• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

ምርቃት ወዲህ ሥራ ወዲያ

July 24, 2014 06:55 pm by Editor 1 Comment

አሁን ላይ በሐገራችን የተገነቡና እየተገነቡ ያሉ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ደረጃዎች የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች ቁጥር ጨምሯል፡፡ በመሆኑም የከፍተኛ ትምህርትን በነባርና አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች በኩል ትምህርታቸውን ተከታትለው እየተመረቁ የሚወጡ ተማሪዎች (ምሩቃን) ቁጥር በዚያው ልክ እያደገ ይገኛል፡፡ በዚህ አመት ብቻ እንኳ በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የተመራቂዎች ቁጥር ከ60 ሺህ በላይ እንደሆነ ይፋ ሆኗል፡፡ ይህ ቁጥር በግል ኮሌጆችና በተለያዩ መለስተኛ የትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን የተከታተሉትን አይጨምርም፡፡

የትምህርት ተቋማትም ሆነ በእነዚህ ተቋማት ገብተው ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች ቁጥር መጨመሩ ይበል የሚያሰኝ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ዳሩ ግን እነዚህ ተማሪዎች በምን ሁኔታ ትምህርታቸውን ተከታትለው እንደሚወጡ ሲታይና ከምረቃ በኋላም ያለውን የሥራ ጊዜ ሲገናዘብ የቁጥሩ መጨመር ፋይዳ ቢስ ሆኖ ይገኛል፡፡ በመንግስት በኩል ውግዘት የገጠመው ሥራ ፍለጋ እና በቃል የሚሽሞነሞነው ስራ ፈጠራ በተመራቂዎች ላይ ያለውን ተጽዕኖ ማየቱ ብቻ ለዚህ እንደ አስረጅ የሚጠቀስ ይሆናል፡፡ ምሩቃን በአካዳሚ ከሚያስመዘግቡት ጥሩ ውጤት ይልቅ የኢህአዴግ ‹ግሬድ› ከፍተኛ ዋጋ በተሰጠበት በአሁኑ ጊዜ በትምህርት ብቁ ሆነው ለመውጣትና ሥራ ፈጣሪ ለመሆን ስንቶች እንደሚችሉ መጠየቁም እውነታውን ለመረዳት ያስችላል፡፡

ሥራ ለመፍጠር . . .

ሥራ ፈጠራ በአየር ላይ የቆመ ቅዠት ሳይሆን በምድር የወረደ እውነታ መሆኑን ማረጋገጥ ተገቢ ነው፡፡ አሁን ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ሥራ ፈጠራ ሲል ኮብል ስቶን መቀጥቀጥን፣ ዶሮ ማርባትን እና የመሳሰሉትን የከፍተኛ ትምህርት ዝግጅት የማይጠይቁትን ማለቱ እንደሆነ በተግባር ባለፉት አመታት የታየ መሆኑን ማስታወስ ይገባል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርትን ተከታትሎ ወደ ድንጋይ መጥረብ የሚሰማራ ሰው እንዴት ሥራ ፈጠራ ላይ ተሰማርቷል ሊባል እንደሚችል ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ በእኔ እምነት ይህን አይነት ሥራ ለመስራት አስራ አምስትና ከዚያ በላይ ዓመታትን በትምህርት ቤት ማሳለፉ ኪሳራ ነው፡፡ ኮብል ስቶን መጥረብ የሚናቅ ሥራ አይደለም፤ የከፍተኛ ትምህርት ዝግጅትን ግን አይጠይቅም፡፡

ስለሆነም ኮብል ስቶን ጠረባ ላይ የተሰማራ አንድ የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ ሥራ ፈጠረ ሳይሆን የሚመጥነውን ሥራ በሀገሩ አጣ ነው ሊባል የሚችለው፤ አሊያ ደግሞ በትምህርት ቆይታው ወቅት አስፈላጊውን እውቀትና ክህሎት እንዲጨብጥ አልተደረገም ማለት ነው፡፡ በእርግጥ ምሩቃን ሥራ ፈጣሪዎች ቢሆኑ እሰየው ነው፤ የሚበረታታም ተግባር ነው፡፡ ሆኖም ግን ሥራ ፈጣሪ የሰው ኃይል እንዲኖር ካስፈለገ (በእኔ እይታ) ሁለት መሰረታዊ ሁናቴዎች መሟላት ይኖርባቸዋል፡፡

አንደኛው ምሩቃን በትምህርት ቆይታቸው ወቅት ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን የአካዳሚያዊና የተግባር እውቀትና ክህሎት በሚገባ ታጥቀው መውጣት ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህም ጥራት ያለው ትምህርትን ተግባራዊ የሚያደርግ ፖሊሲ ሊኖር ያስፈልጋል፡፡ ሆኖም ግን በተቃራኒው አሁን ያለው የትምህርት ጥራት የሚያወላዳ እንዳልሆነ ኢህአዴግም ራሱ የማይክደው ሀቅ ነው፡፡ ስለሆነም ሥራ ፈጣሪ የሰው ኃይልን ለማፍራት ቆንጆ የትምህርት ፖሊሲን መቅረጽና ለትምህርት ዘርፉ ተገቢውን ትኩረት መስጠትን ግድ ይላል፡፡

ቁጥር ብቻውን ግብ አይደለም፤ ተማሪዎች በካድሬነት ተመልምለው፣ ትምህርትን ችላ ብለው፣ የጥገኝነትንና የጥቅመኝነትን አስተሳሰብ ሳይሆን በሚያገኙት ትምህርት ብቁ ሆነውና እውቀትን ታጥቀው ነው ወደ ስራው ዓለም እንዲገቡ መደረግ የሚኖርባቸው፡፡ አሁን ላይ ይህ ሲሆን አይታይም፡፡ ይህን የተማሪዎችን ብቃት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ዩኒቨርሲቲዎችም ያሉ አይመስልም፡፡ ቀደም ሲል የዩኒቨርሲቲዎችን ቁጥር መጨመር አንስተናል፤ ሆኖም ዩኒቨርሲቲዎችን በየመንደሩ መገንባት ብቻ ተፈላጊውን ውጤት አያስገኝም፡፡ በቅድሚያ ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች ምቹና አስፈላጊውን ሁሉ ግብዓት ያሟሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

hire meይህም ብቻ ሳይሆን ምሩቃን ሥራ ፈጣሪ ሆነው እንዲወጡ ካስፈለገ የመምህራንን ብቃት ማሳደግ ላይም በትኩረት መስራትን ይጠይቃል፡፡ መምህራን ከማናቸውም የፖለቲካ ተጽዕኖ ነጻ ሆነው ሥራቸውን እንዲያከናውኑ መፍቀድና ማስቻል፣ እንዲሁም ራሳቸውን በየጊዜው በተከታታይ የትምህርት እድል እንዲያበቁ ሁኔታዎችን ማመቻቸት አስፈላጊ ይሆናል፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ የተመሰረቱ መምህራንንና የትምህርት አስተዳደርን መገንባት ከተቻለ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው አስፈላጊውን እውቀትና ክህሎት በማካበት ሥራ ለመፍጠር የሚያስችላቸው ደረጃ ላይ እንዲገኙ ማስቻል ይቻላል ማለት ነው፡

በሁለተኛ ደረጃ ምሩቃን ተገቢውን እውቀትና ክህሎት ይዘው መጥተውም ቢሆን ለሥራ ፈጠራ ሂደታቸው አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዩች ሊመቻቹላቸው የተገባ ይሆናል፡፡ ለአብነትም ምሩቃን በአዲስ ሥራ ላይ ይሰማሩ ዘንድ ከሚመለከተው አካል (መንግስት) የገንዘብና የቦታ አቅርቦት ሊያገኙ ያስፈልጋል፡፡ አሁን እየሆነ ያለውን ካየን ግን አንድ ምሩቅ የሆነ ሥራ መጀመር ካሰበ የገንዘብ ምንጩ ወገቡን እንደሚይዘው ይታወቃል፡፡ ምሩቃን ከትምህርት ቤት ሲወጡ ገንዘብ ይዘው እንደማይወጡ ለማንም ግልጽ ነው፤ በምትኩ ከምሩቃን የሚጠበቀው እውቀት ነው፡፡ ይህ እየታወቀ ግን ምሩቁ ሥራ ለመጀመር ብድር ቢፈልግ ማስያዝ ያለበት ገንዘብ ወይም የቤት ካርታ ይጠየቃል፡፡ እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ሥራ ፈጠራን ማንኳሰሱ የሚስተዋለው፡፡

አንድ ምሩቅ ከትምህርት ቤት እንደወጣ ብድር ለማግኘት የሚጠይቀውን 20 በመቶ ገንዘብ ከወዴት ሊያመጣ እንደሚችል መገመት ይቻላል፤ ብድር ለማግኘት ሌላ ብድር መግባት ካልሆነ በስተቀር 20 በመቶውን የትም አያገኝም! ስለሆነም ይህ አልሆን ሲል ወደ ሁለተኛው ‹አማራጭ› መሻገር ይከተላል፡፡ ይህ ግን ለምሩቁ የባሰ ከባድ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ ‹አማራጭ› የቤት ካርታ ማስያዝ ጉዳይን የሚመለከት ነው፡፡

አንድ በወላጆቹ እገዛ ትምህርቱን የተከታተለ ወጣት ምሩቅ የማንን ቤት ካርታ ነው እንዲያስይዝ የሚጠበቀው!? የወላጆቹን!? መቼም ስንትና ስንት አመታት በሥራ ላይ የሚከርሙ ኢትዮጵያውያን ቤት በማይሰሩበት በአሁኑ ጊዜ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቀ ወጣት የቤት ካርታ ይኖረዋል፤ እሱንም ለብድር ሲባል አስይዞ ይበደራል ብሎ ማሰብ በምሩቁ ላይ መሳለቅ ነው የሚሆነው፡፡ ለዚህ ነው አሁን ላይ ምሩቃን ሥራ ፍጠሩ በሚለው እሳቤ የተተበተበው ኢህአዴግ ሥራ ፍለጋን ማውገዙ ተገቢ የማይሆነው፡፡

ሥራ ፍለጋ

ከዚህ የምረቃ ጊዜ አንስቶ በርካታ ወጣቶች ሥራ ፍለጋ ሲንከራተቱ፣ የሥራ ያለህ ሲሉ ይስተዋላሉ፡፡ በየማስታወቂያ ሰሌዳውም ዓይኖቻቸውን ያንከራትታሉ፡፡ ብዙዎች የምረቃ ደስታቸውን እንኳ ሳያጣጥሙ የሥራ ፍለጋ ጉዳይ እረፍት ይነሳቸዋል፡፡ የሥራ አጥነት ስጋት (እውነታ) ውስጣቸውን ይረብሻቸዋል፡፡ በእርግጥም አሁን ላይ በሀገር ቤት ሥራ ፈልጎ ማግኘት የሎተሪ ያህል የሆነባቸው አያሌ ተስፈኛና ባለአዲስ ጉልበት ባለቤት ወጣቶች ሞልተዋል፡፡ ዳሩ ግን ሥራ ፍለጋን የሚያወግዘው የሚመስለው ኢህአዴግ መራሹ መንግስት በአስተሳሰቤ ካልተጠመቃችሁ ሥራ አታገኙም ያለ ያስመስለዋል፡፡ ስለሆነም እሱ ባስቀመጠው መስመር ብቻ ግዴታ አስገብቶ በማደራጀት የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን በድንጋይ ፈለጣ ተግባር ላይ ያሰማራቸዋል፡፡

ሐቁ፣ መደራጀት ኃይል ነው፡፡ ግን ደግሞ መደራጀት ለመጠርነፍ ሲሆን መደራጀት አቅመ ቢስነት ይሆናል፡፡ አሁን አሁን በመንግስት የሚደረገው የመደራጀት ሂደት የዚሁ አቅመ ቢስ የመሆን ማሳያ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም መንግስት ወጣቶችን ሲያደራጅ ቀዳሚ ተግባሩ በርካሽ ፖለቲካዊ ትርፍ እሳቤ ውስጥ ሆኖ እንደሆነ ማሳያዎች በመኖራቸው ነው፡፡ ለአብነትም የሚደራጁት ወጣቶች ምንጊዜም ቢሆን ለመደራጀት የበቁት መብታቸው ስለሆነ ሳይሆን መንግስት በደግነቱ ያመቻቸላቸው ዕድል እንደሆነ በአያሌው ደጋግሞ ሲገልጽ መሰማቱ የርካሽ ፖለቲካ ትርፍ ጥማቱን በግላጭ ያሳየ በመሆኑ ነው፡፡ ለዚህም ነው ምሩቃንን አደራጅቶ ከራሱ ማዕቀፍ እንዳይወጡ ለማድረግ ሲባል ሥራ ፍለጋን የሚያወግዘው፡፡

በዚህ ጠርናፊ ማደራጀት ውስጥ ገብተው ሥራ የጀመሩትም ቢሆን ሥንቶቹ ውጤት እንዳሳዩ የሚታወቅ ነው፡፡ ተደራጅተው ሥራ በጀመሩ በጥቂት ወራት ውስጥ ሥራቸውን በኪሳራና ድጋፍ በማጣት እንዲሁም በጣልቃገብነት ምክንያት አቋርጠው ለመበተንና ሀገር ጥለው ለመሰደድ የተዳረጉት በርካቶች ናቸው፡፡ ጥቂቶች እንደተሳካላቸው መካድ ባይቻልም ብዙ ጊዜ በቴሌቪዥን ተጋንኖ የሚነገርላቸው ‹ይህን ያህል፣ ያን ያህል› ንብረት አፈሩ የሚለው ጨዋታ በአብዛኛው ተራ ፕሮፖጋንዳ እንደሆነ ጋዜጠኞች በትዝብት ውስጥ ሆነው በዓይናቸው ካዩት ሐቅ ምስክርነትን የሚሰጡበት ሀቅ ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ሁኔታ መንግስት ሥራ ፍለጋን ለማውገዝ ምን ሞራል ይኖረዋል፡፡

ከመነሻው ‹ሥራ ፍለጋ› የሚለው እሳቤ ጤነኛ አስተሳሰብ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰዎች ሥራ ለመስራት መነሳታቸው ለሥራ ያላቸውን ቀናዒነትና በሀገራቸው ማናቸውም አቅማቸው በፈቀደው ደረጃ ለመስራት ሥራ መፈለጋቸው ተገቢ ጉዳይ ነው፡፡ ሥራ ፍለጋ ማለት ለመስራት ቁርጠኛ መሆን ማለት ነው፤ ከሥራ ጋር አገናኙኝና አቅሜን ልጠቀም የማለት ቅን አስተሳሰብ ነው፡፡ በመሆኑም ሥራ ፍለጋ ፈጽሞ እንደ ውግዘት መታየት አይኖርበትም፡፡

ምሩቃን በግል ድርጅቶችም ሆነ በመንግስት መስሪያ ቤቶች ሥራ ፈልገው በመቀጠራቸው ውግዘት ሊገጥማቸው አይገባም፡፡ እንዲያውም መንግስት ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ የተለያዩ ፖሊሲዎችን በመቅረጽ ሚናውን መወጣት ነው ያለበት፡፡ በአደጉት ሀገሮች መንግስት የሥራ አጥነትን በየጊዜው ለማቃለል የተለያዩ እቅዶችን ይፋ በማድረግ ወደ ሥራ ይገባል፡፡ ዜጎች በተነሳሽነት ሥራ ፈጠራ ላይ እንዲገቡ ዕድሉ ይመቻችላቸዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ ግን መንግስታት ለሥራ ፈላጊ ዜጎቻቸው ሥራ የመፍጠር ኃላፊነት እንዳለባቸው መርሳት የለባቸውም፡፡ በአሜሪካ የሥራ አጡ መጠን ወደ 9 በመቶ ደረሰ ተብሎ የኦባማ አስተዳደር ይህን ሥራ አጥነት ለመቀነስ የወሰደውን እርምጃ የምናስታውሰው ነው፡፡ በመሆኑም መንግስታት ሥራ ፈጠራ ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው መዘንጋት አይኖርበትም፡፡

ሆኖም ግን ይኽ የመንግስት ሚና በእኛ ሀገር የተረሳ ይመስላል፡፡ ዜጎች በራሳቸው ምንም ምቹ ሁኔታ ሳይቀመጥላቸው ሥራ ፈጣሪ ካልሆኑ በሚል ውግዘትን ይከናነባሉ፡፡ ይህ ትክክለኛ ብያኔ አለመሆኑን ግን ማንም መረዳት ያለበት ሀቅ ነው፡፡ እናም ይህን ካለመረዳት ይመስላል ሥራ ፈልጎ ማግኘትም ሆነ ሥራ ፈጠራ ላይ ለመሰማራት ሁኔታዎች ዳገት እንደሆኑ የሚቀጥሉት፡፡ ምሩቃን ቁጥራቸው በየጊዜው ይጨምራል፣ ሥራ ግን የለም፡፡ ለዚህም ነው ምርቃት ወዲህ ሥራ ወዲያ መሆኑ፡፡ (ምንጭ: ነገረ ኢትዮጵያ፤ ሐምሌ 11 ቀን 2006 ዓ.ም ቅፅ 1 ቁጥር 21)

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Social Tagged With: Right Column - Primary Sidebar

Reader Interactions

Comments

  1. andu says

    July 24, 2014 10:50 pm at 10:50 pm

    Best nachwu

    Reply

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • “አስደንጋጭ”! 1 ሚሊዮን ከሚጠጋ ተፈታኝ ተማሪ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገባው 30 ሺህ (3.3%) ብቻ ነው  January 27, 2023 09:11 am
  • የማይዘነጋዉ የኢትዮጵያዊያኖች የጀግንነት ተጋድሎ ታሪክ፡- ኮሎኔል ባጫ ሁንዴ (ታጠቅ) January 27, 2023 06:12 am
  • ጎርጎራ – የመጻዒው ዘመን ሙሽራ! የዉበት ፈርጥ! January 17, 2023 04:18 pm
  • ሁለተኛው መስቀል አደባባይ January 17, 2023 04:13 pm
  • በአቡዳቢ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን January 17, 2023 04:08 pm
  • በንፋስ ስልክ ላፍቶ ስምንት የመሬት ሌቦች ተያዙ January 16, 2023 11:36 am
  • ሺሻ ሲያስጨሱ በተገኙ ሆቴሎችና የምሽት ጭፈራ ቤቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ January 16, 2023 08:50 am
  • በሐሰተኛ መታወቂያ የደኅንነት አባል ነን ብለው ሲያጭበረብሩ የነበሩ ተያዙ January 13, 2023 02:03 pm
  • ተሽከርካሪ ወንበር ለትግራይ – “ናይ ኣካል ጉዱኣት ተሽከርካሪ ዘለዎ ወንበር” January 12, 2023 07:17 pm
  • የአማራው ኩራት፣ የኢትዮጵያ ዘብ፣ የትህነግን ቅስም ሰባሪ! January 12, 2023 04:00 pm
  • በኢትዮጵያ ላይ የተጣሉ ማዕቀብ እና ሌሎች አስገዳጅ ሕጎች ሙሉ ለሙሉ ተሰረዙ January 12, 2023 01:52 pm
  • የቻይና ዕዳ ስረዛ “Payday Loan Diplomacy” ወይስ ኢትዮጵያን ያዳነ ተግባር? January 12, 2023 11:00 am
  • የአዲስ አበባ አስተዳደር ከቋንቋ ጋር በተያያዘ ውሳኔ አስተላለፈ January 12, 2023 10:46 am
  • “አምባሳደሩ” የቀድሞ ጌቶቻቸውን እንዲያቋቁሙ ተሾሙ January 11, 2023 03:47 pm
  • መከላከያ ሸኔን የሚዋጉ ሚሊሻዎችን አሠልጥኖ አስመረቀ January 10, 2023 05:37 pm
  • በሰባት ተጠርጣሪዎች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ January 10, 2023 03:36 pm
  • የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አቅጣጫ January 6, 2023 03:26 pm
  • “ከዕብሪቱ አስተንፍሰነዋል” – ኢሳያስ January 2, 2023 07:29 pm
  • [ኢትዮጵያን] “አስታክኮ ኤርትራን መውጋት ለሚፈልግ ኃይል አንተባበርም” January 2, 2023 07:11 pm
  • የ፰ ወር ሕጻንና ጨቅላ ወንዶች የሚደፈሩባት ትግራይ December 14, 2022 02:49 pm
  • “ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው” የደጎች አውራ የመቄዶኒያው ቢንያም በለጠ December 14, 2022 09:59 am
  • “የሀብት ምዝገባ መረጃው ለሕዝብ ክፍት ይደረግ “ December 13, 2022 10:30 am
  • የኢትዮጵያ ዓለምአቀፋዊ የሌብነት ደረጃ December 13, 2022 09:42 am
  • ለብረት አቅላጮች ለመሸጥ በኤሌክትሪክ የብረት ማማዎች ስርቆት የ100 ሚሊዮን ብር ኪሳራ December 13, 2022 09:26 am

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2023 · Goolgule