የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ ለማረጋጋት እና ክልሉ ወደ ሰላም ተመልሶ የተረጋጋ ሕይወት እንዲቀጥል ለማድረግ የወሰደውን እርምጃ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ እና በቀጠናው የሚገኙ ተቋማት እንዲደግፉ የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪ አቅርቧል።
የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሪቫ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ በዛሬው ዕለት በሰጡ መግለጫ፣ ሩሲያ ወዳጅ ሀገር በሆነችው ኢትዮጵያ ውስጥ እየተከናወነ ስላለው ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለች ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን የውስጥ ችግሮቻቸውን ለመፍታት በአፍሪካውያን ወንድሞቻቸው ድጋፍ የራሳቸውን ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ የሩሲያ እምነት መሆኑንም ገልጸዋል።
አሸባሪው ህወሓት የኢትዮ-ጂቡቲ ኮሪደርን ለመያዝ ባደረገው ሙከራ የሰብአዊ ቀውስን ማባባሱን እና የስደተኞች እና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉንም የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጠቁሟል።
አሸባሪው ህወሓት የትግራይ ክልል አጎራባች የሆኑትን አፋር እና አማራ ክልል ላይ ውጊያ በመክፈት እና አንዳንድ አካባቢዎችን በመቆጣጠር ከዚህ በፊት የጦር ቀጠና ያልነበሩትን አካባቢዎች እያመሰ እንደሆነም ተናግረዋል።
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተከተፈተውን ጦርነት በተመለከተ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እያስተላለፉት ያለው መርዛማ እና መለያየትን የሚፈጥሩ ዘገባዎች የስጋት ምንጮች ሆነዋል ብለዋል ቃል አቀባይዋ።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply