በአንድ ሰኮንድ ውስጥ ስንት ነገሮች ስንት ሁኔታዎች ይታያሉ?፣ ስንት ድርጊቶች፣ ስንት ሥራዎች ይፈጸማሉ? ስንት ሰዎች ይሞታሉ? ስንት ሰዎች ይወለዳሉ? … አንድ ሰኮንድ ባዘለው ጊዜ ውስጥ ብዙ ጥያቄዎች አሉ፤ በአንድ ደቂቃ ውስጥ ባለው ጊዜ ውስጥ ቢያንስ የስድሳ ሰኮንዶችን ያህል ጥያቄዎች ይፈለፈላሉ፤ በአንድ ሰዓት ውስጥ 60*60= 3600 እነዚህ ደግሞ በ24 ሰዓት ሲባዙ 86 400 ይሆናሉ፤ የሚሆኑትንና የሚደረጉትን ነገሮች ሁሉ መዝግቦ፣ የሚነገሩትን ነገሮች ሁሉ አጣርቶ ይዞ ለሚቀጥለው ትውልድ የሚያስተላልፍ አለ ወይ? የትናንትናውን ሃያ አራት ሰዓት በዝርዝር ማስታወስ የሚችል አለ ወይ? ጊዜውና መሣሪያው ያላችሁ የሳምንቱን፣ የወሩን፣ የዓመቱን ሰኮንዶችና ያቀፉትንና ያዘሉትን ጉዳዮች አጣርታችሁ ለማወቅና ‹‹ተረቱንና ታሪኩን›› ለመለየት ሞክሩ፡፡
እንደኔ የጂኦሎጂ ሀሁ የሚያውቅ ደግሞ ሌላም ጥያቄ ሊያቀርብ ይችላል፤ በጂኦሎጂ ታሪክ የሚቆጠረው በሚልዮን ዓመታት ነው፤ የዛሬ መቶ ሚልዮን ዓመት ምድር እንደዚህ ነበረች፤ ከዚያ በኋላ በዚህ፣ በዚህ ተለዋወጠች እያለ ይነግረናል፤ ተረት ነው የምንለው ወይስ ታሪክ? እንዲያውም አንድ እውነት ልንገራችሁ፤
አሜሪካ አኔ በተማርሁበት ዩኒቨርሲቲ አንድ በበረዶ ድንጋይ በዓለም የታወቀ ፕሮፌሰር ነበረን፤ አንድ ቀን ለመስክ ጥናት ወስዶን አንድ አነስ ያለ ሐይቅ ያለበትን ረባዳ መሬት ቁለቁል እያሳየን የድንጋይ በረዶው ከየት ተነሥቶ ወዴት ሲንሸራተት እንደነበረና ምን እንዳገደውና ሐይቁ እንዴት እንደተፈጠረ ነግሮን ሲጨርስ አጠገባችን ቆሞ ሲያዳምጥ የነበረ የአካባቢው ሰው ድምጹን ከፍ አድርጎ ‘ይህንን ሐይቅ የሠራነው እኛ ነንእኮ!’ አለ፤ የኛ ዓለም ያደነቀው ፕሮፌሰር ሁለቱንም እጆቹን ወደሰማይ ዘርግቶ፣ ‘ያውላችሁ የኔ ሀሳብ ብትንትኑ ወጣ!’ አለን! ታሪክን ተረት ማለት ተረት አያደርገውም፤ ተረትን ታሪክ ማለትም ታሪክ አያደርገውም፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ታሪክ ሊቃውንት ሁሉ ኢትዮጵያውያን ከአረብያ ፈልሰው የመጡ ናቸው እያልን ፈረንጆች የነገሩንን እናስተምር ነበር፤ ሁለመናችን ከአረቦች የመጣ መሆኑን አስተምረናል፤ አሁን አንድ ሌላ ፈረንጅ መጣና ‘የለም፣ ሰዎች ከኢትዮጵያ ወደአረብያ ፈለሱ እንጂ ከአረብያ ወደኢትዮጵያ አልፈለሱም፤ ኢትዮጵያ ሰጪ እንጂ ተቀባይ አልነበረችም፤’ ይለናል፤ የቱ ነው ተረት? የቱ ነው ታሪክ? አንዱ የኢትዮጵያ ታሪክ ሊቅ በቅርቡ በጻፈው የፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ታሪክ ውስጥ ‘አጼ ምኒልክ ወደደቡብ ሲስፋፉ’ ብሎ ይጀምራል፤ አጼ ሱስንዮስ ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት ደቡብ እንደነበረ፣ አንድ ንጉሠ ነገሥትም ዘይላ አካባቢ እንደሞተ፣ የደቡብ እቴጌዎች እንደነበሩ ይነገራል፤ ታዲያ ተረቱ የቱ ነው? ታሪኩ የቱ ነው? ፈረንጅን ተከትሎ ማነብነብ የዘመኑ ባህል ሆነ፤ ጎፈሬን እኛ ስንጠላው ፈረንጅ አገር ገባና ስሙን ለውጦ አፍሮ ተብሎ መጣልን!
የፍቅሬ ቶሎሳን መጽሐፍ ከጊዜው የስደተኞች ፖሊቲካ ጋር አያይዘው የፖሊቲካ አስታራቂነት ተልእኮ የሚሰጡት ሰዎች የመጽሐፉ መሠረት የገባቸው አይመስለኝም፤ እኔንም ካላመለጠኝ መጽሐፉ ሁለቱን የዓለም መሠረታዊ ባላ — ቦታንና ጊዜን — አቀራርቦና አዋኅዶ የያዘ በመሆኑ ከጊዜያዊነት ውጭ መስሎ ይታየኛል፤ መጽሐፉ ለብዙዎቻችን ከባድ የሆነውም በዚህ ምክንያት ይመስለኛል፡፡
ስንት የፈረንጅ ተረቶችን ሳንጨነቅ ታሪክ ብለን አስተምረናል? ስንት የራሳችንን ታሪክ ተረት ብለን ጥለናል? ፍቅሬ ቶሎሳ ያቀረበው አዲስ ነገር ነው፤ አበሻ ደግሞ አዲስ ነገርን አይወድም፤ የፍቅሬን መጽሐፍ እኔ መሀከሉ ደርሼ መቆሜን ነግሬዋለሁ፤ ሰኮንዶቹን፣ ደቂቃዎቹንና ሰዓቶቹን፣ ቀኖቹንና ወሮቹን፣ ዓመቶቹን መንጥሮ ያላየ ሰው እንዴት ብሎ በምን መለኪያ ተረቱንና ታሪኩን በእርግጠኛነት መለየት ይችላል? ለመሆኑ የፍቅሬ ቶሎሳን መጽሐፍ ተረት ነው ለማለት የምንችለው ርእሱን በየት በኩል አልፈን ነው? እኔ መጽሐፉን አንብቤ አልጨረስሁትም፤ በሕይወቴ ጀምሬ መጨረስ ያቃተኝ መጽሐፍ የፍቅሬ ቶሎሳ ሁለተኛው ነው፤ ሌላው ከጀመርሁት ሃምሳ ዓመት የሚሆነው መጽሐፍ የፈረንሳዩ ፈላስፋ የዣ ፖል ሳርትር አንድ መጽሐፍ ነው፤ ሁለቱንም መጽሐፎች አንብቤ ሀሳብ ለመስጠት አለመቻሌ የኔ ጉድለት እንጂ የደራሲዎቹ አይደለም፡፡
በበኩሌ እንደፍቅሬ ያሉ ከያለበት ቃርመው፣ የራሳቸውን አእምሮ አስረግዘውና በምጥ አስጨንቀው አዲስ ነገርን የሚያቀርቡልንን ያበርታችሁ እላለሁ! ግን እንድንደርስባችሁ አለምልሙን!
ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም
የካቲት/2009
Leave a Reply