(ለውይይት መነሻ)
በዚህ ጽሁፌ ላንባቢዎቼ ለማቅረብ የፈለግሁት ሁለት ተያያዥ ጉዳዮችን ነው። የመጀመርያው፣ ወያኔ ላለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት ሲፈጽማቸው የነበረውን “ነውሮች” እንዴት እንደ “ጽድቅ” እንደተጠቀማባቸውና የኢትዮጵያንም ህዝብ “ጽድቅ” ነው ብላችሁ ተቀበሉ ብሎ እንዳስገደንና እኛም በመላመድ ብዛት ተዋህዶን እንደተቀበልነው፣ ሁለተኛው ደግሞ ይህንን “ነውር” እንደ “ጽድቅ” በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ጭኖ ሲበድል የነበረው ወያኔ (ህወሃት)፣ በምንም መልኩ የትግራይን ህዝብ እንደማይወክል ለማስረዳት ነው። ግምቱ የግሌ እንጂ የሌላ የማንንም አካል አስተሳሰብ ስላይደለ፣ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ለተካተቱት ግምቶች፣ መረጃዎችም ሆነ መደምደሚያዎች ተጠያቂው እኔ ብቻ ነኝ። ይህ እንግዲህ “ለውይይት መነሻ” የቀረበ ስለሆነ በይዘቱ ላይ ያላችሁን ሃሳብ እንደኔው በጽሁፍ ብታወጡ፣ ባገራችንን ላይ እያንዣባባ ያለውን አደጋ ሙሉ በሙሉ ያስወግዳል ባልልም፣ ሰላምን ለማስፈንና ብሎም ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት በምናደርገው መራራ ትግል የተወሰነ አወንታዊ ሚና ይጫወታል ብዬ እገምታለሁ።
ክፍል አንድ፡
ነውር ቅዱስ ሲሆን፣
ባገራችን “መሆን የሌለበት” ነገር “ሆኖ ስናገኘው” ትክክል ነው ብለን ማመንና መቀበል ከጀመርን ሰንብተናል። የሰው ልጅ ባህርይ የስነ ኅሊና ጠበብት ይህ “መሆን ያልነበረበትን” ክስተት “መሆን እንደነበረበት” አድርጎ መቀበል አደገኛ ስለሆነ በተቻለ መጠን መወገድ አለበት ይላሉ። በዘጠናዎቹ መጀመርያ አካባቢ ለሥራ ጉዳይ ወደ አፍጋኒስታን ሄጄ ገና የደረስኩ ሳምንት፣ ሙጃሄዲኖች ያላንዳች ዕረፍት መዲናዋን ካቡልን በመድፍ ይደበድቡ ነበርና፣ አሩሩ ባረፈ ቁጥር ሲያንቧርቅ ከመቀመጫዬ ብድግ እያልኩ ወደ በሩ ስሮጥ የታዘበኝ የጸጥታ ጉዳይ ኃላፊያችን ቀረበኝና “መደንገጥህ የሰው ልጅ ትክክለኛ ባህርይ ነው፣ ትክክል የማይሆነው ግን ስትለምደውና መበርገጉን ስታቆም ነው፣ ያኔ ይህን አገር ለቅቀህ መሄድ አለብህ” ብሎ መከረኝ። አዎ “ትክክል ያልሆነ” ነገርን “ትክክል” አድርገን መቀበል ስንጀምር፣ አእምሮአችን ነገሮችን የሚገመግመው “መሆን የነበረበት” ከሚለው ሳይሆን “መሆን ያልነበረበትን” ደጋግመን በመስማታችን ወይም በማየታችን ብቻ ተላምደነው “መሆን ያለበት” ክስተት አድርገን ከመውሰድ ነው።
ባለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት ወያኔ የሚፈጽማቸውን አንዳንድ የዜጎችን መብት ጥሰትና፣ እነዚህን ጥሰቶች “መሆን እንደነበረበት” ትክክለኛ ክስተተ አድርገው ካድሬዎቻቸውና ጀሌዎቻቸው በአደባባይ ሲሞግቱና ህዝቡን ሲያሳምኑ ሳስተውል፣ ህዝብም ደግሞ ይህንን “መሆን ያልነበረበትን ክስተት” “መሆን እንደ ነበረበት” ተቀብሎት ሲኖር፣ ምን ያህል ከሰው ልጅ ጤነኛ ባህርይ እንደራቅን ያመለክታል። ድርጊታቸውን ብቻ ሳይሆን የነዚህ የወያኔ መሪዎች ጠባይ ራሱ “እነዚህ ግለሰቦች እውነትም ሰው ናቸው ወይ” ብለን ራሳችንን እንድንጠይቅ አርጎናል። ጠ/ሚኒስትር መለስ ባንድ ስብሰባ ላይ ከልቡ ከት ብሎ ስስቅ አይቼ ከልቤ ደስ አለኝ ብሎ አንድ ጓደኛዬ ሲነግረኝ፣ ምን ደስ እንዳሰኘው አልገባኝምና ብጠይቀው “እኔኮ እነዚህ ሰዎች የሚያደርጉትን ስመለከት የእውነት ሰው አይመስሉኝም፣ ለካ እንደኛው ስሜታ ያላቸውና ደስ ሲላቸው የሚስቁ የግዜር ፍጡራን ናቸው” አለኝ። እንዲያብራራልኝ ስጠይቀው፣ እነዚህ እኮ ሰው ቢሆኑና እንደ ሰው ልጅ በትክክል የሚያስብ ጭንቅላትና ሰብዓዊ ስሜት ቢኖራቸው ኖሮ፣ ያሰለጠኗቸው ገራፊዎችና አሰቃዮች በማዕከላዊ ብቻ በወገኖቻችን ላይ የሚያደርሱትን ሰቆቃ እያዩና እየሰሙ ማታ ማታ ወደ ቤታቸው ተመልሰው በሰላም አያድሩም ነበረ። እንደሰው ልጅ ሰብዓዊ ስሜትና ትክክለኛ አዕምሮ ቢኖራቸው ኖሮ ዘወትር ከማትለያቸው ሽጉጥ አንዱን ጥይት ጠጥተው ከኅሊና ጭንቀት ይገላገሉ ነበር” አለኝ። አሳማኝ አባባል ነው። ግን ደግሞ፣ የኅሊና ጭንቀት የሚሰማው እኮ ኅሊና ላለው ሰው ነው።
እስቲ ለአብነት ያህል ወያኔ እየፈፀመብን ያለውን አንዳንድ “ነውሮች”ንና እኛም እየለመድናቸው መጥተን “መበርገግ ያቆምንባቸውን” ጠቀስ ጠቀስ በማድረግ አደገኝነታቸውን ለማስረዳት ልሞክር። ዓላማዬ “ነውርን” መላመድ ምን ያህል አደገኛ መሆኑን አውቀን፣ ህሊናን አደድቦ ከነውር ጋር ተላምዶ ከመኖር ይልቅ፣ ነውር ፈጻሚዎቹን በመቃወም፣ ቄሮዎችና ፋኖዎች እያደረጉ እንዳሉት በያለንበት በሰልፍ ወጥተን ድምጻችን ከፍ በማድረግ መቃወምና መታገል እንዳለብን ለማሳሰብ ነው።
ሀ) የኢትዮጵያን ህዝቦች በተለይም በአማራና በኦሮሞ ህዝቦች መካከል የነበረውንና የ1975ቱን የመሬት ዓዋጅ ተከትሎ ከሞላ ጎደል ዕልባት ያገኘውን ጥንት ወደነበረበት ሸካራ ግንኙነት ለመመለስ በነበረው ታላቅ የመከፋፈል ዕቅድ፣ በዘጠናዎቹ መጀመርያ ላይ በበደኖ አካባቢ የሚኖሩትን የአማራ ተወላጆች ከመኖርያ ቤታቸው አፍኖ በመውሰድ ወደ ገደል አፋፍ ወስዶ በቁም ሲቀብራቸው በቪዲዮ ቀርጾ “ኦነግ ያደረገው ነው” ብሎ ለህዝብ ሲያቀርብ፣ ድርጊቱ ትክክል እንዳልነበር ሁላችንም እናውቅ ነበር። ነገር ግን የዚያ ሁሉ ሰላማዊ ዜጋ ነፍስ መጥፋት “ኦነግን ከማስጠላት” ባሻገር ሌላ ዓላማ ያልነበረው የወያኔ ሴራ መሆኑን ሁላችንም ብናምንበትምና፣ እስከዛሬም ድረስ አንድም ግለሰብ ለዚህ ወንጀል ተጠያቂ አለመሆኑን እያወቅን፣ የዚያን ሁሉ ንፁሃን ህዝብ በቁም መቀበር ደግመን ደጋግመን ከማየታችን የተነሳ፣ “መደረግ ያልነበረበት” ነገር “መደረግ የነበረበት” አድርገን ስለወሰድን ዛሬ ያ የወያኔ ነውረኛ ተግባር ብዙም አያስበረግገንም። ተለማመድነውና!
ለ) ኦነግ ከሽግግር መንግሥት ራሱን ማግለሉን ተከትሎ እጅግ በጣም ብዙ የኦሮሞ ወጣቶች ከያሉበት ተለቅመው ከተወሰዱ በኋላ ብዙዎቹ እስከዛሬም ድረስ የት እንደደረሱ የማይታወቅና በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ደግሞ በጅምላ ተቀብረዋል፣ ብዙዎቹ ደግሞ የት እንደደረሱ አይታወቅም። በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ወላጆች ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የልጆቻቸውን ዕጣ ለማወቅ ያለማቋረጥ ያደረጉት ጥረት ከንቱ ሆኖ ቀርቶ፣ ከጊዜ ብዛትና ደጋግመን በመስማታችን ብቻ “መሆን ያልነበረበት” የግፍ ሥራን እንደ ትክክል ቆጥረን ኑሮ ቀጠልን። ተዋሃደንና!
ሐ) በምርጫ 97 ጊዜ፣ ምርጫው ተጭበርብሮአል በማለት በመዲናችን የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተሳተፉትን ወደ ሶስት መቶ የሚጠጉ ሰላማዊ ዜጎችን በጠራራ ፀሃይ በጥይት ከቆላ በኋላ፣ “እኛ እኮ ሺህ ሬሳ ላይ ተረማምደን የመጣን ነን” ብሎ ጠ/ሚኒስትር መለስ በአደባባይ የሶስት መቶ ነፍስ መጥፋት ምንም የሚያሳስብ ነገር አለመሆኑን በድፍረት ሲናገር፣ “በብዙ ሺህ ሰው ሬሳም ላይ ተረማምዶ መምጣትም አለ ለካ” ብለን የሶስት መቶ ዜጋን መሞት “መሆን እንደነበረበት” ተቀብለን ኑሮ ቀጠልን። ላንድ አገር እድገት፣ ለብዙሃን ነጻነትና ሰላም ሲባል፣ የብዙ ሰላማዊ ዜጎችን ነፍስ ማጥፋት “መሆን ያለበት” ድርጊት ነው ተብሎ በመደጋገም ስለተነገረን ተዋሃደንና ”ትክክል” እንደሆነ አድርገን መኖርን ቀጠልንበት።
መ) የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን ረቂቅ ዓዋጅ በመቃወም ሰልፍ የወጡትን የኦሮሞ ወጣቶች፣ “ህገመንግሥቱን ጥሳችኋል፣ መንግሥት ለመገልበጥ አሲራችኋል” በማለት ወደ ሃምሳ ሺህ የሚጠጉትን አስሮ ገርፎና አሰቃይቶ፣ የተወሰኑትን ደግሞ “ይቅርታ አስጠይቆና የተሃድሶ ትምህርት” ሰጥቶአቸው ሲፈታ፣ ወላጅ ዘመድ ሁሉ የተደሰተው በእስረኞቹ በሰላም መፈታት እንጂ “ሰዎቹ የተሰለፉት ህገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሰረት ቅሬታቸውን ለመግለጽ ስለሆነ ቀድሞውንም መታሰራቸው “ትክክል አልነበረም” ብሎ ለመጠየቅ ሰሚም መድረክም ስለሌለ “ተቀብሎት” ኑሮውን ቀጠለ። ወያኔም፣ ተሰልፎ ወጥቶ የመብትን መከበር መጠየቅ ህገ መንግሥታዊ አለመሆኑን ደጋግሞ ስለነገረን “ትክክል” ነው ብለን ተቀበልን። ተዋሃደና!
ሠ) የወያኔ ኤሊቶች የሚፈጽሙትን ፀረ ህዝብ ድርጊት ከቅርብ ሆነው ይከታተሉ የነበሩ ጋዜጤኞችና ዓምደኞች፣ ህገ መንግሥታዊ መብታቸውን ተጠቅመው በግልፅ በመጻፋቸውና በመሞገታቸው፣ “ህዝቡን በመንግሥት ላይ ለማነሳሳት ያደረጋችሁ ነው” ተብለው በየወህኒ ቤቱ ተወርውረው ለሥቃይ ሲዳረጉ፣ ሁላችንም ድርጊቱ “ትክክልና መሆን ያልነበረበት መሆኑን” እያወቅን ከዓቅም ማጣትና ለዓመታት መደጋገሙን ስናስተውለው የነበረ ክስተት በመሆኑ “ተዋህዶን” ከተቻለ ስንቅ በማቀበል፣ ውጭ አገር ያለነው ደግሞ አልፎ አልፎ በምናደርገው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ፎቶያቸውን ይዘን በመውጣት ቅሬታችንን በመግለጽ ተወስነናል። አንድ ዜጋ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ፣ በህገ መንግሥታችን መሰረት ሊደረግለት የሚገባው እንክብካቤ ምን መሆን እንዳለበት ግልጽ ሆኖ እያለ፣ በአሳሪዎቻቸው እጅ የሚደርስባቸው ሰቆቃና ግፍን በየቀኑ በእስረኞች ላይ የሚፈጸመውን “መሆን ያልነበረበትን” ነውረኛ ድርጊት “መሆን እንደነበረበት” አድርገን ተቀበለነው።
ረ) ከየእሥር ቤቶቹ የሚፈቱት የቀድሞ የፖሊቲካ እስረኞች ትክክለኛ መረጃን አስደግፈው ለዓለም ህዝብ የሚያሳውቁት የእሥር ቤቱ ሰቆቃ፣ ለጊዜው እጅግ ቢያሰቅቀንም ውሎ አድሮ ግን፣ በየቀኑ በእሥረኞቹ ላይ የሚፈፀም “መደበኛ ድርጊት” – routine በመሆኑ “ለምደነው” እንኳን እንቅልፍ ሊነሳን፣ የቀድሞ ታሳሪዎች በሚዲያ ቀርበው ካልተናገሩ በስተቀር ማስታወስም አቁመናል። አቶ ሃብታሙ አያሌውም በሱና በሌሎች እስረኞች ላይ የደረሰባቸውን ግፍ በተገኘው አጋጣሚ ተጠቅሞ በተደጋጋሚ ቢያስረዳንም ለመጀመርያው ሳምንት ብቻ እጅግ በጣም ቀፈፈን እንጂ፣ ደጋግመን በመስማታችን ብቻ አእምሮአችን ተላምዶት “መሆን ያልነበረበትን አሰቃቂ ድርጊት” “መሆን እንደነበረበት” አድርገን ስለወስደነው፣ እንደድሮው ለጆሮያችን አይቀፈንም።
ሰ) በሶማሌና ኦሮሚያ መካከል በተደረገው “ሰው ሰራሽ ግጭት” ወደ አንድ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በወያኔ አቀነባባሪነት በተሰነዘረባቸው ጥቃት ከመኖርያ ቤታቸው ተፈናቅለውና በየመንገዱ የተኮለኮሉትን ቤተሰቦች፣ ህጻናትና አዛውንት በቴሌቪዥናችን መስኮትና በዩቲዩብ እየተመለከትን፣ መሆን ያልነበረበት የወንጀል ድርጊት መሆኑን እያወቅን፣ ደጋግመን በማየታችንና በመስማታችን ምክንያት ተለማምደነው ወንጀል መሆኑን ቀስ በቀስ እየረሳነው ነው።
ሸ) ሰሞኑን በጨለንቆ ከዚያም በበደሌና ነቀምቴ፣ አሁን ደግሞ በወልድያና ቆቦ በአግዓዚ ጦር የሚገደሉትን ዜጎቻችንን ከቁጥር አንጻር ከማየት አልፈን፣ አንድም የሰው ልጅ ነፍስ፣ ያውም ወንጀል ያልሰራና መብቱን ብቻ የጠየቀ ዜጋ በገዛ ወገኑ፣ ያውም ግብር እየከፈለ ባኖረው “ጸጥታ አስከባሪ“ ተብዬዎች እንደ እንስሳ በቄያቸው በየመንደራቸው በየትምህርት ቤቱ ሲገደሉ፣ እያየንና እየሰማን ”መሆን ያልነበረበት“ የወንጀል ሥራ መሆኑን እያወቅንና ነፍሰ ገዳዮቹም በኢትዮጵያ ህግ መሰረት ለፍርድ መቅረብ የነበረባቸው ግን ደግሞ ከህግ በላይ የሆኑ በመሆናቸው ውስጣችን እየበገነ፣ ሳንፈልገው በግድ በመላመድ ብቻ ወንጀልን እንደ ቅድስና ወስደን የየቀኑ ሥራችን ላይ ማተኮር ቀጠልንበት።
እንደነዚህ ዓይነቶቹን፣ መሆን ያልነበረባቸውን ክስተቶችን ሃያ ስድስት ዓመት ሙሉ ደግመን ደጋግመን ከማየታችንና
ከመስማታችን የተነሳ “ተላምደነው” ተፈጥሮያዊ ስሜታችን ደንዝዞ ሰብዓዊ መልስ መስጠት ሳይችል የቀረበትን ተፈጥሮያዊ ያልሆነውን ሁኔታ ነው እንግዲህ፣ ያኔ ካቡል የነበረው የሥራ ባልደረባዬ “መድፍ ሲተኮስ መበርገግ ያቆምክ ዕለት ከሰው ልጅነት ባህርይ ርቀህ መሄድህን ያመላክታልና አገሩን ለቅቀህ መሄድ አለብህ” ያለኝ። ነውር ተደጋግሞ በመፈጸሙ የተዋሃደንን ያህል ነውረኞቹም ነውርን እንደ ቅዱስ ሥራ በመውሰድ በድርጊቱ ሲቀጥሉበት፣ ሁላችንም ሰብአዊ ስሜትን እያጣን ነው። የሚገርመው ደግሞ እኛ የክስተቱ “ሰለባዎች” ብቻ ሳንሆን “አድራጊዎቹም” እርኩስ ድርጊትን ደግመው ደጋግመው በማድረጋቸው ብቻ ተዋህዶአቸው፣ ክፉ ነገርን መሥራት “ነውር” አድርገው አያዩትም፥ ለዚህም ነው ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትራችን አምላክ ይቅር ይበለውና፣ ሰውን መግደል ትክክል እንደሆነ አድርጎ ሊያሳየን ሲሞክር በመኩራራት “እኛ እኮ ስንት ሺህ ሬሳ ላይ ተረማምደን ነው የመጣነው” ብሎ ስሞታችንን እንደ ጅልነት በመቁጠር ያጣጣለብን።
ለመሆኑ እነዚህ በየመንገዱ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን በጥይት የሚገድሉት “ወገኖቻችን”፣ እንዴት ከሰው ልጅ ያልተፈጠሩናወንድም ወይም እህት የሌላቸው ይመስል ባንድ የግዜር ፍጡር ላይ አልመው ይተኩሳሉ? እንደው እንዴት ቢሰለጥኑና ማንስ ቢያሰለጥናቸው ነው እንደ ዱር አውሬ ሊሆኑ የቻሉት? እነዚህ በማዕከላዊና በሌሎችም እስር ቤቶች ዜጎቻችንን እያሰቃዩ የሚገኙና ይህንኑ በሰማያዊውም ሆነ በምድራዊ ህግ ነውር የሆነውን የሰውን ልጅ “ማሰቃየትን” እንደ አንድ ሙያ አድርገው የሰለጠኑ “ወገኖቻችን”፣ ጧት ጧት እንደ ማንኛውም ሠራተኛ ልብሳቸውን ለብሰው ክራቫት አድርገው፣ “ውይ ረፈደብኝ እባክሽ ልጆቹን ቶሎ ቶሎ አልብሺልኝና ትምህርት ቤት ላድርሳቸው” ብለው ሚስቶቻቸው ላይ የሚያንቧርቁ “አባ ወራ የመንግሥት ሰራተኞች”፣ በወሩ መጨረሻ ላይ ደግሞ እንደማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ ከሙያቸውና ከሰሩት ሥራ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ደመወዝ ተቀብለው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ፣ እንደው ልጆቻቸው አንድ ቀን “አባባ ዛሬ በትምህርት ቤታችን ቲቸር ፎርም ሲያስሞላን፣ ያባታችሁ ሥራ ምንድነው ብሎ ሲጠይቀን መመለስ አልቻልንምና፣ “ለመሆኑ ሥራህ ምንድነው? ቀኑን ሙሉስ ምን ስትሰራ ነው የምትውለው? ተብለው ቢጠየቁ “አሰቃይ” ነኝ ብለው ይመልሱ ይሆን የሚለው ሁሌም የሚዘገንነኝ ጉዳይ ነው። ደግሞ እንደሰው ከሰው ልጅ ተፈጥረው በገዛ ወገናቸው ላይ ይህን ዓይነት ሥቃይ የሚያደርስ የጭካኔ መንፈስንስ እንዴት አድርገው ነው የተካኑት? ራሳቸውም ቢጠየቁ መልሱን የሚያውቁ አይመስለኝም። ጭንቅላታቸው እንደሰው ልጅ ጭንቅላት አያስብምና!
ላለፉት ሶስት ዓመታት እጃቸውን አጣምረው ለሰልፍ በወጡ የኦሮሞ ልጆች ወይም በኮምፒውተር ኪቦርድ ብቻ ይሞግታቸው በነበረው እስክንድር ነጋ ላይ፣ ወይም ደግሞ የሰላምና የአንድነት ሰባኪውን ፖሊቲከኛ በቀለ ገርባን፣ አሁን ሰሞኑን ደግሞ በወልዲያና ቆቦ ሰላማዊ ወገኖቻችን ላይ ኢሰብአዊ ድርጊት እየፈፀሙ ያሉት “አማርኛ ተናጋሪ” ያልሆኑ ናቸው የሚል የጋራ ድምዳሜ ላይ የተደረሰ ይመስላል። ብዙዎቹ የቀድሞ ታሳሪዎችና የስቃዩ ሰለባዎችም አሰቃዮቻቸው ትግርኛ ተናጋሪ መሆናቸውን በግልፅ ይናገራሉ። በመሆኑም አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ በዚህ “አማርኛ ተናጋሪ” ባልሆኑት ግለሰቦች የግፍ አሰራር ምክንያት የትግራይ ህዝብን በጅምላ እንደ ክፉ ማየቱ ባያስገርምም፣ ወያኔ የትግራይ ህዝብ ተወካይ አለመሆኑንና እነዚህን አሰቃቂ ድርጊቶች በዜጎች ላይ ሲፈፅምም የራሱን ኤሊቶችና የጀሌዎቻቸውን ምጣኔ ሃብታዊና ፖሊቲካዊ ሥልጣን ለማደላደል እንጂ ለትግራይ ህዝብ አንዳችም ዓይነት ጥቅም ለማስገኘት እንዳልሆነ ማወቅ ግዴታችን ይመስለኛል።
ክፍል ሁለት፣ ወያኔ የትግራይ ህዝብ ተወካይ አይደለም የሚለው ተከታዩ ጽሁፌም ይህንኑ አሳሳቢ ጉዳይ ለመዳሰስ የታቀደ ነው።
በቸር ይግጠመን።
*****
ባይሳ ዋቅ-ወያ፣ ጄኔቫ 30 January 2018
wakwoya2016@gmail.com
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Ali says
በጣም ግሩም ጽሁፍ!
Mulugeta Andargie says
ምን ግሩም ጽሁፍ ነው?? ያንዳንድ ደደቦች ትንታኔ ነው። በስራ ስህተተ ይፈጸማል። ገሃነም ግባ ይባላል?? ነውር ነው!! እየተማማርን !!!!
Robel Tesfaye says
Nice view!!!
Mulugeta Andargie says
ሰዎች!! እንደዚህ ዓይነቱን ስዕል ኮምፕዩተር በጣም እየሳለ ህዝብ ያታልልበታል!!! ይህ ስዕል መቼ ተሳለ? መቼ ተቀረጸ ብለን ብንጠይቅ፣ የዛሬ ሃምሳ ዓመት ይሆናል!! ኣትመኑት!! ስዕል ባሁኑ ጊዜ ብዙ የማወናበጃ መንገድ ሆኖ ተገኝቷል!!!
Editor says
ይሄማ አንተ ሞትኩለት፤ በረሃ ተዋጋሁለት እያልክ እንደ ተበላሽ ካሴት እየደጋገምክ የምትዘፍነው የህወሃት የወንበዴዎች ቡድን አባል የሆነ አንድ ወንበዴ ሜክሲኮ አደባባይ ላይ አንድን ወጣት ገድሎ አስከሬኑን እንዳያመልጠው ይሁን ወይም መልሶ ሊገድለው እያሰበ ይሁን በማይታወቅ መልኩ ሲጠብቅ ነው የሚታየው፡፡
ሜክሲኮ አደባባይን አንተ ቀን ተሌት የምትዘፍንለት የአሸባሪው የህወሃት ወንበዴ ድርጅት አባላት አፍርሰውት ከቦታው ጠፍቷል፡፡ ከበረሃ ጀምሮ ድልድይ በማፍረስ እና ለረሃብተኛ የተላከ ስንዴ በመሸጥ የሚታወቀው የወንበዴዎች ቡድን ታሪካዊውን የሜክሲኮ አደባባይ አፍርሶ ይህንን በደም የተበከለ ታሪኩን አብሮ ሊያጠፋ ቢፈልግም በፍጹም የሚረሳ አይደለም፤ ማስረጃው ምስክር ነው – ዓይን የሚሠራ ከሆነ ወይም ከህወሓት ወንበዴ ሌላ ማየት የሚችል ከሆነ ፎቶውን በቅርብ ተመልከተው ማስረጃውን ታየዋለህ፡፡
በባዶ ቤት ስለማታውቀው ከተማ ልታወራ አትሞክር፡፡ ይህ አንተ ነበርኩበት የምትለው ሰው አልባና ግፍ የሚፈጸምበት በረሃ አይደለም – ይህ መሃል አዲስ አበባ ነው፡፡
ስለ ፎቶ የምታውቀው መስለህ መቅረብህ የሌላቸውን ዲግሪ ከየወፍጮቤት እየገዙ የዲግሪ ባለቤት እንደሆኑት ጌቶችህ የበረሃ ወንበዴዎች አዋቂ መስለህ ለመታየት ያደረከው ያልተሰካ ሙከራ ነው፡፡
አርታኢ