ጭቃ እያቦካ ጭቃ እየለወሰ
ጭቃ እየጋገረ ጭቃ እየጎረሰ
ያረፈደው አያ
ከጭቃው ገበያ
ያውና ብቅ አለ ከጭድ መሃል ወጣ
በጨመለቅ እጁ ሊጨብጠኝ መጣ።
‘መቼም ከጭቃ ነው ተፈጥሮ ስሪቴ’
ብዬ እንዳልጨብጠው ‘እምቢኝ!’ አለኝ ቤቴ
“ጭቃማ አይደለሁም!
_ ነኝ እንጂ ውብ ሸክላ
ታሽቶና ተቦክቶ በውቅ የተኮላ
ይታጠብ በቅድሚያ አቅርብለት ውሃ
ለጨቀየው ነፍሱ በነገር ቤት ዝሃ”
ብሎ ይሞግተኛል ተላላው መንፈሴ
ውሃውን ረስቼ ጭቃን በማንገሴ
እነሆኝ በል እንካ አንተ ጭቃ ለዋሽ
ኮዳዬን ዘቀዘቅኩ ለእድፍህ አባሽ።
የመንፃት ቀንህን አታርቀው ጓዴ
ውሃዬን ተጠቀም ላፍስልህ ላንዴ
ከዚያም ልጨብጥህ ደርሳለሁ ዘመዴ
ጭቃ እያቦካ ጭቃ እየለወሰ
ጭቃ እየጋገረ ጭቃ እየጎረሰ
ስንቱ ሰው መሰለህ ደግሞ የታደሰ
ከመቡካት በኋላ ውበት የለበሰ።
Leave a Reply