በስራው ላይ ልፈላሰፍ
ቅኔ ልቀኝ ግጥም ልጽፍ
ቸኩያለሁ አልሞት ብሎኝ
የማደንቀው ሰው ነበረኝ
ሳይሞትማ ሳይቀበር
ስሙን ማንሳት እሱን ማክበር
መስሎ ታይቶኝ ልምድን መስበር
የማደንቀው ሰው እያለኝ
ልጽፍለት ተቸገርኩኝ
አቤት! ዕውቀት አይ! ቁመና
ብልህ ደፋር ቆራጥ ጀግና
ሀይማኖቱን አጠንካሪ
ደግ ለጋስ ሰው አክባሪ
ብዬ ልለው ቸኩያለሁ
አልሞት ብሎኝ ታሞ እያየሁ
ዛሬ ቢያጣ ዛሬ ቢርበው
በቁም ሆኖ ከምረዳው
ከማከብረው ከማደንቀው
እደርሳለሁ ሲሞትልኝ
ከምድር በታች ሲውልልኝ
ያንጊዜ ነው ስሙ ገኖ
የሚነሳው እሱን ሆኖ
የብዕር ጫፍ የሚመዘዝ
እንባ የሚረጭ የሚተከዝ
ሚጻፍለት ሚደነቀው
ታሪክ ገኖ ሚነበበው
ገንዘብ ከኪስ ሚመዘዘው
ለሟች በድን አካሉ ነው
ያን አይቼ ልምድ አብቶኝ
የቆየ ወግ አንቆ ይዞኝ
የማደንቀው ሰው እያለኝ
እንዳላደንቅ አልሞት አለኝ
ማስታውሻነቱ ለሀገራችን ላሉና ለነበሩ እውቅና ታላላቅ ሰዎች ይሁን።
Leave a Reply