
ሁላችንም ካለንበት አጣብቂኝ ውስጥ መውጫ መንገድ አጥተን ተፋጠን ሰንብተናል። ስንነካከስ እንዳንጠፋፋ በሚያስፈራበት መልኩ ሁላችንም ግብ ግብ ስንገጥም እዚህ ደረስን። መንግስት በጉልበቱ ሲገፋበት፥ ሕዝብ በአመፁ ሲዘልቅበት፥ አማራጭ ኃይል በሁሉ አቀፍ ትግሉ ሲዘምትበት፥ አካሄዱ ሁሉ ሲያስፈራ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን ያሰኝ ነበር። ሕዝቡ ሁሉ በሁሉም አቅጣጫ ወደ አምላኩ ከመጮህ አልተቆጠበም። በአራቱም አቅጣጫ አንድነቷን እና ብልጽግናዋን በማይወዱ የተከበበች ሀገር ሆና ሳለ፥ ከውስጥ ደግሞ በነውጥ ስትናጥ ተስፋዋ እየመነመነ ጫፍ ደርሶ ነበር። ምን አልባት ታዲያ የማታ ማታ ፈጣሪዋ ኢትዮጵያን ከምጥ ሊገላግላት፣ ውጥረቷን አርግቦ ሰላምን ሊሰጣት አስቦ ይሆን ዶ/ር አብይ እርስዎን ወደ አመራር ያመጣዎት? ካለንበት አጣብቂኝ ለመውጣት ረዥም መንገድ መሄድ እንዳለብን እሙን ነው። ዶ/ር አብይ ለኢትዮጵያ ዘብ በመቆምና እኛም ለእርሳቸው ዘብ በመቆም ይህን የተስፋ ጭላንጭል ጠላት እንዳያጨናግፍ ሁላችንም የየበኩላችንን ድርሻ መወጣት ይገባናል። አሁን ከፊታችን የተደቀነው ወሳኝ ሰዓት እኛ ተመልካች ሆነን፥ ዶ/ር አብይ ደግሞ በፊታቸው ያለውን ፈተና ያልፉ እንደሆነ ለማየትና ብያኔ ለመስጠት በጥርጥር ዓይን የምንመለከታቸው አይደለም። ወይንም እኛ ሁላችን እሳቸውን የምናዋክብበት ጊዜ አይደለም፤ ነገር ግን እኛም ሆንን እሳቸው የመፍትሄው አካል ከመሆን እንዳንጎድል የምንጠነቀቅበት ጊዜ ከምን ጊዜውም በላይ አሁን ነው።
በአንደኛ ደረጃ፥ ህዝብ ካንዣበበት አደጋ አምልጦ በሰላምና በመረጋጋት እንዲኖር ዶ/ር አብይ ራስዎን ከአጣብቂኝ መውጫ አድርገው ለሕዝብ የተሰጡ ይሆኑ ዘንድ የተሰጠዎትን የሕዝብ ፍቅርና አመኔታ አነሳስተዎት ለኢትዮጵያ ዘብ ይቆማሉ ብዬ አምናለሁ። ከዚህ በፊት በተለያዩ መድረኮች ያደርጉ የነበረውን ንግግርዎትንና ስብዕናዎን፣ አምላክ ወደ ብርሃን አውጥቶ በሕዝቡ ልብ ውስጥ እርስዎን አስቀምጧል። ሕዝቡ ትልቅ ተስፋም እንዲኖረው አድርጓል። እርስዎ ታማኝነትዎን ለመንግስት ዕድሜ ቅጠላ ሳይሆን ሰሚ ላጣው ሕዝብ እንዲሆን ማድረግ ተገቢ ነው። ለጠ/ሚ ስልጣንም ያበቃዎት በቀዳሚነት የሕዝብ ትግል ነውና። በመንግስት ዘንድ የሕዝብ ጆሮና ዓይን በመሆን የሕዝብ ጠበቃ እንዲሆኑና የሚመሩትን መንግስት ወደ አዲሲቷ ኢትዮጵያ አዋላጅነት እንዲያሻግሩ ታሪካዊ ጥሪያዎን ይወጡ ዘንድ ተልዕኮዎን ለአንዲትም ደቂቃ መዘንጋት የለብዎትም። ይህንንም ሃላፊነትዎን እንዲወጡ ፋታ ባገኘሁ ይሉ ይሆናል። ግን ፋታ እንዲሰጥዎት የሚያደርጉት እርስዎ ራስዎ በሚያደርጉት ተግባር ነው። በማስተዋል በመመላለስ ሁለት ነገሮችን ቢያደርጉ ፋታ የሚያገኙ ይመስለኛል።
በመጀመሪያ የሕዝብን ጥያቄ በየደረጃው ለመመለስ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ መንቀሳቀስን ቸል የማይሉት ነገር ሆኖ ሲገኝ ነው። በሁለተኛ ደረጃ የምንሄድበትን አዲስ አቅጣጫና ራዕይ እየነገሩንና አድራሻችንን እያሳዩን፥ አንድ ልብ ኖሮን እንደ አንድ ቤተሰብ የምንሄድበትን አካሄድ ለማስጨበጥ የሚተጉ ሆነው ሲገኙ ነው። አባቶች ደማቸውን አፍሰው በመሞት ኢትዮጵያን አቆይተው ዛሬ ለዚህች እናት ኢትዮጵያ ጠ/ሚ ለመሆን ታድለዋል። በተራዎ እርስዎ ራስዎ ለኢትዮጵያ በመኖር ኢትዮጵያን የሁሉ በእኩልነት የመኖሪያ እና የማረፊያ ሀገር እንድትሆን የበኩሉዎን ታሪካዊ ድርሻ መወጣት ይጠበቅብዎታል። ሁሉም መልካም ምኞቱንና በጎ ፍቃዱን እንደለገሰዎት በማወቅ ለተሰጠዎት ለዚህ ታላቅ ፀጋ ታማኝ እንዲሆኑ ማስተዋል ይብዛልዎት። በሁሉ ነገር መልካም እንዲሆንልዎት የመላው ኢትዮጵያዊ ፀሎትና ሰላማዊ ትግል እንደማይለይዎት ጽኑ እምነቴ ነው።
በሁለተኛ ደረጃ፥ ኢሕአዴግ ራሱን ለማትረፍ ከዶ/ር አብይ የበለጠ መውጫ አያገኝምና ለዶ/ር አብይ ዘብ በመቆም ህልውናውን በሀቅ ምርጫ ለማስቀጠል ራሱን ካለው የጊዜው የሕዝብ ጥያቄ ጋር ማጣጣም ይኖርበታል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በቅንነት አገልጋይ ለሆነ ሁሉ የሃይማኖት የጎሳና የፖለቲካ ፓርቲ አባልነቱ ማንነት ውሳኔውን ሳያዛባ በአስተሳሰቡ ምንነት ላይ ብቻ ተደግፎ ፍቅሩን እንደሚለግስ በዶ/ር አብይ ምርጫ ምክንያት የታየው ደስታ ያረጋግጣል። ይህም የኢትዮጵያ ሕዝብን ቅንነትና ታላቅ ስብዕና ያሳያል። እስካሁን መንግስት የሄደበት አካሄድ ስልጣንን በጉልበት እንጂ በእውነተኛ ምርጫ አላገኝም ብሎ ያመነ ይመስል ከዲሞክራሲ የተፋታ ነበር።
ታዲያ ዛሬ በእነ ክቡር አቶ ለማና ክቡር አቶ ገዱ ሕዝብን የማዳመጥና የማገልገል አስተሳሰብ ራሱን አጥምቆ ቢንቀሳቀስ፥ በእውነተኛ ምርጫ ለስልጣን የመታደል ዕድል ሊያገኝ እንደሚችል ጭላንጭል እየታየ ነው። የትኛውም በጦር የመጣ መንግስት እኔ እስከማውቀው ድረስ እንዲህ ያለ የመሸጋገሪያ ድልድይ ከራሱ አብራክ በወጣው ልጅ ዕድል ሲያገኝ አላየሁም ደግሞም አልሰማሁም። በጎም ሆነ ክፉ እያደረገ ለ27 ዓመታት እንደፈለገው ገዝቶ ሲያበቃ፥ እንደገና በዲሞክራሲ በመዳኘት በምርጫ ስልጣኑን ቢያጣ እንኳን እንደ ኢሕአዴግ ህልውናውን ከመጥፋት አስመልጦ ማስቀጠል የሚችልበትን ዕድል አግኝቷል። ታዲያ ለዚህ ምክንያት የሆኑት ዶ/ር አብይን በሙሉ ስልጣን የመመራት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ የኢሕአዴግ ምክር ቤት አባላት በመረባረብ የውስጥ እንቅፋት የሚሆነውን ሁሉ በማሳመን ሕዝብን ማክበር ይኖርባቸዋል።
በሦስተኛ ደረጃ፥ ተቃዋሚው ሃይል ለኢትዮጵያ አማራጭ ሃይል ለመሆን ዶ/ር አብይ ሁነኛ መውጫ ሊሆኑ ብቃት ያላቸው ይመስላሉና ለዶ/ር አብይ ዘብ በመቆም ለሰላሙ ትግል ሃይሉን አጠናክሮና አቀናጅቶ መቅረብ ይኖርበታል። ተቃዋሚው እውነተኛ ምርጫ እንዲዳኘው የሚያስችል የዲሞክራሲ ምህዳር ቢኖርለት የአመፅ ናፍቆት የለውም። የዲሞክራሲው ምህዳር እንዲሰፋና እንዲንሰራፋ መድረኩ ክፍት ከሆነ፥ በውጭም ሆነ በውስጥ ያሉት ተቃዋሚዎች አማራጭ ሃይል ለመሆንም ሆነ ለመተባበር ዕድል ፈንታ ይሰጣቸዋል። ለዚህም ነው ተቃዋሚ ሃይሎች ዶ/ር አብይን ለዲሞክራሲ ጉዞ ከአጣብቂኝ መውጫ ይሆኑ ዘንድ ደጀን በመሆን እውነት ራሷ ይህንን የዲሞክራሲ አካሄድ የሚቃወሙትን እንድትሞግትና እንድትረታ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ይበልጥ መቀናጀት የሚያስፈልጋቸው።
ለማንኛውም የዛሬ ሁለት ዓመት ሊመጣ ያለውን ምርጫ ከቁጥር በማስገባት እስከዚያው ድረስ ዶ/ር አብይ ለምርጫው ፍትሀዊነት ሁሉን እያሳተፉ የለውጥ ዋዜማ ሽታ እስካመጡ ድረስ በትዕግስትና በመረዳት ፋታ መስጠት የግድ ነው። አሁን ዶ/ር አብይን በተመለከተ በሁሉም አማራጭ ሃይሎች ዘንድ የሚታየው በጎ ፍቃድና የእምነት ተስፋ እጅግ የሚያበረታታቸው ይመስለኛል። ይህም መልሶ ለሕዝብ እንዲኖሩ ግፊት እያደረገ የሕዝብ እውነተኛ አገልጋይ እንዲሆኑ ጉልበት ይሆናቸዋል።
ላለፉት 44 ዓመታት በወጀብ ስትናወጥ የነበረችው ኢትዮጵያ ዛሬ ደግሞ በአዲስ መንፈስ መሪዋና ሕዝቡ በፍቅር እጅና ጓንት ሆነው አዲሲቷ ኢትዮጵያ እንድትወለድና ሀገራችንም ለመጀመሪያ ጊዜ እፎይ የምትልበት ዘመን ይህ ጊዜ ይሁንልን። ይህ መለኮታዊ ዕድል አያምልጠን። ልባችን ለዚህ ውልደት ዘብ ለመቆም ይጨክን!
የኢትዮጵያ አምላክ ኢትዮጵያን አሰበ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
ዶ/ር ዘላለም እሸቴ – ኢሜል፡ ethioStudy@gmail.com
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Dr.Zelemem, yihin kemeselew wib hasabiwo gar becher yinuru.
Ethioipiawinet shall prevail.