በቡራዩ ብር የማይሰጥ አገልግሎት አያገኝም
በአዲስ አበባ ዙሪያና ውስጥ የባዶ መሬትና የኮንዶሚኒየም ቤቶች ገበያ ደርቷል። በርካቶች እንደሚሉት ይህ የደራ ገበያ ምሥጢር ባለመሆኑ ከከንቲባ ታከለ ኡማ አስተዳደር የተሰወረ አይደለም። ምን አልባትም የአዲስ አበባ መሬትና የኮንዶሚኒየም ቤቶች የጠራራ ጸሃይ ገበያና የባለቀንነት ሽሚያ፣ በማኅበራዊ ጉዳዮች ባላቸው ተሳትፎ ሰፊ ተቀባይነት ላላቸው ታከለ ኡማ ጉዞ ጋሬጣ እንዳይሆንባቸው የሚፈሩም አሉ። በተመሳሳይ በቡራዩ ነዋሪዎች ከመሬት ጋር በተያያዘ ሰፊ ቅሬታ ያሰማሉ። በቡራዩ ብር የማይጠበቅበት አገልግሎት እንደሌለም አመልክተዋል።
የአየር ጤና ነዋሪ መሆናቸውን የገለጹ ለጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ እንዳስታወቁት ለውጡን ተከትሎ በርካታ ቦታዎች ታጥረውና ሳይታጠሩ ባለቤት አልባ ሆነዋል። እንደ እነሱ ገለጻ ባለቤቶቻቸው ጠፍተዋል፣ ተሸሽገዋል፣ ወይም በፍርሃቻ ቀን እየጠበቁ ነው፤ አለያም ህጋዊ ሰነድ ያልነበራቸው ነበሩ።
በዚሁ መነሻ ማንነታቸው የማይታወቁ ሰዎች ባለቤት አልባ የሆኑትን ቦታዎች እያጠሩ፣ የታጠረም ከሆነ እየወረሱ ከክፍለከተማ አመራሮች ጋር በመመሳጠር የግል እያደረጓቸው ነው። በዚህ አግባብ በርካታ እንግዳ የሆኑ አዳዲስ ሰዎችና ደላሎች ተደራራቢ መሬት እየወሰዱ መሆናቸውን ነው ነዋሪዎቹ የሚናገሩት።
የባዶ መሬት ንግድና ወረራ በሚገርም ደረጃ መጧጧፉን የሚገልጹት ነዋሪዎች ድርጊቱ የቡድን መልክ እንዳለውም ጠቁመዋል። የቀደሙት ጥለው ሲሄዱ የአሁኖቹ እየተረከቡ ነው። ለመቆጣጠርና ለማስቆም የሚሞክር አካልም አይታየም። እንደ ጥቆማ ሰጪዎቹ ከሆነ የመሬት መቀራመቱና ንግዱ የሚከናወነው በአደባባይ ነው።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአዲስ አበባ አስተዳደር የመካከለኛ እርከን ሠራተኛ “ዓለም ባንክ፣ አየር ጤና፣ ቤቴልና ዙሪያውን እንዲሁም ወደ ቃሊቲ መሬት የመቀራመት ጉዳይ አለ። ይታወቃል። ችግሩ ሥራው የሚሠራው በቡድን መሆኑ ነው። አስተዳደሩ ቁርጥ አቋም ሊወስድ ይገባል” ሲሉ የውሳኔ ሰጪው አካል ድክመት እንዳለ አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ 40/60 መርሃ ግብር ገንዘብ ቆጥበው የኮንዶሚኒየም ቤት የደረሳቸውና በመጠባበቅ ላይ ያሉ ምሬት እያሰሙ ነው። እኒህ ዜጎች ከዕለት ጉሮሮ ቀንሰው በቆጠቡት ገንዘብ የተገነባን ቤት ኃላፊነት የጎደላቸው ወገኖች አላግባብ በመመሪያ እያከፋፈሉት መሆኑንን ይናገራሉ። “ለማን አቤት እንበል?” የሚሉት ወገኖች ደላሎች የአሳዛኙ ድራማ ዋና ተዋንያን መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ እንደሰማው ዕጣ እንዳይወጣባቸው የተደረጉት የኮንዶሚኒየም ቤቶች ምንም እንኳን ለሽግግሩ ወቅት ለሚመደቡ ኃላፊዎች እንደ መጠባበቂያ ማስቀመጡ አግባብ ቢሆንም አሁን እየታየ ያለው ተግባር ግን አሳፋሪ ሆኖባቸዋል።
“በመመሪያ፣ በደብዳቤና በቃል ይታዘዛል” የሚሉት እነዚህ ክፍሎች “ጉዳዩን የሚያስፈጽሙት ደላሎች ናቸው። ካስፈጸሙና የቤቱ ዝውውር ካለቀ በኋላ አየር በአየር የሚያገበያዩትም እነሱው ናቸው። ይህ ዓይነቱ ንግድ በግልጽ የሚታይ ሆኖ ሳለ እርምጃ የሚወስድና የሚያስተካክል አካል መጥፋቱ ደግሞ ከሁሉም ጉዳዩን አሳዛኝ ያደርገዋል” ሲሉ ጥቆማ ሰጪዎች ያስረዳሉ።
ይህንኑ ከሚያስፈጽሙት መካከል አንዳንድ የክፍለ ከተማ አመራሮች በዚሁ በትዕዛዝ በሚከናወን የቤት ሽሚያ መሰላቸታቸውን ተመዝግበው፣ ገንዘብ ቆጥበው፣ ወረፋ ጠብቀው፣ ዕጣ ደርሷቸው እየተንከራተቱ ያሉ ለአቤቱታ ቢሯቸው በሄዱበት ወቅት እንደገለጹላቸው አስረድተዋል።
ዕጣ ከወጣላቸው በኋላ ቤታቸውን እንዳይረከቡ የተደረጉት ዜጎች ጉዳይ ምንም እልባት ሳያገኝ መቆየቱ ብቻ ሳይሆን ከስር ከስር ቤቶቹ ለሌላ አካል እየተዘዋወሩ መሆኑ ከሕግም ሆነ ከሞራል አንጻር የኢንጂነር ታከለ ኡማን አመራር እያደር ተጠያቂ ማድረጉ እንደማይቀር የደራውን ንግድ የሚከታተሉ እየገለጹ ነው። በድሆች ላይ እየተከናወነ ያለውን ዘረፋ እያዩ ዝም ማለት ለታከለ ኡማም ሆነ በዙሪያቸው ላሉ ደላሎች ስለማይጠቅም ከዛ በፊት ነገሮችን ቢያጸዱ እንደሚሻልም እነዚሁ ክፍሎች መክረዋል።
በአዲስ አበባ መሬት መቀራመትና በውድ ዋጋ ማስተላለፍን በተመለከት አፍ ውስጥ የገቡ ኃላፊዎች ጉዳይ ምርመራ እየተደረገበት እንደሆነ፣ አንዳንዶችም በአካል ተጠርተው ቢመከሩም ሊሰሙ አለመቻላቸው የጎልጉል የመረጃ ሰዎች ተናግረዋል።
በሹመት ወደ አዲስ አበባ መምጣቷን የምትገልጽ አንዲት ሴት፣ የተሰጣትን የኮንዶሚኒየም ቤት ሸጣለች። ሽያጩን ያከናወኑትና የፈጸሙት ደላሎች ናቸው። ሽያጩ ከተጠናቀቀ በኋላ “አሁን ቤት ሸጠሽ የት ትኖሪያለሽ?” በሚል ስትጠየቅ “ሌላ እወስዳለሁ። እንደገና እወስዳለሁ” ማለቷን ምስክሮች ለጎልጉል አመልክተዋል።
አርቲስቶች፣ ጋዜጠኞች፣ ከክልል የሚመጡ ባለሥልጣናት የኮንዶሚኒየም ቤቶችን እንዲወስዱ መመሪያ የሚሰጥ ሲሆን፣ መመሪያ ሰጪዎቹ አብረው አየር በአየር ደላሎቹ በሚያቀርቡት መሠረት የቤት ዕደላውና የአየር በአየር ንግዱ ፈር የለቀቀበት ደረጃ ደርሷል። የቁጠባ ደብተር ይዘው፣ ከገቢያቸው ቆጥበውና ዕጣ ደርሷቸው የሚጠብቁ ወገኖች ወደኋላ ተብለው ደላሎች ቤታቸውን እንዲቸበችቡት እየተደረገ ነው።
መረጃ አቅራቢዎቹ የደላሎቹን ስምና እስከ አዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ ቢሮ ድረስ እጃቸው ረዥም የሆኑትን ወገኖች በስም፣ በሰፈርና በግንኙነት ደረጃ ለይተው ለጎልጉል አስታውቀዋል። ከፍተኛ የሚባሉት የአስተዳደሩ ሰው የሸጡትን ስፍራም ለይተው አስታውቀዋል። ይሁን እንጂ ጎልጉል ለጊዜው ከማተም ተቆጥቧል። በተለይም ከከንቲባው ቢሮ ጋር ትሥሥር ፈጥረው እየሠሩ ያሉትን ደላሎች በተመለከተ ጎልጉል በቂ መረጃ የሰበሰበ ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱ ይፋ ያደርጋል። ይህ አዲስ አበባን ሊደፋ የተነሳው የደላላ ኃይል ላይ ክትትልና መረጃ ተሰብስቦ መጠናቀቁን ጎልጉል ስለሚያውቅ የመንግሥትን የክትትል ሥራ ላለማበላሸት ነው ማንነትን ጠቅሰን ለማተም ያለውደድነው። ይሁን እንጂ አዲስ አበባ ላይ ተራ ጮሌነት የትም እንደማያደርስ ጎልጉል ለማስታወቅ ይወዳል።
በተመሳሳይ ዜና በቡራዩ ከመሬት ጋር በተያያዘ ካርታ ለማውጣት፣ ለማደስና የይዞታ ማረጋገጫ ለመውሰድ በግልጽ ገንዘብ የሚጠየቅ መሆኑንን ነዋሪዎች ለጎልጉል አስታውቀዋል። ነዋሪዎች እንደሚሉት ብር የማይሰጥ አገልግሎት አያገኝም። ገንዘብ የሚጠየቀውም በግልጽ በአደባባይ ነው።
ለየአገልግሎት ዓይነቱ የተቀመጠ የገንዘብ መጠን መኖሩን የሚናገሩት ወገኖች፣ መንግሥትንና ሕዝብን የሚያቃቅሩት እንዲህ ያሉ ዜጎች በመሆናቸው የኦሮሚያ ክልል ቢያስብበት ሲሉ ጥቆማቸውን አቅርበዋል። የኦሮሚያ ክልል የበታች መዋቅሩን ባስቸኳይ ማስተካከል እንዳለበት በተደጋጋሚ አስተያየት ይሰጣል።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።
golgul-aba-gora says
እንዲህ ስትሉ ምን ማለታችሁ ይሆን?
“ከፍተኛ የሚባሉት የአስተዳደሩ ሰው የሸጡትን ስፍራም ለይተው አስታውቀዋል። ይሁን እንጂ ጎልጉል ለጊዜው ከማተም ተቆጥቧል። በተለይም ከከንቲባው ቢሮ ጋር ትሥሥር ፈጥረው እየሠሩ ያሉትን ደላሎች በተመለከተ ጎልጉል በቂ መረጃ የሰበሰበ ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱ ይፋ ያደርጋ”
ለመሆኑ ጊዜ ካለፈ በኋላ “ይፋ” ልታወጡት ነው መረጃውን ወይስ “በመረጃው” ጥራትና አስተማማኝነት አላመናችሁበትም? ወይስ “መረጃው” በማስረጃ ያልተደገፈ ነው? በትኖሩበት የምዕራብ አገራት ምን እንደሚደረግ የምታውቁ ናችሁ፤ እንዲህ ዓይነት በማስረጃ የተደገፈ “መረጃ” ልፖሊስ/አቃቤ ሕግ/ ፓርላማ ወይም አግባብ ባለው ሚንስት/ባለሥልጣን/ኮሚሽን/ኤጀንሲ የኦዲትና ፖሊሲ አስፈፃሚ አክል ይተላለፋል፤ ታልሆነም የታክለ ዑማ ያለመመረጥ – ምርጫ ታለ ለዛውም – ዕድልን ማስፋቱ ይሆናል ያሳሰባችሁ፤ በደል ከሚደርስበት ዜጋ በላይ፤ ለነዚህ ዜጎች ስትሉ እባካችሁ “ይፋ” ባታደርጉትም የሰበሰባችሁትን “መረጃ” ለሚመለከተው ክፍል አስተላልፉ፤
ደሞ እንዲህ ተባልን ብላችሁ አትበሳጩ መልዕቱን እንጂ መልዕከተኛው ተዉት – ተወዲህ ለማሳሰብ ያህል
Editor says
በጽሁፉ ውስጥ የተጠቀሰውን በትክክል ወይም በጽሞና ባለማንበብ የተሰጠ አስተያየት ነው፤ ዜናው ላይ ይህንን ብለናል፤
” . . . ይህ አዲስ አበባን ሊደፋ የተነሳው የደላላ ኃይል ላይ ክትትልና መረጃ ተሰብስቦ መጠናቀቁን ጎልጉል ስለሚያውቅ የመንግሥትን የክትትል ሥራ ላለማበላሸት ነው ማንነትን ጠቅሰን ለማተም ያለውደድነው። . . .”
የጎልጉል አርታኢ
golgul-aba-gora says
ለመጨመር ያህል፤ “መረጃ” ደርሶኛ ወይም ሰብስቤያለሁ ግን ይፋ አላደርገውም ማለት፤ አንድ – ወንጀል ሲሠራ አይቶ እንድማለፍ ያለ የዜግነትና ሕጋዊ ግዴታን አለመወጣት ነው፤ ሁለተኛ – ጠፋጥኞችን ተጠንቀቁ የሚል ደወል እንደ ማሰማት ነው፤ ማንኛውንም የገንዘብ ይዞታቸውን፤ የተጭበረበሩ ዶኪውመንቶቻቸውን፤ የግንኙነት መረባቸውን እንዲሰውሩ፤ ምናልባትም ራሳቸውን እንዲሰውሩ ማንቂያ ይሆናል፤ ትክክለኛው አሠራር የመረጃ ዶሴያችሁን ለፖሊስ ወይ ዐቃቤ ሕግ መጀመሪያ አቅርባችሁ ከሚከተለው ምርመራን ወይም የክሥ ሂደትን በማይጣረስ ብኩል ዜናው ማቅረብ ነው፤ ያንጊዜ መረጃ አለን ይፋ አናደርግም ሳይሆን መረጃውን ቀደም ብለን ለሚመለከተው ክፍል አስተላልፈናል ትሉና አንባቢም ያደንቅችሁአል፤
Editor says
በጽሁፉ ውስጥ የተጠቀሰውን በትክክል ወይም በጽሞና ባለማንበብ የተሰጠ አስተያየት ነው፤ ዜናው ላይ ይህንን ብለናል፤
” . . . ይህ አዲስ አበባን ሊደፋ የተነሳው የደላላ ኃይል ላይ ክትትልና መረጃ ተሰብስቦ መጠናቀቁን ጎልጉል ስለሚያውቅ የመንግሥትን የክትትል ሥራ ላለማበላሸት ነው ማንነትን ጠቅሰን ለማተም ያለውደድነው። . . .”
የጎልጉል አርታኢ
wakeup says
The following website is one
of the most trustworthy
alternative media world
wide.Read it to know about
the Covid and other deadly
vaccines.
http://www.globalresearch.ca/theme/science-and-medicine