በአገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል መሥሪያ ቤት ላይ ኅብረተሰቡ የሚያሰማው እሮሮ ኤሌክትሪኩ መጥፋቱ ብቻ አይደለም፡፡ መብራቱ ሄዶ ሲመጣ የሚያደርሰው ጥፋት የትየለሌ ነው፡፡
የኤሌክትሪኩ ኃይል መጠን ከመደበኛው ውጭ ከፍና ዝቅ ሲል የሚያደርሰው ጥፋት ቤት ይቁጠረው፡፡ ማቀዝቀዣው፣ ቴሌቪዥኑ፣ አምፖሉ፣ ልዩ ልዩ “ቻርጀሮች” የተለያዩ ኤሌክትሮኒክስ ውጤቶች ተቃጠሉብን የሚል የሕዝብ እሮሮ በየጊዜው ይሰማል፡፡ የሚመለከተው መሥሪያ ቤት ፈጣን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ አገልግሎት የማይሰጠውን “905” ላይ ደውላችሁ አስመዝግቡ ከማለት ያለፈ መልስ የለውም፡፡ “የኤሌክትሪክ ምሰሶው ሊወድቅብን ነው፣ ዘሟል፣ ኧረ ድረሱልን” እያሉ ለሚወተውቱም ፈጣን ምላሽ መስጠት እንዳልተቻለም ማስረጃ ከሚሆኑ ትዕይንቶች (በፎቶዎቹ የሚታዩት) መካከል በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 እንደራሴ አካባቢ ያሉ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ለአደጋ መጋለጣቸው ነው፡፡ (በዚሁ ሰበብ በሳምንት ውስጥ የአካባቢው ኅብረተሰብ በርካታ የኤሌክትሮኒክስ ውጤቶቹ ከጥቅም ውጭ ሆነውበታል) ቀደም ሲል ለመውደቅ አስግቶ የነበረው ምሰሶ እንዲደግፈው የተተከለው ጉርድ መበስበሱን ተያይዞታል፡፡ ይህን ያዩት ሰፈርተኞች “ሙቅ በገንፎ ሲደገፍ” ብለውታል፡፡ ከራስ ሙሉጌታ መንገድ ወደ ካዛንቺስ ቶታል በሚያመራው መንገድ በስተቀኝ የቆመው የኢትዮ ቴሌኮም ምሰሶ ከዋናው ኤሌክትሪክ መስመር ላይ ተጋድሞበት ይታያል፡፡ የአካባቢው ነዋሪ ኧረ መላ በሉ ቢል ተቋማቱ ጆሮ ዳባ ብለዋል፡፡ “የፉክክር ቤት …” እንዲሉ፡፡ (ምንጭ: ሪፖርተር)
Leave a Reply