በፈረንጆች ባህል እውቀት ሥልጣን ነው፤ እንዲያውም እውቀት ኃይል ነው ይላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ባህል እውቀት ሥልጣን የለውም፤ እንዲያውም ሥልጣን እውቀት ይመስለናል፡፡
በ1951 ዓ.ም. በትግራይ ችጋርን በዓይኔ አይቻለሁ፤ በጆሮዬ ሰምቻለሁ፤ በአካሌ ቀምሼዋለሁ፤ ጠኔ ይዞኝ ተደግፌ ወደቤቴ ገብቻለሁ፡፡ በመቀሌ ያየኋት አንዲት የመቀሌ ወጣት እናት ከነሕጻንዋ በአእምሮዬ ተቀርጸውና ተቆራኝተውኝ በሕልሜም በእውኔም እየወተወቱኝ ስለችጋር እንዳጠና አስገደዱኝ፡፡
ችጋርን እያገላበጥሁ ከሰባት ዓመታት በላይ አጠናሁ፤ የጥናቴ ውጤት RURAL VULNERABILITY TO FAMINE IN ETHIOPIA: 1958-1977 በሚል ርእስ በህንድ አገር፣ በኒው ዴልሂ ከተማ ታትሞ በ1977 ዓ.ም. (በአአ በ1984) ወጣ፤ በአሜሪካ የተማርሁበት ክላርክ ዩኒቨርሲቲ ለጥናቱ ድጎማ የሚሆን የ$30,000 ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በእኔ በኩል አበርክቶአል፤ ለእኔ የተረፈኝ አንድ መቶ መጻሕፍት ብቻ ነበር፡፡
እአአ ከ1984 ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ መጽሐፉ ይሸጣል፤ እኔ ሳልጠየቅ አንድ INTERMEDIATE TECHNOLOGY Publications (9 King Street, London WC2E 8HW,UK), የሚባል የእንግሊዝ ኩባንያ እአአ ከ1986 ጀምሮ በተደጋጋሚ እያሳተመ ይቸበችበዋል፤ ለእኔ አንድ ሣንቲም አልደረሰኝም! በዚህ የችጋር ምክንያት ሌሎች የደረሱብኝን ነገሮች መግለጹ አይደለም፤ ጥቁር ከመሆን፣ ኢትዮጵያዊ ከመሆን፣ … የተነሣ የተሰነዘሩ ነገሮች አሉ፡፡
ከዚያም በኋላ አንዳንድ ጥያቄዎችን ለመመለስ ስል በሰሜን ሸዋና በደቡብ ወሎ አውራጃዎች በጣም ዝርዝር የሆነ ጥናት በሁለት መቶ ሰማንያ አምስት መንደሮች ጥናት አካሂጄ ውጤቱ እአአ በ1991 SUFFERING UNDER GOD’S ENVIRONMENT: A Vertical Study of the Predicament of Peasants in North-Central Ethiopia, (Published by AFRICAN MOUNTAINS ASSOCIATION AND GEOGRAPHICA BERNENSIA, Marceline, Missour, USA, 1991) ታተመ፡፡
ዛሬ በቴሌቪዥን ስለድርቅ፣ ስለችጋር የሚያወሩና በተለያየ ቦታ የሚጽፉ ኢትዮጵያውያን እነዚህን ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን መጽሐፎች ሲሆን ሁለቱንም፣ አለዚያ አንዱን ያላነበቡ ከእግር ጥፍራቸው እስከራስ ጸጉራቸው በእፍረት ይከናነቡ፤ የኢትዮጵያ ታሪክም ሆነ ማኅበራዊ ሁኔታ በእውቀት፣ ማለትም በተጣራ እውቀት እየዳበረ ከትውልድ ወደትውልድ እንዳይተላለፍ የሚያደርገው ይህ አስመሳይነትና የመንፈስ ውርደትና የአእምሮ ስንፍና ነው፤ እውቀት የማኅበረሰብ ሞተር ሆኖ ወደፊት የሚያራምደው ከቀደመው ትውልድ የተረከቡትን በሚገባ አጥንተውና አዳብረው ለሚቀጥለው ትውልድ ሲያስረክቡ ነው፤ ወይም የተረከቡት የማይረባ መሆኑን አስመስክረው ሲጥሉትና በሌላ ሲተኩት ነው፡፡
ሰሞኑን የማየውና የምሰማው ያሳፍረኛል!
በዚህም ምክንያት ከትውልድ ወደትውልድ እውቀት ሆኖ የሚተላለፈው ከሥልጣን ጋር የተያያዘው ብቻ ነው፤ ሥልጣን፤ የእህል ምርት እጥረት፤ የእህል ምርት እጥረት የሚከሰተው ድርቅ የተፈጥሮ ቀውስ፣ ችጋር በጭቆና መኖር፣ ችጋር ማንን ያጠቃል?
ሰሞኑን ብዙ ጸሐፊዎች ስለችጋር ያወራሉ (አብዛኛዎቹ የሚሉት ረሀብ ነው)፤ እንደሚመስለኝ እነሱ መጻፍ ከመጀመራቸው በፊት ስለችጋር ማንም ያሰበ፣ ማንም የጻፈ አይመስላቸውም፤ ስለዚህም በነሱ ቤት የሚጀምሩት ከዜሮ ነው፤ ስለዚህም በረሀብና በችጋር መሀከል ያለውን ልዩነት አያውቁትም፤ ስለዚህም በድርቅና በችጋር መሀከል ያለውን ልዩነት አያውቁትም፤ ስለዚህም በችጋሮች መሀከል ያለውን ልዩነት አያውቁም፤ ሳያውቁ ለማሳወቅ መሞከር ከምን ይመጣል?
ኅዳር 2008
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply