ሰላማዊ ፓርቲ የመጀመሪያውን ጥሩ አቅጣጫ አመልካች ሰላማዊ ሰልፍ ግንቦት ፳ ፭ ቀን ፳ ፻ ፭ ዓመተ ምህረት በአዲስ አበባ በማድረግ፤ የሕዝቡን የነፃነት ፍላጎት ባደባባይ አሳዬ። ይህ ታሪካዊ ነው። ተደጋጋሚ ሰላማዊ ሰልፎች መጪ መሆናቸውንና አይቀሬነታቸውን አረጋገጠ። ካሁን በፊት ታጋዮች፤ በተደጋጋሚ፣ በየቦታው፣ ሰላማዊና የትጥቅ አመፅ በማድረግ ግባቸውን ለመምታት ጥረት አድርገዋል። በሕዝቡ ላይ በደል እስካለ ድረስ፤ አመፅ በተለያዬ መልክና በተለያዩ ቦታዎች መቀጠሉ፤ የሕልውና ግዴታ ነው። ለዚህ ምስክር አያሻም። ሕዝባዊ ግቡ አንድ በሆነበት ወቅት ደግሞ፤ ለሕዝባዊ ግቡ የትግሉ አንድ መሆን፤ ግዴታ ነው። ማሳየት የፈለግሁት፤ ሰማያዊ ፓርቲ በጀመረው ሰላማዊ ሰልፍ ተነሳስትን፤ አሁንም የተለያዬ ሰላማዊ ሰልፍና የተነጣጠለ ትግል እያካሄድን፤ ሕዝባዊ ድል ለማግኘት ማሰብ የትም እንደማያደርሰን ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ፤ አሁን ያለንበትን የፖለቲካ ሀቅ እያሻሻልን መሄድ ካልቻልን፤ ወደፊት የሚጠብቀን የባሰ ቀውስና ማጥ መሆኑን መገንዘብ አለብን። ለዚህ ደግሞ፤ የትግሉን ሀገራዊነት ማጠናከር፣ የአንድ ሀገራዊ ድርጅት አስፈላጊነትን ማስመር፣ ዛሬ የምናደርገው እንቅስቃሴ የነገውን ኢትዮጵያዊነት መልክና የግቡን ምንነት ወሳኝ መሆኑን መረዳት አስፈላጊነቱን ማድመቅ ነው። በለዘብተኝነት ወይንም ሌሎች ያደርጉታል በማለት የምንተወው ጉዳይ አይደለም። ባሁኑ ሰዓት ሁላችን እያወቅናቸው የመጣነው ሀቆች አሉ። አንደኛ በሥልጣን ላይ ያለው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ወዶ ለሕዝቡ ፍላጎት አለመገዛቱን ነው። ሁለተኛ በአንድነት እስካልተነሳን ድረስ፤ የተነጣጠለው ትግል ውጤቱ ሕዝባዊ አለመሆኑን፤ ሰላማዊም ሆነ የትጥቅ አመፁ ውጤቱ ሕዝባዊ የሚሆነው፤ ሕዝቡ በአንድነት የተሰለፈበት፣ ሕዝቡ የመራው መሆን ያለበት መሆኑን ነው። ሶስተኛ ደግሞ፤ በአንድ ድርጅት የተዋቀረ እስካልሆነ ድረስ ለየብቻ የምናደርገው ጥረት የትም እንደማያደርሰንና አንድ ድርጅት አስፈላጊ መሆኑን ነው። ለዚህ ሁሉ መሠረቱ ደግሞ በግልፅ መነጋገር መቻል ያለብን መሆኑ ነው።
ምን እያደረግን ነው? ሰላማዊ ፓርቲ ለትግሬዎች ነፃ አውጪ መንግሥት የሶስት ወር እድሜ ሠጥቶታል። አንድነት ፓርቲ ከዚያ በፊት የሚደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች ጠርቷል። ይህ የተነጣጠለ ሰላማዊ ሰልፍ የሕዝቡ ሰላማዊ ጥሪ እንዲሆን እፈልጋለሁ። አንድነት ፓርቲ ከሰላማዊ ፓርቲ ጋር ውድድር ገጥሞ የበለጠ መሆኑን ለማሳየት ያደረገው እንዳልሆነ ይገባኛል። በተጨማሪም አንድነት ፓርቲ ብቻውን የትግሬዎችን ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ለመጣልና ሥልጣን ለመውሰድ የተነሳ እንዳልሆነ ይገባኛል። ከዚህ በመነሳት፤ አሁን ያለንበትን የፖለቲካ ሀቅ በቅጡ ተገንዝበን፤ ወደፊት የምንሄድበትን መንገድ በማሻሻል፤ ሊገጥመን የሚችለውን ቀውስና ማጥ በማስወገድ፤ ትክክለኛ ግባችንን የምንመታበትን ዘዴ መተለም ይኖርብናል። አሁንም ለየብቻችን የምናደርገው ጉዞ፤ ምንም ሌሎቹን ተባበሩን እያልን በየበኩላችን ብንጠራም፤ ውጤቱ፤ የጋራ ሳይሆን የግል ነው። የወደፊቱም በግልና በጋራ መካከል ባለው ልዩነት የተመሠረተ ጠብ ነው። የትግሉ ዓላማ በሥልጣን ላይ ያለውን አድሏዊ አምበገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ መንግሥት አውርዶ፤ በሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት የተወከለ መንግሥት ማቋቋም ነው። ለዚህ ደግሞ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ሳይሆኑ አንድ ድርጅት ብቻ ነው አስፈላጊው። ግቡን ሲመታ ለውድድሩ ተዘጋጅተን መቅረብ እንችላለን። ልዩነቱ፤ ለሕዝባዊ ድሉ ድርጅታችንን እናስቀድማለን ወይንስ የድርጅታችንን ሕልውና ለሀገራዊ ሕልውና እንሰዋለን ነው። ድርጅቶች ምን ጊዜም በመርኅ ግብራቸው ተመርኩዘው በማንኛውም ጊዜ ይመሠረታሉ። ሀገር ግን ያ ምርጫ አይሠጠውም። እናም ከምንኛውም በፊት ሀገር ብለን መነሳት ያለብን፤ ግባችን ሀገራችን ከሆነ፤ አሁን ነው። የለም ድርጅቴን መሪዬ አድርጌ ነው የምሄደውና ሀገሬን በድርጅቴ ነው የምታገልላት ማለት፤ ድርጅትን ከሀገር በላይ ማድረግ ነው።
የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት የሕዝቡን ሰላምና መረጋጋት ለማግኘት፤ በሀገር ፀጥታና በብሔሮች ነፃ መውጣት ስም አምታትቶ፤ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በመንፈግና የመሪዎችን ኪስ በማሳበጥ፤ የውሸት ሀገራዊ ዕድገትን ለመሸፋፈን መሞከሩ የትም አላደረሰውም። ይልቁንም በሕዝቡ የኑሮ ሁኔታ ቁማር መጫወቱ ራሱን ዞሮ መቶታል። መሠረታዊ የሆነውን የመንግሥት ተልዕኮ ስቷል። በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መንግሥት ማለት፤ የሕዝብ ተወካይ ማለት ነው። መንግሥት ማለት በሕዝብ ፍላጎት የቆመ ማለት ነው። መንግሥት ማለት በሕዝቡ መካከል እኩልነትን የሚጠብቅና የሚያሰጠብቅ ማለት ነው። መንግሥት ማለት ለሕዝብ ደኅንነት፣ ለሰላምና ለሀገር ዕድገት የቆም ማለት ነው። መንግሥት ማለት የሕዝብ አገልጋይ ማለት ነው። የትግሬዎች ነፃ አውጪ መንግሥት ከላይ የዘረዘርኳቸውን አንዳቸውንም አላሟላም።
የደርግን መንግሥት የኢትዮጵያ ሕዝብ የጠላበት ምክንያት፤ በአረመኔነቱ፣ ያለሕግ የፈለገዉን በማድረጉ፣ የግለሰቡ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ባለመከበራቸው፣ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክልል ሠርቶ የማደርና የመበልፀግ በሩ በመዘጋቱ፣ የባለሥልጣኖች ወገን የሆኑ የሁሉም ነገር ፈላጭ ቆራጭ በመሆናቸው ነበር። ታዲያ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መጥቶ የቀየረው ነገር ቢኖር፤ በደርግና በኢሠፓ ቦታ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መሪዎችና ፓርቲ መተካታቸውን ብቻ ነው። ግድያውና የሀገር ሀብት ዝርፊያው ብሷል። ጥቂቶቹ በሃብት መጨማለቃቸውና አብዛኛው በድኅነት መማቀቁ የዕለት እውነታ ሆኗል። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መሪዎችና ሀብት ነጣቂ አባሪዎቻቸው፤ የሕዝቡን የነፃነት ፍላጎትና ሠርቶ የማደር ጉጉት በስግብግብ የግል ጥቅም ማካበት ሩጫቸው አመድ አስጋጡት። ሀገሪቱን በጣጠቋት። ደንበሯን ሸጡት። ለሙን መሬት ከባለቤቱ ነጥቀው ለራሳቸውና ለውጭ ከበርቴዎች በርካሽ ቸበቸቡት። ይህ የሕዝቡን ቁጣ አስነስቶ መቃብራቸውን እንዲቆፍር ገፍቶታል። ለሥልጣናቸው በር መክፈቻ የተዋቀረው የክልል ግዛት፤ እንዳቋቋመው ፌዴራላዊ ግዛት ውስጡ በስብሶ ንቅዘቱ ሕዝቡን ቀስቅሶታል። ይህን ማስተካከል አሁን የሕዝቡ ኃላፊነት ነው። የአንድ ቡድን ወይንም ፓርቲ ግዴታና ውዴታ አይደለም። በአንድነት የሁላችን ነው። የትግሬዎችን ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት በሌላ አንድ ፓርቲ ባሁኡ ሰዓት ለመለወጥ የትዮጵያሕዝብ ፍላጎት አይደለም። ሀገር አቀፍ የሆነ አንድነትንና ሰላምን ማግኘት ነው የሕዝ ፍላጎት። ይህ ደግሞ የሚተገበረው፤ ሀገር አቀፍ የሆነ ድርጅት ትግሉን በአንድ አጀንዳ ሲመራው ነው። በአሜሪካ የእስራዔላዊያን ደጋፊ ማህበር በብዙ ሺ የሚቆጠሩ አባላትን ሰብስቦ፤ የእስራዔልን ጥቅም ለማስጠበቅ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። እኛ ከብዛታችን፣ ከሀብታችን፣ ከዕውቀታችን፣ ከሀገር ወዳድነታችንና ለወገናችን ካለን ፍቅር የተነሳ፤ የበለጠ ማድረግ የምንችል ነን። የጎደለን ነገር ቢኖር፤ በአንድነት የመሰባሰቡ ጉዳይ ነው። አአንድ ስንሆን፤ አይደለም የትግሬዎችን ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ማስወገድ፤ ሀገራችን በብልፅግና ከዓለም ጎላ ብለው ከሚታዩት አንዷ መድረግ እንችላለን።
የሚያሳዝነው ሀቅ ደግሞ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ብቻውን እስከቆመና እስከታገለ ድረስ፤ አቸነፈም አላቸነፈም ውጤቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይሆን የዚያ ድርጅት ብቻ ነው። መነሻው ባሁኑ ሰዓት ሕዝቡን እኔ ብቻ እወክላለሁ የሚል አንድ ድርጅት የለምና ነው። የተለያዩ የነፃ አውጪ ግንባሮች ኢትዮጵያዊ ያልሆነ አጀንዳቸውን እያራመዱ ነው። የውይይቱን ይዘት እነሱው አሽከርካሪ ሆነዋል። በተደራቢ ደግሞ፤ ሥልጣን የቋመጡ ግለሰብና ቡድኖች አራጋቢ በመሆን ይኼንኑ እየገፉ ነው። ይኼ የነገን አይቀሬ ጠብ አድልቦታል። መለየት ያለበት፤ ይህ የኢትዮጵያዊያን ትግል ነው ወይንስ የሌሎች የሚለው ነው። በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እምነት ያለን ማንኛችንም ታጋዮች፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወሳኝነቱን ተቀብለን ባንድ ለመታገል ፍርሃት ሊኖረን አይገባም። ድርጅት የመታገያ መሣሪያእስከሆነ ድረስ፤ አሁን የምንሻው ኢትዮጵያዊ የሆነ አንድ ድርጅት ነው።
ሕዝቡ በትግሬዎች ነፃ አውጪ መንግሥት የዕለት ተዕለት ፀረ-ኢትዮጵያ ተግባር ከቀን ወደ ቀን አንጀቱ እያረረ ነው። የመሪዎቹን ኪስ ማበጥ በዓይኑ እየተመለከተ ወገኖቹ በየመንገዱ እየተራቡ ማየቱ ዘግንኖታል። ሀገር እየተቆራረሰች ነው። በየክልሉ የተመደቡት ኩልኩል አገልጋዮች የክልላቸውን ሰዎች የግል ባሪያዎቻቸው እያደረጓቸው ነው። የውሸት ምርጫው ሕዝቡን እንደማያሳትፍ በተደጋጋሚ ታይቷል። የሚያጋልጡ ግለሰቦች ጥቃቱ በተደጋጋሚ ሕይወታቸው ማጣት ሆኗል። በትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር ባለሀብቶችና በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ያለው የኑሮ ልዩነት መለኪያ በሌለው ክፍተት ተራርቋል። ሥልጣንና ሀብት በተወሰኑት እጅ መካተቱ ትግሉን በጣም ለይቶ አውጥቶታል። በተደጋጋሚ ለገጠመው እድል በሩን ግጥም አድርጎ በመዝጋት፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ራሱን አግልሎ አስቀምጧል።
ይህ ትግል፤ የጠራ ራዕይና አንድ ትክክለኛ ድርጅት እስካላበጀ ድረስ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ድል በቀጠሮ ለወደፊቱ ተላለፈ ማለት ነው። እናም ደጋግመን ማንሰላሰል ያለብን፤ ጥረታችን የኢትዮጵያን ሕዝብ የትግል ግብ ገሀድ ለማድረግ እንጂ፤ ለመጪዎቹ ትግል ለማውረስ እንዳይሆን ነው።
በምኞትና በበጎ ፍላጎት የሚፈፀም ነገር የለም። ምኞት የዕቅድ መነሻ ሆኖ ለተግባር መንገድ ከፋች ይሆናል። በዚህም መነሻ በመሆኑ ጠቃሚ ሚና አለው። ከዚያ አልፎ ግን ምኞት ከስኬት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የለውም። ስኬት ቀጥተኛ ዝምድና ያለው ከተግባር ጋር ብቻ ነው። በሚጠሩት ሰላማዊ ሰልፎች ሁላችን ልንሳተፍና ልናበረታታቸው ይገባል። ውጤቱ ሕዝባዊ እንዲሆን ከፈለግን ግን፤ ኢትዮጵያዊያን ታጋዮች በሙሉ በመሰባሰብ በአንድ ተደራጅተን የአንድነት ጥሪ ማቅረብና ሰላማዊ ሰልፉ በዚህ የአንድነት ኃይል እንዲመራ ማድረግ ብቻ ነው። ያለ አንድነት የአንድነት ውጤት የለም።
አንዱ ዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ፤(eske.meche@yahoo.com)
Leave a Reply