የአገር ጉዳይ ለጥቂቶች የሚተው አይደለም፤ አያገባህም ሊል ወይም ሊባል የሚገባው ዜጋ የለም። እያንዳንዱ በቻለው መጠን አሳቡን ማካፈልና ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር መትጋት አለበት። መንግሥት የሕዝቡ አካልና አገልጋይ እንደመሆኑ ዜጎች ተሳትፎአቸው እንዳይገታ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ግዴታው ነው። አሁን የሚታየው አዝማሚያ እጅግ አሳሳቢ ነው። ሕዝብና መንግሥት፣ ሕዝብና ሕዝብ፣ መሪዎች ተፈራርተዋል። መተማመን አቅቷቸዋል። አይመለከተኝም ማለት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። የተለያየ ዓላማ ያነገቡ ቡድኖች ከየአቅጣጫው መንቀሳቀሳቸው ነገሮችን አወሳስቦአቸዋል። እነዚሁ ቀጥተኛ ዓላማቸውን ማስረዳት ሆነ እርስ በርስ መስማማት አልቻሉም። አንዳንዶችም ሁሉን ጠርገን አስወግደን አዲስ አሠራር እንመሠርታለን የሚሉ ናቸው። በስድሳ ስድስት እና በሰማንያ ሦስት ማግሥት ያየነውን ስንፍና መድገም ብቻ ሳይሆን ለባዕድ መንግሥታት መፈንጫ ልንሆን ጫፍ ላይ ደርሰናል። መስማማትና መተማመን ስለጠፋ በስድሳ ስድስት የተበተብነውን ከሁለት ትውልድ በኋላም መፍታት አልተቻለንም። አዲስ ተስፋ ጠበቅን፤ ፍርኃትና ሥጋት አተረፍን።
ገዥው ፓርቲ ብቻ ነው ትክክል ማለት ሌላው ስሕተት ነው፤ ፓርቲው አገሪቱን በመምራት ረገድ ለሃያ አምስት ዓመታት በብልሹ አስተዳደር መታመሱንና መፍትሔ እንዳጣለት ራሱ እየነገረን ነው። ሥራ አጥነት፣ ስደት፣ በጉልበተኛ ከቀዬ መፈናቀል፣ ብቃት ኖሮአቸው በአሳብ ያልተስማሙ ዜጎች መገፋትና መገለል፣ የኑሮ ውድነት፣ ረሓብ፣ ፍርኃት፣ ወዘተ ተደማምረው እስካሁን የተጀመሩትን መልካም የልማት እንቅስቃሴዎች ውጤት አደብዝዘውታል። የሚሠራጩትን ዜናዎችና ምንጮቹን፣ የተጋነኑ ዐይን ያወጡ ውሸቶችና ዘገባዎችን በጥንቃቄ ማጣራት የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ የሚሆነው ለዚህ ነው።
ለገዥው ፓርቲ ቅርበት ካላቸው ዋነኛው ሪፖርተር ጋዜጣ ረቡዕ ሐምሌ 25/2008 አገራችን የገባችበትን ማጥ በ“ርዕሰ አንቀጽ”፣ በ“ፖለቲካ” እና በ“ዜና” ዓምዶቹ ሥር አስፍሮታል። በርዕሰ አንቀጹ፦ ሕገወጥነት ሲሰፍን ዜጋ ሀብት የማፍራት፣ የመሰለውን አመለካከት የማራመድ መብቱን ያጣል፣ አምባገነንነትና “ፀረ ዲሞክራቲክ” ድርጊቶች ይበዛሉ፣ ወዘተ፤ የሕግ የበላይነት ሲኖር ማንም ከሕግ በላይ አይሆንም። አሁን የሚታየው ግን ሕግ አውጭና አስከባሪው ክፍል ሕግ የማይገዛው ሆኗል። ተቃዋሚው በንብረት ላይ “መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ውድመት አድርሷል፤” ስለዚህ “የሕግ የበላይነትን የሚጋፉ ድርጊቶች ይወገዱ” ብሏል። ሪፖርተር ውድመቱ የትና መቸ፣ ምን ዓይነትና በማን እንደሆነ ማስረጃ አላቀረበም። ጋዜጣው እየጠፋ ያለውን የሰው ሕይወት ከነአንካቴው አልጠቀሰም። በ “ፓለቲካ” ዓምዱ፦ የሕዝባዊ ተቃውሞ መነሻው ብልሹ አስተዳደር እንደሆነ ገዥው ፓርቲ ተገንዝቦታል። ብልሹ አስተዳደር ሲል፦ ሥልጣን በመጠቀም የሕዝብን ንብረት መዝረፍ፣ ከድሃ ነጥቆ ለባለሃብቱ መስጠት [ደርግ ከባለሃብቱ ነጥቆ ለደሃው እንደሰጠ ሁሉ]፤ ብቃት የሌላቸው ከገዥው ፓርቲ ጋር በሥጋና በወረት በመዛመድ ቁልፍ የኃላፊነት ቦታ ላይ መቀመጣቸው፣ ላደረሱት ጉዳት አለመጠየቃቸው፤ “ፈጣን ልማት” ሕዝቡን ያላሳተፈ ብቻ ሳይሆን የሕዝቡ ጉዳት የልማት አንድ ገጽታው ነው መባሉ፤ ኢንቬስተሮችን ከማስቀየም ሕዝብ ነገ ኑሮው እንዲሻሻል የዛሬውን ጉዳቱን ጥርሱን ነክሶ መቻል አለበት መባሉ ነው። ብልሹ አስተዳደር ደግሞ በክልል መስተዳደሮች መካከልና፣ በክልል መስተዳደሮችና በመንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት ይመለከታል። ሪፖርተር ጋዜጣ ባለሙያዎችን አነጋግሮ ሲዘግብ፣ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት የጎንደርን ድንበር መግፋቱ ያስከተለውን ግጭት በምሳሌነት ጠቅሷል። የአማራን ክልላዊ መንግሥት ሳይጨምር፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሳይላክ፣ ወደ ትግራይ ክልላዊ መንግሥት ጉዳዩን መምራት ችግሩን እያባባሰው ነው ብሏል። በ“ዜና” ዓምዱ፦ “ሁሉም የፀጥታ ኃይሎች የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብሩ” በገዥው ፓርቲ መታዘዛቸውን ጠቅሷል። በጦር ኃይል “የሕግ የበላይነትን ማስከበር” በተግባር ሲተረጎም ምን ማለት እንደሆነ ሳያብራራ አልፎታል። ትእዛዙ ግን በብዙዎች ዘንድ ሥጋት፣ ግራ መጋባትና ቁጣ አስነስቶአል።
ችግሩ ከምንሰማው እጅግ የከፋ ነው። የከፋው ዛሬ ከሚታየው በላይ ገና ለትውልድ የሚተርፍ አሣር መቋጠሩ ላይ ነው። ገዥው ፓርቲ ብቻውን መፍትሔ ማምጣት እንደማይቻለው ግልጽ ሆኗል። በአመራሩ ላይ አመኔታ ያጡትን፣ ለአገር በጎ አሳብና ብቃት ያላቸውን ዜጎችና ዜጋ ድርጅቶችን ሳያካትት ለማኅበራዊ/አገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ያስገኘ አንድም መንግሥት የለም። በዚህ ወቅትና ከዚህም በፊት የጠፋው መፍትሔ ሳይሆን ቅንነት ነው። የጠፋው ትኅትናና ርኅራኄ ነው። ሕዝብና መንግሥት ተፈራርተዋል። ጭከና፣ ራስ ወዳድነትና ማናለብኝ ባይነት በርትቷል። አፄ ኃይለሥላሴ፣ “ሕዝባቸው” በረሓብ ሲያልቅ ያስጨነቃቸው በዓለም መንግሥታት ፊት የሚዋረደው ክብራቸው ነበር። ራስ እምሩ ስለ መሬት ይዞታና መልካም አስተዳደር መሻሻል እርምጃ እንዲወሰድ በጊዜ መክረው የሚሰማቸው አላገኙም። ንጉሡ ዙፋናቸው እንደማይገረሰስ፣ በእግዚአብሔርና በታማኝ ሎሌዎቻቸው እና በኃያሏ አሜሪካ ተማመኑ። ታማኝ ሎሌዎችም ንጉሡ ሊሰሙ የሚፈልጉትን ብቻ ነገሯቸው። ሹመት እንዳያሳጣቸው ሊሰሙ የማይፈልጉትን አልነገሯቸውም። ደሃው ተረሳ ያሉ ተማሪዎች “ቁንጥጫ ያላዩ ልጆች” ተብለው በልምጭ ተገረፉ፤ አንዳንዶች ወደ ካምፕ ተወሰዱ፤ ከነዚህም አንዳንዶቹ አሁን አገር የሚመሩት ናቸው። ሌሎቹ ወንበዴ፣ ሽብር ፈጣሪዎች፣ ሽፍቶች፣ የአረብ ቅጥረኞች ተባሉ። በቀውጢዋ ሰዓት አሜሪካ ጥላ ፈረጠጠች፣ የሶማልያ ደጋፊ ሆና ተገለጠች። የፍትኅ አምላክ ነውና እግዚአብሔር ለተገፋው በየነ። በሰዓቱ ቢደረግ ኖሮ መፍትሔው ቀላል በሆነ ነበር፤ ምን ያደርጋል ታዲያ? ሰዓቲቱ ተላለፈች፤ ሁሉንም አሳለፈች።
ደርግ፦ በታሪካዊ ሂደት፣ በፓርቲውና በአመራሩ ቆራጥነት ድል ተቀዳጀሁ አለ። ለሕዝቡ ኢኮኖሚውንና ዲሞክራሲያዊ መብቱን ላላ እናድርግለት፣ ከተቃዋሚ ኃይላት ጋር ፖለቲካዊ ስምምነቶችን እንፍጠር፣ እንደዚህ መቀጠል አይቻልም ያሉ ነበሩ። ቆይቶ ሕዝቡን ዲሞክራሲ እናለማምደው ተባለ። በየአዳራሹ ስብሰባ ተጠራ። ፓርቲው አስቀድሞ በመረጣቸው ላይ ጠቋሚዎች ተመደቡ። ሕዝባዊ ምርጫ ተካሄደ ተባለ፣ ተጨበጨበ። የአብዮቱን ድሎች የሚያወሩ እንጂ ያፈጠጠውን እውነታ የሚክዱ ባለሥልጣናት በዙ። ሥልጣን አስክሯቸው ነበር። የደፈሩ ታሰሩ፣ የምክራቸውን ፍሬ ሳያዩ ተመነጠሩ። በራዦች፣ ሽፍቶች፣ ሽብር ፈጣሪዎች፣ አድኃሪዎች፣ አብዮትና ልማት ቀልባሾች ተባሉ። “የስታሊን በትር”፣ የጦር ኃይላችን፣ ቆራጥ መሪያችን፣ የሶቭየት አጋርነት ካሉልን ምንም አንሆንም አሉ። “እናሸንፋለን” “ተፈጥሮን እንቆጣጠራለን” “ረሓብ የለም፣ የጠላት ወሬ ነው” “ጃፓንን እናክላለን” “ኢኮኖሚአችን በዕመርታ ላይ ዕመርታ አሳየ” “ከፓርቲውና ከዙፋኑ በላይ የለም” “ከቆራጡ መሪያችንና ከፓርቲያችን ጋር ወደፊት” አሉ። በጭንቅ ሰዓት ሶቭየቶች ፈረጠጡ። እግዚኦታ። እግዚአብሔር! እግዚአብሔር! በሉ መጣ። ያ ኃያል የጦር ሠራዊት በአንድ ጀንበር ተበተነ። መፍትሔው ግን ቀላል ነበረ። ምን ያደርጋል ታዲያ? ትኅትናና ቅንነት ስለ ጠፋ መልካካሙ ከአጥፊው ጋር ጠፋ። ብልሹ አስተዳደር ይህን ይመስላል፦ ስለራሱ የተሳሳተ አስተያይ አለው፤ ማንም አያርመኝም፣ እግዚአብሔርም እንኳ አይተካኝም ማለት ይቃጣዋል።
ይኸን መሳይ ታሪክ በቅርቡ በሊብያና በግብጽ፤ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በጀርመን፤ ጥንት በግሪኮች አገር ተፈጽሟል። ይኸ ነገር አያዋጣም ያሉ ተገፉ እንጂ አልተደመጡም። ዕድሜአቸውን ለማራዘም አመራራቸውን በቤተሰብ አደራጁ። ያም ከአደጋ አላዳናቸውም። ችግሩን ማስቀረት ሲቻል መሪና አገር አብረው ተማገዱ። ሕይወት መንገዷ መንታ ነው። አንደኛው የሰላም፣ ሌላኛው የጠብ መንገድ ነው። አንደኛው ቅርብ አዳሪ፣ ሌላኛው ሩቅ አሳቢ ነው። አንደኛው ራስ ወዳድ፣ ሌላው ቸርና አምላክ ፈሪ፣ ሕዝብ አክባሪ ነው። ለአገርና ለሕዝብ ቆምን ያሉ እንዴት እርስበርስ አንዱ ሌላኛውን ለማስወገድ እንደተሠለፉ ማየት የሚያሳፍር ባሕል ነው። መሪዎች ሕዝቡን በእስርና በረሓብ በሥራ አጥነት የጦርነት ሰለባ በማድረግ እንዳገላቱ ማየት የሚያምም ነገር ነው። ሳያስፈልግ፣ አማራጭ ሳይጠፋ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ከአብራኩ የወጡ ሲፈራረቁበት፣ ከባዕዳን ጋር ተባብረው ሲፋለሙ አክብሮት ሲነሡት ሥቃዩን ችሎ ቂም ሳይይዝ አምላኩን እየጠራ ኖሯል። ብርሃነመስቀል ረዳ፣ ኃይሌ ፊዳና ሠናዬ ልኬ ቢስማሙ ኖሮ …? አፄ ኃይለሥላሴ ምክር ሰምተው ቢሆን ኖሮ…? ደርግ ምክር ሰምቶ ቢሆን ኖሮ…? የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዚህ ሁሉ አሣር ባልተዳረገ! ስንት ነው ያለቀው ትውልድ? የወደመውስ ንብረት? ስንቱ ነው ዕድሜውን በከንቱ የፈጀ? ሳያስፈግ፣ አማራጭ ሳይጠፋ። ስንቱ ለአገር ስንት ማድረግ ሲችል በስደት በፍርኃት በእስር በስድብ ናዳ በውንጀላ ተተብትቦ መና ቀረ? በሦስት ትውልድ፣ በአገር ደረጃ ከተጠቀምነው ይልቅ ጉዳታችን በብዙ እጥፍ በልጧል።
ምክር መቀበል ትኅትናን ይጠይቃል። የረጅሙን ውጤት ማሰብን፣ ለአገር መስዋዕት መክፈልን ይጠይቃል። የግብጹ ሳዳት አንድ ብቸኛ ምሳሌ ትተውልናል። ሳዳት ከእስራኤል ጋር የማያልቅ ጠብ ለአገራቸው እንዳልበጀ ተረዱ። ሶቭየቶችን መተማመን ሶቭየቶች ከአሜሪካ ጋር ላላቸው ቅራኔ መረማመጃ ከመሆን ውጭ ፋይዳው ብዙ እንዳልሆነ ተረዱ። በወቅቱ የማይታሰብ፣ ማንም የማይደፍረውን እርምጃ ወሰዱ፤ በ1971 ዓ.ም. ከእስራኤል ጋር እርቀ ሰላም ተፈራረሙ። በተፈራረሙ በሁለተኛው ዓመት በእላማውያን ጥይት ተገደሉ። የፈረሙት የሰላሙ ውል ግን ፍሬው እስከ ዛሬ ዘልቋል።
የጠቃቀስናቸውን ታሪኮች መካድ ራስን ማታለልና ከታሪክ አለመማር ነው። ትኅትናና ቅንነት ማጣት ነው። ከዘጠና ሚሊዮን ኢትዮጵያዊ መሓል አንድ አስተዋይ የሚታመን የሚደመጥ መሪ እንዴት ይታጣ? ቤተክርስቲያን አዳኟንና መሪዋን ዘንግታ፣ ተልዕኮዋን ስታ፣ መንታ አሳብ ባላቸው መሪዎቿ የማያዘልቅ የሁለት ጎዳና ጉዞ ተያይዛለች።
“ጥበብን ማግኘት ምንኛ ከወርቅ ይሻላል! ማስተዋልንም ማግኘት ከብር ይልቅ የሚመረጥ ነው። የቅኖች መንገድ ከክፋት መራቅ ነው፤ መንገዱን የሚጠብቅ ነፍሱን ይጠብቃታል። ትዕቢት ጥፋትን፥ ኵሩ መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል። ከዕቡያን ጋር ምርኮ ከመካፈል ከትሑታን ጋር በተዋረደ መንፈስ መሆን ይሻላል። ቃልን የሚያዳምጥ መልካም ነገርን ያገኛል፤ በእግዚአብሔር የታመነ ምስጉን ነው” [ምሳሌ 16፡16-20]።
የሮብዓም ታሪክ
“ኢዮርብዓምና የእስራኤል ጉባኤ ሁሉ መጥተው ለሮብዓም። አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር፤ አሁንም አንተ ጽኑውን የአባትህን አገዛዝ፥ በላያችንም የጫነውን የከበደውን ቀንበር አቃልልልን፤ እኛም እንገዛልሃለን ብለው ተናገሩት። እርሱም። ሂዱ፥ በሦስተኛውም ቀን ወደ እኔ ተመለሱ አላቸው። ሕዝቡም ሄዱ። ንጉሡም ሮብዓም። ለዚህ ሕዝብ እመልስለት ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድር ነው? ብሎ አባቱ ሰሎሞን በሕይወቱ ሳለ በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ሽማግሌዎች ጋር ተማከረ። እነርሱም። ለዚህ ሕዝብ አሁን ባሪያ ብትሆን ብትገዛላቸውም፥ መልሰህም በገርነት ብትናገራቸው፥ በዘመኑ ሁሉ ባሪያዎች ይሆኑልሃል ብለው ተናገሩት። እርሱ ግን ሽማግሌዎች የመከሩትን ምክር ትቶ ከእርሱ ጋር ካደጉትና በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ብላቴኖች ጋር ተማከረ። እርሱም። አባትህ የጫኑብንን ቀንበር አቃልልልን ለሚሉኝ ሕዝብ እመልስላቸው ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድር ነው? አላቸው። ከእርሱም ጋር ያደጉት ብላቴኖች። አባትህ ቀንበር አክብዶብናል፥ አንተ ግን አቃልልልን ለሚሉህ ሕዝብ። ታናሺቱ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች። አሁንም አባቴ ከባድ ቀንበር ጭኖባችኋል፥ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችኋል፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ በላቸው ብለው ተናገሩት። ንጉሡም። በሦስተኛው ቀን ወደ እኔ ተመለሱ ብሎ እንደ ተናገረ ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ሁሉ በሦስተኛው ቀን ወደ ሮብዓም መጡ። ንጉሡም ሽማግሌዎች የመከሩትን ምክር ትቶ ለሕዝቡ ጽኑ ምላሽ መለሰላቸው። እንደ ብላቴኖችም ምክር። አባቴ ቀንበር አክብዶባችሁ ነበር፥ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ ብሎ ተናገራቸው። እግዚአብሔርም በሴሎናዊው በአኪያ አድርጎ ለናባጥ ልጅ ለኢዮርብዓም የተናገረውን ነገር እንዲያጸና ከእግዚአብሔር ዘንድ ተመድቦ ነበርና ንጉሡ ሕዝቡን አልሰማም” [1ኛ ነገሥት 12፡3-15]። አማካሪስ አልጠፋም ነበር፤ የአስተዋይ መሪ መጥፋት ግን ቀላሉን ነገር አወሳሰበው፤ ውጤቱ ሰልፍና በአንድ ሕዝብ መሓል መለያየት ሆነ [ከቁጥር 16-33 ይመልከቱ]።
ፈርኃ እግዚአብሔር የሌላቸው፤ ለሰው ርኅራኄ የላቸው፣ ጨካኞችና ራስ ወዳዶች ናቸው።
“ነገር ግን በክፉ ልባቸው አሳብና እልከኝነት ሄዱ ወደ ፊትም ሳይሆን ወደ ኋላቸው ሄዱ እንጂ አልሰሙም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም” [ኤርምያስ 7፡24]። ሰነፍ በልቡ። አምላክ የለም ይላል። በሥራቸው ረከሱ፥ ጐስቈሉ፤ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም። የሚያስተውል እግዚአብሔርንም የሚፈልግ እንዳለ ያይ ዘንድ፤ እግዚአብሔር ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ። ሁሉ ዐመፁ በአንድነትም ረከሱ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም፤ አንድም ስንኳ የለም። ጕሮሮአቸው የተከፈተ መቃብር ነው፥ በምላሳቸው ሸነገሉ፤ ከከንፈራቸው በታች የእባብ መርዝ አለ፤ አፋቸው መርገምንና መራራን ተሞልቶአል፤ ደምን ለማፍሰስ እግራቸው ፈጣን ነው፤ ጥፋትና ጕስቍልና በመንገዳቸው አለ፥ የሰላምን መንገድ አላወቁአትምና፤ እግዚአብሔርን መፍራት በዓይናቸው ፊት የለም። ሕዝቤን እንደ እንጀራ የሚበሉ ኃጢአት የሚሠሩ ሁሉ በውኑ አያውቁምን? እግዚአብሔርንም አይጠሩትም[መዝሙረ ዳዊት 14፡1-7]።
ታዲያ መፍትሔው ምንድነው? መፍትሔው ከመሪዎች ጀምሮ “እግዚኦ መሓረነ ክርስቶስ!” ማለት ነው [ሌሎች የእምነት ክፍሎችም እንደዚሁ በራሳቸው መንገድ]። ለሰላም ሲባል በኢትዮጵያ አንድነት ጥላ ሥር መሰባሰብ ነው። ኃይል ተጠቅሞ ሕዝብን መምራት የትም እንደማያደርስ ቶሎ መገንዘብና ለአገራቸው በጎ የሚያስቡ አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ማመቻቸት፤ ከሁሉም በላይ መተማመንና ሰላም የሚፈጥሩ እርምጃዎችን መውሰድ፦ የታሠሩትን መፍታት። ሕዝቡ ከቀዬው ላይ እንዳይፈናቀል ዋስትና መስጠት። የሕዝብ ንብረት የዘረፉትን ፍርድ ፊት ማቅረብ። የሕዝብን ብሶት ችላ አለማለት፤ አመጽ ነው ብሎ አለመናቅ። አለመተማመንን ዘርቶ መተማመንን ማጨድ ከቶውን አይቻልም። የዜጎች መገደል በመቶ ሺዎች ቅራኔ እንደሚመነዘር መረዳት [ሟች ወንድም እህት፣ አባት እናት አያቶች ጓደኞች ባል ሚስት የሠፈር ልጆች አክስት አጎት ከነቤተሰቦቻቸው ቤተሰቦቻቸው ከነቤተሰቦቻቸው፣ ወዘተ አላቸው]። የሕዝብን ተቃውሞ በሰላም ሳይሆን በኃይል ማስቆም መሞከር የሚከዳ አሸዋ ላይ እንደመቆም እንደሆነ አለመዘንጋት። ሬሳ በተከመረ ቁጥር አሸዋው እየከዳ ቋሚውን ያሰጥመዋል።
ዛሬም ዕድሉ ያመልጠን ይሆን? ወይስ አምላክ ማስተዋል ሰጥቶን ከማጡ እናመልጣለን? የቀረበልን ምርጫ ግልጽና ቀላል ነው፦ ከጠብ እንራቅ። ከዕብሪተኛነት እንራቅ። ከጭከና እንራቅ። የሰላምን መንገድ እንምረጥ፤ የትኅትናን መንገድ እንምረጥ። የርኅራኄን መንገድ እንምረጥ። እግዚኦታ የሚያስፈልገው አሁን ነው። እግዚኦ! እንበል። እግዚአብሔር ይርዳን። (ጽሁፉን ከነፎቶው እንድናትምላቸው የላኩልን)
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Sisay says
የዚህ ጽሑፍ ደራሲ ማነው?
Sisay says
ውድ ጎልጉል፣
ይቅርታ ሊንኩን አገኘሁት። ጽሑፉ ከ5 አመት በፊት የተጻፈ ቢሆንም የምንገኝበትን ቁልጭ አርጎታል! ቢሆንም የደራሲውን ስም ጨምሩ።