
… እንዴት ነበር ከቶ ውጣ-ውረዱ…?
…ተረተር፣ ሸለቆ…፣ አቀበት፣ ቁልቁለቱ…፣
…ጉድባው፣ ጉብታው…፣ አባጣ-ጎርባጣው…፣
…እሾኽ፣ እንቅፋቱ…፣ መሰናክል፣ ምቱ…፣
…ጠመዝማዛው ጉዞ…፣ እንዴት ነው መንገዱ?
የያሬድ ልጅ ጠቢብ – መንፈስ የማኅሌታይ፣
የሰልስቱ ዜማ – ግዕዝ፣ እዝል፣ አራራይ፣
ነፍስን መሳጭ ቅኝት፣ ገነተ-ሕይወት አምሳል፣
አንቺሆዬ፣ ባቲ፣ ትዝታ፣ አምባሰል፣
ዓለም ኖታ ሳይነድፍ – የነበርንን እኛን፣
ሕዳሴ-ወጥበብ – ዳግም አስተዋውቀን፤
የ”ክፉ ቀን” ጓድህን፣ የደስታ ምንጭህን፣ የውጥን አጋርህን…
ፒያኖህን ይዘህ ምጠቅ ክበርበት፣
ውጣ ተራራውን እስክትደርስ ከጫፉ…
ከምኩራቡ ስፍራ ያምላክ ቃል ካለበት፤
ፍጹም ልቀህ ቆመህ ከዚያ ክቡር ማማ፣
የገደል ማሚቶው ዘልቆ እስከሚሰማ፣
በአምባሰል መንፈስ፣ በዕልልታ ድምጸት፣ በሰመመን ቃና…፣
መስክር ባለም ዙሪያ – ዘላለም መኖሯን ኢትዮጵያችን ገና!
ዶ – ሬ – ሚ .. ሶል – ላ .. ዶ – የሙዚቃን ሳይንስ፣
ከሽነህ ክተበው – ለሁሉ እንዲዳረስ፤
አሳየው ለትውልድ – የረቂቅ ሙዚቃን፣
የተመስጦ መንፈስ – ውብ ረቂቅነቱን፤
አርቅ፣ ቀምር፣ ዘምር…
ሕያው ጥበብ ስራ – ዘመን እሚሻገር፤
ባለዋሽንት እረኛ፣ ለአንጋፋው ክብር ዕሴት አገርኛ፣
ሰላም እና ፍቅር፣ – የርግብ መልዕክተኛ፣
ጨዋታ…፣ ዕልልታ…፣ የክብር የደስታ ምስጋና ስጦታ..፤
.. ቁልቁል በየመስኩ – የጥበብ ወንዝ ይፍሰስ፣
ጋራ-ሸንተረሩን… ለምለም መሬት ያርስ፣
ያንን ተመግበው ቁጥቋጦች ይፋፉ፣ አበቦች ይድመቁ፣
ለታታሪ ንቦች – ተስፋን ይሰንቁ፤
ለዘላለም ዓለም – ሲቆጠር ዘመኑ፣
ለዘላቂው ሕይወት – ያገር አድባር ዋርካ ሞገስ እንዲሆኑ!
ያልተቻለው – ይቻል፣ ይቀጥል ጥረቱ፣
ይሁንልን በጎ – ላገር ተምሳሌቱ!
ክበር፣ ተመንደገው – በመረጥከው ሙያ፣
ግርማ! ሞገስ ሁናት ለእማማ ኢትዮጵያ!
ጌታቸው አበራ
ግንቦት 2007 ዓ/ም
(ሜይ 2015)
ግጥሙን በPDF ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ
____________________________________________________________
ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋ ገና ከጠዋቱ ጀምሮ፣ በያዘው ሙያ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ፣ እማይቻል እሚመስለው ነገር ተችሎት ዛሬ ካለበት እርከን ላይ የደረሰ እውቅ የሀገራችን ፒያኒስት (ክላሲካል ፒያኖ ተጫዋች)እና የረቂቅ ሙዚቃ ደራሲ ነው። በያዘው ሙያ ለሀገራችን ከፍተኛ አስተዋጽዖ በማድረግ ላይ ከመሆኑም በላይ፣ አርአያነቱም በሁሉም መስክ ለሀገራቸው በጎ ተግባር ለመከወን ወጥነው ለተነሱ ሁሉ የሚተርፍ ነው። ስለዚህም ኢትዮጵያውያን ግርማ የጥበብ ስራዎቹን በሚያቀርብባቸው ስፍራዎች ሁሉ በመገኘት ከረቂቅ ሙዚቃ ማዕዱ ልንቋደስና ለበለጠ ስራ ልናበረታታው ይገባል እላለሁ። በዚህ አጋጣሚ ግርማ ይፍራሸዋን፣ ለጥረትህ ፍሬ በመብቃትህ እንኳን ደስ ያለህ እያልኩ፣ በጀመርከው ረዥም የዳገት ጉዞ፣ ከ’ተራራ’ው ጫፍ ላይ በመድረስ፣ ለግልህ ከፍተኛ እርካታን፣ ለሀገርህ የላቀ አበርክቶትን፣ ለወገንህ ኩራትና አልኝታነትን በላቀ ደረጃ ታጎናጽፍ ዘንድ መልካም ምኞቴንና ሙሉ ተስፋዬን ለመግለጽ እወዳለሁ።
Leave a Reply