
የሰው ልጅ ማህበራዊና ግላዊ ተፈጥሮ ስላለው ለማህበራዊ ኑሮውና ለግላዊ ኑሮው የተለያዩ ጠገጎችን እያበጀ ይኖራል። እነዚህ የሚሰራቸው ጠገጎች ለግል ህይወቱም ሆነ ለማህበራዊ ህይወቱ ወሳኝ ናቸው። ሰው የዚህን ዓለም ኑሮውን ለመግፋት ከሚያስችሉት መሳሪያዎች ኣንዱ እነዚህ ጠገጎቹ ናቸው። የሰው ልጅ በህይወቱ የሚፈጥራቸው እነዚህ ጠገጎች ሃይማኖታዊ ወይም ባህላዊ ወይም ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትርፍ ያስገኙለታል። ታዲያ ይህ የሰው ልጅ በዓለም ላይ ከሚፈጥራቸው ጠገጎች መሃል ከፍተኛውና ጠንካራው ሃገር የሚባለው ጠገጉ ነው። በርግጥ ከዚህ ኣልፎ ዛሬ ጊዜ ሌላ ከፍ ያለ የጋራ የዓለም ጠገግ ህዝቦች ኣበጅተው ስያሜውን ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ብለውታል። ነገር ግን የሰው ልጅ ከቀን ተቀን ህይወቱ ጋር በጣም የተሳሰረው ጠገግ አገር ሲሆን ለዚህ ጠገግ የተለያዩ ስምምነቶችን ኣስፍሮ በዚህ ጥግ ስር ይኖራል። ሃገር የሚባለው ጠገግ ጠባብ ኣይደለም። የሰው ልጅ በዚህ ጠገግ ስር ብዙ መለስተኛ ጠገጎችን ሊፈጥር ይችላል። ለምሳሌ የባህል የሃይማኖት ወይም ሌላ ዓላማ ያለውን ጠገግ በዚህ ሰፊ ጠገግ ውስጥ ሊሰራ ይችላል። ሃገር የሚባለው ጠገግ እነዚህን ሁሉ ኣቅፎ መያዝ የሚችል ሰፊ ኣዳራሽና ከፍ ያለ ጠገግ ነው። እንደ ብሄር የሃይማኖት ስብስብ ያሉ ጠገጎች በተፈጥሯቸው ልዩነትን በውስጣቸው ኣይዙም። ልዩ ልዩ ቡድኖችን ኣቅፎ በውስጣቸው ለማስኖር የሚያስችል ተፈጥሮ የላቸውም። ከነዚህ ስብስቦች ከቡድናቸው ስምምነት ወይም ደንብ ውጭ የሆነ ቡድን ቢመጣ በውስጣቸው ያለ ቅራኔ ሊኖር ኣይችልም። በመሆኑም ነው ኣገር የሚባለው መዋቅር ከነዚህ የቡድን ጥጋጥጎች ተላቆ ሁሉን ማቀፍ የሚችል ጠገግ ሆኖ በዘመናዊቷ ዓለም የተሰራው።
ወደ ሃገራችን ኢትዮጵያ ስንመጣ ኢትዮጵያም በውስጧ ብዙ ቡድኖችን የያዘች ሰፊ ጠገጋችን ናት። ይሁን እንጂ በተለይ ባለፉት ሃምሳ ኣመታት ግድም በውስጧ ያሉትን ሌሎች ጠገጎች በተለይም ብሄርን ለማስተናገድ ይመረጣል ተብሎ የሃገራችንን የፖለቲካ ሲስተም የተቆጣጠረውን የብሄር ፖለቲካ እያካሄድን ነው። በዓንድ ሃገር በተለይም ብዙህ በሆኑ ህዝቦች ውስጥ በተለይ የፖለቲካው ለሂቅ የሚከተለው የሶሺዮ ፖለቲካ ፍልስፍና የዚያን ሃገር የፖለቲካ ውቅር በቀጥታ ተጽእኖ ይፈጥርበታል። ሃገር መስርተን እየኖርን ያለን ብዙ ብሄሮች ስለዚህ ስብስብ ያለን ፍልስፍናና ይህን ስብስብ ልናስተናግድበት የምንፈልገው መንገድ የሃገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ህይወት ሁሉ ይለውጣል። ዛሬ በዚህ ጽሁፍ ስር በጥልቀት የምናየው ጉዳይም ይሄው የኢትዮጵያ የሶሺዮ ፖለቲካ ፍልስፍናና ያመጣውን ተጽእኖ እንዲሁም ይህንን ተከትሎ ከመጣው ችግር የመውጫውን መንገድ ነው። በአንድ ሃገር ውስጥ የዴሞክራሲ ስርዓትን ለመገንባትም ይሁን ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ለመገንባት የሶሺዮ ፖለቲካ ኣመለካከታችን ወሳኝ ነው። የዚህ ጽሁፍ ዓላማም ለዴሞክራሲ ስርዓት የሚሆን ምቹ እርሻን ለመፍጠር የተሻለ የሶሺዮ ፖለቲካ ኣስተሳሰባና ሲስተም ለማሳየት ነው። ይህ ሲስተም በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ ኣንድነት የተሰኘ ፍሬም ወርክ ሲሆን በውስጡ የአዲስ ቃል ኪዳን ጥሪ፣ የህገመንግስት ለውጥ፣ የመንግስት ኣወቃቀርና የቋንቋ ማኔጅመንትና ኣጠቃቀምን የሚመለከት ይሆናል። ፍሬም ወርኩ በነዚህ ኣራት ጉዳዮች ላይ የሚሰጠው ኣሳብና ሲስተም የተባበረች ኢትዮጵያን እንደገና ለማነጽ ኣማራጭ ሲስተም ይሆናል። (ፎቶ አርአያ ጌታቸው)
(ሙሉውን ጽሁፍ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ)
ገለታው ዘለቀ (geletawzeleke@gmail.com)
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Leave a Reply