ስደተኞች ወደኢትዮጵያ የሚልኩት ጠገራ ብር ብዙ እንደሆነ አውቃለሁ፤ አንዳንድ ስደተኞች ለእንደኔ ያለ ወገኖቻቸው በብዙ መንገድ እርዳታ እንደሚያበረክቱ አውቃለሁ፤ በአንጻሩም አንዳንድ ስደተኞች ትንሽ ጠገራ ብር ይዘው መጥተው የሀኪም ቤትና ሌላም ዓይነት የንግድ ድርጅት (ሀኪም ቤቱን ከንግድ ጋር ያገናኘሁት አውቄ ነው) እያቋቋሙ ደሀውን የኢትዮጵያ ሕዝብ እየገፈፉ የሚከብሩም እንዳሉ አውቃለሁ፤ ስደተኞች በአጠቃላይ ለአገራቸውና ለወገናቸው መብት በፖሊቲካው መስክ የሚያደርጉትን ትልቅ አስተዋጽኦ አውቃለሁ፤ ይህም ሁሉ ሆኖ የሚከነክነኝ ነገር አለ፡፡
ለእኔ ዜግነት ማለት የአገር ባለቤትነት ነው፤ የአገር ባለቤትነት መብቶችንና ግዴታዎችን ያጎናጽፋል፤ አንድ ሰው ስደተኛ ሲሆን የተወለደበትን አገር ባለቤትነት ከነመብቶቹና ግዴታዎቹ በፈቃዱ ትቶ ለሌላ አገር የሚያስረክብ ይመስለኛል፤ እዚህ ላይ የሕግ ጨለማ ውስጥ እንደገባሁ ይሰማኛል፤ አንደኛ ስደተኞች ሁሉ በድሎት አልወጡም፤ ሁለተኛ ስደተኞች ሁሉ ዜግነታቸውን በወጉ አልለወጡም፤ ብዙ ስደተኞች ለአገራቸውና ለወገናቸው ያላቸው የፍቅር ስሜት ገና አልደበዘዘም፤ ይህ ሁሉ እውነት ቢሆንም አንዳንድ ስደተኞች ሀብት የማግኘት ትንሽ ፍንጭ ሲያዩ ከአገራቸው የተሰደዱበት ፍርሃትና ስጋት፣ ለአገዛዙ ካላቸው ጥላቻ ጋር ሙልጭ ብሎ ከውስጣቸው ይወጣና ያላቸውን ቀርቅበው ወደአገር ቤት ይመጣሉ፤ በአገዛዙ በኩል ስለሚፈጥሩት ቁርኝት ምንም መናገር አልፈልግም፡፡
ሌላ በአንዳንድ ስደተኞች ላይ የሚታይ ከስግብግብነት የባሰ ራስ-ወዳድነትና ብልጣብልጥነት አለ፤ ቤት ወይም ትንሽ መሬት በስማቸው ያለ ወላጆች ሲሞቱ ለቀብር ያልተገኙት ስደተኞች ንብረት ለመካፈል ከተፍ ይላሉ! አገር ቤት ሆነው ደፋ ቀና እያሉ ወላጆቻቸውን ያስታመሙትን እኅቶቻቸውንና ወንድሞቻቸውን፣ ሌሎች ዘመዶቻቸውንም እየገፉ እነሱ ባለቤት ለመሆን የሚጥሩ አይቻለሁ፤ እነዚህ ግዴታቸውን ሳይወጡ ባለመብት ለመሆን የሚጥሩ ስደተኞች በሌላ መልክ ማየት እንገደዳለን፤ አገር ውስጥ ሆነው እየተቸገሩና እየደከሙ ያስታመሙ ሰዎች ሩቅ አገር ኖረው ዘር ቆጥረው ከሚመጡ ስደተኞች ጋር እኩል ይካፈሉ ማለት ፍርደ-ገምድልነት ይመስለኛል፡፡
ስደት ጮሌነትን ብቻ የሚያስተምራቸው ሰዎች ወገናቸውን ይጎዳሉ፤ ተጠንቅቀን ልናስተናግዳቸው ይገባል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁሉ እንደሞኝ ባላገር የሚመለከቱትን መክቶ መቋቋም ያሻል፤ በተጨማሪም ለወገኖቻቸው ብዙ ጥሩ ሥራ የሚሠሩትን ስደተኞች የሚያጎድፉ ናቸውና ለይተን ልናውቃቸው ይገባል፡፡
ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም
የካቲት 2009
Leave a Reply