
በኢትዮጵያ ምድር፥ ምኒልክን (ዮሴፍን) ‘ማያውቅ፥ አዲስ ንጉሥ መ’ቶ፣
“ለነፃነት” ብሎ፥ የነፃነትን ጧፍ፥ ረጋግጦ አጥፍቶ፣
“ከኔ ወዲያ ላሳር!”፥ አለን አፉን ሞልቶ፣
ያ’ባቶችን ክብር፥ አፈር መሬት ከ’ቶ።
ያገሬ ፈርዖን፥ ልቡ እጅግ ደንድኖ፣
የፈጣሪን ፈቃድ፥ እንዳይሰማ ሆኖ፣
“እንደ’ኔ ያለ ንጉሥ!”፥ እያለ ይጽናናል፣
የበትሩን ምሬት፥ በጠገበ ጉልበት፥ ከተማን ያጸናል።
ስንት አሮን ተላከ? ስንት ሙሴ መጣ?
“የሠራዊት ጌታ፥ ‘ህዝቤን ልቀቅ’ ይላል!”፥ የሚል ቃል ሊያወጣ፣
ስንት ምርጫ ሆነ፥ ስንት ምርጫ ሄደ፣
ደንዳናው ፈርዖን፥ በህዝብና ፍትህ፥ እንደተጓደደ።
ምልክቶች ታዩ፥ ታምራትም መጡ፣
ፈተናው ጸና እንጂ፥ የእብሪተኞችን ልብ፥ ቅንጣት አ’ለወጡ።
የባሰው መጣና፥ የ’እብራውያን’ በኩር፥ እየተሰደደ፣
መልአከ ሞት ጥላ ፥ ‘የፈርኦንን በኩር’፥ ካቻምና ወሰደ፣
ፈርዖን ልቡ ጸንቶ፥ ዘንድሮም ገፋበት፥ ህዝቡን እንዳራደ።
እናማ ህዝቤ ሆይ፣ ጊዜው እጅግ ቀርቧል፥ ነፃነት ሊመጣ፣
ጓዝ ስንቅህን ይዘህ፥ ከተስፋ ዳርቻ፥ ተሰብስበህ ውጣ፣
ማሳደዱ አይቀርም፥ ፈርዖን ከነጭፍራው፥ ይመጣል ሊቀጣ፣
ጥቂት ጭንቅ ይሆናል፥ የድል ቀን ሲመጣ።
ሆኖም ህዝቤ በርታ፥ በደርቅ መሬት ላይ፥ እንሻገራለን፣
ፈርዖን ተከትሎ፥ ወጥመድ ውስጥ ሲገባ፥ ዞረን እናያለን፣
ታዲያ የዛን ጊዜ፥ “እሰየው” አንልም፥ “እግዚኦ!” እንላለን፣
ጌታ በማረን ልክ፥ ለፈርዖን ጭፍራ፥ ምህረት እንሰጣለን።
አደባባይ ወ’ተን፥ “ይቅርታ”ን ዘምረን፣
በደሎቻችንን፥ ፍፁም ተማምረን፣
ከባቢሎን ወንዞች፥ ወዲህ ተሰብስበን፣
በኢትዮጵያ (በጽዮን) ቅጥር ውስጥ፥ እንዳበባ አብበን፣
ለፍቅር እናልፋለን፥ ለተተኪው ትውልድ፥ ፍቅርን አስረክበን።
ጽናልኝ አገሬ፥ ባህር ይከፈላል፥ አዲስ ቀን ይመጣል፣
የእግዚአብሄር ህዝብም፥ በእረፍቱ መስክ ላይ፥ ተዘ’ሎ ይቀመጣል።
03 Feb 2015
Leave a Reply