የእንቅልፍ ምቀኛ
(ከዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ)
እወራረዳለሁ በአንድ ሚሊዮን ብር
ሸለብ ሲያደርግህ ነው ስልክህ የሚል ቅርርር!
ሚያዝያ 9፣ 2008 ዓ.ም. (አፕሪል 17፣ 2016 እ.ኤ.አ.)፤ ምንጭ፡- ፌስቡክ
ምላሽ ለዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ
ለንቅልፍህ አትሳሳ
ወለላዬ
ይከሰታል አዎን! ልክ ነህ ዶክተሬ
የት ይጠፋል ብለህ የሚል ፍቅሬ ፍቅሬ
ደግሞም ትክክል ነው እንዳተ ለሚጽፍ
በዚህ በአሁን ጊዜ ምን ይሠራል እንቅልፍ
ላገራችን ችግር ስላለው አበሳ
ካልተጻፈ በቀር በፍቅሬ ቶሎሳ
ማን ይመጣል ብለህ ሁሉም እኮ አለቁ
ካገሪቷ ጠፉ በሞት ተነጠቁ
ቢቻልማ ኖሮ እነሱን መቀስቀስ
እንኳን ስልክ ማጮህ ባናወጥነው በተኩስ
ቢነሳማ ኖሮ ስልክ በማንጫረር
በአሉን በጠራን ከዋጠችው ምድር
ባስነሳነው ነበር ፀጋዬን ከጉድጓድ
እንዲመለከተው የደረሰውን ጉድ
ምንለው ነበረን ለአቤ ጎበኛ
እንዴት እንደሆንን ባሁን ዘመን እኛ
ብንችልማ ኖሮ ማስነሳት ከንቅልፉ
ብዙ በነገርነው ለደበበ ሰይፉ
ቀና ብሎ ቢያየን ደወሉን ቢሰማ
ጉዳችንን ገልጸን ለመንግሥቱ ለማ
ባወራነው ነበር ሁሉንም ዘርዝረን
እኛኑ በሱ ዓይን መዝኖ እንዲጥፈን
አዲስ አለማየሁ በዛ ብዕራቸው
እንዴት እንደሆነች የአሁኗ ሀገራቸው
የደረሰብንን ውርደትና ውድቀት
በደወልን ነበር በዓይናቸው እንዲያዩት
ብዙ ደክመን ነበር ጀግኖችን ስንጠራ
አልጠቀመም እንጂ የስሙ ቆጠራ
ስለዚህ አንችልም ጸሐፍትን መቀስቀስ
አትተኛ እስካለህ ዶ/ር ፍቅሬ ተነስ
ወገንህ ሲታረድ እንዲህ በየቦታው
ሊመችህ አይችልም በፍጹም መኝታው
በሚደወል ቁጥር ከመኝታህ ንቃ
ለሀገሪቷ ችግር መቶም ፍቅሬ አይበቃ
ቀሰቀሱኝ ብለህ አይክፋህ በለሊት
በደሉን የሚጽፍ ህዝቡ ማን ይምጣለት
ጸጋዬ አይነሳም አራግፎ ያን አፈር
በአሉም አይመጣም ፈልቅቆ መቃብር
ደበበም አይገኝ አቤም አይነሳ
ግዴለም ወንድሜ ለንቅልፍህ አትሳሳ
እነዚህ ያልካቸው የንቅልፍ ምቀኞች
ሆነውስ እንደሆን የሞት ሰለባዎች
በደሉን ችግሩን ለማን ይናገሩ
ምን ልንሠራላቸው ለኛ ቢያንጫርሩ
እንቅልፉን ቀንሰን ከሠራን በጋራ
ማለፍ እንችላለን ይኼንን መከራ
አትተኛ ፍቅሬ አትተኛ ይቅር
ካለፉት ቀሪ ነህ ከጥንቶቹ ድምር
በደወሉ ቁጥር ብዕርህን አንሳ
የዘለዓለሙ አለ ለንቅልፍህ አትሳሳ።
***
ሚያዝያ 11፣ 2008 ዓ.ም. (አፕሪል 19፣ 2016 እ.ኤ.አ.)
Leave a Reply