅም፡፡ እንግዲህ ልብ በሉ እንኳንና ይሄ ሁሉ ጦርነት አንድ ጦርነት ብቻ እንኳ የአንዲትን ሀገር የሰው ኃይሏን ጨምሮ የሚበላው ሀብትና ጥሪት ከሥልጣኔዋ እስከ ቅርሷ የሚያደርሰውን ውድመት ልብ ላለ ሰው ሀገራችን ኢትዮጵያ ይሄንንም ያህል እንኳ በመኖሯ የእግዚአብሔር ቸርነት ነው ብሎ ፈጣሪን ካላመሰገነ እራሱን ለትዝብት ይዳርጋል፡፡
ሀገራችንና ሕዝባችን ባለፉበት የፈተናና የመከራ ሕይወት ሌላ ማንም ሀገርና ሕዝብ ቢያልፍ ገና ከድሮው ድምጥማጡ ጠፍቷል፡፡ ሀገራችን ካለችበት ስትራቴጅካል (ስልታዊ) አቀማመጥ ወይም ሥፍራ፣ ከረጅሙ ታሪካዊ ዳራችን ተከትሎን የመጣው ጣጣ፣ ለብዙ አፍሪካ ሀገሮች ነጻነት የተጫወትነው ሚና በቅኝ ገዥዎች ያስከተለብን የበቀል እርምጃ በመሳሰሉት ምክንያቶች በዚህ መከራ ማለፍ ግዴታ ሆኖብናል፡፡
ወደ ቀደመው ነገራችን እንመለስና ወያኔ የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን የአንድ ብሔረሰብ ጠበቃና ውላጅ ናት የሚለው አስተሳሰቡ ቤተክርስቲያንን ለሰይጣናዊ ጥቃቱ አጋልጧታል፡፡ አባ ጳውሎስና መሰሎቻቸው በዚህ 20 ዓመታት በሥውርና በግልጽም የሚታዩ የጥፋት ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ ከዶግማ ዶክትሪኗ እስከ ቀኖናዋ የሊቃውንትና የሕዝበ ክርስቲያኑ ምላሽና ሁኔታ እየታየ ለመሸራረፍ ጥረት አድርገዋል፡፡ ለዚህ ትሩፋታቸው የበለጠም እንዲያጠፉ ለማትጋት ከአፅራረ ቤተክርስቲያን ሞገስን አሰጥቷቸው ከቤተክርስቲያናችን ፍላጎትና ከቃሉ ትዕዛዝ ውጭ ከአጽራረ ቤተክርስቲያን ጋር ባላቸው አጋርነት የዓለም አብያተክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዘዳንትነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ አንዳንድ የኔ ቢጤ የዋሀን አባ ጳውሎስ የነገረ ሃይማኖት ምሁር ሆነው በዓለም ካሉ የነገረ ሃይማኖት ትምህርት ዐዋቂዎች (theologian) የላቀ ወይም ተመራጭ ዕውቀትና ብቃት ኖሯቸው ያንን ቦታ የያዙት የሚመስላቸው አይጠፋም፡፡ ቤተክርስቲያን አስተምህሮዋ ብቻ ሳይሆን ብዙ የማይተኩ ብርቅና ድንቅ ቅርሶቿም በረቀቀ ዘዴ እንዲሰወሩ ወይም የገቡበት ሳይታወቅ እንዲጠፍ ተደርጓል መጻሕፍቶቿም ተቆነጻጽለው እንዲታተሙ ተደርጓል ወዘተ፡፡
በተለይ በተለይ ደግሞ ቤተክርስቲያን ባለፉት 10 ዓመታት ብቻ 6 አእላፋት (ሚሊዮን) ልጆቿን እንድታጣ መደረጉ ነው፡፡ ይህ ቁጥር ቀላል ቁጥር አይደለም ከብዙ የአውሮፓ ሀገራት ሕዝብ ቁጥር የላቀ ቁጥር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ማዕከላዊ ሕዝብና ቤት ቆጠራ መ/ቤት ኦፊሴላዊ (ይፋዊ) መረጃ መሠረት በ1989 ዓ.ም በተደረገው የሕዝብ ቆጠራ ላይ ከ53 ሚሊዮኑ (አእላፋቱ) የኢትዮጵያ ሕዝብ 27 ሚሊዮኑ ወይም 50.6% የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ተከታይ ነበር፡፡ በ1999 ዓ.ም በተደረገው ቆጠራ ግን ከ 73 አእላፋቱ (ሚሊየኑ) የኢትዮጵያ ሕዝብ 38 ሚሊዮን መሆን ሲኖርበት 32 ሚሊየኑ (አእላፍቱ) ማለትም ከ50.6% ወደ 43% ወርዶ 7.6% ልጆቿን ማለትም 6 ሚሊየን ምእመናን እንዲበሉባት ተደርጓል፡፡ ልብ በሉ ይህ የሆነው 1989 – 1999 ዓ.ም ባለው 10ዓመታት ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ከ1989ዓ.ም በፊትና ከ1999ዓ.ም. በኋላ እስከ አሁን ያለውን ብናስብ ደግሞ ከዚህም ሁለት እጥፍ በላይ መንጋ እንደተበላባት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
ይህንን ኪሳራ ያደረሱት የበግ ለምድ ለብሰው የገቡ ተኩሎች ወይም መናፍቃን እንደሆኑ ይታወቃል እነኝህ ግለሰቦችና ቡድኖች ሳይታወቁ ቀርተው አልነበረም ነገር ግን ከቤተክርስቲያኗ የበላይ አካላት ከፓትርያርኩ ጽ/ቤት በግልጽ የሚታይ ድጋፍ ስለሚደረግላቸው እንጅ፡፡ አምና ‹‹ሲኖዶስ›› በእነኝህ ተኩላት ግለሰቦችና ቡድኖች ጉዳይ ሲነጋገሩና ሰዎቹም ሲመረመሩ የእንቅስቃሴው ሥር አባ ጳውሎስ ሆነው በመገኘታቸው የሲኖዶስ አባላት አባ ጶውሎስን “ሃይማኖትዎ ምንድን ነው” ብለው ለመጠየቅ እንደተገደዱና በማግስቱ በሚቀጥለው የሲኖዶስ ስብሰባ ይህንን እንዲመልሱ ተቀጥሮ እንደነበር ነገር ግን አባ ጳውሎስ በማግስቱ ሳይገኙ እንደቀሩ ጥያቄውም በዚያው ተዳፍኖ እንደቀረ የሚታወቅ ጉዳይና የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ አባ ጳውሎስ ለወያኔ ይሄንን እመርታ አስመዝግበው አልፈዋል፡፡ ባለተራው ካድሬ ወይም መናፍቅ ‹‹ፓትሪያርክ›› ሲመጣም አይበለውና ሌላ ቀጣይ ከ10–15 ዓመታት ቢሠራና ቆጠራ ቢደረግ የቤተክርስቲያኗ አባላት ወይም ክርስቲያኖች በመላው ሀገሪቱ ሲቆጠሩ ከአዲስ አበባ ሕዝብ ባነሰ ወይም ቤተክርስቲያኗ አለች ተብሎ ለመናገር የማያስደፍር ደረጃ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም የሚጠፋው መንጋ ቁጥር እየጨመረ በሄደ ቁጥር አባላቷ ባዶ ላይ ለመድረስ የሚጠይቀው ጊዜ እጅግ እየተፋጠነ ይሄዳልና፡፡
የሰይጣን ጆሮው ይደፈንና ይህች ከሕገ ልቦና ጀምራ በየኪዳናቱ ስሟ እየተቀያየረ ለዚህች ሀገርና ለዚህ ሕዝብ ህልውናና ልዕልና ውድ ልጆቿን እየገበረች እየደማች እየቆሰለች ያልከፈለችው የመሥዋዕትነት ዓይነት ሳይኖር ለሽዎች ዓመታት የቆየችው ቤተክርስቲያን በጣት ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ነበረች ተብሎ ሊነገርባት ነው ማለት ነው፡፡ ሁሉም ሰው ማለት ይቻላል ሃይማኖት ሲባል በአብርሃም ፣በሙሴ ወይም ከዚያ በኋላ በክርስቶስ ዘመን የተጀመረ ይመስለናል፡፡ ነገር ግን ሃይማኖት የነበረው ከአዳም ጀምሮ ነው፡፡ ሃይማኖት ማለት “ማንነቱን በትክክል በተረዳ መልኩ እግዚአብሔር የሚባል አምላክ መኖሩን ዐውቆና አምኖ እሱን ማምለክ ለእርሱም መገዛት” ማለት ነው፡፡ ይሁዲነት ወይም ክርስትና ሃይማኖቶች አይደሉም ከአዳም ጀምሮ በነበረችው በአንዲቷ ሃይማኖት ውስጥ ያሉ ኪዳናት ናቸው እንጅ፡፡ ለዚህም ነው የአግዚአብሔር ቃል በትን. ኤር. 6፤16 ያለውን መሠረት በማድረግ በኤፌ. 4÷5 ላይ አንድ ሃይማኖት ብቻ መኖሩን የሚናገረው፡፡
እናም ይህች ቤተክርስቲያን ከአዳም ወደ ሕገ ልቡና ማለትም የተጻፈ ሕግ ሳይኖር በውርርስ ከዛ ወደ ኦሪት አሁን ደግሞ በመጨረሻ ወደ ክርስትና ስሟ እየተቀያየረ ህልውናዋ ሳይቋረጥ በኢትዮጵያ ሰዎች ዘንድ ቆይታ ነበር፡፡ ይህንን መጽሐፍ ቅዱስን በመመርመር መረዳት ይቻላል፡፡ እናም ይሄንን ያህል ታሪክና መሠረት ያላት ቤተክርስቲያን አጋንንት ግብዓት መሬቷን ፈጽመው ሊፋንኑ ጥቂት ዓመታት ብቻ ተቀጥሮላታል ቢባል ማን ያምናል? ለአንድ ኢትዮጵያዊስ ከዚህ የከበደና የከፋ አስደንጋጭ መርዶ ሊኖር ይችላልን?
ለሚሰማኝ ሁሉ ልናገር የምፈልገው ነገር ቢኖር የወያኔ (የጎግ-ወማጎግ) ደጋፊ ወይም አባል ሆኖ እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው ሰው ካለ ለነገሩ ይኖራል ብየ አልገምትም ሁሉም እውነቱን ልቡናው ያውቀዋልና ነገር ግን ወያኔ ለዚህ እንዲረዳው በፈጠረው የኑሮ ውድነትና ሌሎች ነገሮች ታንቆ ስለተያዘ እንጅ፤ ወያኔ የሱ ደጋፊ ካልሆኑ በስተቀር መኖር እንዳይቻል ስላደረገ አይ ካለ ከሥራው ይፈናቀላል፣ ቤቱ ይፈርሳል፣ ገንዘቡ ይወረሳል ምክንያት ተፈልጎለት ወይም ተፈጥሮለት ወደ እስር ቤት ይወረወራል፣ የመማር ዕድል እንዳያገኝ ይደረጋል፣ በግሉም እንኳን ቢሆን ሠርቶ መኖር እንዳይችል ይደረጋል በእነዚህ ምክንያቶች ግድ ሆዱን ብቻ እንዲያስብ ኅሊናውን ከጭንቅላቱ አውጥቶ እንዲጥል አድርገውታል፡፡ አስቀድሞም የእግዚአብሔር ቃል “የአውሬውም ስም ወይም የስሙ ቁጥር ያለው ምልክት የሌለበት ማንም ሊገዛ ወይም ሊሸጥ እንዳይችል ያደርጋል” ተብሎ ተጽፏልና ራዕ 13÷17፡፡
ነገር ግን ምናልባት አንዳንድ የዋሀን አይጠፉምና የወያኔ ደጋፊ አቀንቃኝ ወይም አባል ሆናቹህ እግዚአብሔርን የምታመልኩ የሚመስላቹህ ወይም ማምለክ የምትችሉ የሚመስላቹህ ካላቹህ እራሳቹህን እያታለላቹህ እየሸነገላቹህ ፈጣሪን ለማታለል እየሞከራቹህ እንደሆነ ላረጋግጥላቹህ እወዳለሁ፡፡ የወያኔ ደጋፊ ወይም አቀንቃኝ ስትሆኑ ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቹህ ግንኙነት ያኔውኑ ተቋርጧል፡፡ ምክንያቱም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ወያኔ በቅድስት ቤተክርስቲያን (በእግዚአብሔር) ላይ ለሚሠራው ጥፋትና ውድመት ወይም ጠላትነት አባሪ ተባባሪ ሆናቹሀልና፡፡ በመሆኑም ወያኔ ሆኖ ክርስቲያን መሆን አይቻልም፡፡ “ምን እናርግ” ብሎ ክርስትና የለም አባት አናቶቻችን “ምን እናድርግ” ብለው እጅና እግራቸውን አጣምረው በመቀመጥና የአላዊያን ነገሥታትንና የመናፍቃን ጳጳሳትን ግፍና ጥፋት በዝምታ በመመልከት አልነበረም ቤተክርስቲያንን ከእኛ አድርሰዋት የነበረው ማቄን ጨርቄን ሳይሉ አስፈላጊውን መሥዋዕትነት በመክፈል እንጅ፡፡ ክርስቶስ ከእኔ ይልቅ ሌላ ምንም ነገርን የሚወድ ለኔ ሊሆን አይገባም ብሏልና ልጆቸን፣ ወላጆቸን ፣ ኑሮዬን በሚል “ምን ላድርግ” የሚል ምክንያት ከክርስቶስ ፊት አይሠራም፡፡ ነገር ግን በጽናት በስሙ መከራ መቀበል ብቻ ነው የክርስቶስ የሚያሰኘው በፊቱም ሞገስን የሚያሰጠው መንግሥቱንም ለመውረስ የሚያበቃው፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ተገዶ ለወያኔ ያደረ ሰው ከደሙ ንጹሕ ይሆን ዘንድ ቢያንስ ቢያንስ ዕለት ዕለት ስለዚህች ቅድስት ቤተክርስቲያንና ስለዚህች ቅድስት ሀገር በእግዚአብሔር ፊት ተግቶ ማዘን ፈጣሪን መማፀን ይኖርበታል፡፡ ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ?
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ዕንቁ መጽሔት ቅጽ 5 ቁጥር 89 መጋቢት 2005ዓ.ም.
Leave a Reply