* እንደተለመደው ኢህአዴግ የድርቅ አደጋና የምግብ እጥረት ስጋት የለም እያለ ነው
ባለፉት ሁለት ወራት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተከሰተው የዝናብ እጥረት የድርቅ አደጋ እንዳይከሰት ስጋት የፈጠረ ሲሆን ግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ፤ የዝናብ እጥረት ቢኖርም የድርቅ አደጋና የምግብ እጥረት ስጋት የለም ብሏል፡፡
በአፋር ክልል ግን ሁኔታው ተባብሷል፡፡ በየቀኑ እስከ 100 የሚደርሱ ከብቶች በመኖና በውሃ እጥረት እየሞቱ መሆኑን ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡
የአፋር ክልልን አቋርጠው ወደ ጅቡቲ ወደብ ከሚጓዙ ሹፌሮች አንዱ ለአዲስ አድማስ እንደገለፀው፤ በመንገድ ዳርና ዳር በርካታ በጎችና ፍየሎች ሞተው ይታያሉ፡፡
በክልሉ ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር ጀምሮ እስካሁን ድረስ ዝናብ የጣለባቸው ቀናት በጣት የሚቆጠሩ መሆናቸውን የጠቆሙት ምንጮች፤ የድርቁ ሁኔታ እየተባባሰ ቢሆንም በመንግስት በኩል ፈጣን እርምጃ አልተወሰደም ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል። የግብርና ሚኒስቴር ግን በዚህ አይስማማም። የዝናብ እጥረቱ የፈጠረው ድርቅ በእንሰሳቱ ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ከክልሉ መንግስት ጋር በመቀናጀት የመጠጥ ውሃና መኖ በማቅረብ ላይ መሆኑን ጠቁሞ ከብቶች እየሞቱ ነው ስለሚባለው ግን መረጃው እንደሌለው ገልጿል፡፡
በክልሉ የተከሰተው ድርቅ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል አስፈላጊው ሁሉ እየተደረገ ነው ያሉት የሚኒስትሩ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ም/ኃላፊ አቶ ወንድሙ ፍላቴ፤ “ሀገሪቱ በቂና አስተማማኝ የአደጋ መከላከል ዝግጁነት አላት” ብለዋል፡፡
ምንጮቻችን እንደሚሉት፤ በተለይ በአማራ ክልል በወሎ እንዲሁም በሐረር አካባቢ በተከሰተው የዝናብ እጥረት የድርቅ ስጋት አንዣቧል፡፡
ዘንድሮ በአገሪቱ የሰሜንና ምስራቅ እንዲሁም መካከለኛ ክፍሎች በአየር ፀባይ ለውጥ (ኤሊኖ) የተነሳ የዝናብ እጥረት መፈጠሩን የጠቆመው ግብርና ሚኒስቴር፤ በሰኔና በሐምሌ ይጠበቅ የነበረው ዝናብ መቆራረጥ ቀድሞ የተዘሩ ሰብሎች እንዳይበቅሉ ቢያደርግም ከነሐሴ ጀምሮ መዝነብ መጀመሩንና ቀጣይነት እንደሚኖረውም ገልጿል፡፡
“ገበሬዎች ዝናብ ሲዘንብ ጠብቀው ውሃውን በማቆር ለሰብሎቻቸው እንዲጠቀሙ እየተደረገ ነው፤ የግብርና ልማት ጣቢያ ሰራተኞችም የወትሮው የግብርና ስራ እንዳይስተጓጎል ያልተቋረጠ ድጋፍ እያደረጉ ነው” ብለዋል ም/ኃላፊው፡፡
በአሁኑ ወቅት ግብርና ሚኒስቴር የዝናብ እጥረቱን መቋቋም የሚችሉ የድንች፣ ስንዴ፣ ማሽላ፣ ጤፍና የመሳሰሉ ሰብሎችን ምርጥ ዘር በማቅረብ ችግሩን ለመከላከል ጥረት እያደረገ መሆኑንም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ በተለይ የሰብል አምራች በሆኑ አካባቢዎች የተከሰተው የዝናብ እጥረት በቀጣይ ዓመት የሃገሪቱ የምርት አቅም ይቀንሳል፣ ረሃብም ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ምንጮቻችን የገለፁ ሲሆን ግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ፤ የተፈጥሮ ክስተቱ ፈታኝ ቢሆንም ሃገሪቱ በቂ የአደጋ መከላከል ዝግጁነት እንዳላት ጠቁሞ፣ በቂ ምርት ማግኘት እንደሚቻልና የምግብ እጥረት ስጋት እንደማይኖር አስታውቋል፡፡ (ምንጭ: አዲስ አድማስ)
Leave a Reply