
(ይህንን ጽሁፍ በከፊል ከሁለት ዓመት በፊት በ16-08-2011. “ሁለቱም መስመሮች ይጎዱናል” በሚል አርዕስት አውጥቼው በተለያዩ የኢንተርኔት ድኅረ ገጾች ተነቦ የነበረ ቢሆንም፣ አብዛኛው ጽንሰ ሃሳብ፣ ሰሞኑ እየተካሄደ ካለው ጽንፈኛ የጎጥ ፖለቲካ ጋር፣ ብዙ ተያያዥነት ያለው ስለሆነ፣ አንዳንድ ከወቅቱ ሁኔታ ጋር የማይሄዱትን አስተካክዬ፣ ካሁኑ ሁኔታ ጋር አያይዤ ነው ያቀረብኩት፡፡ ፒዲኤፉ ብቻ ስለሆነ በእጄ የቀረውና ከፊሉን ማረም ስላልቻልኩኝ፣ ስለጥራቱ አስቀድሜ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡)
ሰሞኑን በዲያስፖራ የፓልቶክ የውይይት መድረኮች፣ የአጼ ሚኒሊክንና እና ቴዲ አፍሮን በሚደግፉና በሚቃወሙ፣ በመቶዎች በሚቆጠሩ ታዳሚዎች መሃከል ይካሄድ የነበረውን ውንጀላና፣ መከላከልን እኔም ለጥቂት ቀናት እያዳመጥኩኝ ስከታተል፣ ሁኔታው እንዳሳዘነኝ የገባት ባለቤቴ፣ ወንበሯን ስባ ተጠግታኝ፣ እሷም በእንግሊዘኛ የሚጻፈውን ቴክስት ለማንበብ እየሞከረች “ሰሞኑን ደሞ ምን ተፈጠረ? ደስተኛ አትመስልም!”አለችኝ፡፡ እኔም ጠቅለል ባለ መልኩ፣ አዲስ በተከፈተው “የጄኖሳይድ. . . ክፍል በአጼ ሚኒሊክና በአርቲስት ቴዲ አፍሮ ላይ ይካሄድ ስለነበረው “ዘመቻ”፣ የሰማሁትን በመጠኑ ነገርኳት፡፡ በተላይ በንግግርና በቴክስት ይመላለሱ የነበሩትን አንዳንዶቹን እንክኳን ለሷ ልነግር ለራሴ መስማት ዘግንኖኝ እንዳላየ ባልፋቸውም፣ እሷ ግን አጠገቤ ተቀምጣ የሚጻፈውን ቴክስት ማንበብ ቀጠለች፡፡
ይካሄድ የነበረው ዘመቻ ሆነ ብለው ነገሩ እንዲባባስና ልዩነቱ እንዲሰፋ ጽንፈኛ አመለካከት በነበራቸው ግለሰቦችና ቡድኖችም ጭምር እንደታጀበም አልደበኳትም፡፡ አንዱ አጼ ሚኒሊክን ብቻ ሳይሆን ያወግዙና ይከሱ የነበሩት፣ አንዱ የሌላውን ዘር በወራሪነት፣ በጨካኝነትና በመጤነት የሚካሱና እራሳቸው እዛች ሐገር ውስጥ፣ ከመሬትና ከድንበር ጋር አብረው ተፈጥረው፣ ተዘርተው እንደበቀሉ፣ የሚያምኑ እንዳሉና፣ የማይፈልጉትን ከአካባቢያቸው እነስወጣለን እያሉ የሚዝቱና የሚያስፈራሩትን በተደጋጋሚ አንብባ ሲበቃት እራስዋን ነቅንቃ ጥያቄ ጠየቀችኝ፡፡ “እንዴት እነዚህ ሰዎች ሰሞኑን እንኳን የሱዳንንና፣ የሴንትራል አፍሪካን ሬፑብሊክ እየተካሄደ ያለውን የእርስ በእርስ እልቂት፣ ሕዝቦች ሲፈናቀሉ፣ ሕጻናት ሳይቀር የሚታረዱበት ዘግናኝ ቀውስ እየተካሄደ ካለበት ሁኔታ መማር አይችሉም? ደግሞስ አንድ ሕዝብ ሆነው አንዱ ከሌላው በላይ ለምን የባለቤትነት ስሜት ይሰማቸውል? ደግሞስ ከሐገራቸው ወዴት ነው የሚሄዱት? አልገባኝም” ብላ እራስዋን ነቀነቀች፡
እውነትም አንዳንዶቹ እንደፈለጉ የመጣላቸውን የሚናገሩ ናቸው ባይባልም፣ በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርተው ሳይሆን፣ ታሪክን እራሳቸው ሊያምኑ በሚፈልጉበት መንገድ እየትረጎሙ፣ በስሜትና በእልህ በመነሳሳት ለረዥም ጊዜ መሪዎቻቸው ያስተማሩዋቸውን፣ ተከታዮቻቸው ወደ ተግባር ለመቀየር የሚፈተኑበት ወቅት ይመስላሉ፡፡ ይህንን አደገኛ አካሄድ ለመከላከልና ስህተቱን ለማሳየት ብዙ ታዳሚዎች በአግባቡ፣ ታሪክ እያጣቀሱ ስህተቱን ሊያመላክቱ ይስተዋሉ የነበሩትና፣ በተጨማሪ ሌሎችም ሆነ ብለው ይህንን ችግር ለማባባስ፣ በሁለት ቦታ የወገኑ መስለው፣ ችግሩን የሚያቀጣጥሉ ተላላኪዎች፣ ያባብሳል ብለው የሚገምቱትን ነገር ሁሉ “እሳት ውስጥ እየወረወሩ ሊያጫርሱ ሲራወጡ” ማየት የሚያያሳዝን ተውኔት ነበር፡፡ ይመታ የነበረው የጦርነት ከበሮ በአማራው ሕዝብ ላይ ያነጣጠረውን፣ መነሳሳት የሚያበረታታ አደገኛ አካሄድ ነበር፡፡ ይህንን የተሳሳተና ሐገራችንን ሊያፈርስ የሚችል አካሄድ፣ ወደ ሕዝባችን ለመግፋት እየሞከሩ ያሉበት ሁኔታ አሳሳቢ ስለሆነ ዝም ተብሎ ተንቆ ሊታይ አይገባውም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ጉዳይ አስፈጻሚ እንጂ፣ “ሰንቀው” የሚልኳቸው ከኋላቸው ሌሎች እንደሆኑ ግልጽ ነው፡፡ አከአገዛዙ ጀምሮ ይህንን መከፋፈል የሚፈልጉ የሐገራችንን እድገትና መረጋጋት እንዲኖር የማይፈልጉ የአካባቢው መንግስታት ጭምር ከዚህ ተንኮል ጀርባ በትጋት ቀንና ሌሊት ተግተው ስለሚሰሩ፣ እንደነዚህ አይነት በጥላቻ የታወሩን ቡድኖችን በቀላሉ እንደ መሳርያ ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ፡፡
ብዙ ለጆሮ የሚቀፉ፣ በሕዝባችን፣ በታሪካችንና፣ በዕምነታችን ላይ ያነጣጠረ ውንጀላ፣ ስድብና፣ ማስፈራራት በስፋት ይነገር ነበር፡፡ ይህንን ሁሉ የሚያደርጉት በሐገርና በሕዝብ ስም፣ እየማሉና እየተገዘቱ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ አሳፋሪ ውንጀላ አልበቃ ብሎ አንዱ ሌላውን፣ ከሌላ ፕላኔት እንደመጣ፣ “መጤ” እያሉ በዓለም ላይ እንደሚካሄዱት አስቀያሚ በዘርና በሃይማኖት ምክንያት እንደሚካሄዱት እልቂቶች፣ እኛንም ተመሳሳይ እልቂጥ ውስጥ ሊከቱን፣ የማይቆፍሩልን ጉድጓድ የማይፈጥሩልን አዲስ ታሪክ አልነበረም፡፡ “ለኦሮሞ ሕዝብ እንቆረቆራለን” ከሚሉ ዘረኛ ምሁሮች የሚነገራቸውን በማመን የሰሜኑን ክፍል ወገኖቻችንን ከአረብ ሐገር እንደመጡና፣ የኦሮሞ ሕዝብ ብቻ እውነተኛ አፍሪካዊ እንደሆኑ፣ ለማሳመን የማያጣምሙትና የማይደልዙት ታሪክ አልነበረም፡፡ በተቃራኒውም “ለአማራው እንቆረቆራለን” የሚሉትም እንደዚሁ፣ ኦሮሞውን ሕዝባችንን “ከማዳጋስካር ፈልሶ የመጡ ስለሆነ፣ ካላረፉ እናባርራቸዋለን” ቅስቀሳ እያካሄዱ፣ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን እያራገቡ፣ ሕዝባችንን ሊያራርቁና፣ አንድነታችንን ሊንዱ ሲሞክሩ መስማት ያሳፍር ነበር፡፡
የምሰማውን በሙሉ ለባለቤቴ መንገሩ አስፈላጊ ሆኖ ባላገኘውም፣ እነዚህ ክፍሎች በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን፣ “እንደ የመሳፍንት ዘመን” በዘር ክልል አጥር ወስጥ ተገድበው፣ በጥላቻ ተውጠው፣ የተጀመረው እሰጥ እገባ እየተካረረ ከሄደ ሊያስከትልየሚችለውን አደጋ፣ ምን መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል አለመገመታቸው እንዳሳሰበኝ አልደበኳትም፡፡
ባለቤቴም “ለእነዚህ ላልገባቸው ሰዎች፣ ለምን ምሁሮቻችሁ ስለ የሰው ዘር ግኝት፣ እድገትና፣ የአሰፋፈር ታሪክ አያስተምሩም? እንኳን እንናንተ የመጀመርያውና የሰው ልጅ ዘር (ሆሞሳፒያንስ….) መኖር ከጀመረበት ምስራቅ አፍሪካና፣ መካከለኛው ምስራቅ …..አካባቢ፣ እስከ አሁን ድረስ የምትኖሩ ሕዝቦች ቀርቶ፣ እኛ አውሮፓውያን እንኳን፣ ከናንተ አካባቢ እርቀን የምንገኘው ቀደምት ሃረጋችን ከእናንተ አካባቢ ነው ብለን ነው የምናምነው፡፡ በመለው ዓለም ተሰራጭቶ ያለ የሰው ዘር፣ መጀመርያ እንደ ሰው መኖር የጀመረው ከናንተ አካባቢ ለመሆኑ፣ በቂ የአርኪዮሎጂና የሳይንስ መረጃዎች ቀርበው ሁሉም የተስማማበት ነው፡፡ ቦኋላ ነው ቀስ በቀስ ወደ መላው ዓለም የተሰራጨው፡፡ እኛ ፈረንጆቹ መሠረታችን ከምስራቅ አፍሪካ አባይ ተፋሰስ አካባቢ እያልን፣ እንዴት እናንተ አንድ ሕዝብ እዚያው ከመሠረቱ ያልራቃችሁ፣ አንተ ከዚህ እሱ ከዚያ መጣ ትባላላችሁ? አረብም ይሁን ማዳጋስካር፣ ባጠቃላይ የዓለም ሕዝብ ከእናንተ አካባቢ ተነስቶ በመላው ዓለም ተሰራጨ እንጂ፣ ማንም ከውጪ ወደ እናንተ የተገላቢጦሽ የመጣ የለም፣ ሊሆንም የታሪክ እውነታው አይፈቅድለትም” ብላ ትንሽ አስቃኝ ውይይቱን ቀጠልን፡፡
እኔም እንዴት ላስረዳት እንደምችል ግራ ገብቶኝ፣“ችግሩ እኮ ሳያውቁ ወይም ሳያነቡ ቀርተው አይደለም፡፡ ሁለቱም ወገኖች ማመን የሚፈልጉት ያለውን ሃቅ ሳይሆን፣ የሚመኙትን ነው፡፡ ዋቢ የሚጠሩትም ሆነ፣ የሚያነቡት ማስረጃ፣ ለነሱ ተመችቶ ማሸነፍ የሚችሉበትን እንጂ ቀናነትማ ቢኖራቸው፣ አንቺ እንዳልሸው ከሰው የፍጥረት ዘመን የመጀመርያ ታሪክን ማጣቀስ አሻፈረን ብለው፣ ከአስራ አምስተኛው የኦሮሞ መስፋፋት ዘመንና፣ ከአስራ ዘጠነኛው ዘመን ከአጼ ሚኒሊክ የሐገር ግንባታ፣ (ከዘመንና ከታሪክ፣ ወገብ) ላይ የሚጀምሩት ወደ መስማማት እንዳይቀርቡ ነው፡፡ ከተስማሙ እኩል መብት ሊኖራቸው ስለሆነና፣ ሁለቱም ወገን፣ ሥልጣንንም ሆነ ጥቅምን ለራሳቸው ማዳላት ስለሚፈልጉ፣ ላለመስማማት ነው የሚያካሄዱት ክርክር ፡፡ ከአአዳም የመጀመርያው አባታችን ጀምረው ሁላችንም የአንድ ግንድ ዘር ነን ብለው መስማማት ሲገባቸው፣ አንዱ ከአብረሃም ሌላው ከኢስማኤል፣ አንዱ ከሰለሞን፣ ሌላው ከገዳ…ወዘተ እያሉ በታሪክ ወስጥ እየተደበቁ የግል ፍላጎታቸውን ሊጭኑብንና ያረገዙትን ጥላቻቸውንና፣ ዘርኝነታቸውን እንድንቀበላቸውና በነሱ የጥፋት ጎዳና እንድንተባበር ነው የሚጥሩት፡፡ ይሁንና ቀድሞ እንደነገርኩሽ ይህንን የነዚህን አክራሪዎች ስሜት አብዛኛው የኦሮሞው ወገናችንም ይሁን የአማራ፣ የትግሬውም ይሁን የጉራጌው ሕዝባችን አይጋራቸውምና አትስጊ” ብዬ ጉዳዩን በቀላሉ ላስረዳት እንደማልችል ገብቶኝ ውይይቱን ዘጋሁት፡፡ በእርግጥ እኛ አሁን ያለንበት ሁኔታ ፈረንጆች ከመቶዎች ዓመታት በፊት ያለፉበት መንገድ ቢሆንም፣ የአሁኑ ትውልድ አፍሪካውያኖችንን በጥቅሉ የሚመለከቱት “በጎሳ፣ በዘር፣ በድንበር፣ በግጦሽ፣ በእምነት ልዩነት“ እንደምንጣላ ያውቃሉ እንጂ፣ የዘር ጥላቻ ሲጦዝ፣ እራስን ከሰውነት ደረጀ ዝቅ አድርጎ አዕምሮን እንዴት ሊያሳውር እንደሚችል ብዙዎቹ ሊገባቸው አይችልም፡፡
ችግሩን ለባለቤቴ ቀለል አድርጌ ለማስረዳት እንደሞከርኩት አልነበረም ውስጤ የተሰማኝ፡፡ በመገረም፣ በሃዘን በብስጭት ነበር የተወሰኑ ቀናት አልፎ አልፎ አዳምጣቸው የነበረው፡፡ ክፍሉን ከፍተው የተቆጣጠሩት በጥላቻ የታወሩ አክራሪዎችም ቢሆኑም፣ አልፎ አልፎ በጎ አመለካከት የነበራቸውና፣ አስታራቂ ሃሳብ ሊያቀርቡ የሚሞክሩ፣ገንቢ አስተያየት የሚሰጡ፣ ሚዛናዊ (ሞደሬት) አቀራረብ የነበራቸውና፣ ነገሩን ለማብረድ ይጥሩ የነበሩ፣ የቁርጥ ቀን የሐገር ልጆች ስለነበሩ፣ እስከ ተወሰነ ደረጃ አልፎ አልፎ እየከበደኝም ቢሆን እየገባሁ ማዳመጤንና፣ በቴክስት መሞነጫጨሬን፣ በልቤ የማስበውን ለሚናገሩ አውራ ጣቴንና፣ በነጻ የሚቀጠፈውን የፓልቶክ አበባ ከመበተን አልቦዘንኩም ነበር፡፡ ከነዚህ የዘር ጥላቻ ከተናወጣቸው ሰዎች ጎን፣ የመከፋፈሉን ሁኔታ በደንብ ለመጠቀም፣ የኦሮሞ ተቆርቋሪ መስለው አማራውን የሚሳደቡና፣ የአማራው ደጋፊ መስለው ኦሮሞውን የሚሳደቡ፣ ኦሮሞው መጠራት በማይፈልግበት ስምና፣ አማራውን ያበሳጫል ብለው በሚገምቱት ስድብ፣ ሁሉንም ዘር የሚሰድቡ፣ ሦስተኛና አምስተኛ እረድፎች በትጋት ለማጣላት ሲሞክሩና፣ በሚነደው እሳት ላይ ቤንዚን ሲያርከፈክፉ ማየትና ማዳመጥ የሚያሳፍርና የሚያሳዝን ነበር፡፡ እነደነዚህ አይነት የታመሙ ሰዎች መሃከላችን እንዳሉ ብንገምትም፣ አንዳንድ የምሰማቸውና የማነባቸው ስድቦች ከግምቴ በታች በጣም ዝቅ ስላሉብኝ፣ ከሁለት ምሽት ማዳመጥ ቦኋላ፣ እራሴን ከዛ ሰፈር አገለልኩኝ፡፡
ይህ መረን የለቀቀ የጅምላ ስድብና ማስፈራራት፣ በምንም አይነት ሚዛን፣ በውይይት ወይም በመወቃቀስ መስፈርት ሊቀመጥ የማይችል አጸያፊ የጥላቻ ዘመቻ ስለነበረ፣ በመጀመርያ ማዘን ያለብን እንደ እነዚህ አይነት በጥላቻ ለታወሩና፣ በምንም ነገር ውስጥ፣ በጎ ነገር ማየት ለሚሳናቸውን ሰዎች ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚህም ትልቅ ትምህርት የምንወስደው፣ ዘረኝነት ከሮ ሲጦዝ፣ የሰው ልጅ ምን ያህል ከሰውነት ደረጃ ዝቅ እንደሚልና፣ ጥላቻና እልህ፣ የማመዛዘኛ ህዋሳቶቻችንን እንደሚያመክን ነው፡፡ ዘረኝነት ልክ እንደ “ሴክት” እራሳቸውን ከውጪው ነባራዊ ሁኔታና ክስተት ገድበው፣ በግል ማሰብንና ማመዛዘን አቁመው፣ መሪዎቻቸው የሚነግሯቸውን ብቻ እንደ አንድ ሰው ሆነው እየተቀበሉ፣ መልሰው ያንኑ እንደወረደ ሌላውን ለማሳመን የሚለፉት፡፡ በሰለጠነው ዓለም ግለሰቦች እዚህ ደረጃ ላይ እንደደረሱ በቤተሰቦቻቸውም ሆነ በወዳጆቻቸው ምልክቶቹን ሲያዩዩ፣ በእንደዚህ አይነት በሽታ የተጠቁትን እራሳቸውን እንዳይጎዱም ሆነ ኅብረተሰቡን ለመከላከል፣ አስቸኳይ እርዳታ ነው ገለል ተደርገው እስከሚድኑ የሚሰጣቸው፡፡
በዓለማችን በዘረኛም ይሁን በሴክት አክራሪ ሓይማኖቶችን ጨምሮ፣ በሚቀሰቀሱ ችግሮች ምክንያት የብዙ ንጽህ ሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል፡፡ እንደ እነዚህ አይነት ጥንፈኛ ተከታዮች፣ ሁሉን ነገር ከዘር ወይም ከእምነት ጋር ብቻ ማሰብና መመዘን ከጀመሩ? “እነሱ” የሚላቸውን በጥላቻና በጠላትነት የሚያዩ ስለሆነ፣ የጎሳ፣ የሓይማኖት ወይም የሴክት መሪ የሚያዘውን ማንኛውንም አሰቃቂ ተግባር ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ከማንኛውም ሰፈር የሚመጣ ጥንፈኛነትና ጥላቻ፣ ለዘመናት አብሮ ክፉና ደጉን ባሳለፈና፣ ጎን ለጎን አብሮ በኖረ ሕዝብ ውስጥ የተገነባውን የአንድነት አፍርሶ፣ ከሰብዓዊ የአስተሳሰብ ደረጃ አውጥቷቸው ወደ የማያባራ የእርስ በእርስ መተላለቅ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ይህ ሰሞኑን በተለያዩ ጎራ ውስጥ ሆነው ለራሳቸው የተደበቀ አጀንዳ፣ ሕዝባችንን ወደ ብጥብጥ የሚገፉ ቀለም የቆጠርን ነን የሚለው ክፍል(ኢሊት) በወገናችን ላይ የሚያሳዩት ግዴለሽነት፣ ንቀት፣ ጥላቻና የስልጣን ጥማት፣ የጨዋውና የተከበረው የኦሮሞና የአማራ፣ የትግሬውና የደቡቡ ሕዝብ … ወዘተ ፍላጎት አይደለም፡፡ ይህ ማለት ግን ሕዝብ በተሳሳተ መንገድ አይገፋም፣ ወይም ስህተት አይሰራም ማለትም አይደለም፡፡ በታሪካችን በጥቂት ሰዎች አማካይነት በተጀመሩ፣የዘርና የሃይማኖት የተሳሳተ የጥላቻ ቅስቀሳ፣ ብዙ ችግር ላይ የወደቁ ሐገራት እንዳሉ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡
በዓለም ዙርያ በዘር ግጭቶች ምክንያት የደረሱትን ጥፋት እነደሚታወቀው ሆኖ፣ ለምሳሌ በአኅጉራችን በአፍሪካ፣ በናይጄርያ፣ በኮንጎ፣ በሩዋንዳ፣ በሱዳን፣ በኬንያና በመካከለኛው አፍሪካን ሪፐብሊክ…ወዘተ ሃገራት ደርሶ የሰማነው፣ እየተካሄደ ያለው፣ ጦርነት፣ በምስል ተቀርጾ ያየነው እልቂት፣ የሰው ልጅ በየመንደሩ “በዘርና በዕምነት” ተከፋፍሎ በሜንጫ እየተራረደ፣ የሰው ፍጡር በየጫካውና በየወንዙ ለአውሬ ሲሳይ እየሆነ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በየትም ሐገር የተካሄደው የእርስ በእርስ መተላለቅ፣ ስደትና መፈናቀል፣ የተጀመረው ሰሞኑን እንደምንሰማቸው ጥቂቶች ነገር ግን ሃላፊነት በማይሰማቸው አክራሪ ቡድኖች ምክንያት ነው፡፡ ከሰባትና ስምንት ጎሳዎች (ክላን) የማይበልጡ፣ በሃይማኖት ልዩነት የሌላቸው፣ ጎረቤታቸን ሶማሌ፣ አዲሷን ሱዳን ጨምሮ የደረሰውን ቀውስና መበታተን መዘዙ የዘር (የክላን)ና የስልጣን በሽታ፣ እንደነበር ሁሉም የሚያውቀው ነው፡፡ በዓለም ላይ በዘርና በሃይማኖት ግጭቶች ምክንያት እያለቀ ያለው ሕዝብ፣ እየወደመ ያለው ታሪክና ቅርስ፣ ከሐገር ደረጃ ወደ ኋላ ተጉዘው፣ በጎሣ መሪዎችና በጦር የጎበዝ አለቆች፣ በዘራፊ ሽፍቶች ጭምር እንዲተዳደሩ የተገደዱት የጎረቤት ሃገሮች ጭምር እያየናቸው ያሉ ሃቆች ናቸው፡፡ ከነዚህ ጥፋቶች አለመማርና በተመሳሳይ መንገድ በእልህ መጓዝ፣ ድንቁርና ካልሆነ ምን ሊባል እንደሚችል አይገባኝም፡፡
እነዚህን ሁሉ በዘመናችን የሰማናቸውና የምናውቃቸው አስፈሪ ችግሮች እያወቁ፣ እየሰሙና እያነበቡ፣ ነገር ግን በጥላቻ ስለ ታወሩ፣ “እኛ” እና “እነሱ” ብለው ተነስተው፣ እንወክለዋለን፣ ወይም ቆመንለታል፣ በሚሉት ሕዝብ ስም ሽፋን አመቺ ጊዜ ሲያገኙ፣ ወደ ሕዝብ በመቅረብና፣ ወደ ኋላ ተመልሰው ያለፉ አሉታዊ ታሪኮችን ብቻ በመምዘዝና በማጦዝ፣ መጥፎ ስሜትን በሕዝብ ወስጥ በማነሳሳት፣ የራሳቸውን አጀንዳ በሥራ ለመተርጎም፣ የሚያስጀምሩት እልቂት፣ በየትኛውም የግጭት ታሪክ በመጀመር የሚታወቀው፣ ቀለም የቆጠረው ምሁር ነው፡፡ ባጠቃላይ ምሁር ወይም የተማረ ዜጋ፣ ለአንድ ሐገር እድገትና ስልጣኔ የሚያደርገው አስተዋፆ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ሁሉ፣ በቁጥር አነስተኛም ቢሆኑም፣ ከየትኛውም ማኅበረ-ሰብ አካባቢ ብቅ የሚሉ፣ ከሃገራዊ አንድነት ይልቅ በጎጥ፣ ከትልቅ ሕዝብ ይልቅ መንደር፣ የሰውን ልጅ፣ በሰውነቱና በተግባሩ ከማክበር ይልቅ በዘሩ፣ በሃይማኖቱ፣ በጎጡ ነው መቅረብና መመዘን የሚፈልጉት፡፡ በዚህ አይነት መንገድ መጓዝ በተሻለ የተደበቀ ግባቸውን ለማሳካት ይቀላል ብለው ያምናሉ፡፡
በሃገራችንም ተጨባጭ ሁኔታ፣ እንደማንኛውም በእድገት ሂደት እንዳሉ ደሃ ሃገሮች፣ ከሌላው ሃገር ባልተለየ ሁኔታ በሕዝባችን ውስጥ፣ አንዳንድ ኋላ ቀር በሆኑ ባህላችን ምክንያት በሁሉም አካባቢ የየራሳቸው አካባቢ ችግሮች እንደነበሩ ባይካድም፣ በተለይ ወያኔ የሥልጣን ወንበሩን ከተቆጣጠረ ቦኋላ፣ “የብሔር፣ ብሔረ ሰብ ጭቆና” የሚባለው የቀድሞ አጀንዳ፣ ከሚፈለገው በላይ ተናፈሰ፡፡(ሁሉንም አይነት የፌደራል ሥርዓት ለመቃወም ሳይሆን)፣ በቋንቋና በዘር ላይ የተመሠረተ የፌደራል ሥርዓት ሕጋዊ ድጋፍ ስለተሰጠው፣ አንዱ ሌላውን በገዛ ሐገሩ”በባዕድነትና” እንዲመለከትና፣ ተገንብቶ የነበረው የአንድነት መንፈስ እንዲላላ መንገድ ከፍቶ፣ ችግሮቹ እየተበራከቱ መሄድ ቀጠሉ፡፡ ለዚህ ጥሩ ምስክር የሚሆነው፣ ዛሬ በስፋት የምናየው በአማርኛ ተናጋሪው ላይ ያነጣጠረ የማፈናቀልና የእልቂት ቅውስ ማየት ይበቃል፡፡ ድርጊቱ እየተለመደና፣ ተቀባይነት እያገኘ የሄደ ስለመሰለ፣ ቅውሱ እየተስፋፋ የኦሮምኛ ተናጋሪዎችን ጨምሮ በሌሎችም አካባቢ ብዙ ወገኖቻችንን ማፈናቀልና መጤ እየተባሉ የመባረሩን ዜና ያልሰማ ያለ አይመስለኝም፡፡
በመሰረቱ በአማራውም ይሁን በኦሮሞው ወይም በየትኛውም አካባቢ በሚኖረው ወገናችን ላይ በተናጠል ለሚደርሰው ጥቃት፣ ሕጋዊ መንገድን ተጠቅሞ ማስቆም የማይችልበት ችግር ሲገጥም፣ ጥቃቱን ቀድመው ማየት የቻሉ፣ በማንኛውም መንገድ ተደራጅተው የሚጎዳውን ሕዝብ ብሶት ለወገን ማሰማትና፤ ጥቃቱን ለመከላከልና መሞከር፣ ተገቢ ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮዋዊም ግዴታ ስለሆነ ስህተቱ አይታየኝም፡፡ማንኛውም ዜጋ፣ እንደዚህ አይነት እንቅስቃሴዎችን ለመደገፍ ደግሞ፣ የሰው ፍጥረት መሆን እንጂ፣ ችግሩ እንዲሰማን፣ የዚህ ወይም የዚያ የጎሳ አባል መሆን አይጠበቅብንም፡፡
ጭቆና ተጠናክሮ ግፉ ሲበዛ፣ ድምጽ ታፍኖ መፈናፈኛ ቀዳዳ ሲጠፋ፣ አቤት ተብሎ ዳኛ ሲለግም፣ በማንኛውም መንገድ ተደራጅቶ የሌላውን መብት ሳይጋፋ፣ ችግሩን ማጋለጥና፣ ጥቃትን መከላከል፣ የሚመለከተው ተጠቂውን ክፍል ብቻ ሳይሆን፣ ማንኛውም ለፍትህ የቆመና ሰብዓዊነት ለሚሰማው የሰው ፍጥረት ነው፡፡ እያንዳንዳችን ላይ ችግሩ እስከሚደርስ መጠበቅ የለብንም፡፡ በማንኛውም ዜጎቻችን ላይ የሚሞከሩ ጥፋቶችን፣ ምልክቶች ሲታዩ ያለምንም መለሳለስና ድብብቆሽ፣ መከላከልና ማጋለጥ የማንኛውም ዜጋ ግዴታ ቢሆንም፣ በተለይ ደግሞ የፖለቲካ፣የእምነትና የሲቪክ ተቋሞች፣ “አልሰማንም” ሳይሉ፣ ችግሩ ስር ሳይሰድ፣ በማቀራረብ በማስማትና፣ እንቢ ያለውን አቅዋም ወስዶ ማጋለጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አገዛዙም ይሁን የተቃዋሚ ድርጅቶች፣ ላጭር የፖለቲካ ጥቅም ብለው፣ በረዥሙ የሐገራችንን አንድነት ሊያፈርሱና፣ ሁለተኛና የተደበቀ አጀንዳቸውን ሊያስፈጽሙ፣ በስልት የመንግሥት ደጋፊም መስለው ይሁን የተቃዋሚ ድርጅቶች አጋር፣ ለሽፋን እየተጠቀሙብን ያሉትን ሳንጃጃል ነቅቶ መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡
ባሳለፍናቸው ኋላ ቀር የአስተዳደር ሥርዓትና፣ እየተደናቀፈም ቢሆን በተካሄደው የሐገር ግንባ ታሂደት የተሰሩትን አሉታው ችግሮች ብቻ ከፖለቲካ ጋር እያያዝን፣ አሁን በደረስንበት የግንዛቤ ደረጃ፣ “አጼ ሚኒሊክንንና ፕሬዘዳንት ኦባማን እያነጻጸርን” ለመካሰስ አብረው ያያዙንን መልካም ነገሮች መርሳትን የምንመርጥ ከሆነና፣ ነገሮችን ከጊዜያቸው ውጪ መገንዘብ ከፈለግን፣ እንኳን ሰው ፈጣሪ ሊያስማማን አይችልም፡፡ ፈጣሪ፣ ነገሮችን አመዛዝነን የምንረዳበት እዕምሮ ፈጥሮልን ውሳኔውንና ምርጫውን ለኛ ትቶታል፡፡ ተባብረንና ተደጋግፈን ለማደግ መሞከር፣ በችግሮቻችን ዙርያ ተከባብረን ስንመካከር እንጂ ወደፊት ማደግ የምንችለው፣ ታሪክን እያጣመሙ ሕዝብን በማሳሳት አይደለም፡፡
ችግሩ በየተራ በሁሉም አካባቢ እየደረሰ እንደሆነ ቢታወቅም፣ በተለይ አማራውን ዒላማ ውስጥ አስገብቶ እንዲጠቃ፣ ከኖረበት እንዲፈናቀልና፣ ንብረቱን እንዲቀማ እየተደረገ ያለው ከሌሎቹ በከፋ ሁኔታ ላይ ነው፡፡ ይህ ነዋሪውን “መጤ” የሚል ስም እያሰጡ፣ ለፍቶ ሰርቶ ከሚኖርበት ሃገሩ፣ እያፈነቀሉና ንብረቱን እየዘረፉ “የመበቃቀል ባዕድ ባህል” ለማንም የማይበጅ መንገድ የሚያበረታቱት ሕዝብ፣ “ነገ” የነካካ እጁ ለምዶበት፣ ከየትኛውም አካባቢ መጥቶ በሰላም እየሰራ በሚኖረው ወገናችን ላይ ጥቃት እንዲፈጸምበት፣ ትምህርት እያስተማሩት እንደሆነና፣ ይህ መጥፎ ልማድ፣ ነገ የአስተማሪዎቹንም ቤት ጭምር ሊያንኳኳ እንደሚችል መዘንጋት የለብንም፡፡ ይህ በጎረበት ሃገሮች የጠላነው፣ የእርስ በእርስ ግጭት አንዴ ከተጀመረ፣ የሚያጠፋው ሁሉንም እንጂ ማንም ከዚህ ቀውስ ሊያተርፍና ሊተርፍ እንደማይችል ማመን ያስፈልጋል፡፡ ምናልባት የስልጣን ዘመንን ለማራዘምና ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲያመች በአገዛዙም ጭምር የሚራገብ፣ ወይም ይህንን ቀውስ ተጠቅመው የፖለቲካ ትርፍ ለማካበት የሚፈልጉ የተቃዋሚ ድርጅቶች ቢኖሩ፣ አሊያም በዚህ ግር ግር የምንፈልገውን ሃገር ገንጥለን ዘውድ እንጭናለን ብለው የሚያልሙ ጎሰኞች… ወዘተ ቢኖሩ፣ ሁሉም ምኞታቸው ቅዠት እንጂ የሚሆነው በተግባር እንደማይሳካ ማመን አለባቸው፡፡
“የምንለማውም ሆነ የምንጠፋው” አብረን እንደሆነና፣ ካሁን ቦኋላ አንዱ በሌላው ኪሳራ እያተረፈ መኖር መቀጠል እንደማይችል በቅጡ ሊጤን ይገባዋል፡፡ ይህ በሕዝብ ስም የሚገፋው የጥላቻ ፖለቲካ፣ የሕዝብ ፍላጎት አይደለም፡፡ ችግሮች እንደነበሩ ባይካድም፣ ሁሉም እንደ ባህሉና እንደ ዕምነቱ፣ ተከባብሮ ለዘመናት አብሮ ኖርዋል እንጂ፣ ብሔረተኝነትንና እምነትን እያጣመረ ወገኑ ላይ ለመዝመት አልቃጣም፡፡ ሁሉ ነገር እኩልና እንከን የለሽ ነበር ባይባልም፣ “ሐይማኖት የግልነው፣ ሐገር ግን የጋራ“ የሚል ቢያንስ በመርኅ ደረጃ የተቀመጠውን፣ ተግባራዊ እንዲሆን፣ የዘር ሃረግ መቁጠር ሳያስፈልገው ከሁሉም ማዕዘን በኅብረት የተነሳው፣ ያ ትውልድ፣ ልፋቱ ቢጨናገፍም፣ “በእኩልነት ላይ ለተመሠርተች ሐገርና፣ ሃይማኖት” ታግሎ መስዋዕት ሲከፍል፣ ለዚህ ዕምነት ወይም ለዚያ ዘር አልነበረም፡፡
በየትኛውም ማዕዘን ያለው አብዛኛው ሕዝባችን ላለፉት ዘመናት በሰላም አብሮ ተስማምቶ ተቀላቅሎ ደጉንና ክፉውን ጊዜ እዳሳለፈው፣ በዛ መንገድ ነው መቀጠል የሚፈልገው፡፡ ነጻ አውጡኝ፣ ታገሉልኝ፣ በኔ ስም ሕዝብ በድሉ፣ ተሳደቡ ሐገር አፍርሱ፣ የፓልቶክ ክፍል ከፍታችሁ የግል ጥላቻችሁንና የውስጥ ብስጭታችሁን በወገናችሁ ላይ አውጡ ብሎ “እንወክለዋለን” የሚሉት ሕዝብ ማታገያ ፈቃድ አልሰጣቸውም፡፡ እዚህ አውሮፓና አሜሪካ የቅምጥል ሕይወት እየኖሩ፣ ሥራ ፈተው መደበሪያ ሲያጡና መቆዘም ሲፈልጉ ቀልብ ለመሳብ ከመቶ ዓመት በፊት “የተሰራውን ስህተት” ብቻ እየመዘዙ፣ ሕዝብን በሕዝብ ላይ ማነሳሳት፣ ትልቅ ጥፋት ነው፡፡ አባቶቻችን አብረው ሆነው በጋራ ለዛች ሃገር፣ እንደ ሃገር እንድትቀጥልና ከውጪ ወራሪዎች ጥቃት ለመከላከል የሕይወት ዋጋ ከፍለው አቆይተውልናል፡፡
እኛም ልጆችዋ ድሮ በየትኛውም አካል የተሰራው ስህተት እንዳይደገም እየተመካከርን፣ ለአንድነታችንና ለእድገታችን በኅብረት እየሰራን፣ ፍትህ የሰፈነባት የሰዎች መብት የሚከበርባትና በእኩልነት ላይ የተመሠረተች ጠንካራ ኢትዮጵያችንን አድጋ ነው ማየት የምንፈልገው፡፡ ነገር ግን ትግሉ ቢረዝም፣ ትግስታችን ቢያልቅና ባለው ላይ መገንባት ቢያቅተን፣ የተገነባውን የአንድነት መንፈስ ማፍረስ ግን የለብንም፡፡ የችግሩ መፍትሄ መሆን ባንችል፣ የችግሩ አካል ሆነን፣ በሚነደው እሳት ላይ ቤንዚን መርጨት፣ ነገ እራሳችንን ጭምር እሳቱ እንደሚበላ ማወቅ አለብን፡፡
ዛሬ በሕዝብ ስም እየማላችሁ፣ ወገናችንን ወደ እልቂትና፣ እርስ በእርስ ወደ መጠፋፋት የምታመቻቹ፣ ነገ በታሪክም ሆነ በሕግ ፊት በተጠያቂነት እንደምትቆሙ ካሁኑ ልታጤኑ ይገባል፡፡ በዚህ የቴክኒዎሎጂ ዘመን፣ ከፓልቶክ ጀርባ ማድፈጥ፣ ወይም በውሸት ስም መደበቅ ይቻላል ብለው የሚያስቡ ካሉ የሚያታልሉት እራሳቸውን ብቻ ነው፡፡ መረጃ የመሰብስብ ባህሉ አድጓል፡፡ የግል አይፒና መለያና፣ ሃርድ ዲስክ አንዴ የመዘገቡትን በመዶሻ ቀጥቅጦ፣ ወይም በእሳት አቃጥሎ ባሕር ውስጥ ቢጥሉት ማጥፋት አይቻልም፡፡ ዛሬ እነሱ ለዚህ ጉዳይ የተሰሩትን የቴክኒዮሎጂ ውጤቶችን ትተን፣ እነ ጉግል እንኳን በዘዴ ለጠየቃቸው የሰው ልምድና ባህሪ ማሳበቅ፣ ብቻ ሳይሆን፣ ማን ከማን ጋር እንዲሚቀራረብና እንደሚሰራ”መረጃ መስጠት” የጀመሩበት ወቅት ስለሆነ፣ ቴክኒዎሎጂ ተመቸ ብለን ለጥፋት ባንጠቀምበት ይበጃል፡፡
በታሪካችን የሚያኮሩንም ሆነ የምናፍርባቸው ሂደቶች እንደተከናወኑ ማንም የሚክድ ያለ አይመስለኝም፡፡ ያ ልማትም ይሁን ጥፋት፣ የሁላችንም አሻራ አለበት፡፡ በበዳዩ ሆነ በተበዳዩ ሰፈር ሁላችንም አለንበት፡፡ ወደ ኋላ ተመልሰን ስህተቶችን ማረም አንችልም፡፡ ወደፊት ግን እንዳይደገም ሁላችንንም የሚያስማማ፣ አስተማማኝ ሥርዓት ፈጥረን፣ በተገነባው በጎ ነገሮች ላይ እያዳበርን መሄድ እንችላለን፡፡ ወደ ኋላ መመልከት ያለብን፣ ካለፈው ለመማር እንጂ ለመካሰስና ለመወነጃጀል መሆን የለበትም፡፡ ይህንን ደግሞ ለማድረግ በመጀመርያ፣ ለመደማመጥና፣ ሰከን ብሎ ለመነጋገር መዘጋጀትና ፈቃደኛ መሆን ያስፈልጋል፡፡ በስሜታዊነት ተገፋፍቶ ለማሸነፍ ብቻ የሚካሄድ መጯጯህ፣ የራስን ህዋሳት አጋግሎ ጊዜያዊ እርካታ ይሰጣል እንጂ ምንም ትርፍ አያመጣም፡፡ እንዳንስማማ፣ እንዳንተባበርና፣ አብረን እንዳንቆም ሃያ አራት ሰአት ተግተው የሚሰሩ፣ ያለ የሌለ ንዋያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ተንኮላቸውን አቀናጅተው የሚሰሩ የሐገራችን ጠላቶች ጥቂት አይደሉም፡፡
ሁሉም የየራሳቸው የተለየ ምክንያት ቢኖራቸውም፣ ሳይነጋገሩ አብረው በመግባባት መስራት የሚችሉ ናቸው፡፡ የጋራ ግባቸው ውድቀታችን ነው፡፡ የመጨረሻ ዓላማቸው እንደ ሐገር መኖር እንዳንቀጥልና፣ እርስ በእርስ ተጣልተን እንድንበታተን ነው፡፡በዚህ ውጤት የራሳቸውን ሐገር ብሔራዊ ጥቅም ባስተማማኝ ሁኔታ ያስጠብቃል ብለው ያምናሉ፡፡ ከቀድሞው የግብጽ ፕሬዘዳንት ሞርሲ ከነተቃዋሚዎቹ በይፋ ማንን እረድተው፣ እንዴት ሊያበጣብጡን ይወያዩ እንደነበር፣ ሳያውቁት ሾልኮ በወጣው የፊዲዮ ምስል ያላየው ያለ አይመስለኝም፡፡ ይህ ሁሉ የሰሞኑ ግር ግርም፣ የዛ ቲያትር ቅጥያ እንዳይሆንም ስጋት አለን፡፡
የ ዓደዋ በዓልም ይሁን የአጼ ሚኒሊክ ማስታወሻ ሲታሰብ የመጀመርያው አይደለም፡፡ እኚህ ታላቅ መሪ፣ ከእኛ አልፎ በመላው ዓለም የነጻነት አፍቃሪ ልብ ውስጥ ልዩ ስፍራ አላቸው፡፡ በሃገራችን ውስጥ ስለሰሩት በጎ ተግባር ብዙ ስለተጻፈ እዚህ ላይ አላደክማችሁም፡፡ እኝህ ታላቅ መሪ ፍጹም ናቸውና፣ ሊሳሳቱ አይችሉም የሚል የለም፡፡ በየትኛውም አህጉር በሐገር ግንባታ ሂደት እንደሚደርሰው ጥፋት፣ እሳቸውም ሆነ እራስ ጎበና በሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ የጦር ፈረሰኞች ይዘው ወደ ደቡብ ሲዘምቱ፣ እንዳሁኑ በደሞዝ የሚተዳደር የሰለጠነ ወታደር እንደነበረ፣ አድርጋችሁ አስባችሁ ካልሆነ? ብዙ ስህተት ሊደርስ እንደሚችል ለመገመት መመራመር አይጠይቅም፡፡ እነዚህ በዛ ሁኔታ ሊፈጠሩ የሚችሉ ስህተቶችን ብቻ እያራገቡ፣ የተሰሩትን በጎ ነገሮችና፣ በክብር ያጎናጸፉንን የነጻነት ኩራት ጥላ ሊያጠሉበት አይገባም፡፡
በዚህ ዘመቻ ጉዳት ያደረሰውም ይሁን ጉዳት የደረሰበት የራሳችን ወገን መሆኑን መገንዘብ እንጂ፣ “የአማራ ወታደር ከጎበና ፈረሰኞች ያነሰ ጥፋት ነው ያደረሱት“ አይነት ጉንጭ አልፋ ክርክር ውስጥ መግባባት አያቀራርበንም፡፡ ወደ ደቡብም በነፍጠኝነት የሰፈሩት፣ በተለምዶ የአማራ ነፍጠኞች ይባል እንጂ፣ ሁሉም አለበት፡፡ ማወዳደር የግድ ካስፈለገ? ከነ ደጃዝማች በቀለ ወያ፣ ደጃዝማች ባልቻ አባ ነብሶ፣ ከነደጃዝማች ገረሱ ዱኪ፣ ራስ ደስታ …ወዘተጋር በተለያየ ጊዜ አብሮ በመሄድ ለሐገራቸው ዘብ ሊቆሙ፣ ነፍጠኛ ሆነው ወገናቸውን ያገለግሉ የነበሩት፣ ከአማራው ቁጥር ባላነሰ፣ ኦሮሞዎች፣ ጉራጌዎችና…ሌሎችም ጭምር በብዛት ነበሩ፡፡ ከፊሎቹም ለመንግሥት ሥራ፣ ለንግድ..ወዘተ፣ ሆኖ ሄደው በዛው ተቀላቅለው፣ ተዋህደው መኖር የጀመሩ ናቸው፡፡ ከዛ ከታሪክ አጋጣሚ ጀምረው አብረው ቋንቋውን እየተናገሩ የአካባቢውን ባሕል አክብረውና የራሳቸው አድርገው አብረው ተዋህደው ኖሩ፡፡ ለምሳሌ ሲዳሞ የሚኖሩ ዘመዶቻችን ለሥራ ጉዳይ ውይ ሊጠይቁን ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ፣ እርስ በእርስ የሚያወሩት እንኳን በሲዳምኛ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ አውሮፓና አሜሪካ የሚኖሩ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ቤት ውስጥ እንኳን የሚያወሩት በሲዳሞኛ ነው፡፡ ለሕዝቡ፣ ለባህሉና ለቋንቋው ጭምር ልዩ ፍቅር ነው ያላቸው፡፡ እራሳቸውን እንደ ሲዳሞ እንጅ የሚቆጥሩት ወደ ኋላ ተመልሰው የዘር ሃረግ ሲቆጥሩ አልሰማናቸውም፡፡ እኛም ሲዳሞዎቹ ዘመዶቻን ነው የምንላቸው እንጂ የዘር ሃረጋቸው ትዝ ብሎንም አያውቅ፡፡ ወደ ኋላ ተመልሶ ሂሳብ ማወራረድ ከተጀመረ?፣ የሁሉም አሻራ ሁሉም ቦታ ስለ አለ፣ ገለልተኛ ዳኛ ማግኘት ያስቸግራል፡፡ ዳኛችን ሊሆን የሚገባው የራሳችን ኅሊና ነው፡፡ “ወርቁ ቢጠፋ፣ ሚዛኑ አይሰበር” እንደሚባለው፡፡ ለጆሮዋችሁ የሚስማማ ታሪክ እየመረጡ የሚያስተምሯችሁን ምሁሮች ችግር ውስጥ እንዳያስገቧችሁ ሁለት ጊዜ አዳምጧቸው፣ ማለትም ሁሉን ነገር እንደ አቦል ቡና እንደወረደ አትቀበሉ፡፡
ይሄ በተለምዶ በአንድ ዘር ላይ ብቻ ለማነጣጠር፣ “የአማራ ነፍጠኛ የደቡብን ሕዝባችን ሊወር እንደዘመተ” ተደርጎ በማወቅም ይሁን በድንቁርና የሚቀርበው የተሳሳተ ሕዝባችንን የመከፋፈያ ቅስቀሳ ሊታረም ይገባዋል፡፡ ነፍጠኛ ማለት ሐገሩን፣ ዳር ድንበሩን ነፍጥ(መሳርያ) ታጥቆ የሚጠብቅ ማለት ስለሆነ ልናከብረውና ልንመካበት እንጂ ልናጣጥለው አይገባም፡፡ነፍጠኛ አማራው ብቻ ሳይሆን፣ ኦሮሞውም፣ ጉራጌውም፣ ትግሬውም ወላይታውም….ወዘተ ከሁሉም ማእዘን በፈቃደኝነት ሃገራቸውን ነፍጥ አንግበው ያገለገሉ ናቸው፡፡ እነዚህ በነፍጠኝነት የሚከሰሱት ሃገራቸውን ለመከላከል በየማእዘኑ ይዋደቁ የነበሩት ተገደው ሳይሆን በፍቃደኝነት፣ የራሳቸውን ስንቅ ሰንቀው ሁለት ሦስት ወር በእግር ተጉዘው፣ ውጣ ውረዱን ድካሙን ተቋቁመው በሕይወታቸው ዋጋ እየከፈሉ ነበር ሐገራችንን ያቆዩልን፡፡ ዛሬ ታሪክ በራዦች እንደሚነግሩን ተገደው ወይም ለዝርፊያ አልነበረም የተሰማሩት፡፡ ወቅቱ አሁን ከምንኖርበት በጣም የተለየ ስለነበር፣ ብዙ አይነት የእርስ በርስም ግጭቶችና ችግሮች ቢኖሩም፣ ታሪክ ለማበላሸት የሚጠቅመንን ብቻ እየመዘዝን፣ በቀደምት አባቶቻችንንና በአኩሪ ታሪካችን ላይ መዝመት አግባብ አይደለም፡፡
እንደ አሁኑ ዘመን በቅጥር ደሞዝ እየተከፈላቸው፣ ካንፕ ውስጥ የሚኖሩ ወታደሮች ስላልነበሩ፣ በሚያስፈልግ ጊዜ ለሐገራቸው ሕይወታቸውን ጭምር እየገበሩ፣ በሰላሙ ጊዜ አርሰውና፣ ነግደው፣ እንደ ደሞዝ ኑሮዋቸውን እንዲደጉሙ በሚሰጣቸው “ሰው ያልሰፈረበት” መሬት፣ ጫካ እየመነጠሩ፣ ከዱር አውሬ ጋር እየተፋጠጡ ኑሮዋቸውን እየገፉ አካባቢውን አልምተው የአካባቢው አካል ይሆናሉ፡፡ እነዚህ የሁላችንም ነፍጠኞች ሕይወታቸውን ለወገናቸው እየገበሩ ሐገራችንን ከጠላት እየተከላከሉ፣ ላቆዩልን ከፍተኛ አድናቆትና ክብር እንጂ የሚያሰጣቸው፣ ውለታቸውን ልናጣጣለው አይገባም፡፡ እንደ እኔ ቢሆን እንዲያውም በሔራዊ በዓል ደረጃ በዓመት አንድ ቀን፣ በመላው ሐገርቷ የነፍጠኛ ቀን ተብሎ ማክበርና ማስታወስ ብንጀምር፣ ብዙ ሐገሩን የሚወድ ጀግና ትውልድ እንዲወጣና፣ በታሪኩ እንዲኮራ ይረዳል ብዬ አምናለሁ፡፡ እንጂ ያሁኑን ችግር ለማስረሳት የመቶ ዓመት እሬሳ እየቆፈሩ “ለመጋረጃነት” መገልገል ጅልነት ነው፡፡
የቴዲ አፍሮ “ጥቁር ሰው” አልበም ካወጣው በትንሹ ሁለት ዓመት ያልፈዋል፡፡ ስለ ሰላምና ፍቅር በዘፈነ፣ ለአንድነት አቅዋሙ ዋጋ በለከፈለ፣ ጀግኖች አባቶቻችንን ስላስታወሰ፣ በዘር ስላልተገደበ ለምን ይወነጀላል?፡፡ እነዚህን ወንጃዮች የፈረንጅ ቢራ ተዝናንተው እየኮመኮሙ፣ የራሳቸውን ደሃ ሐገር በምስኪን በበደሌ ቢራ ላይ፣ ከአውሮፓ እስከ አሜሪካ ተጠራርተው፣ ጡሩንባ እየነፉና አቧራው እስከሚጨስ ነጋሪት እየጎሰሙ ለመቃወም ለምን ይህን ጊዜ አሁን መረጡ ? በቋንቋና፣ በእንጀራ ላይ “ማእቀብ መጣል” ጋብቻ መከልከል….ሃይማኖት መሳደብ፣ ማስፈራራት፣ ስንቱን አስደመጡን? ጥላቻው ገደብ አላለፈም ወይ ጎበዝ?፡፡ ተጋብቶና ተቀላቅሎ እንደ አሸዋ የተባዛውን፣ ሚሊዮኖች ወገናችንን በማንኛውም የደም ዘር መመርመርያ (ዲ ኤን ኤ) መሳርያ ማጥራት፣ ወይም ያልተቀላቀለ ማግኘት አይቻልም፡፡ የኦነግ አርባ ዓመታት ምንም አልሰራህም የሚባለውን ወቀሳ ለማካካስ፣ በኦፒዲዮ የውስጥ አርበኝነት ሐገር ውስጥ መቆጣጠር ያቃተውን ነጻ መሬት፣ ፓልቶክ ውስጥ አንድ ሁለት ክፍል ነጻ አውጥቶ ሊያካክስ ካልሆነ? እንደ የየካቲት66 ሰሞን ፖለቲካ “በደሌ ቢራ ይውደም!! የሚኒሊክ ሃውልት ይፍረስ፣ ቴዲ አፍሮን እንፋረዳለን …” ወዘተ ማለት አሁን የጀመሩት ለምን ይሆን?፡፡
የአቶ ሄርማን ኮሄን ወያኔንና ሻቢያን ለማስታረቅ የጀመረው ሽምግልና መስመር ይዞ፣ ሁለቱም ወገኖች፣ `ለፕሮክሲዎቹም ልፋት፣ ተጠቅመውባቸው ጣሏቸው እንዳይባል፣ ትንሽ ድጎማ ተፈቅዶ፣ ለሚቀጥለው ምርጫ እንዲሳተፉ፣ የተሰጣቸው ቅድመ-ሁኔታ ይሆን? ወይስ ከመለስ ኅልፈት ቦኋላ፣ ወያኔን እንደቀድሞው ጠንካራ መሆን ስላቃተው፣ ወደ ቀድሞው ጥንካሬ እስከሚመለስ፣ በአባ ዱላ ገመዳ በኩል የተሰጠን የቤት ሥራ? ወይስ ግብጽ ተጠናክራ አስተማማኝ መንግስት እስከምታግኝ፣ በነጆሃር/ገብረ አብ በኩል የተዘጋጀልን (ጆሃሪዝም) የማተራመስ ቅጥያ?ብሎ ብዙ ሴናሪዮ ማየት ይቻላል፡፡
እነዚህ ባጭሩ ከላይ የተዘረዘሩት “የቀውሱ ተጠቃሚዎች” በተጠቀሱት የተለያዩ ምክንያቶች ዙርያ፣ ሳይነጋገሩ ለመስማማት ይችላሉ ብሎ ለመገመት፣ መጽሃፍ ገላጭ ወይም የቡና ሲኒ አንባቢ ማፈላለግ እንደማያስፈልግ እርግጠኛ ነኝ፡፡ የእነዚህ ተልዕኮ ለማስፈጸም፣ ከሐገር ውስጥ እስከ የዲይስፖራ “በየተቃዋሚ ድርጅቶች ውስጥ ጭምር” በቂ የሰው ሃይል አላቸው፡፡ ኢትዮጵያዊ አይደለንም የሚሉ ብዙ የጲላጦስ ተከታዮች ጭምር ማሰለፍ ችለዋል፡፡ እነዚህን ሁሉ ከውጭና ከውስጥ የተዘረዘሩትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች አብረን ቆመን፣ ተባብረን ታግለን እንዳናስወግድ፣ እንቅፋት የሆኑ ብዙ የተወሳሰቡ ችግሮች ከመኖራቸውም በላይ፣ የፖለቲካ ልምድና ተቻችሎ የመስራት ባህል፣ የትግል ስልት ልዩነት ..ወዘተ ሁሉ ሲደማመሩ እንኳን ተለያይተን አብረንም ብንቆምም እንዲህ በቀላሉ የምንወጣው ችግር አይደለም፡፡
እስካሁን ድረስ አብረን እንዳንቆም፣ በትግላችን ላይ የጉሮሮ አጥንት ሆነው ካስቸገሩን ምክንያቶች ውስጥ፣ አደገኛውና ወደፊትም ለመበታተናችን ምክንያት የሚሆነው፣ ከኢትዮጵያዊነት ወርደን በዘር፣በጎጥና በመንደር እየተጠራራን፣ ለጋራ ችግራችን “የተናጠል መፍትሄ“ ለመሻት መነሳታችን ነው፡፡ እንደ የጋኖ ጅብ ከየቦታው ተጠራርተው ሐገራችንን ለማፍረስ የተሰማሩት፣ የአንድነቱ ሰፈሩ በሆነ ባልሆነ “ተከፋፍለው ተዳክመዋል” የሚል እምነት አድሮባቸው ነው፡፡ ያች ሐገር ግን የቁርጥ ቀን ልጆች እንዳልዋት ሊያምኑ ይገባል፡፡ በታሪካችንም የሐገራችን ወራሪ ጠላቶች፣ እንደዚህ አይነት የተሳሳተ ግምት ላይ እየወደቁ ነው፣ እየተዋረዱ የተመለሱት፡፡ እርስ በእርስ እንናቆር እንጂ፣ በሐገራችንና በአንድነታችን አደጋ ሲመጣ ነው የምንፋቀረው፡፡ ከላይ እንደገለጽኩት በተለያየ አስገዳጅ ምክንያት በሚፈጠሩ በማንኛውም በዘርና በዕምነት ላይ በሚመሰረቱ እንቅስቃሴዎች ውስጥ፣ በጥላቻ የታወሩ ግለሰቦች እንደዚህ አይነት እንቅስቃሴ ሲፈጠር፣ ሁኔታውን ተጠቅመው የራሳቸውን ጽንፈኛ አመለካከት ለማስፋፋትና፣ “በመቆርቆር” ሽፋን ሕዝብን ለመከፋፈል ይጠቀሙባታል፡፡
እንደ እነዚህ አይነት አክራሪ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች፣ “እንወክለዋለን” ለሚሉት ሕዝብ/ሃይማኖት የተቆረቆሩ መስለው ከማንም በላይ ጩኅታቸውን ያስተጋባሉ፡፡ ያለፈ መጥፎ ታሪክን ብቻ እየቆፈሩ በማውጣት፣ በሕዝብ መሃከል ጥላቻ ያስፋፋሉ፡፡ ከብሔራዊ አስተሳሰብ ወርደው ቡድናዊ አመለካከትና፣ ወደ ስሜታዊ ተነሳሽነት ወርደን እንድንዋጥና በጋራ ጥቅምና እድገት ላይ እንዳናተኩር ይገፋፋሉ፡፡ለሌላ አካባቢ ሕዝብ ባህል፣ እምነት፣ ልማድ አክብሮት የላቸውም፡፡ በጋራ ከተገነቡ በጎ ታሪኮችና ትውስታዎች ይልቅ፣ የሚያተኩሩት፣ በታሪክ አጋጣሚ በተሰሩ ስህተቶች ለይ ነው ቀልባቸው የሚካድመው፡፡ እነዚህ አይነት አክራሪዎች በየትኛውም ማእዘን በሚኖሩ ጤናማ ማኅበረሰባችን ውስጥ እንዳሉ ቢታወቅም፣ አንገታቸውን ብቅ አድርገው ተመሳስለው ተደባልቀው ጥላቻቸውን ለማራባት፣ ሁሌ ተስማሚ ጊዜና አመቺ ሁኔታ አድፍጠው ይጠብቃሉ፡፡ ቀውስ ዋና ማዳበሪያቸው ስለሆነ ይፈልጉታል፡፡
ሰሞኑን በኢትዮጵያዊነት ላይ ፓልቶክ ክፍልን “የዘመቻው ማዕከል” አድርገው በተንቀሳቀሱት ጸረ-አንድነቶች ምክንያት፣ ብዙዎች የተለያዩ የፓልቶክ ክፍል ታዳሚዎችን ጉዳዩ አስቆጥጥቷቸው፣ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ በመስጠት፣ የፖለቲካ መስመር ወይም የአቅዋም ልዩነት ሳይገድባቸው፣ የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጆች ባስቸኳይ ወደ አንድ አቅጣጫ ተሰባስበው፣ እየተሞከረ የነበረውን ማጥቃት በመመከት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሚያስመሰግናቸው ነው፡፡ ሆኖም ብዙ የተቃዋሚ የፖለቲካና የሲቪክ ድርጅቶች በቀጥታ በዚህ ጉዳይ ላይ አቅዋማቸውን ግልጽ ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ እንደዚህ አይነት ጸረ አንድነት ሙከራ ሲካሄድ፣ ችግሩ ከመባባሱ በፊት መፍትሄ ሊያመላክቱ ይገባ ነበር፡፡ የወደፊት መሪዎቻችንን ብቃት የምንመዝናቸው በእንደዚህ አይነት የችግር ወቅት በሚያሳዩት ቆራጥነትና የአመራር ችሎታ ነው፡፡ ወተት እንደሰረቀች ድመት፣ ጥግ ጥጉን እየሄዱ “አልሰማንም አላየንም” የሚሉትም፣ ሕዝባችን እንደሚታዘባቸው ይወቁ፡፡
በእርግጥ ይህ የፖለትካ ድርጅቶች ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ የማንኛውም ሃገር ወዳድ ወገናችንም ሃላፊነት ስለሆነ፣ ሁላችንም የየድርሻችንን ግዴታ በምንችለው መንገድ መወጣት ጭምር ይጠበቅብናል፡፡ጉዳዩን አቅልሎ በማየት፣ ወይም ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት በመፍራት የመሃል ሰፋሪነት አቅዋም መያዝ አያዋጣም፡፡ የሃገር ሽማግሌዎችም ሆኑ፣ የሐይማኖት መሪዎች፣ የኮሚኒቲ ተመራጮችን ጨምሮ፣ እንደዚህ አይነት በጎረቤት ሐገርች የደረሰውን አይነት የእርስ በእርስ እልቂት የሚያበረታታ ሁኔታ ምልክቱን ሲያዩ፣ ስር ሰዶ ችግር ከመፍጠሩ በፊት፣ የተሳሳተውን የመምከር፣ ያፈነገጠውን የማቀራረብ፣ የላላውን የማጠናከር፣ አቀራርቦ የማወያየትና የመምከር ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የራዲዮና የድሕረ ገጽ ሓላፊዎች፣ የስነ ጽሁፍና የመወያያ መድረኮች፣ ገጣሚዎች፣..ወዘተ ሁሉም በየዝንባሌው.በዓለም ላይ ስለደረሱ አሰቃቂ በዘርና በሃይማኖት ልዩነት ምክንያት ስለደረሱ ግጭቶችና እልቂቶች፣ ያስከተሉት ጥፋት፣ ለሁላችንም ትምህርት ሊሆነን በሚችል መንገድ፣ ከምንም ነገር በፊት ቅድሚያ ሰጥተውት ትኩረት ቢያገኝ ይጠቅማል፡፡
በተረፈ ከላይ እንደገለጽኩት፣ በማንኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ እንደሚስተዋሉት፣ በእኛም ሃገር በተለይ በተወሰነው ምሁሩ አካባቢ ለጋራ ችግራችን በኅብረት መፍትሄ ማፈላለግ ሲገባቸው፣ አንዳንዶች ይህንን ችግራችንን በዘር፣ በእምነት ዙርያና፣ የብቻ በተናጠል የፖለቲካ አካሄድ፣ በሕዝብ ስም እንታገላለን እያሉ፣ እንዲያውም ችግሩን ይበልጥ የሚያባብስ፣ የሚያራርቅ አክራሪ መንገድ መርጠው እየተንቀሳቀሱ የተናጠል መፍትሄ እናመጣለን ይሉናል፡፡ ለምሳሌ እስካሁን ድረስ ጎልተው ከሚታዩት አክራሪ መስመሮች፣ በሕዝብ ስም፣ እየገፉ ችግራችንን በጋራ እንዳንቀርፍ እንቅፋት በሆኑብን ላይ፣ በተግባር የሚመሳሰሉበትንና የሚለያዩበትን ከላይ እንደገለጽኩት ከጥቂት ዓመታት በፊት በጽሁፍ ያሰፈርኩትን የአብዛኛው ወገናችን የሚያምንበት ሕዝባዊ መስመር እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ስለ “የብቻ ጉዙ” የምለው አለኝ፡፡
የኢትዮጵያ አንድነት፣ ወይም አንድ ኢትዮጵያ ስንል፣ ባጭሩ ዘር ሃይማኖትና ባህል ሳያለያየን፣ ለራዥም ዘመን በበጎም ይሁን በክፉ፣ በችግርም ጊዜ ይሁን በድሎት፣ በሠላም ጊዜም ይሁን በጦርነት፣ አኩሪም ይሁን አንገት አስደፊ፣ ውጣ ውረዶችን፣ አብረን እያሳለፍን ረዥም መንገድ ተጉዘን ፣ በጋራ የሚያያገናኘን ታሪክ፣ ለዚህም መሠረቱ በመልካዓ ምድሯ ላይ የምንኖረው የሕዝብ ትስስር አለ ብለን ስለምናምን ነው፡፡ የቋንቋችን፣ የባህላችንና የሃይማኖት ዕምነታችን መብዛት፣ ጌጣችን ሃብታችን፣ ልዩ የሚያደርገን እውነታ ስለሆነ ልንኮራበት እንጂ ልናፍርበት አይገባም፡፡ ሐገራችንን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ሊቆጣጠርዋት ይፈልጉ የነበሩ የውጭ ወራሪዎችም ሆኑ፣ ከጥንት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ሐገሪቷን ያስተዳድሩ የነበሩትና፣ ያሉት እነዚህን ልዩነታችንን ለራሳቸው በሚያመች መንገድ እየከፋፈሉን፣ የሥልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም ተጠቅመውበታል፡፡
ከላይ ልጠቁም እንደፈለኩት፣ ይህ በሰሞኑ የተጀመረው “እሰጥ እገባ” በአጼ ሚኒሊክና አርቲስት ቴዲ አፍሮ ..ወዘተ ምክንያት፣ ይሁን እንጂ፣ ከኋላው ብዙ የተደበቁ ሁለተኛ አጀንዳ ባላቸው “የጥቅም ተካፋዮች” እንደታጀበና፣ ነገ ያሰቡት ተሳክቶላቸው ሃገሪቷ ቀውስ ውስጥ ገብታ ብንዳከም፣ እውነተኛ አጀንዳቸውን ይዘው ብቅ እንደሚሉ አንዘንጋ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በዛሬ እውነተኛ ችግራችን ላይ ሳይሆን ባለፈው ታሪክ ላይ ብቻ እንድናተኩርና፣ አሁን እየተካሄደ ባለው ችግራችን ላይ ሕብረት ፈጥረንና ወደ አንድ አቅጣጫ ተሰባስበን እንዳንታገል፣ እያደርጉን ካሉ ብዙ ምክንያቶች ውስጥ፣ ጎላ ብለው ከሚታዩት፣ በሐገር ውስጥም ሆነ በዲያስፖራ በሁለት ተጻራሪ ጫፍ ከተሰለፉት፣ አክራሪ አመለካከት ያላቸው ጎጠኞች፣ ከላይ የተገለጸውን ጽንሰ ሃሳብ፣ አክራሪ አቅዋማቸውን ስለሚያበላሽባቸው አይቀበሉትም፡፡ ሁለቱም የዓላማ ልዩነት ቢኖራቸውም፣ በአካሄድ አንድ ስለሆኑ ሊያደርሱ የሚችሉት ጥፋት ምንም ልዩነት ስለሌለው ከሁለት ዓመታት በፊት በሌላ ጽሁፌ “ምልክታቸውን“ ለማሳየት የሞከርኩት እንደሚከተለው ነበር፡፡
በ”የእኛ” በሚሉት ጠባብ ክፍል ስለሆነ ሁለቱም ለአንድነታችን ጸሮች ናቸው፡፡
እነዚን ሁለት ክፍሎች ከላይ ወደ ተገለጸው የብዙሃን መስመር ውስጥ አስገድዶም ሆነ አሳምኖ ለማስገባትም ቀላል እንዳልሆነ ቢታወቅም፣ ለሐገሪቷ ብሔራዊ ድኅንነትም ሆነ በረዥሙ ለዘላቂ ሰላም፣ እነዚህ ቡድኖችን ወደ የብዙሃኑ መስመር “አስገድዶ” ማስገባት ያስፈልጋል፡፡
ከየትኛውም ማእዘን ለሚቀርቡት ማንኛውም፣ ችግሮች፣ ጥያቄዎችና ቅሬታዎችን፣ በሕዝባዊ ግፊት ተጽዕኖ በማሳደር፣ በማቀራረብና በማወያየት፣ የጋራ ችግሮቻችንን በጋራ ተቀራርበን ከመፍታት ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለን መቀበል ያስፈልጋል፡፡ ለእንደነዚህ አይነት ዘርፈ ብዙ ችግሮች በነዚህ ሁለት ተጻራሪና አክራሪዎች አቅዋም መሃል፣የብዙሃኑ ሕዝባችንን ፍላጎትና፣ ጥቅም ሊያንጸባርቅና ሊያስከብር የሚችል፣ አማራጭ መፍትሄ ማቅረብ መቻል አለበት፡፡ ሐገራችንን በጋራ ከውደቅት ለማዳን፣ ሁሉም ወገን ሰከን ብሎ ለጋራን ችግር፣ ተቻችሎ በጋራ መፍትሄ ከመሻት፣ውጪ ሌላ አማራጭ የለንም፡፡ ለሐገራችን የጋራ ችግር ለመወያየት ፈቃደኝነት ማሳየት እንደ “መሸንፍ” የመቁጠር ኋላ ቀር ባህል፣ ችግርን አባብሶ ያራርቀናል እንጂ አይጠቅመንም፡፡ በዚህ የሚጠቀመው አካል ቢኖር ከላይ እንደተገለጸው፣ የራሳቸው የተለየ የግል አጀንዳ ያላቸው የሐገሪቷ ጠላቶች ብቻ ናቸው፡፡ ሐገራችንን ከእንደዚህ አይነት አደጋ ለመከላከል፣ ይሁላችንንም ተሳትፎ እንደሚጠይቅ ግልጽ ቢሆንም፣ ትላንት እራሳቸውን ከኦነግ ነጥለው፣ “በአንድነቱ እቅፍ ውስጥ ገብተን ከወገኖቻችን ጋር አብረን ለዲሞክራሲ ታግለን የሕዝባችን ችግር በጋራ መፍትሄ እናመጣለን” ብለው “ይበጅ” ያልናቸው እንቅስቃሴዎችም፣ ሆኑ አጋሮቻቸው እንደዚህ አይነት አደገኛ አካሄዶችን በግልጽ መቃወምና፣ የመፍትሄው አካል መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡
ለመወያየት ወይም ለመደራደር ፈቃደኛ መሆን ማለት ደግሞ፣ አንደኛው ክፍል የሚጠይቀውን ብቻ እንዲሟላ መጠበቅ ሳይሆን፣ ሁለቱንም ክፍሎች ወደ መሃል አምጥቶ፣ ሁሉንም ክፍል ሊያስማማ የሚችል አስተማማኝ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ወደሚፈጠርበት መስመር ውስጥ መግባት ይጠይቃል፡፡ ይህንን በማይቀበሉና፣ የራሳቸውን አጀንዳ ብቻ ለጭኑብን ለሚፈልጉ፣ ማናቸውም ቡድኖችን ማጋለጥና፣ በሕብረት መታገል የማንኛውም ሐገር ወዳድ ግዴታ ናው፡፡
ለዚህ ደግሞ በመጀመርያው እርምጃ መወሰድ የሚገባው ፣ በሚረባውም ሆነ በማይረባው ተከፋፍሎና ተበታትኖ፣ ተዳክሞ ያለውን የአንድነት ሃይሉን፣ ከዘርና ከእምነት ነጻ በሆነ መንገድ አሰባስቦ በማደራጀት፣ ወደፊት በሚፈጠረው ሰፊ መድረክ ላይ የራሱን ሚዛን እንዲደፋ ለማድረግ፣ የራስን የቤት ሥራ መስራት እንጂ ፣ በምናወግዘውንና በምንንኮንነው መንገድ እየተጓዝን ለራሳችን የሚመቸንን ምክንያት እየመረጥን መጓዝ ችግሩን ያባብሰዋል እንጂ መፍትሄ ሊሆን አይችልም፡፡
አለበለዚያ እነዚህ አክራሪዎች በሚፈልጉት መንገድ ተጠልፈን ገብተን፣ የጎጠኞቹ ጥያቄ እንወክለዋለን የሚሉትን ሕዝብ አቅዋም ነው ብለን አምነንና ተደናብረን፣ “የዘር ሃረጋችንን፣ እየመረመርን፣ ጨዋታ ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ ብለን፣ ወደየመንደራችን ማሰብ ከጀመርንና?፣ እኛ እና እነሱ” የሚለውን የመከፋፈያ ቃል ተቀብለን እኛም ካስተጋባን?” እየተባበርን ያለነው፣ ውድቀታችንና መበታተናችንን ለሚፈልጉት ጠላቶቻችን ነው፡፡ ማንኛውንም ዓይነት አክራሪነት፣ የዘርም ይሁን የሐይማኖት፣ ከየትኛውም ማእዘን ብቅ ሲል ተረባርበን፣ ሳንለሳለስ መቃወምና፣ መሠረት እንዳይዝ፣ መታገል የሁሉም፣ ያቺ ሐገር እንደ ሐገር እንድትቀጥል የሚፈልግ ዜጋ ሃላፊነት ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር እንዳለብን እንቀበል፡፡