
በኢትዮጵያ ውስጥ የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ ጉዳይ፣ የመሬት ላራሹ ጉዳይ ሙሉ መልስ ጠፍቶት እነሆ ግምሽ ምዕተ ዓመትን ፈጀብን። ዛሬም ግን ይህ ጥያቄ እንደገና ተቀጣጥሎ እልባት ካላገኘ አገራችን ከችግር ትወጣለች ማለት የማይሆን ነገር ነው።
የመሬት ይዞታን ጉዳይ በተመለከተ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ወገኖች የተለያየ ኣሳብ ያላቸው ይመስላል። አንዱ ወገን ችግሩ መሬት የመንግስት መሆኑ ሳይሆን የመንግስት የፖለቲካ ቁርጠኝነቱ ዝቅተኛ መሆኑ ነው ይላል። መንግስት ጠንካራና ለሃገር ኣሳቢ ቢሆን መሬት በመንግስት መያዙ ጥሩ ነው አይነት ይከራከራሉ። በሌላ በኩል በተለይም ከመንግስት ኣካባቢ ደግሞ የመሬት ባላቤትነት ጥያቄ እውን ከሆነና ገበሬው እስከ መሸጥና መለወጥ ሃላፊነት ከተሰጠው ምን አልባት መሬቱን እየሸጠ በሰፊው ይፈናቀላል የሚል ነገርም አለ። ይሁን እንጂ ታዲያ መንግስት መሬት እንዲሸጥ እንዲለወጥ የማልፈልገው ገበሬው ይፈናቀልብኛል ይልና እራሱ መንግስት ግን ሚሊዮን ህዝብ ሲያፈናቅል ይታያል። የሆነ ሆኖ መሬት ወደ ግል ይዞታ መዛወር አለበት የሚለውን ኣሳብ የሚቃወሙ ሌሎች ምክንያቶችም አሉ። ነገር ግን ሁሉም ሚዛን የሚደፉ ሆነው አይታዩም። በኢትዮጵያ ውስጥ መሬት በመንግስት ብቻ መያዙና በተለይ ገበሬው ከተፈጥሮ መብቱ ላይ ተቆንጥሮ መሸጥና መለወጥን ስለተከለከለ ከባድ አገራዊ ኪሳራዎች አምጥቶብናል። ዛሬ በዚህች ጽሁፍ ስር ውይይት የምናደርገው መንግስት መሬትን በስስት የራሱ ኣድርጎ በመቆየቱ ሳቢያ በተፈጠሩ ጉልህ ችግሮች ዙሪያ ነው።
እነዚህ ችግሮች የሚከተሉት ናቸው
- ኢኮኖሚያዊ ችግሮች
መሬት ከትራንዛክሽን ሲወጣና መሸጥ መለወጥ ሲከለከል ኣንድ የምንገድበው ትልቅ ሃይል ዲማንድ (ፍላጎት) ነው። ይህ ረቂቅ ሃይል ደግሞ የእድገት ዋና ሞተር ነው። መሬት ትልቅ እና ሰፊ ሃብት ሲሆን ይህ ሃብት ከገበያ ሲወጣ ከሚመጣው ችግር አንዱ ዲማንዲንግ ወይም ፈላጊ የሆነ አርሶ አደር ማፍራት አለማስቻሉ ነው።
መሬት ከገበያ ሲከላ ገበሬው በተለይም በከፍታ ቦታ ላይ የሚኖረው በአማካይ ኣንድ ሄክታር በታች ነው የሚያርሰው የሚባለው ህዝብ ዘላለም ህይወቱ በአንድ ሄክታር መሬት ዙሪያ ብቻ እንዲወሰን ያደርገዋል። ራእያማ አይሆንም። መሬት ገበያ ላይ ስለሌለ ለከርሞ ጠንክሬ ሰርቼ ትንሽ መሬቴን ሰፋ ኣድርጌ ሁለት ሶስት ሄክታር አርሼ ኑሮየን አሻሽላለሁ ብሎ አያስብም። ይሄ ደግሞ ገበሬውን “ቢዝነስ ማይንድድ” እንዳይሆን ስለሚያደርገው ገበሬው በዓመት ሁል ጊዜ የሚያመርተው ለዚያች ከእጅ ወደ አፍ ለሆነች ለራሱ ትዳር ብቻ ነው። ለገበያ አያመርትም ማለት ነው። ይህ ችግር በአጠቃላይ በአገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ ላይ የኢኮኖሚ ድንዛዜን (economic stagnation) ያመጣል። የኢኮኖሚው እንደረጋ ውሃ መሆን ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ ከሚጨምረው የህዝብ ብዛት ጋር ተዳምሮ ድህነት በፍጥነት እንዲያድግ ያደርግብናል።
ኢትዮጵያ ወደ መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው አገሮች እየተጓዝን ነው ትላለች። እንዴት ሆኖ ነው በአንድ ሄክታር መሬት ላይ በታሰረ ገበሬ ወደ መካከለኛ ገቢነት የምንሻገረው? በአማካይ ስድስትና ኣምስት ቤተሰብ ይዞ ኣንዲት ሄክታር የሚደነጉረው ገበሬ የቱንም ያህል ቴክኖሎጂ ያፈራውን የእርሻ ምርት ግብዓት ይጠቀም በዚያች መሬት ላይ የሚያመርተው ምርት ውሱን ነው የሚሆነው። የቱንም ያህል ምርት ቢጨምር ከወጪ ቀሪ የሚያገኘው ገቢ ገበሬውን የተሻለ ቤት የሚያሰራው፣ ኤሌክትሪክ እንዲጠቀም የሚያደርገው፣ ስልክ እንዲጠቀም የሚያደርገው፣ ምቾት ያለው አልጋ እንዲገዛ የሚያደርገው፣ ልጁን በጥሩ ሁኔታ ለማስተማር የሚያስችለው፣ ቴክኖሎጂ ያፈራቸውን ቁሳቁስ እየገዛ እንዲጠቀም የሚያስችል ገቢ የሚያስገኘው ኣይሆንም። ለምን ካልን ችግሩ የመሬት ጥበት ነውና። ችግሩ የመሬት አጠቃቀም ነውና። ስለዚህ ኢትዮጵያ በዚህ የመሬት ፖሊሲ ወደ መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው አገሮች እያደገች ነው የሚለው አባባል የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ከመሆን እንደማያልፍ ያሳያል። ከዚህ በተቃራኒው ግን ከዚህ ፖሊሲ የተነሳ ድህነት ሊጨምር ይችላል። እየሆነም ነው። በመሆኑም የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ ከፍትህ ጥያቄው ባሻገር ለድህነታችን ከፍተኛ ሚና ኖሮት ይታያል። የኢትዮጵያ የግብርና መር ፖሊሲ ዘላቂ ግብ ሰማኒያ በመቶ የሚሆነውን ህዝብ መሬት እንዳይሸጥ እንዳይለውጥ አድርጎ በማሰር ተግባራዊ አይሆንም። አገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ ስታድግ የገበሬው ቁጥር እየቀነሰ ነው የሚሄደው። ሰባ ሚሊዮን ህዝብ ገበሬ አድርገን በመሬቱ ላይ ጥፍር አድርገን አስረን አይደለም ወደ ኢንዱስትሪ የምንዘረጋው። መሬትን በትራንዛክሽን ውስጥ በማስገባት የገበሬው ቁጥር እየቀነሰ ይሄድና ኢንዱስትሪው እየሰፋ ይመጣል። ሁሉም አገር የገበሬ ቁጥር እየቀነሰ ነው የሚመጣው። ጃፓንን ብናይ ግማሽ ሚሊዮን ህዝብ የማይሞላ ነው የሚያርሳት፣ አሜሪካንን የሚያህል ግዙፍ አገር ሶስት በመቶ የማይሆን ነው የሚያርሰው ይባላል። ኢትዮጵያ ውስጥም የገበሬው ቁጥር ይቀንሳል የሚል ነገር አይደለም ሊያሳስበን የሚገባው። የሚያሳስበን ያ ግብርናን ትቶ ወደ ከተማ የሚመጣው ሰው ጉልበቱን የሚያፈስበት ኢንዱስትሪ መኖሩ ላይ ነው። በመሆኑም በሂደት ቁጥሩ ይቀንሳል። ነገር ግን ሰባ ኣምስት ሚሊዮኑን ህዝብ እዚያው ብጥስጣሽ መሬቱ ላይ እንዲቆይ ካደረግነው አጠቃላይ እድገታችንን አደንዝዞ የሚያቆይ ይሆንብናል።
በአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖውን ስናይ ይህ የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ ጉዳይ በማክሮ ኢኮኖሚያችን ላይ ጉልህ ተጽእኖ ፈጥሮብን ይታያል። መሬትን የሚያህል ትልቅ ሃብት ከገበያ መርህ አውጥቶ እናድጋለን ማለት ብዙ መሰናክሎች አምጥቷል። መሬት ይሸጥ ይለወጥ ሲባል የመሬትን ዋጋ እንደ ሸቀጥ ዝቅ ማድረግ ኣይደለም። መሬት እጅግ የከበረ ሃብት ነው። አንድ ገበሬ መሬት ሲገዛ አየር ንብረት ነው የሚገዛው፣ መኖሪያ ኣገር ነው የሚገዛውና ውሳኔው ትልቅ ነው። ይህን ትልቅ ሃብት ገበሬው በሃላፊነት ቢሰጠው ህዝቡ ሁሉ ሊሸጥና ችግር ሊፈጠር ይችላል ብሎ ማሳብ ትልቅ ስህተት ነው። ሌሎች አፍሪካ አገራት እንደዚያ አላደረጉም በተለይ የኢትዮጵያ ገበሬ ደግሞ የተሻለ ነገር ካላየ ዝም ብሎ አይሸጥም። ዋናው ጉዳይ ግን የመሸጥ የመለወጥ ህጉ በራሱ በኢኮኖሚ ላይ የሚያመጣውን ተጽእኖ ነው ማየት ያለብን። መሬት በዲማንድና ሰፕላይ ህጎች ስር ሊተዳደር ይገባዋል። ይህ ሲሆን ስራና ሰራተኛ ይገናኛል፣ ገበሬው በገበያ መሃል ፈጣን ተዋናይ ይሆናል። ስለዚህ የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ በኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ የኢኮኖሚ ጥያቄያችን ነው። የመሬት መሸጥ መለወጥ ጉዳይ በ GDP መጨመር ላይ ጉልህ ሚና ኖሮት ያታያል። ስለመሬት ባለቤትነት ስናወራ መንግስት ምንም መሬት አይኑረው ማለት አይደለም። የኢትዮጵያ መሬት ሊያዝ የሚገባው በመንግስት፣ በኮሙኒቲዎችና በግለሰብ መሆን አለበት። ከተሜውና ገበሬው በይዞታው ላይ ሙሉ ስልጣን ሲኖረው፣ ኮሙኒቲዎች በጋራ የሚይዙት መሬት ኖሮ ያንን ሲያለሙ፣ መንግስት ደግሞ በግለሰቦችና በኮሙኒቲ ያልተያዙ መሬቶችንና ወንዞችን የተፈጥሮ ሃብቶችን ተራሮችን ደኖችን ይዞ ሁሉም በየፊናቸው ሲሰሩ ነው GDP የሚያድገው። መሬት የህዝብ ነው ይባላል። ነገር ግን አበበ መሬት የለውም፣ በርሶማ መሬት የለውም፣ ኦባንግ መሬት የለውም፣ ከሲቴ መሬት የለውም፣ ሃልቼ መሬት የለውም፣ ኪሮስ መሬት የለውም። እነዚህ ባንድ ላይ ህዝብ ቢባሉም መሬት የላቸውም። ይህ የሚያሳየው መሬት የህዝብ ነው የሚለው ፍልስፍና ማታለያ እንጂ በርግጥ መሬት የመንግስት ብቻ ነው።ይሄ ኣሰራር በራሱ የኢኮኖሚውን እንቅስቃሴ በቀጥታም በተዘዋዋሪም ይጎዳል። በመሆኑም ዛሬም የኢትዮጵያ ልጆች ከድህነት ለመውጣት፣ ከአሳፋሪ ረሃብ ለመላቀቅ የመሬት ላራሹን ጥያቄ እንደገና ሊያነሱ ይገባል።
- የመንቀሳቀስ መብትን መገደብ
ሌላው ጉልህ ችግር ደግሞ መሬትን መንግስት በህዝም ስም ብቻውን ስለተቆጣጠረ በተለይ ገበሬው ከቀበሌ ቀበሌ፣ ከቆላ ደጋ ልዛወርና የእርሻ ስራየን ልቀጥል ብሎ እንዳያስብ ሆኗል። የመንቀስቅቀስ መብት በህገ-መንግስት የተቀመጠ ቢሆንም ከአንድ ቀበሌ ወደ ሌላ ኣካባቢ ሄዶ መሬት ገዝቶ ለመኖር አያስብምና መሰረታዊ የመንቀሳቀስ መብቱን ተነፍጎ ይታያል። ዘዴ በተሞላበት ሁኔታ ገበሬው ታስሯልና የመሬት ላራሹ ጥያቄ ነጻ ሊያወጣው ይገባል። መንቀሳቀስ በራሱ ትልቅ ነገር ነው። ኦፖርቹኒቲዎችን ለማየት፣ አማራጭ የህይወት አቅጣጫዎችን ለማየት ሊሆን ይችላል የሚንቀሳቀሰው። ስለዚህ ይህ መብቱ ይከበር ዘንድ ዛሬም ልጆቹ የመሬት ላራሹን ጥያቄ ሊያነሱለት ይገባል።
- መሬት ለሌላቸው መሬት እንዳያገኙ እንቅፋት መሆን
አገራችን አንድ የገጠማት ችግር ደግሞ በዚያች በተጣበበች መሬት ላይ የሚኖረው ገበሬ የወለዳቸው ልጆቹ ለአቅመ አዳምና ሄዋን ሲደርሱ ትዳር ያምራቸዋል፣ መሬት ይሻሉ። ገበሬው ያቺን አንድ ሄክታር መሬት ሲያካፍል ድህነት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጣ። ከዚህ ይልቅ መሬት በሃገሪቱ ገበያ ላይ ቢገኝ ኖሮ ያ የተወለደ ልጅ እዚህም እዚያም ብሎ ቆላና ደጋ ወርዶና ወጥቶ ባለ መሬት መሆን በቻለ። መሬት የመግዛት ነገር ፈጽሞ በኢትዮጵያ ገበሬ አእምሮ የማይታሰብ መሆኑ ያመጣው ነገር ያ ጎጆ ያማረው ወጣት ወይ ተሰዶ ወደ ከተማ ይሄዳል ወይ ከዚያው ከባቱ ጋር እየተጋፋ ይኖራል። ይሄ ከፍተኛ ችግር ሊፈታ የሚችለው በመላ ሃገሪቱ መሬት በገበያ ላይ እንዲውል በማድረግና መረጃን ለገበሬው በማድረስ ነው።
- ግብርናውን ከሁለ ገብ ስራ እንዳይወጣ ማድረጉ
መሬት የመሸጥና የመለወጥ መብቱ ለገበሬው ይተው ሲባል የሞኝ ኣሳብ ማሰብ ትክክል አይደለም። ይሸጥ ይለወጥ በተባለ ማግስት እየሸጠ ይሄዳል የሚባለው ነገር ስህተት ነው። ወዴት ይሄዳል። ከሁሉ በላይ ያቺ መሬትስ ስንት ታወጣለችና ነው። ሁለቱን በሬዎቹን ቢሸጥ ከመሬት ሽያጩ ሊበልጥ ይችላል። በሮቹን ሸጦ ኣገር ጥሎ ኣይጠፋም። ዋናው ነገር ገበሬው የሚሸጠው ከአንድ የግብርና ስራ ወደ ሌላ ሊዛወር ይሆናል። አንድ ገበሬ አንድ ሄክታር መሬት ሸጦ አንዲት ከፍተኛ የወተት ምርት የምትሰጥ ላም ቢገዛና ያቺ ላም በቀን ሃያ ኣምስት ሊትር ብትታለብ ከዚህ ከወተት ሃብት የሚያገኘው ገቢ ከዚያ ኣንድ ሄክታር ላይ ከሚያገኘው ሰብል በእጥፍ ይበልጣል። ስለዚህ ገበሬውን ኣማራጮችን በማሳየት ግብርናው ትኩረት እንዲያደርግ ማሳየት ነው ከችግር የሚያወጣን። ይህ ሁሉ ግን ከመሬት ባላቤትነት ሙሉ መብት ጋር ይያያዛልና እንደገና መሬት ላራሹ::
- ገበሬው ከባንክ ብድር እንዳያገኝ መሰናክል መፍጠሩ
ይነስም ይብዛ በተለይ ገበሬው መሬቱን ኣስይዞ ከባንክ የመበደር መብቱ ሊጠበቅ ይገባዋል። ብድር ለግብርናው መነሳት ዋና ሞተር ነው። ገበሬው ከአገሩ ሃብት የመካፈል የመበደር መብቱም ሊጠበቅ ይገባዋል። ጥያቄው የኢኮኖሚ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የፍትህ ጥያቄም ነውና ገበሬው ቀጥታ የብድር ተጠቃሚ ይሆን ዘንድ ዛሬም መሬት ላራሹ ሊነሳ ይገባዋል። ብድር በቡድን እንሰጣለን የሚል ነገር አይሰራም። በግለሰብ ደረጃ የመሬት ባለቤትነት መብቱ ተከብሮለት መሬቱ ተተምኖ ያወጣለትን ያህል ተበድሮ ሊሰራበት ይችላል። አንዳንዶች ይህ አሰራር ባንኮችን ያከስራል ይላሉ። ገበሬው ተበድሮ መክፈል ቢያቅተው መሬቱ ያን ያህል ተሽጦ ላያወጣ ይችላል ብለው ይሰጋሉ። በኢትዮጵያ ሁኔታ መሬት መሸጥ መለወጥ ከተጀመረ ገበያው ይጦፋል ፈላጊ ይጨምራል እንጂ የሚያከስር አይሆንም። የህዝብ ብዛቱን ማየት አለብን። መሬት የሌለውን ማየት አለብን። ስለዚህ ይህ ኣሳብ ኣሳሳቢ ኣይደለም።
- ገበሬውን የፖለቲካ ጥገኛ ማድረጉ
መሬት የመንግስት በሚል ስም ደርጉ ህዝቡን መያዣ ኣድርጎት ነበር። አንድን ገበሬ ከመሬቱ ማፈናቀል ቀላል ጉዳይ ነበር። ህወሃት የመራው መንግስት ስልጣን ሲይዝ ደግሞ መሬት የመንግስትና የህዝብ ነው በሚል ያንኑ ደርጉ የነበረውን ሶሻሊስታዊ የመሬት ኣያያዝ ተግባራዊ አድርጓል። ኢትዮጵያውያን በተፈጠሩበት ምድር የኣንድ የፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊ ካልሆኑ መሬት ማስፈራሪያ እንደሆነ ይገለጻል። በምርጫ ጊዜም ገበሬው የፈለገውን እንዳይመርጥ የስነ ልቡና ጫና መፍጠሪያ ዘዴ በመሆኑ በርግጥ የኢትዮጵያ ህዝብ ከዚህ ኣስከፊ ተጽዕኖ ነጻ ይወጣ ዘንድ ዛሬም መሬት ላራሹ የሚል ትውልድ ያስፈልጋል።
- ሙስናን ማብዛቱ
አንዱ የሃገራችን ትልቅ ችግር በተለይ በአሁኑ ሰዓት ከመሬት ጋር የተያያዘ ሙስና ነው። በመሬት አስተዳደር አካባቢ የሚሰሩ ሰዎች እንደሚያጋልጡት በኢትዮጵያ ውስጥ እንደ መሬት አስተዳደር በሙስና የተዘፈቀ መስሪያ ቤት የለም። በተለይ በከተማ ቦታ አካባቢ ከፍተኛ ሙስና አለ። መሬት የመንግስት ብቻ ሳይሆን የግልም ቢሆን መንግስት ለቡድንና ለግልም ቢያካፍል ይህ ችግር በጣም ይቀንስ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ዜጎች መፈናቀል ሊገጥማቸው ሲል ለመብታቸው ቆመው በገበያ ተደራድረው የሚገባቸውን ተቀብለው ኣካባቢውን ሊለቁ ይችላሉ። በአሁኑ ሰዓት ያለውን ችግር እንመልከት። የአዲስ አበባውን ማስተር ፕላን ተግባራዊ ለማድረግ በሚል በአዲስ አባባ ዙሪያ የሚገኙ ገበሬዎች ላይ የማፈናቀል ችግር መጣ። ትልቁ ችግር የሆነው የአዲስ አበባ መስፋፋት ሳይሆን እነዚህ የሚፈናቀሉ ገበሬዎች በመሬቱ ላይ ሙሉ መብት ስለሌላቸውና መብቱን መንግስት ስለነጠቃቸው በዋጋ መደራደር አልቻሉም። መንግስት የሆነች ተመን ሰርቶ ያባርራቸዋል። ይህቺ ካሳ ተብላ ለሚፈናቀለው ገበሬ የምትሰጠው ገንዘብ ደግሞ ለኣንድ የመንግስት ሰራተኛ የአንድ ወር ደመወዝ ናት። እስከ ሃያ ሺህ ብር በወር የሚያገኙ ባለ ሙያዎች አሉ። ይህ ገበሬ ትዳሩን ሁሉ አፍርሶ እንዲሄድ የሚደረገው በዚህች በአንድ ወር ደመወዝ መሆኑን ስናይ በርግጥ አገራችን ውስጥ ከፍተኛ የፍትህ መጓደል እንዳለ ቁልጭ ኣድርጎ ያሳየናል። ሌላው ትልቅ ችግር ደግሞ የመሬት ነጠቃው ነው። ሬኒ ሌፈርት የተባለ ፈረንሳዊ ተመራማሪ እንደዘገበው ኢትዮጵያ ሰባት ሚሊዮን የሚሆን መሬት ለመሬት ነጠቃ አዘጋጅታለች። የተሰጠውና ሊሰጥ የታሰበው ተደምሮ ማለት ነው። ይህ ሁሉ መሬት በመንግስት የሚሰጠው በምስጢር ሰነድ ነው። ብዙ ግልጽነት የሌለው ቢዝነስ ውስጥ መንግስት ገብቶ ይታያል። እነዚህ መሬት ነጣቂዎች የውጭ አገር ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ኢትዮጵያውያንም ናቸው። እነዚህ ሃይላት ደግሞ ገበሬው የመሬት ባለቤት እንዲሆን የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ እንዲነሳ ኣይፈልጉም ምክንያቱም መሬት የመንግስት ስለሆነ ነው የመሬት ነጠቃ በሰፊው የሚኖረው። ይህ ሁሉ ችግር ዞሮ ዞሮ ከገበሬው የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ ጋር ስለሚያያዝ እነሆ ዛሬም የኢትዮጵያ ገበሬ መሬት ላራሹን ይሻል።
- የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ችግሮች
በርግጠኝነት መናገር የምንችለው ነገር ቢኖር በኢትዮጵያ ውስጥ የመሬት ባለቤትነት ቢረጋገጥ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራው ይጠናከራል ይጨምራል። በአሁኑ ሰዓት አንዱ ትልቁ ኣሳሳቢ ጉዳይ የአፈር ክለት ነው። በየዓመቱ ወደ ሰላሳ ሺ ሄክታር መሬት የሚደርስ አፈር እየታጠበብን ይገኛል። ይሄ በረጅም ጊዜ በጣም ኣሳሳቢ ጉዳይ ነው። ብዙ ነገር ብናጣ ልንተካው እንችላለን። ዛፍ ቢቆረጥ ልንተክለው እንችላለን። የኣፈር ክለት ግን በጣም የሚጎዳን ጉዳይ በመሆኑ በዚህ ላይ ትኩረት ካላደረግን የምግብ ዋስትናችን ከችግር ኣይወጣም። በርግጥ ገበሬው መሬቱ የራሱ እንደሆነ ሲያውቅ በከፍተኛ ሁኔታ መሬቱን የመጠበቁ ስራ ስለሚጨምር ኣጠቃላይ በሃገሪቱ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ላይ ጉልህ ሚና ይኖረዋልና ዛሬም መሬት ላራሹ ያስፈልጋል።
- ዜጎችን ወደ ህገ ወጥ ስራ መምራቱ
መሬት ላራሹ ሲባል ለገበሬው ብቻ ሳይሆን ለከተማውም የሚል መልእክት አለው። ይህ መፈክር በአዲስ መንፈስ ሲነሳ ከተማውንና ገጠሩን ሁሉ ኣገናዝቦ ነው። በመሆኑም ኣንዱ የመሬት ባለቤትነት መብት ሲከበር የሚመጣው ጉዳይ ዜጎች ላልሆነ ህገ ወጥ ድርጊት አይጋለጡም። ቦታው ያንተ አይደለም ቤትህን ስትሸጥ ጣራና ግድግዳውን ብቻ ሽጥ የሚባል ነገር ዜጎችን ለሌላ ተጨማሪ ውል ዳርጎ ታይቷል። ዜጎች የርስታቸው ገመድ በወደቀባት ምድር መሬትን የማግኘት መብት ያላቸው ሲሆን ይህ መብታቸው ሲነካ ለተለያየ ችግር እንደሚጋለጡ ኣንዱ ማሳያ ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያውያን የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ የከተሜውንም የገጠሩንም ህዝብ ኑሮ ግራ ያጋባና ችግር ፈጣሪ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን የመሬት ላራሹን ጥያቄ ኣንስተው በድል ሊቋጩት ይገባል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ አገራችን የመሬት ላራሹን ጥያቄ ከፍ አድርጋ ልታነሳ የሚገባበት ዘመን ላይ ናት። ይህ ጥያቄ በዚህ ዘመን ሲነሳ ጠለቅ ባለ መረዳት ላይ ሊመሰረት ይገባዋል። ስለ መሬት ፖሊሲ ስናወራ በዚህ ስር የሚጠቃለሉ ጉዳዮች አሉ። እነሱም የመሬት አጠቃቀም፣ የመሬት ማኔጅመንት፣ የመሬት ኣስተዳደርና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄዎች ናቸው። የመሬት ማኔጅመንታችንን ስናይ ምንም እንኳን መንግስት ግብርና መር ነው ዋናው ፖሊሲየ ቢልም ግን በተግባር መሬቱ ለኣፈር ክለት ሲጋለጥ፣ የተፈጥሮ ደን ሲመናመን፣ የመስኖ አጠቃቀም በጣም ዝቅተኛ ሆኖ እናያልለን። በአንድ ወቅት እስከ ኣርባ በመቶ የሚሆነው የሃገሪቱ መሬት በደን የተሸፈነ ነው እየተባለ የሚነገርላት ኣገር ዛሬ የተፈጥሮ ደን ሽፋኗ ወደ ሁለት ፐርሰንት አካባቢ ነው። ይሄ በጣም ኣሳሳቢ ጉዳይ ነውና ለመሬት ላራሹ ጥያቄ ለመሬት ፖሊሲ መሻሻል ጥያቄ አንዱ አነቃቂ ጉዳይ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የመሬት አጠቃቀማችንን ስናይ በአሁኑ ሰዓት ወደ ኣስራ ሁለት ሚሊየን ሄክታር መሬት የታረሰ ሲሆን ከዚህ ውስጥ እጅግ እጅግ ብዙው ከፍታ ቦታ ላይ ባሉ ገበሬዎች የታረሰ ነው። በሌላ በኩል ከፍ ሲል እንዳልነው እስከ ሰባት ሚሊየን ሄክታር ደግሞ ለመሬት ነጠቃ ተዘጋጅቷል። ይህ መሬት በመስኖም በዝናብም ይለማል። በዚህ ላይ በአሁኑ ሰዓት ኣስር ሚሊዮን በላይ ህዝብ እየተራበ ነው። ይህ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በአግባቡ ቢታረስ እነዚህ ወገኖቻችን ኣይራቡም ነበር። እሁን እኛ ኢትዮጵያውያን ርቦናል ብለን ዓለምን የምንለምነው እንደዚህ እያልን ይመስላል። ይቅርታ የዓለም ህዝብ ሆይ! ቆላ ያለውን መሬታችንን ሳናርሰው ቀረን፣ በመስኖ ከሚለማው መካከል ኣስር በመቶ የሚሆነውን እንኳን ሳንጠቀምበት ቀረን በመሃል የኣየር መዛባቱ መጣና ረሃብ ላይ ነንና እርዱን እያልን ነው። ሰው የሚታረስ መሬት፣ ውሃ፣ ጉልበት እያለው መራብ የለበትም። ይህንን ስናይ ሁሉን ኣሟልተን የጎደለን የፖለቲካ ቁርጠኝነትና የፖሊሲ ጉዳይ በመሆኑ ኢትዮጵያዉያን የመሬት ላራሹን ጥያቄ ከብሄራዊ ክብራችን ጋር ኣያይዘን የምር ልንነሳ ይገባል። ስለ መሬት ኣስተዳደር ሙስና ከፍ ሲል ስለገለጽኩ ኣልደግመውም። በኣጠቃላይ ከላይ የዘረዘርናቸው ኣራት የመሬት ፖሊሲ ኣቅጣጫዎች እኛን ኢትዮጵያውያንን በምግብ ራሳችንን እንድንችልም እንዳንችልም ያደርጋሉ። ጥሩ ፖሊሲና የፖለቲካ ቁርጠኝነት ካለ ኣገራችን ወደ ተሻለ ምእራፍ ትሻገራለች። ይህ ካልሆነ ግን የህዝብ ብዛት ሲጨምር ርሃብና የኑሮ ውድነት ስለሚያጠቁን ኢትዮጵያውያን እንደገና መሬት ላራሹ።
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!
አስተያየት ካለዎ በሚከተለው ኢሜይል ያገኙኛል: geletawzeleke@gmail.com
Leave a Reply