
ከአቶ ሀብተማሪያም ሞገስና ከወ/ሮ ደስታ አየለ በ1935 ዓ.ም የተወለዱት ደራሲ መስፍን ሀብተማርያም በ 71 ዓመታቸው በአዲስ አበባ ከተማ አረፉ።
ደራሲ መስፍን በልጅነታቸው ባህላዊ የቤተ ክህነት ትምህርት የተማሩ ሲሆን ፣ በሞጆና በአንቦ የአንደኛና የሁለተኛ ደራጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል። በወቅቱ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርስቲ ተብሎ በሚጠራው የትምህርት ተቋምም በመግባት በቋንቋዎችና ሥነ-ፅሁፍ ክፍል በማዕረግ በቢኤ ዲግሪ ተመርቀዋል።በመቀጠልም ካናዳ በሚገኘው ቫንኩበር ከተማ በመሄድ ዪኒቨርስቲ ብሪቲሽ ኮሎምብያ ገብተው የፈጠራ ሥነ- ፅሁፍ የማስተር ድግሪ አግኝተዋል።
ደራሲ መስፍን ሀብተማሪያም አገራቸው ከተመለሱ በኋላ በአማርኛ ቋንቋ በኢልብወለድ አጻጻፍ የትምህርት መስክ በተለያዩ ቦታዎች አስተምረዋል በአዲስ አበባ ዪኒቨርስቲም በቋንቋዎች ጥናት ተቋም የስነጽሁፍ ኮርሶችን በመስጠት ቆይተዋል። ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ሬድዮና በኩራዝ አሳታሚ ድርጅትም ሰርተዋል።
በህዝብ ዘንድ ከሚታወቁባቸው ድርሰቶቻቸው መካከል የቡና ቤት ስዕሎችና ሌሎች ወጎች፣አዜብና ሌሎች አጫጭር ልብወለዶች፣ዓውደ አመት እና የለሊት ድምጾችና ሌሎች ወጎች ቅድሚያውን ስፍራ የያዙ ሲሆኑ።በሬዲዮና በቴሌቪዢን የሚነበቡ ምርጥ ስራዎች ነበሯቸው።
ደራሲ መስፍን የሚጽፏቸው ጽሁፎች ከትምህርት ሰጪነታቸው እኩል የማዝናናትም ኃይል እንዳላቸው የሚመሰክሩት አንባብያን ብቻ ሳይሆኑ ደራሲያኑም ጭምር ነበሩ።በተለይም ባለቅኔ ደራሲና መምህር ደበበ ሰይፉ ይበልጥ አድናቂያቸው እንደነበሩ ይነገራል።እዲሁም የሳቸውን ሥራ በመመርኮዝ የመመረቂያ ጽሁፍ ያቀረቡም ብዙዎች ናቸው።
ደራሲው በራሳቸው ፈቃድ ስራቸውን ለቀው ከሥነ-ጽሁፍ ሙያ ጋር የተያያዙ ልዩ ልዩ ስራዎች በመስራት የቆዩ ሲሆን ሐምሌ 6 ቀን 2006 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ጋዜጠኛ ደራሲና አርታኢ መስፍን ሐብተማርያም ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት ነበሩ። (ለጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ዜናውን የላኩት ወለላዬ ከስዊድን ናቸው)
I would like to be notified of new articles
When you open an article/news on the bottom right corner you will see a subscription link. Please sign up there.
Thanks
Editor