
ኢትዮጵያ ወደ ፍጹም ህብረት! Towards a Perfect Union! ቀን 1/27/20
የኢትዮጵያ ጣምራ ፌደራሊዝም ተቋም የመጀመሪያ ሰሚናሩን አጠናቀቀ!
የኢትዮጵያ ጣምራ ፌደራሊዝም ተቋም (DFIE Dual Federalism Institute for Ethiopia) በ January 18, 2020, በኢትዮጵያ ኤምባሲ አዳራሽ ውስጥ ክቡር አምባሳደር ፍጹም አረጋን ጨምሮ የተለያዩ የፖለቲካና ሲቪክ ድርጅት ተወካዮችና ምሁራን በተገኙበት የአንድ ቀን ሙሉ ሰሚናር አድርጓል።
በዚህ ሰሚናር ላይ ለኢትዮጵያ ተብሎ የተዘጋጀውን አዲስ ቅርጸ መንግስት (Government Structure) አስተዋውቋል። ይህ አዲስ ቅርጸ መንግስት የኢትዮጵያ ጣምራ ፌደራሊዝም ይሰኛል። በዚሁ እለት የኢትዮጵያውያንን ህብረት ታሪካዊ ጉዞ በመገምገም ህብረታችንን ወደ ፍጹም ህብረት ሊያደርስ ይችላል በተባለው በዚሁ በጣምራ ፌደራሊዝም እሳቤ ዙሪያ ሰፊ ገለጻና ውይይት ተደርጓል። ኢትዮጵያ ያለፈችባቸው የሃገረ መንግስት ግንባታ (Nation Building) ሂደቶች በጥልቀት ተገምግመዋል። በዚሁ መሰረት ከምስለት ጀምሮ “ኢትዮጵያ ትቅደም!” ከዚያም “ብሄር ይቅደም!” ከዚያም አፍርሶ ማነጽ (deconstruct identities in order to construct identities) የተከተልናቸው የህብረታችን ወይም የሃገረ መንግስት ግንባታ ጥበቦቻችን ሲሆኑ እነዚህ ጥበቦቻችን በሙሉ ችግሮች ያሉባቸውና ህብረታችንን የሚፈታተኑ አደጋዎች እንደሆኑ ተገልጿል።
ስለሆነም ኢትዮጵያ በሀገር ግንባታ ሂደቷ ኣዲስ የተሻለ ሃገረ መንግስት የማነጽ መንገድ ልትከተል እንደሚገባ በተቋሙ መሪዎች በአጽኖት ተገልጿል። ስለሆነም ጣምራ ፌደራሊዝም እስከዛሬ የሄድንባቸውን መንገዶች አሻሽሎ ማንነቶችን አጣምሮ ብዝሃነትን የሚያስተናግድ ዘዴ እንደሆነ በጥልቀት ትንታኔ ተሰጥቶበታል። የጣምራ ፌደራሊዝምን አደረጃጀት በሚመለከት ሲገለጽ ጣምራ ፌደራሊዝም የጣምራ ፌደራል ስቴት ግንባታ እንደሆነ ተተንትኗል። ጣምራ ፌደራሊዝም ማለት “የብሄር ባህላዊ ፌደራል ስቴትና የዜግነት ፌደራል ስቴት በመመስረት እነዚህን ሁለት ስቴቶች በሃገራዊ ኪዳን ስር በማጣመር በራሳቸው ምህዋር ላይ እየዞሩ ብዝሃነትን ጠብቀው ለጋራው በጎነታችን (common good) የሚሰሩበት ቅርጸ መንግስት ማለት ነው!“ ሲሉ የጥናት ወረቀት አቅራቢዎች የጣምራ ፌደራሊዝምን ብያኔ አስረድተዋል::
ጣምራ ፌደራሊዝም የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታዎች፣ ታሪክ፣ የፖለቲካ ጥያቄዎችና ብዝሃነትን ያገናዘበ ሁነኛ ቅርጸ መንግስት መሆኑ ተብራርቷል። ይህ ተቋም ዓላማው ይህ ሃገር በቀል ቅርጸ መንግስት ብሄራዊ ፍኖተ ካርታ ሆኖ የፖለቲካ ሃይላትና መላው ኢትዮጵያዊ ተስማምቶበት ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት መጫወቻ ሜዳ እንዲሆን ብሎም ጣምራ ፌደራሊዝም ብዝሃነትንና ዴሞክራሲን ለማስተናገድ ምቹ የሆነ ስርዓት ስለሆነ ሃገራችን ይህንን ስርዓት ተክላ በፍጥነት ወደ ዴሞክራሲና ልማት እንድታመልጥ ነው። በዚህ ስብሰባ ወቅት አሁን ያለው የፌደራል ስርዓት ያሉት ህጸጾች በጥልቀት ተገልጸዋል። ባህልና ፖለቲካን አደባልቆ መኖር ችግሮቹ ብዙ እንደሆኑ በአንክሮት ተገልጿል። ባህል ከፖለቲካ ተለይቶ ለሃገር ሁለንተናዊ እድገት የራሱን ሚና መጫወት እንዳለበት በሰፊው ትንታኔ ተሰጥቶበታል።
በመጨረሻም የጣምራ ፌደራሊዝም ተቋም ንቅናቄ ዓላማ ህብረታችንን በጣምራ ፌደራሊዝም ስርዓት ወደ ፍጹም ህብረት ማሳደግ ነው ተብሏል። የተቋሙ መስራቾች ሲናገሩ በአሁኑ ወቅት ያለው የኢትዮጵያውያን ህብረት ፍጹምነት የጎደለው በመሆኑ ህብረታችን ፈራሽ ሳይሆን ፍጹምና ዘላለማዊ ሆኖ በሌላ በኩል ደግሞ ብዝሃነትን የሚያስተናግድ እንዲሆን ኢትዮጵያ ጣምራ ፌደራሊዝም ስርዓትን መትከል እንደሚገባት ምክር ቀርቧል። ኢትዮጵያ በዚህ ኣዲስ የፌደራል ስርዓት አማካኝነት ወደ ፍጹም ህብረት ልታድግ ይገባል ተብሏል። ተሰብሳቢዎች በቡድን በቡድን እየሆኑ በእሳቤው ላይ በስፋት የተወያዩ ሲሆን ገንቢ ሃሳቦችን ሰጥተዋል። በቀውጢ ወቅት የደረሰ ችግር ፈቺ ነው የተባለው ይህ ሃገር በቀል የፌደራል ስርዓት ወይም ቅርጸ መንግስት እሳቤ ወደፊት ተከታታይ ውይይቶች ተደርገውበት ብሄራዊ ፍኖተ ካርታ እንዲሆን ጥረት እንደሚደረግ የጣምራ ፌደራሊዝም ተቋም መሪዎች እስረድተዋል። ኢትዮጵያ ካሉባት ስርዓታዊ ችግሮች ዘ-ጸዓት አውጃ ከችግሮቿ ልትወጣ እንደሚገባ አቋም ተወስዷል።
በመጨረሻም የጣምራ ፌደራሊዝም ዓላማው ተሳክቶ፣ ኢትዮጵያ ይህንን ስርዓት ተክላ፣ የስርዓት ችግሮቿን እድትፈታ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የሲቪክ ድርጅቶች፣ ምሁራንና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፉን እንዲቸር ተጠይቋል።
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣበ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Leave a Reply