አቶ ዠ ደብዳቤ ጻፉ። 40 አመት ሙሉ መፈክር ሲጽፉ ኖረው፣ ኖረው፣ ኖረው አሁን አርቲስት ለመሆን የሚያበቃውን ዝግጅት የጨረሱ መስሎ ተሰማቸው። ሰሞኑን ለወጣው ማስታወቂያ “ብቁ ነኝ” ብለው አሰቡ።
ይድረሥ፣ ለ“ኢሃዲግ ፍቅር” ቴአትር ቤት “ሥራ አስቀማጭ”፣ ይቅርታ በቀድሞ ሥሙ የሃገር ፍቅር ቴአትር ቤት በመባል ለሚታወቀው … ሥራ አስኪያጅ፣
ጉዳዩ፣ በ 23/2/2008 የወጣውን ማስታወቂያ አስመልክቶ፣ ከታች እንደሚታየው፣ የተለያዩ ኪነጥበባዊ ሥራዎችን ለማቅረብ “ልማታዊ” ፍላጎትን ሥለመግለጽ።
የወጣውን ማስታወቂያ አስታኮ የተለያዩ ልማታዊ ኪነጥበባዊ ሥራዎችን ለማቅረብ 40 አመታት ሙሉ ተዘጋጅቻለሁ፣ ብቃት ያለኝም ነኝ። ከዚህ ኪነጥበባዊ ሥራ የሚገኘው ገቢም በከፊል ለታላቁ “ውዳሴ” ግድብ ቦንዳ (ይቅርታ “ቦንድ”) መግዣ እንዲውል ለመስማማት በገዛ ፍላጎቴ እገደዳለሁ። ይቅርታ ህዳሴ ማለቴ ነው። እኔ ዠ “ግድቡ ገና ሳይጀመር እራሳችሁን ለማወደስ ትጠቀሙበታላችሁ፣ ማለቁን እስኪ ለማየት ‘ገብረ እግዚሃብሄር’ ያብቃን” ብዬ በመጻፍ አልሳሳትም።
እነዚህ ኪነጥበባዊ ሥራዎቼን ለመከተብ የምጠቀምባቸው እስክሪብቶዎች ከዶማ ባለተናነሰ ወረቀቴን እየቆፈሩ ልማታዊ አርቲስት ለመሆን መነሳሳቴን ይመሰክራሉ ብል መንግሥታችን “ጣምራ ዲጂት እድገት አስመዘገብኩ” እንደሚለው አይነት መልካም ምኞት እንጂ አንዳንድ ኢ-ልማታዊ አሸባሪዎች እንደሚያቀርቡት ለዛ ቢስ ትችት እንደማይታይብኝ የሥራ አስቀማጭነትዎ የሰላ አይምሮ አይስተውም ብዬ ልጽፍ አልደፍርም።
ከውዳሴው ግድብ ተጨማሪ ስለሴቶች ተጠቃሚነትም ለመጻፍም ልማታዊ ምኞቴ ነው። መንግስታችን ሴቶች እህቶቻችንና እራሱን ተጠቃሚ ለማድረግ ልማታዊ ፈቃዱ በመሆኑ እልፍ አእላፍ ሴቶች ወደየአረብ ሃገራት እንዲሄዱና የእነዚህን ሃገራት ጓዳዎች እንዲያለሙ “መንገዱን ጨርቅ ያርግላችሁ” ብሏል። እነዚህ የሚሄዱት ሴቶች ደግሞ ድሆች በመሆናቸው በሌላ መልኩ መንግስታችን ድህነትን ለመቅረፍ የተጠቀመበት፣ በጣም የታሰበበት የተራቀቀ የGrowth and Transformation Plan – GTP እንጂ የGet out and Transform to slave Plan ተሰደጂና ባሪያ ሁኝ ስትራተጂ አለመሆኑን ለነዚህ ኢ-ልማታዊ አርቲስቶች ማን በነገራቸው? ክቡር ሥራ አስቀማጭነትዎ እንደሚገነዘቡት ለዚህ ነው የመፈክር መጻፊያ ብዕሬን ወደ ኪነጥበባዊ ብዕር ለመቀየር የተነሳሳሁት።
ደግሞ፣ ልማታዊው መንግሥታችን ወጣቶችን ተጠቃሚ አርቲስት ለማድረግ ከፍተኛ እቅድ በመያዙ ለምሳሌ ያክል ድንጋይ መልካም ቅርጽ እንዲኖረው በመጥረብ ኮብል ስቶን እንዲያነጥፉ ቤቶችን በማፈራረስ ጎዳናዎችን አዘጋጅቷል። እንግዲህ ይህ ጥበባዊ ሥራ ነው። እነማይክል አንጀሎ ድንጋይ በመጥረብ አይደለም እንዴ ታዋቂ የሆኑትና ጣልያንን ገናና ያደረጉት?
በሌላ መልኩ ደግሞ መንግስታችን ገደላ ገደል፣ በረሃ ሳይፈራ የባቡርና የመኪና መንገድ እያስፋፋ ነው። ክቡር ሥራ አስቀማጭነትዎ ደብዳቤዬን ከማጠቃለሌ በፊት አንድ የባቡር ሃዲድ ታሪክ ታሪክ ልጻፍልዎ።
ሃዲዱ የሺምላ ካልካ የባቡር ሃዲድ ነው። ህንድ ውስጥ የሚገኝ፣ በእንግሊዞች የተሰራ። ደልሂ ከተማን ከሂማልያ ተራሮች እግር የሚያገናኝ የባቡር ሃዲድ። ይህ ሃዲድ ሲዘረጋ እጅግ አስቸጋሪ ነበር። ተራሮችን ሰርስሮ መሿለኪያ መሥራት ያስፈልግ ነበር። ከሁሉም ረጅሙ መሿለኪያ 1143 ሜትር ይረዝማል።
ይህንን መሿለኪያ(tunnel)የቀየሰው የእንግሊዝ መሃንዲስ ባሮግ ይባላል። ኢንጂነር ባሮግ ሥራውን በቶሎ ለማጠናቀቅ ይረዳው ዘንድ ተራራው በሁለት በኩል እንዲቦረቦር ያቅዳል። እቅዱም ከሁለት አቅጣጫ መሿለኪያዎች ሲቦረቡሩ መሃል ላይ ይገጣጠማሉ የሚል ነበር። ሆኖም ግን ቅያሱ ትንሽ ስህተት ስለነበረበት ከሁለት አቅጣጫ የተቦረቦሩት መሿለኪያዎች እንደታቀደው ሳይገናኙ ቀሩ። በዚህ የተናደደው የብሪታንያ መንግሥት ኢንጂነር ባሮግን አንድ ሩፒ ቀጣው። ሩፒ የህንድ ገንዘብ ነው።የተጣለበትን ሃላፊነት አለመወጣቱን የተገነዘበውና ይህ ፕሮፌሽናል ሥህተት ያበሣጨው ኢንጂነር ባሮግ ደግሞ እራሱን ገደለ። ዛሬ ያ መሿለኪያ የባሮግ መሿለኪያ – Barog Tunnel በመባል ይታወቃል።
እንግዲህ እንደዚህ ያሉ ትላልቅ ፕሮጄክቶችን፣ ለምሳሌ የሥኳር ፋብሪካዎችን፣ የሚወጥነው ልማታዊው መንግሥታችን፣ ብዙ ገንዘብ አፍስሶ ውጥኑ ሳይሳካለት ቢቀር እራሱን ያጥፋ የሚል አመለካከት ያላቸው ኢ-ልማታዊ የሆኑ፣ ጥቂት ግለሰቦች ሊኖሩ ይችላሉና በልማታዊ ብዕር ልንዋጋቸው ይገባል ባይ ነኝ።
ፊርማ
ዠ
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply