• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

እትጌ ጣይቱ ቫለንታይን ፍቅርና አድዋ

February 14, 2016 12:38 am by Editor 1 Comment

ይህን የያዝነውን የየካቲት ወር እኔ የምኖርበት ቀዬ ምዕራባውያን የጥቁሮች ወር በማለት ወሩን በሙሉ የሀገሩን ጥቁር ገድል ሲዘክሩ በወሩ አጋማሽ አንዱን ቀን ደግሞ የ(ሮማው ቅዱስ) ቫለንታይን በአል፣ በቫለንታይን ማግስት ደግሞ የቤተሰብ ቀንም ብለው ስራ ዘግተው ያከብራሉ። ቫለንታይን አሁን አሁን የፍቅረኞች በአል ቢባልም ሲጀመር ሰማዕቱ ቅዱስ ቫለንታይን የንጉሱ ህግ ለከለከላቸው ጋብቻን በማፈጣጠም፣ ለተከለከሉ ክርስቲያኖች ቃለ-እግዚአብሔርን በማስማት፣ የታመሙትን በመፈወስ ነው ታሪክ የሚያውቀው፤ ፊታውራሪ ገበየሁ አባጎራውንም የአምባላጌውን ጀግና የአድዋውን ሰማዕት ታሪክ የሚያውቀው “የአድዋ ስላሴን ጠላት አረከሰው ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው” እየተባለ ሲወሳለት ነው። የሁለቱም ሰማዕትነት ደግሞ ከውትድርና፣ ከተገፉ፣ ነፃነታቸውን ከተገፈፉ ሰዎች ጋር መያያዙ ነው። ካለፉት አስርት አመታት ጀምሮ በሀገራችንም ይሄ የቫለንታይን፣ የተውሶ በአል በህግ ባይደነገግም ይከበራልም፤ ይሸቀጣልም። መዋዋስ በአለም ያለ ስለሆነ ደግ ደጉን መዋስ ክፋት የለውም። ባይሆን ለእኛ እንደሚመች አድርጎ መዋስ ነው። እኛም እኮ ለአለም ቢያንስ ቡናን ጠንከር ካለም በእነ ድንቅነሽ (ሉሲ) ዘመንም እንደዛሬው እየተሰደድን ነበር ምድርን በሰው እንድትሞላ ያደረግነው። ህንድ የሚገኙ ዘመዶቻችን ሲዲዎችን፣ ሩሲያዊው ባለቅኔ ፑሽኪንንም ለአፍሪካም አሳማን ያበረከትን እኛ ነን። መዋዋስ ያለ ነው ለማለት ነው።

እኛም ታዲያ በሰማዕቱ ቅዱስ ቫለንታይን መንፈስ በሰማዕቱ ፊታውራሪ ገበየሁ አባጎራው መንፈስ የጥቁር የነፃነት መንፈስ – አድዋን ጣይቱን ፍቅርን አጣምረን እናወጋለን። የአድዋ ከብረት የጠነከረ መተሳሰብን፣ የአድዋ የፍቅር የነፃነት መንፈስን በጣይቱ እናያለን። ስለ ነፃነታችን ተምሳሌዎች ከዚህም በላይ ቢወራላቸውስ? እነሱ እኮ እንዲህ ባዮች ናቸው፤ ወዳጄ አለም በየነ ታዋቂው ብዕረኛ ሙሉጌታ ሉሌን ጠቅሶ እንደተረከልን “ከአድዋ ድል በኋላ መኳንንቱና ወታደሮቻቸው በንጉሠ ነገሥቱ ፊት በየተራ እየቆሙ በፉከራና በሽለላ አገሩን ያደባልቁት ነበር፡፡ ተራው የራስ መኮንን በሆነ ጊዜ ግን እንዲህ ብለው ተናገሩ፡፡ ‘ጃንሆይ ይህንን ድል የሰጠን ቸር ፈጣሪ ምናለ የልጅ ልጆቻችንን ጠላቶች ዛሬ በእጃችን ላይ ቢጥልልን? በነካ እጃችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አውድመንላቸው እናልፍ ነበር’፡፡” ከራሳቸው አልፈው የእኛንም ስራ ነበር ማቃለል የሚመኙት። መታደል ነው የነሱ ትውልድ መሆን። ማን ያገኘዋል?

በኦርጂናሉ የቫለንታይን መንፈስ የጥቁር የነፃነት መንፈስ – አድዋን ፍቅርን በእቴጌ ጣይቱ በአምባአላጌው ጀግና በአድዋው ሰማዕት ፊታውራሪ ገበየሁ አባጎራው እና በስመ ጥሩው ራስ መኮንን አውድ የፍቅርን የእርቅን ሀያልነት አጣምረን እንዘክራለን። ዋናው የዚህ ፅሁፍ ምንጭ የቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ የእቴጌ ጣይቱ የሕይወት ታሪክ ሲሆን፤ ቀኛዝማች ታደሰ የፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስንም ሕይወት ታሪክ ደርሰዋል። እነዚህ የቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ መጸሕፍት አስገራሚ ናቸው ሁላችሁም ከየትም ፈልጋችሁ አንቡ። ለምታገኙት እውቀት ዋቢ እሰጣለሁ።

አምባአላጌ – ገበየሁ- መኮንን

የታሪካችን መጻሕፍት እንደሚያስነብቡት የአድዋው ጦርነት ከመካሄዱ ጥቂት ቀደም ብሎ አላጌ ተራራ (አምባአላጌ) ላይ የመሸገውን የጠላትን ጠቅላላ የጦር አያያዝ ለመገመት በፊታውራሪ ገበየሁ አባ ጎራ የሚመራ 1200 የሚያህል ጦር የአምባአላጌን ዙሪያ አስሶ እንዲመለሥ በራስ መኮንን ታዘዘ። ጦሩ ተንቀሳቅሶ ከአምባው ተጠጋ የዚያን ጊዜ ከጣልያን ቃፊሮች ጋር ተገናኘ እና ተኩሥ ልውውጥ ሆነ። በሙሉ አምባው ላይ የነበረው የጣልያን ጦር ለውጊያ ተንቀሳቀሰ። የገበየሁ ጦር አምባውን ለመውጣት በሚሞክርበት ጊዜ የጣልያን ጦር ከላይ ወደ ታች ያጠቃ ጀመር።

የኢትዮጵያ ወታደር ከፊት ያለው ጓደኛው ሲወድቅ እራሱም እስኪወድቅ ድረስ ወደ ፊት እንጂ ወደ ኋላ አላለም። ሁኔታው ሲታይ የፊት መንገድ ብቻ እንጂ የኋላ መንገድ የሌለ ነበር የመሰለው። በእንዲህ አይነት ሁኔታ አርድ፣ አንቀጥቅጥ ውጊያ ነበር ኢትዮጵያውያኑ ከአምባው አናት ደርሰው የጨበጣ ውጊያ የጀመሩት። ለቅኝት የወጣው ጦር ፍልሚያ ገብቶ ጀግኖች እነ አባ ወርጂ እነ ጊድር አንገት ለአንገት ተናንቀው ተሰውተው ፊታውራሪ ገበየሁም ቆስለው የጣሊያንን የአምባ አላጌን ጦር ከነአዛዡ በመግደልና በምርኮ በድል አጠናቀቁ። ዝርዝሩን ላነበበ ዝርዝሩን ለሰማ ጉድ ያሰኘ የውጊያ ገድል ነበር ምኒልክ ሳይደርሱ፣ ዋናው ጦር ሳይደርስ፣ እቴጌ ጣይቱ ሳይደርሱ፣ ራስ መኮንን ሳይደርሱ የተፈፀመ የጦር ገድል። ይህ የአምባአላጌ ውጊያ ለኢትዮጵያውያን የድል ጉሽ፤ የምስራች ሲሆን ለወራሪው የነጭ ጦር ደግሞ ምልኪ ነበር። መጪውን የተነበየ ታላቅ ተጋድሎ። ቀጣዩን ኩነት ግን ዛሬ ሆነን ስናየው አስገራሚ ነበር። ዜናውና ጀብዱው በነራስ መኮንን ሰፈር ሲደርስ ለየት ያለ ነገር ተፈጠረ። ጀግናው ፊታውራሪ ገበየሁ ያለ ዋናው አዛዥ ራስ መኮንን ፈቃድ ጦርነት በመግባታቸው ወደ ማረፊያ ቤት ገቡ።

የፊታውራሪ ገበየሁ በራስ መኮንን መታሰር በሁለቱ የግንባር-ቀደሙ ጦር አዛዦች መካከል ቅሬታን ፈጥሯል ወደፊት ደግሞ የመቀሌና የአድዋ ጦርነቶች አሉ ቂም ተያይዞ ጦር ሜዳ ተሂዶ! እንዴት ይሆናል? በተለይ ደግሞ በእኛ በዛሬ እውቀት ማለትም የገበየሁን ማለፍ እና መኮንን እና ገበየሁ ሳይታረቁ ይቅር ለእግዚአብሔር ሳይባባሉ ቢያልፉ ኖሮ መኮንንም ቢሆኑ ፀፀቱም የሚለቃቸው አይመስልም። በተለይ ደግሞ ነገሩን ያወሳሰበው ሳታስፈቅድ ለምን ተዋጋህ? እስሩና የ”ለምን ታሰርኩ” ቅሬታው ከፊታውራሪ ገበየሁ የአምባ አላጌ ድል በሁዋላ መሆኑ ነበር። ነገሩን ይበልጥ ያወሳሰበው ደግሞ በጣሊያንና በአስካሪው ጦር ክፉኛ በተደጋጋሚ የተጎዳው እና የተመታው መንፈሱም የተሰበረው ለአድዋ ድል ወሳኝ ሚና የተጫወተው የትግራይ ነፍጠኛ ዘንድ ግርምታ ጉምጉምታ መፍጠሩና ጥያቄ ማጫሩ ነው። የማይሸነፈውን የጣሊያን ጦር ያሸነፈ መሸለም ሲገባው እንዴት ይታሰራል? የትኛው ብልሃት የትኛው የፍቅር መፍትሄ ይሆን የፊታውራሪ ገበየሁና የራስ መኮንን የግንባር-ቀደሙን ጦር አዛዦች ቅሬታ የሚፈታው? የፍቅር መፍትሄዋ እትጌ ጣይቱ ይሆኑ? እንዴት? በሰማዕቱ ቅዱስ ቫለንታይን መንፈስ የጥቁር ኩራትን – አድዋን ጣይቱን ፍቅርን የፍቅር መላ የፊታውራሪ ገበየሁና የራስ መኮንን እንዲሁም የትግራይን ጦር ያረጋጋ መፍትሄ ምን ነበር?

ቀጣዩ ትረካ በቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ የጣይቱ ብጡል የሕይወት ታሪክ መፅሐፍ (ገጽ 22-23) ላይ የተመረኮዘ ነው። እዚህ እልባት ጋር ይፈቀድልኝና አቶ ፍስሓ አጥላውን ላመስግን የቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ የጣይቱ ብጡል መፅሐፍን እንዳገኝ ስላደረገ።

የኢትዮጵያን ጦር ትግራይ ዘልቆ እንዳይገባ መክቶ ይይዛል የተባለው አምባአላጌ ላይ እርድ የሰራው ግምባር-ቀደሙ የጣሊያን ጦር በዋናው ሳይሆን በቃፊሩ የኢትዮጵያ ጦር ፍርክስክሱ ወጣ። ዜናውና ጀብዱው በዋናው ጦር አፄ ምኒልክ ሰፈር ሲደርስ ወዳጄ አለም እንዳወጋኝ ጦሩ አዘነ፤ ከፈረስ ወርዶም አለቀሰ አሉ። በድል ማግስት ለቅሶ፣ ጉዳዩ ወዲህ ነው። እዚህ ድረስ ተጉዘን መጥተን ሳንዋጋ ልንመለስ ነወይ ነው የሀዘኑ ምክንያት? ከጦርነቱ በሁዋላም ጀግናው ፊታውራሪ ገበየሁ ያለ ዋናው አዛዥ ራስ መኮንን ፈቃድ ጦርነት በመግባታቸው ወደ ማረፊያ ቤት ገቡ። ዜናው ጀብዱውም የገበየሁ መታሰር በእነ እቴጌ ጣይቱ ሰፈር ግን ችግር እንደፈጠረ ነው የታየው። በዚያ ዘመን ጣይቱም ምኒልክም ኢትዮጵያም ሙሉ ትኩረታቸው የነጩን የአውሮፓን ጦር በሙሉ ትኩረት በሙሉ መንፈስ በሙሉ ልብ በሙሉ ትጋት መርታትና ማባረር ነው። ይሄን የሚያደናቅፍ ምንም ነገር ትንሽም ሆነ ትልቅ በተለይ ጣይቱ ዘንድ የሚታለፍ አልነበረም። የአድዋ ድል አንዱ ማጠንጠኛም ይሄ ይመስለኛል። በዚያ ዘመንም ሆነ ዛሬም ሆነን ስናየው የፊታውራሪ ገበየሁ በራስ መኮንን መታሰር በሁለቱ የግንባር-ቀደሙ ጦር አዛዦች መካከል ቅሬታን ፈጥሯል። ቂም ተቋጥሯል። ይህንን ያለ ጣይቱ የፍቅር የእርቅ ጥበብ ማን ይፈታው ነበር? ይህንን ፀሐፌ ትዕዛዝ ገብረስላሴም መስክረዋል።

ቀኛዝማች ታደሰ ስለሁኔታው ሲገልፁ እንዲህ ይላሉ። “እትጌይቱ ባንድ በኩል ውጊያው ጠላትን ከትልቁ ጦርነት በፊት በማዳከም ረገድ የተወሰደ እርምጃ መሆኑን በመገንዘብ የፊታውራሪ ገበየሁን መፈታት በመሻት በሌላ በኩል በሁለቱ ባለ ስልጣኖች ቂም ምክንያት ሊከተል የሚችለውን ጥፋት በመገመት በአስታራቂነት በመቅረባቸው አስጊውን ሁኔታ በማስወገድ ይጠበቅ ለነበረው የአድዋ ጦርነት የህብረትና የትብብር ግንኙነት እንዲመሰረት አደረጉ።” ስለ ጉዳዩ ክብደት እና የጣይቱን የሀገር አደጋን፣ ጥልን፣ ፀብን በተደጋጋሚ የፍቅር ሀይል መቋጨት የራሳቸው ገለፃ ያልበቃቸው ቀኛዝማች ታደሰ የአፄ ምኒልክን የሰርክ ውሎና ታሪክ ፀሐፊን ፀሐፌ ትዕዛዝ ገብረ ስላሴን በዋቢነት በመጥቀስ እንዲህ ይላሉ “እቴጌ ጣይቱ በዚያ ወራት ያከናወኑትን ተግባር የተመረጠ ዠግና እንኳን ሊያጠናቅቀው እንደማይችል በመቁጠር አስተያየታቸውን ገልጸዋል”። ፍቅር የማያሸንፈው ነገር እዚህ አለም ላይ ምን አለ?

“እትጌ ጣይቱ” ይላሉ ቀኛዝማች ታደሰ “የጦር አበጋዙን ራስ መኮንንን ለጌታዬ የጦር ድግስ አላቆይም ብሎ ጠላቱን ተዋግቶ ድል ባደረገ ያሰርከው ድል ቢሆን ኖሮ ምን ልታደርገው ነበር?”

ራስ መኮንንም “ስለጦርነቱ በቅድሚያ ሳያማክሯቸውና ሳያስፈቅዷቸው መዋጋታቸውን በመቃወም እንዳሰሯቸው” ገለፁ።

“እትጌ ጣይቱ” ይላሉ ቀኛዝማች ታደሰ የተሰጣቸውን መልስን በመገምገም “እርሱ ሲዋጋ አንተ ጠላት ሲሰራው ለነበረው አጥር ጭቃ ታቀብል ኖሯል? ብለው የተግሳጽ ቃል ተናገሩዋቸው”። ፊታውራሪ ገበየሁም ተፈቱ።

“ጀግና እንደ ገበየሁ መሳሪያ እንደ ጎበዝ አየሁ” የተባለላቸው ፊታውራሪ ገበየሁ ድሮውንም ቢሆን የእቴጌን አስተዋይነት ፍትሕ ዐዋቂነት የሚያውቁትና የሚተማመኑት” ፊታውራሪ ገበየሁ ስለ ጉዳዩ በወቅቱ “የጌታዬን ጠላት [ደምስሼ] እንኳን ጣቶቼ በክር ታሰሩ እንጂ እኔንስ ነገ ጌታዬና እመቤቴ መጥተው ይፈቱኛል” አሉ ተብሎ ይነገራል። በዚህም “እትጌይቱ … በሁለቱ ባለ ስልጣኖች ቂም ምክንያት ሊከተል የሚችለውን ጥፋት በመገመት በአስታራቂነት በመቅረባቸው አስጊውን ሁኔታ በማስወገድ ይጠበቅ ለነበረው የአድዋ ጦርነት ሁለንተናዊ የህብረትና የትብብር ግንኙነት እንዲመሰረት አደረጉ”። የአድዋ ጦርነት ብዙ አስገራሚ ነገሮች አሉት። ወደፊትም ብዙ ይባልለታል። በዚህ ዘመንም ቢሆን ቫለንታይንን ፍቅርን ሰንቃ ጣይቱን የምትሆን ለኢትዮጵያ ታስፈልገናለች መቶ ሀያ አመት ሆነን እኮ። እናንተስ ምን ትላላችሁ?

መልካም የፍቅር ሰማዕታት ቀን!

አበቃሁ። (February 14, 2016)

ላስተያየታችሁ በዚህ ኢ-ጦማር አድራሻ ተጠቀሙ <danlinet@yahoo.com>

[Portrait of the Empress by. Georgios Prokopiou (1905)]

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Uncategorized Tagged With: Right Column - Primary Sidebar

Reader Interactions

Comments

  1. Nannte yimer says

    February 14, 2016 10:01 pm at 10:01 pm

    በእውነት በኢትዮጵያዊነቴ ኮራሁ !
    እውነትም ዲፕሎማስያዊ ቫለንታይን
    እናመሰግናለን ወንድማችን
    የጣይቱ ታሪክ እኮ አይጠገብም

    Reply

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • የሲኖዶሱ ውዝግብ አካሄድና መጪው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ February 6, 2023 02:03 am
  • የእሁዱ ሰላማዊ ሰልፍ ተራዘመ፤ ተጠባቂው ዕርቅ ፍንጭ እያሳየ ነው February 3, 2023 05:17 pm
  • የብላቴ: የውጊያ ማርሽ ቀያሪ ሠራዊት መፍለቂያ ማዕከል February 3, 2023 10:06 am
  • በኢትዮጵያ 27 በመቶ የሚሆነው የአእምሮ በሽተኛ ነው ተባለ February 3, 2023 09:47 am
  • “አስደንጋጭ”! 1 ሚሊዮን ከሚጠጋ ተፈታኝ ተማሪ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገባው 30 ሺህ (3.3%) ብቻ ነው  January 27, 2023 09:11 am
  • የማይዘነጋዉ የኢትዮጵያዊያኖች የጀግንነት ተጋድሎ ታሪክ፡- ኮሎኔል ባጫ ሁንዴ (ታጠቅ) January 27, 2023 06:12 am
  • ጎርጎራ – የመጻዒው ዘመን ሙሽራ! የዉበት ፈርጥ! January 17, 2023 04:18 pm
  • ሁለተኛው መስቀል አደባባይ January 17, 2023 04:13 pm
  • በአቡዳቢ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን January 17, 2023 04:08 pm
  • በንፋስ ስልክ ላፍቶ ስምንት የመሬት ሌቦች ተያዙ January 16, 2023 11:36 am
  • ሺሻ ሲያስጨሱ በተገኙ ሆቴሎችና የምሽት ጭፈራ ቤቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ January 16, 2023 08:50 am
  • በሐሰተኛ መታወቂያ የደኅንነት አባል ነን ብለው ሲያጭበረብሩ የነበሩ ተያዙ January 13, 2023 02:03 pm
  • ተሽከርካሪ ወንበር ለትግራይ – “ናይ ኣካል ጉዱኣት ተሽከርካሪ ዘለዎ ወንበር” January 12, 2023 07:17 pm
  • የአማራው ኩራት፣ የኢትዮጵያ ዘብ፣ የትህነግን ቅስም ሰባሪ! January 12, 2023 04:00 pm
  • በኢትዮጵያ ላይ የተጣሉ ማዕቀብ እና ሌሎች አስገዳጅ ሕጎች ሙሉ ለሙሉ ተሰረዙ January 12, 2023 01:52 pm
  • የቻይና ዕዳ ስረዛ “Payday Loan Diplomacy” ወይስ ኢትዮጵያን ያዳነ ተግባር? January 12, 2023 11:00 am
  • የአዲስ አበባ አስተዳደር ከቋንቋ ጋር በተያያዘ ውሳኔ አስተላለፈ January 12, 2023 10:46 am
  • “አምባሳደሩ” የቀድሞ ጌቶቻቸውን እንዲያቋቁሙ ተሾሙ January 11, 2023 03:47 pm
  • መከላከያ ሸኔን የሚዋጉ ሚሊሻዎችን አሠልጥኖ አስመረቀ January 10, 2023 05:37 pm
  • በሰባት ተጠርጣሪዎች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ January 10, 2023 03:36 pm
  • የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አቅጣጫ January 6, 2023 03:26 pm
  • “ከዕብሪቱ አስተንፍሰነዋል” – ኢሳያስ January 2, 2023 07:29 pm
  • [ኢትዮጵያን] “አስታክኮ ኤርትራን መውጋት ለሚፈልግ ኃይል አንተባበርም” January 2, 2023 07:11 pm
  • የ፰ ወር ሕጻንና ጨቅላ ወንዶች የሚደፈሩባት ትግራይ December 14, 2022 02:49 pm

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2023 · Goolgule