* ኃላፊዋ በዕለቱ አለመገኘታቸው “ለወደፊቱ እንዳይደገም” ማሳሰቢያ ተሰጣቸው
በዛሬው ዕለት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የ2015 /2016 በጀት አመት የፓስፖርት አገልግሎት አሰጣጥና ውጤታማነትን በተመለከተ የተከናወነ የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት እንዲሁም የ2015 የሂሳብ ኦዲት ሪፖርት ላይ ለመወያየት ስብሰባ ጠርቶ ነበር።
ነገር ግን የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ስብሰባው ላይ ሳይገኙ መቅረታቸው ቁጣን ፈጥሯል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሺእመቤት ደምሴ (ዶ/ር) ምን አሉ?
“በመሰረቱ ምክር ቤቱ ተመርምረው የቀረቡለትን የዋና ኦዲት ሪፖርቶችን ይፋዊ ውይይት የሚያደርግባቸው የመስሪያ ቤቱ የበላይ ኃላፊ ነው።
“እኔ የመጣችሁትን የተመርማሪ መ/ቤት ኃላፊዎች ኃላፊነታችሁን አከብራለሁ ነገር ግን ዋና ኃላፊ በኦዲት ሪፖርት ምርመራ ላይ መገኘት ግዴታ ነው።
“ዋና ኃላፊዋ በሀገር ውስጥ የሉም። ነገር ግን ደብዳቤያችን ከደረሳቸው በኋላ ነው የወጡት። ይህ ድርጊት ተገቢ አይደለም።
“እኛ ከ10 ቀን በፊት ነው የምናሳውቀው ከ10 ቀን በፊት የምናሳውቅበት የራሱ ምክንያት አለው። መገኘት የማይችሉ ከሆነ reschedule መደረግ ካለበት reschedule መደረግ አለበት አለበለዚህ ግን ችግር የለውም ባላቹ ሰዎች መካሄድ ይችላል ተብሎ ወደ ጎን የሚተው ተግባር አይደለም።
“ይሄ እኮ የመ/ቤቱ ቁልፍ ተግባር ነው።
“ምክር ቤቱ ሃብት ነው የሚሰጠው፣ ይህ ሃብት በአግባቡ፣ በህግ እና በስርዓት መዋሉን ማረጋገጥ መቆጣጠር ይፈልጋል በዛ በሚቆጣጠርበት ሰዓት ኃላፊነት የሰጣቸው አካል አለመገኘት ተገቢ አይደለም።
“በርካታ ስራዎች ሊኖሩ ይችላሉ ግን ከበርካታ ስራዎች የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው (በኦዲት ምርመራ ሪፖርቱ ላይ መገኘት)።
“ይህ የሚያመላክተው ለኦዲቱ የሰጣችሁትን ትኩረት ነው። ትኩረት መስጠታችሁ አንዱ ማሳያ ተገኝቶ ይሄን ተምሪያለሁ፣ ፈጽሚያለሁ፣ ይሄን አልፈጸኩም ብሎ ፊት ለፊት ያልፈጸመበትን ምክንያት ማስረዳት ከአንድ ኃላፊ የሚጠበቅ ነው። ለወደፊቱ እንዳይደገም አሳስባለሁ” ብለዋል።
ምንም እንኳን ዋና ኃላፊዋ ባይገኙም ስብሰባው ምክትል ዋና ዳይሬክተሮቹ ቢቂላ መዝገቡ እና ጎሳ ደምሴን ጨምሮ ሌሎችም አመራሮች በተገኙበት ተካሂዷል።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሮቹ በተፈጠረው ነገር ይቅርታ ጠይቀው “ድጋሚ አይደገምም” ሲሉ ቃል ገብተዋል።
ዋና ኃላፊዋ መገኘት የማይችሉ ከሆነው ቀድመው መናገር ነበረባቸው ተብሏል።
በዚህ አይነት መንገድ (ዋና ኃላፊዋ በሌሉበት) ስብሰባውን ማድረግ የማይገባ ቢሆንም ከዋና ኦዲተር ጀምሮ፣ ከጠ/ሚ ፅ/ቤት ፣ ከተለያዩ ተቋማትም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጊዜያቸውን መስዕዋት አድርገው “ዋና ተግባራችን ነው” ብለው ስለተገኙ ብቻ ስብሰባው መደረጉ ተገልጿል።
በዛሬው ስብሰባ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በ2015/2016 በጀት ዓመት የክዋኔ እና ሂሳብ ኦዲት ሲመረመር በርካታ ገድለቶች መገኘታቸው ተገልጿል።
ከሪፖርቱ በመነሳት ቋሚ ኮሚቴው በርካታ ጥያቄዎችን አቅርቧል። በጥያቄዎቹ ላይም የአገልግሎቱ ኃላፊዎች ምላሽ ያሉትን ሰጥተዋል።
“ዜጎች ምን ያህል እንደሚንገላቱ የአይን ምስክር ነኝ” – የሺእመቤት ደምሴ (ዶ/ር)
ዛሬ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የፓስፖርት አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ በተካሄደው የ2015/2016 የክዋኔ እና ኦዲት ሪፖርት ስብሰባ ላይ በመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኩል ስለ ሰራተኞች ስነምግባር፤ ስለ ዜጎች እንግልት ተነስቷል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሺእመቤት ደምሴ (ዶ/ር) መ/ቤቱን “ሁላችንም የምንረግጠው በር ነው ያላችሁ” ሲሉ ገልጸዋል።
“ነገር ግን ሁላችንም ተጠቂ / Victim የሆንበት ጉዳይ ነው እውነቱን ለመናገር” ሲሉ ተናግረዋል። ይህንን ያሉት ስለ ሰራተኞች ስነምግባር እና ስለ ተገልጋይ እንግልት ባነሱት ሃሳብ ነው።
በጉዳዩ ላይ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ኃላፊዎች ለምክር ቤቱ “አጃቢዎቻቸው፣ በቋንቋ፣ ቦታ ባለማወቅ … በተለያዩ ምክንያቶች አጅበዋቸው የሚመጡት እንጂ አገልግሎት ፈላጊዎቻችን አይደለም የሚንገላቱት” ብለዋል።
የምክር ቤት አባልና የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ ግን “እኔ ምስክር ነኝ እኔ ተንገላትቻለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
“እኔ ተንገላትቻለሁ፤ እኔ ተገፍቼ ወጥቻለሁ ያውም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መታወቂያ እያሳየሁ፤ ተጎትቼ ወጥቻለሁ ይህንን ከማንም አይን እማኝ አይደለም እኔ ላይ የደረሰ ነው። እኔ ይሄንን የምለው እኔ ተበድያለሁና እኔ ለምን ተበደልኩ ብዬ አይደለም” ብለዋል።
“እኔ ይህን ሃሳብ እያቀረብኩ ያለሁት ከኃላዬ ያለው ዜጋ ምን ያህል እንደሚንገላታ የአይን ምስክር ነኝ ለማለት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
“ይህንን ፈትሹት ፤ ሩቅ አይደለም የሩቅ ጊዜ ትዝታ አይደለም እየናገርኳችሁ ያለሁት ዛሬ ላይ እየተፈጸመ ያለ ነው” ብለዋል።
“አገልግሎት ፈላጊው ወረቀት ይዞ፣ የሞላውን ፕሪንት አድርጎ ይዞ በጣም እየተንገላታ፤ እየተገፋ ያለበት ሰዓት ነው ያ መሆን የለበትም” ሲሉም አሳስበዋል።
አክለው “ለዜጎቻችን መስጠት የምንችለውን አቅማችን የፈቀደውን አገልግሎት በአግባቡና በስርዓት ልንሰጥ ይገባል እንጂ ከዛም አልፎ መንገላታትን ልንጨምርበት አይገባም” ብለዋል።
መ/ቤቱ ያሉትን ቅርንጫፎች አቅም እንዲያጠናክር እና ዜጎችን ከሚያንገላታ አሰራር እንዲታረም በጥብቅ አሳስበዋል። (ቲክቫህ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply