ከአመታት በፊት በአዲስ አበባችን ውቧ ቅዳሜን በውቧ አዲስ ነገር ጋዜጣ በምናጣጥመበት ግዜ አንድ በጣም የማከብረው አምደኛ በኢትዮጲያ ስላለው የጋዜጠኝነትና የመፃፍ ነፃነት ያለው ቃል በቃል ባይሆንም በጥቅሉ ይህ ነበር፣
“ . . . በኢትዮጲያ የጋዜጠኝነት ሞያ በአግባቡ የተተገብረው እንዲሁም በነፃነት መፃፍና መተንተን የሚቻለው ስለ አውሮፓ እግር ኳስ በተለይም ስለ እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ቡድኖች ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት ነዳጅ ጨመረ ፖለቲካ ነው ፣ ነዳጅ ቀነሰም ፖለቲካ ነው ፣ ኑሮ ተወደደ ፖለቲካ ነው ፣ ታክሲ ጠፋ ፖለቲካ ነው ፣ ምርጫ ደረሰ ፖለቲካ ነው ፣ ሁሉ ነገር ፖለቲካ ነው። ታዲያ በጋዜጠኝነት የተመረቁ ፣ በፅሁፍና በትንተና የተካኑ ስለምን ይፃፉ ሰው መቼም ቋንቋ እያለው ሳያወራ ፣ ሳይፅፍ አይኖር . . . “
ይህ ፀሃፊ ያለው እውነቱን ነው አብዛኛው የሃገራችን ህዝብ በተለይም ወጣቱ (እኔንም ጨምሮ) ለአድማጭ በሚስማማ መልኩ በሚያምር ቋንቋና አቀራረብ እየተመጠነ የሚቀርበው የአውሮፓ እግር ኳስ መረጃ ኢትዮጲያውያን ከአንድ አውሮፓዊ ባልተናነሰ መልኩ ስለ አውሮፓ እግር ኳስ እውቀትና ፍቅር እንዲያድርብን አድርጓል። (ይህ ማለት እንግዲህ የሃገራችን ህዝብ ክጅምሩ ያለውን በወገንተኛነት ላይ ያልተመሰረተ ንፁህ የእግር ኳስ ፍቅር ሳንረሳ ማለት ነው)
የሆነው ሆኖ ዋናው ይህችን ፅሁፍ የጀመርኩበት መነሻዬ በሃገራችን የጋዜጠኝነትና የመፃፍ መብት የስፖርቱን አንድ መቶኛ ያህል እንኳን ቢፈቀድና ከስፖርቱ ውጪ ስለሌላ ነገር መፃፍ የሚያሰቅል ወንጀል ባይሆን የሃገራችን ህዝብና ወጣት ስለ በጎ የዲሞክራሲ ስርዓት ጥቅምና አስፈላጊነት ፣ ስለማህበረሰባዊ አንድነት ፣ ስለ መልካም አስተዳደር ፣ ስለ ሃገር ፍቅርና እድገት እንዲሁም ስለበርካታ ጠቃሚ ነገሮች በነፃነት እየተፃፈና እየተወያየን የሃገራችን ከድህነት መውጫ ቀናት በተቃረበልን ነበር። ያለው እውነታ ግን ዜጎች ስለሚኖሩት ኑሮ እንኳን በነፃነት አይደለም በሹክሹክታ ማውራትም እንደ ችግር ፈጣሪነት እየተቆጠረ ነው።
በሃገራችን በተለያዩ የመንግስት ስልጣናት ላይ ተቀምጠው ህዝብን የማገልገል ሃላፊነት ወደጎን በመተው ስልጣኑን ለግል ጥቅማቸው በግድ ይዘው እንደልባቸው ያሻቸውን በማድረግ እየኖሩ “እንዴት በጋዜጠኛ ፣ በፀሃፊና በማህበራዊ ሚዲያዎች ስሜ ተነሳ” ብለው “ሃገር ይያዝ” የሚሉ ሃላፊነት የጎደላቸው የመንግስት ባለስልጣናት ጥቂት አይደሉም። ገና ምኑን አይታችሁት በሉልኝ።
ባደጉ ሃገራት የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የጋዜጠኝነት ፣ የመፃፍና የሚዲያ ነፃነት ምን ያህል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያረግ እንዲሁም በዲሞክራሲ ላይ በተመሰረት የሃገር አገዛዝ የመፃፍ ፣ የመናገርና የነፃ ሚዲያዎች መኖር ምን ያህል ታላቅ በጎ ሚና እንደሚጫወት የዲሞክራሲና አገዛዝ ታሪካቸው ያትታል። ነገር ግን እንደሃገራችን ኢትዮጲያ አይነት የዲሞክራሲና መልካም አስተዳደር ስርዓት ይቅርና እጅግ መሰረታዊ የሚባሉት ሰብዓዊ መብቶች በእንጭጩ የቀሩባት ሃገር መናገርና መፃፍ እንደወንጀል እየተቆጠረ ነው። ሀገርንና ህዝብን አስተዳድራለው ብሎ ከዜጎች ይሁንታ ውጪ ስልጣኑን የተቆጣጠረው እንደ ህወሃት መንግስት ያለ አምባገነናዊ ስርዓት እንዴት ስሜ በጋዜጠኛና ፅሁፍ ይነሳል ብሎ ለሃገርና ለህዝብ ኑሮ መሻሻል በጎ እሳቤ ያነሱ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባትና ለሃገር ማደግ በጨዋነት እይታቸውንና እውቀታቸውን ለማካፈል ብዕራቸውን ያነሱ ሁሉ እየሰበሰቡ በየእስር ቤቱ ማጎር ፣ የማህበራዊ ዲሞክራሲያው እሳቤዎች መወያያ መድረኮችን ማፈን ምን ይሉታል?
በአንድ ሃገር የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የዜጎች በሰብዓዊ መብት ፣ በዲሞክራሲ ፣ በፖለቲካ እንዲሁም በህዝብና ሃገር አስተዳደር ዙሪያ ያላቸው ንቃተ ህሊና የሚጫወተው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው። የሲቪክና የፖለቲካ ማህበራት ፣ የጋዜጠኞችና የነፃ ሚዲያዎች መብዛትና ተሳትፎ የማህበረሰብ በዘርፉ ያለውን ንቃተ ህሊና መጨመሪያ መሆናቸው አሌ የማይባል ሃቅ ነው። ነገር ግን ዘርፉን በበጎ መልኩ አይቶ ከማበረታታት ይልቅ ህዝብን ለማስተዳደር የተያዘን ስልጣንንና ጉልበት ለዚሁ ዘርፍ ተግዳሮት ማዋል ግን የለየለት ፀረ ዲሞክራሲያዊ ወንጀል ነው።
የህወሃት መንግስት በግድ ለህዝቡ እኔ አውቅልሃለው ፣ እኔ የምለውን ብቻ ዝም ብላችሁ ተቀበሉ የሚል ያረጀ ያፈጀ የማናለብኝነት ድርጊት ከግዜ ወደ ግዜ እየባሰበት ነው። የኢትዮጲያ ህዝብ የሚበጀውንና የማይበጀውን አይቶ ፣ አመዛዝኖ እንዲሁም አጣርቶ ማወቅ የሚችል የበሰለ ህዝብ ነው። ህዝባችን የተፃፈ ሁሉ እያነበበ በስሜት የሚነዳ ህዝብ አይደለም። በርካቶቻችን ከምናስበው በላይ የሚሆነውንና የሚጠቅመውን በሚገባ ያውቃል። ነገር ግን የህወሃት መንግስት ለብዙ ሃገርና ህዝብ ጠቃሚ ነገሮች ሊውል የሚችል በሚሊዮን የሚቆጠር የሃገር ሃብት የተለያዩ ሚዲያዎችን ለማፈንና ለመሰለል ሲውል እጅግ ያሳምማል። ይህ ድርጊት በውሸትና በተራ ፕሮፓጋንዳ የተሞላውን የመንግስት ሚዲያ በግድ በህዝብ ጆሮ እንዲደርስ በማድረግ ዜጎች ስለሚወዷትና ስለሚኖሩባት ውድ ሃገራቸው አገዛዝና ኢኮኖሚ ስርዓት የግል አስተያየታቸውን እያነሱ በተለያዩ መወያያ መድረኮችና ማህበራዊ ሚዲያዎች እንዳይወያዩ ማድረግና የወንጀል ያህል እንዲቆጠር ማድረግ ዜጎችን በገዛ ሃገራቸው ባይተዋር የማድረግ ሂደት አንዱ ዋነኛ የህወሃት መንግስት ስራ ሆኗል።
የህወሃት መንግስት ከሌሎች አምባገነናዊ መንግስታት የሚለየውና የባሰ ያደረገው ደግሞ ስለህዝብና መንግስት አስተዳደር በጎ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ሚዲያዎችን ማፈኑና መከልከሉ ብቻ ሳይሆን ህወሃት እንደጦር ከሚፈራው የዲሞክራሲ ምንነት አስገንዛቢ ሚዲያዎች ባሻገር ዜጎችን እያዝናኑ የተለያዩ የኑሮ ክህሎትና እውቀት የሚያስጨብጡ ሚዲያዎችን አለምፍቀዱም ነው። አማራጭ የፖለቲካ ስርዓት አመንጪ አካላት ለህዝብና ለሃገር የሚጠቅሙ እሳቤዎችን ህዝብ ጆሮ አለማድረሳቸው ከሚፈጥረው ጉዳት ባሻገር በተለያዩ ያደጉ ሃገራት ለዜጎች ከፍተኛ ጥቅም በመስጠት የሚታወቁትን የህዝብን ንቃተ ህሊና የሚያዳብሩ እንዲሁም የኑሮ መላ የሚያቀብሉ በጎ ሚዲያዎችን ከህዝብ እይታና እውቅና ውጪ ማድረግ እጅግ የሚያሳምም ወንጀል ነው።
በዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን የሰብዓዊ ፍጡርን ስለሚኖረው ህይወትና ስለሚኖርበት ሃገር ያለውን አስተያየትና አመለካከት እርስ በርስ እንዳይካፈል ማገድ ፀረ ዲሞክራሲያዊነት ብቻ ሳይሆን ፀረ ተፈጥሮ መሆንም ነው። የዜጎችን ድምፅ አለልክ ማፈንም የስርዓቱን መጨረሻ ማፋጠን መሆኑን ህወሃቶች ሊረዱት ይገባል። በተጨማሪም ሊረዱት የሚገባው ነገር የጨቆኑት ህዝብ ከሚያስቡትና ከሚገምቱት በላይ አመዛዛኝና አርቆ አሳቢ መሆኑን የሚነዙት ተራ ፕሮፓጋንዳ ከማሰልቸትና መጨረሻቸውን ከማፋጠን ውጪ ሌላ የሚፈይደው ነገር አለመኖሩን ነው። አሁንም ደግሜ ደጋግሜ የምናግረው ህዝባችን የሚበጀውንና የሚሆነውን በሚገባ ያውቃል። ስለሚወዳትና ስለሚኖርበት ሃገር በነፃነት እንዳይወያይ ማገድ ፀረ ዲሞክራሲያዊ ወንጀል ነው። የህዝብን አመዛዛኝነትና ጨዋነት በሌላ ተርጉሞ በህዝብ ጫንቃ ላይ እንደልብ መሆን መጨረሻውን አጉል ያደርገዋል እላለው።
ህዝባችንና ሃገራችን ለዘላለም ይኑሩልን!!!
Leave a Reply