ሀገራችን ካሏትና ሐበሻን እንደ ሐበሻ ኢትዮጵያን እንደ ኢትዮጵያ ከሌሎች ተልይታ እንድትታወቅ ካደረጓት ታሪካዊና ባሕላዊ መለያዎቿ ምንጫቸው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን እንደሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በጉልህ ከሚታወቁት ባሕላዊ ኩነቶቻችን ውስጥ ሃይማኖታዊ አሻራ ያላረፈበት አንድም ባሕላዊና ታሪካዊ ክንውን እሴትና ቅርስ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም ፡፡ ይህ ሁኔታ በሌላ በኩል ሕዝቡን ሃይማኖቱን ከባሕሉ ጋር ማዋሐድና ማሰላሰል እስከመቻል የደረሰ ቅሩበ እግዚአብሔር ሕዝብ በማሰኘት አድናቆትን ሲያስቸረው ቆይቷል፡፡ ከነዚህ ሀገራችንንና ሕዝባችንን እንደ ሀገርና ሕዝብ መለያው ወታወቂያው እንዲሆን ካደረጉት ድንቅና ብርቅ እሴቶች ውስጥ አሁን ህልውናቸው አደጋ ላይ ከወደቁት አንዱን አንስተን እናወራለን፡፡ የጥምቀት በዓል አከባበርን ፡፡ ሌሎቹን በሌላ ጊዜ እናያለን ፡፡
የጥምቀት በዓል ከሀገራችን ሌላ በዚህ ጥልቀት ድምቀትና ስፋት በሌላ በማንኛውም ሀገር አይከበርም፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ በሚደረጉ በትናንሽ ሥርዓት ደረጃ ግን አስበውት የሚውሉ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ የሩሲያ፣ የግሪክ፣ የአርመን፣ የኮፕት(የግብጽ)፣ የህንድ፣ የሶሪያ አብያተክርስቲያናት፡፡ በአጠቃላይ ግን የጥምቀት በዓል በነዚህ ሁሉ ሀገራት መከበር የጀመረው በ4ኛው መቶ ክፍለዘመን ማለትም ከመጀመሪያው ሲኖዶስ ከጉባኤ ኒቅያ በኋላ መከበር እንደጀመረ የቤተክርስቲያን ታሪክ ይናገራል፡፡ በመሆኑም የጥምቀት በዓል አከባበር ታሪክ በሀገራችን ከ16መቶ ዓመታት በላይ ታሪክ ያለው ሃይማኖታዊ ቅርስነው ማለት ነው፡፡ የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባሻገር ብዙ ዓይነት ከውዝዋዜ እስከ አለባበስ ያሉትን ባሕላዊና ማኅበራዊ እሴቶችንና ኩነቶችን አቅፎ የያዘ ክፍት ወይም ግልጽ የአደባባይ ሙዚየም (ቤተ-መዘክር) እንደሆነ ይታወቃል፡፡
በመሆኑም በተለየ ሁኔታ የጎብኝዎችን (Tourists) ለመሳብ ጠንካራ አቅም እንዲኖረው አስችሎታል፡፡ ለረጅም ጊዜም ጎብኝዎች በዚህ አስደሳች መሳጭና አዝናኝ በዓል ለመታደም ከተለያዩ ሀገራት ቀደም ብለው ወደሀገራችን የሚገቡ ጎብኝዎች በርካቶች ናቸው፡፡ ይህ እንግዲህ የቱሪዝም ገብያ ይባላል፡፡ መስኩም ጭስአልባው ኢንዱስቲሪ (ምግንባብ) በመባል ይታወቃል፡፡ ሀገራችን በብዙ ሀገራት ባልተለመደ መልኩ ከዘመን በኋላ ከመጣው ከአንዱ የመስሕብ ዓይነት ማለትም ከዘመናዊ ኪነ-ብጀታ (Technology) ውጤት በስተቀር ሁሉንም ዓይነቶች የቱሪዝም (የጎብኝ መስህብ) ማለትም ተፈጥሮአዊ፣ባሕላዊ ፣ታሪካዊና ሃይማኖታዊ መስሕቦችን አሟልታ የያዘች ዕድለኛ ሀገር ብትሆንም ካላት አቅም አኳያ ጨርሶ ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻለች ካሉ መረጃወች መረዳት ይቻላል፡፡
ወደሌሎች ሀገሮች ስንሄድ ግን ከእኛ በጣም ያነሰ ከሁለት የመስሕብ ዓይነቶች ያልበለጡ መስሕቦችን ይዘው በቢሊዬኖች (በእልፊታቶች) የሚቆጠር ዶላር በማፈስ ከሀገራቸው ገቢዎች ዋነኛውን ድርሻ እንዲይዝ ማድረግ የቻሉ ብልህ ሀገራት በርካቶች ናቸው፡፡ የቱሪዝም (የጉብኝት) ኢንዱስትሪ (ምግንባብ) በረከት የሞላበት የመሆኑን ያህል የመርገም ቋትም ነው ፡፡ አስፈላጊውና ጠንካራ ጥንቃቄ ካልተደረገበት በስተቀር በቀረብን ኖሮ የሚያሰኝ በርካታ አስቀያሚና ነውረኛ ኮተቶች አሉበት ፡፡ እንደኛ ያለች ሀገር ይሄንን ነውረኛና ሕገ ወጥ የወንጀል ድርጊቶች ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅም ከሌላት መስኩን ለገበያ ክፍት አለማድረጉ ይመረጣል፡፡ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ለቻለ ግን ከሌሎች የገቢ ምንጮች አንጻር ያለ ምንም ድካም የሚበላበት ወይም ከፍተኛ ጥቅም የሚገኝበት እጅግ ጠቃሚ መስክ ነው ፡፡
ሀገራችን ካላት ሀብት አንጻር ከመስህቦቹ የምናገኘው ገቢ ለመጥቀስም የሚያሳፍር ነው፡፡ ይህንን ኢንዱስትሪ (ምግንባብ) በሚፈለገው ደረጃ እንዳንጠቀምበት ካደረጉን ችግሮች አንዱና ዋነኛው ሀገራችን ካሏት መስህቦች ከ95% በላይ ያለው በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን እጅ በመሆኑ አሁን ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት እመራበታለሁ በሚለው ሕገ መንግሥት እንዲሁም ፖሊሲ (መመሪያ) ምክንያት እነዚህን መስሕቦች ማስተዋወቅና ለመስሕቦቹ እንክብካቤ ድጋፍም ወይም ልዩ ትኩረትና ጥበቃ ማድረግ የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን ወይም አንድን ሃይማኖትን ከሌሎች ለይቶ መደገፍ ተጠቃሚ ማድረግ ነው በሚል ያልበሰለ አመለካከት የተነሣ እነዚህን መስሕቦች በሚገባቸው ደረጃ ለጎብኝዎች ማስተዋወቅና ገቢ ማግኘት እንዳይቻል አድርጎታል፡፡ እነዚህ የሀገር ሀብትና ቅርሶች የሚገባቸውን ድጋፍና እንክብካቤ በማጣታቸው ብዙዎቹ ተጎድተዋል፣ጠፍተዋል፣ከባድ አደጋዎችም ተጋርጠውባቸዋል፡፡ እንደዚህም ሆኖ ግን መስሕቦቹ ባላቸው ብርቅ ድንቅነትና የጥራት ደረጃ የተነሣ ያለምንም ማስታወቂያ በራሳቸው ጥንካሬ ጎብኝዎች በተባራሪ ዜና በሚደርሳቸው ጥሪ ምቹ ሁኔታወች ባይኖሩም እነኳን አሁን ያላቸውን የጎብኝ ብዛት ያህል ለመጥራት ችለዋል፡፡
ከላይ እንደገለጽኩት ለአደጋ ከተጋለጡት ቅርሶቻችን አንዱ የጥምቀት በዓልና አከባበሩ ነው፡፡ ይህ በዓል በዋናነት ሁለት ዐበይት ችግሮች ተጋርጠውበታል፡፡ አንደሚታወቀው የጥምቀት በዓል የአከባበሩ ሥርዓት የአደባባይ ወይም ከቅጽረ ቤተክርስቲያን ውጭ ከሚደረጉት ክብረ በዓላት አንዱ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ታቦታተ ሕጉ ከየ አብያተክርስቲያናቱ ወጥተው የሚያድሩበት ጥምቀተ-ባሕር በመባል የሚጠሩ ጥብቅ ሥፍራዎች አሏቸው፡፡ ከነዚህ ቦታዎች ውስጥ በተለይም የከተሞቹ ጥቂት የማይባሉት በልማት ሳቢያ ተነጥቀዋል ወይም ተወስደዋል፡፡ የተቀሩትም ተመሳሳይ የመወረስ አደጋ ተጋርጦባቸዋል፡፡
ሁለተኛው ችግር ደግሞ ይህንን በዓል በሌላ አዲስ ከነሥያሜው ኢትዮጵያዊ ባልሆነ በዓል ለመድፈቅ ለማፈናቀልና ከጊዜ ብዛትም እንዲረሳ የማድረግ እንቅስቃሴ ነው፡፡ በዚህ አጭር ጊዜ እንኳን ቀድሞ በዜና የጥምቀት በዓል አከባበር ተብሎ ይዘገብ የነበረው አሁን የካርኒቫል በዓል አከባበር ተብሎ እስከመዘገብ ተደርሷል፡፡ ይህ እንቅስቃሴም በሀገራችን የጥምቀት በዓል አከባበር በከፍተኛ ድምቀት በሚከበርባት ጎንደር ከአራትና አምስት ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ ቅንጅት እየተካሄደ ይገኛል፡፡ በጥንታዊው ሃይማኖታዊው ታሪካዊውና ባሕላዊው ጥምቀት በዓላችን ላይ ተደርቦ እንዲከበር እየተደረገ ያለው መጤው በዓል ከላይ እንደጠቆምኩት ካርኒቫል በማለት ይጠሩታል፡፡ ካርኒቫል እያሉ የሚጠሩት በዓል ከጥምቀት በዓል ጋር ለምን ተደርቦ እንዲከበር ለማድረግ እንደተፈለገ ፣ዓላማው ምን እንደሆነ ይህንን እያደረጉ ካሉ አካላት ለሕዝቡና ለቤተክርስቲያን አሳማኝ ምክንያት ማቅረብ አልቻሉም፡፡ በሕዝቡና በቤተክርስቲያን ፍላጎት እንዳልተደረገም ይታወቃል፡፡
እንዲያውም የሀገረ ስብከቱ የደብራትና አብያተ ክርስቲያናት አለቆችና ሊቃውንት በሊቀ ጳጳሱ ሰብሳቢነት ተነጋግረው አቋም በመያዝ በግልጽ በዓሉ በሚከናወንበት መድረክ ተቃውሟቸውን ለሕዝበ ክርስቲያኑ አሰምተዋል፡፡ በዚያ በዓል አከባበር ከሚታደመው ሐበሻ ሕዝብ ቁጥር ባልተናነሰ ቁጥር ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡት ጎብኝዎችም በዚህ ችግር ቅር እንደተሰኙ የመጡት ካገራቸው የሌለውን ልዩ የጥምቀት በዓል አከባበር ለመካፈል ለመታደም ለመጎብኘት እንጂ እጅግ በበለጠ ድምቀት አቅምና ፌሽታ (ፈንጠዝያ) በሀገራቸው የሚከወነውን ካርኒቫል ለመጎብኘት እንዳልመጡ በከፍተኛ ቅሬታ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
ሲጀመርም ሁለቱን በዓላት የሚያገናኛቸው አንድም ነገር የለም፡፡ ካርኒቫል በዋናነት የደቡብ አሜሪካ ሀገሮች ወይም የላቲኖች ባሕላዊ በዓል አከባባር ነው፡፡ ዓላማውም በደስታና በፈንጠዝያ እራስን ማስደስት ነው፡፡ የበዓሉ መሠረትም ባዕድ አምልኮ እንደሆነ ይነገራል፡፡የበዓሉ የአከባበር ሁኔታም የተለያዩ የጭራቅ፣የአውሬና የሰይጣን ተምሳሌትነት ያለቸውን ሥዕሎችና ቅርጻ ቅርጾች በጭምብል መልክና በግዙፍ ቅርጽ ተሠርተውና ተይዘው በራቁት ወይም በዕርቃን የሚደነስበት የሚጨፈርበት ፍጹም ሥጋዊ የሆነ በዓል ነው፡፡
የጥምቀት በዓል ግን ክርስቶስ የሰው ልጆችን የዕዳ ደብዳቤ ለመደምሰስ የተጠመቀውን ጥምቀት ለማሰብ የቃልኪዳኑን ታቦት፣የክርስቶስን መስቀል፣የልዑል እግዚአብሔርንና የቅዱሳኑን ሥዕለ አድኅኖ፣ የምሕረት ቃልኪዳኑን ምልክት ወይም ትእምርተ-ኪዳን (ምንም ዓይነት ምልክት የሌለበት ሰንደቅ) የመሳሰሉት ንዋየ ቅድሳት ተይዞ መዝሙሮችና ስብሐተ እግዚአብሔር እየቀረበ፣እየተሸበሸበ፣እንደ የእስራኤል ንጉሥ ዳዊት በመላ ኃይል በደስታና በእልልታ እየተዘፈነና እየተጨፈረ (መጽሐፈ ሳሙ.ካል. 6፤16-23) እግዚአብሔር የሚከብርበትና የሚመሰገንበት ፍጹም መንፈሳዊ የሆነ በዓል ነው፡፡ በመሆኑም ሁለቱ በዓላት ከታሪካቸው መሠረት እስከ ዓላማቸው ፍጹም ተቃራኒና የማይስማሙ እንደመሆናቸው ሁለቱን ለማዋሐድ ወይም ነባሩን በአዲስ ለመደፍለቅ መሞከር ራሱ አማኞችን የሚያስቆጣ ሌላኛው የጥፋት ድርጊት ወይም የደነቆረ ዓላማ ነው፡፡
በመሆኑም ምንም እንኳ ይህ ተማፅኖ እና ማሳሰቢያ ሊቀርብ የሚገባው በቤተክርስቲያኗ ከፍተኛ የአመራር አካላት (ሲኖዶስ) ቢሆንም እስከምናውቀው ጊዜ ድረስ ይህ የሆነበት ሁኔታ ባለመኖሩ ይህንን እንቅስቃሴ እያካሄዱ ያሉ አካላትና ግለሰቦች ምናልባት እያደረጉት ያለው ነገር ምን ያህል ኃላፊነት የጎደለው፣ ወጥ (original) የሆነውን ማንነት መበረዝ፣ ቤተክርስቲያን የቅርሶቿንና የትውፊቶቿን ወጥነት (originality) የመጠበቅ መብት መጋፋትና መጣስ፣ ታሪክንና ባሕልን በገዛ እጃችን በባዕዳን ባሕልና ማንነት እንዲበረዝና እንዲከለስ እንዲጠፋም እያደረግን እንደሆነ ሳይረዱ ሳይገባቸው ቀርቶ ከሆነ ይሄንን እያደረጉ ያሉት ይህንን ጥፋት እየሠሩ እንደሆነ ተረድተው በተሎ ከዚህ የጥፋት ድርጊት እንዲቆጠቡ በአንፃሩ ግን ኃላፊነታቸውና የሥራ ድርሻቸው የዜግነት ግዴታቸውም ብርቅና ድንቅ ባሕላችንን ቅርሶቻችንን እና ትውፊቶቻችንን ወጥነታቸውን (their originality) ጠብቀው ሳይበረዙና ሳይከለሱ እንዲዘልቁ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገሩ ማድረግ መሆኑን ተገንዝበው ይህንኑ ኃላፊነታቸውንና ግዴታቸውን በተገቢው መንገድ እንዲወጡ ይህ ሲሆን ብቻ መስሕብነቱን ጠብቆ የሚቆይ መሆኑንና ይህንን ማድረግ አንድን የእምነት ተቋም ለይቶ መንከባከብ አለመሆኑን ወደድንም ጠላንም የማንነታችን መገለጫ ነውና ተመሳሳይ ገጽታ ያላቸውን ነገር ግን ማስተዋል የተሞላበት ፖሊሲ (መመሪያ) በመንደፍ ከቱሪዝም (ከጉብኝት) ከፍተኛ ጥቅም እያገኙ ያሉትን ሀገሮች ተሞክሮ በመቅሰም ወጥነቱን (its originality) በመጠበቅና በመንከባከብ ለጎብኚዎችም በሚገባ የማስተዋወቅ ሥራ እንዲሠራ በማድረግ ለሀገር ኢኮኖሚ (ምጣኔ ሀብት) እድገት የማይተካ ሚናውን እንዲወጣና እንዲያበረክት በማድረግ የብልህና የባለ አእምሮ መንገድ እንዲከተሉ እንደዜጋም እንደ አማኝነቴም በታላቅ ትሕትና እጠይቃለሁ አመሰግናለሁ፡፡
Habtamu says
Tanks
samuel esayas says
Kalehiwoten yasmalen, yihe neger hulim yasasbgnal kidus sinodosm tebk wesani woseno liyawogzew yigebal. 10q