ሰላም ጤና ይስጥልኝ አንባቢያን እንደምን አላችሁ? ይሄውላችሁ እንደምታውቁት ጥቂት ከማይባል ዓመታት ወዲህ ቀድሞ ከነበረን የሥነ-ኪናችን አትኩሮት በተለየ መልኩ አልፎ አልፎ ብቅ ከሚሉ አንዳንድ ዘፈኖች ወይም ሙዚቃዎች በስተቀር (በነገራችን ላይ ሙዚቃ የሚለው ቃል አማርኛ አይደለም፡፡ ሙዚክ ወይም ሚዩዚክ የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል በአገርኛ ለዛ ሲጠራ ነው፡፡ ልክ አፍሪካ አፍሪቃ፣ ስኩል አስኳላ እንደተባለው ማለት ነው፡፡) እናም ከጥቂት ዘፈኖች በስተቀር የዘፈኖቻችን በአንድ ነጠላ ርእሰ ጉዳይ ማለትም ጾታዊ ፍቅር ላይ እንዲያተኩሩ መደረጉ ሥነ-ኪን ወይም በዘልማድ ኪነጥበብ ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት ልታበረክተው የምትችለው የማይተካ ሚና ሀገራችን እንዳታገኝ መሆኗ እንደ ዜጋ አሳስቦኝና የድርሻየን ለመወጣት በዜጎች ሰብአዊ ልማት ላይ ያተኮረ “ፋሽን” የተሰኘ አንድ ዘፈን ዜማና ግጥሙን ደርሼና እራሴው ተጫውቼ በመሣሪያ ታጅቦ ተቀናበረና ጥር 2004ዓ.ም. ለየነጋሪተወጉ (ለየሬዲዮው) “አቤት አቤት” አሁን ብዙ ሬዲዮ ጣቢያዎችና አማራጭ የብዙኃን መገናኛዎች ያሉን አላስመሰልኩም? ለየሬዲዮው ስል ያው ላሉት ማለትም አዲስ አበባ ለሚገኙት ማለቴ እንደሆነ ተረዱልኝ እናም ለእነሱና ለየሬዲዮ መዝናኛ ዝግጅቶች አዘጋጆች ካሉቱ ከሁለት ሦስቱ በስተቀር ለሁሉም እየዞርኩ አደልኩ፡፡ የዘፈኑን ግጥም ይዘት ወደኋላ የምገልፀው ይሆናል፡፡
እዚህ ላይ እላይ የጠቀስኩት ችግር ማለትም ሥነ-ኪናችን በፆታዊ ፍቅር ብቻ የማተኮሩ ችግር ለመከሰቱ ምንአልባት ምዕራባዊያኑ እንደ አርአያ ተወስደው ከሆነ እነርሱ በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ ቢያተኩሩ ምኞታቸውን ሁሉ አሳክተው ማለትም ሀገርን ከማበልጸግ አንፃር የቤት ሥራቸውን ሁሉ ጨርሰው ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ሥልጣኔ ያመጣባቸውን አጓጉል ልማዶች ከመከላከል አኳያም የሥነ-ኪንን ጠንካራና ፍቱን አቅም ሊጠቀሙባት እንደመቻላቸው ብዙ አልተጠቀሙበትም፡፡ እኔ ትክክለኛ በሆነ መንገድ ይሁን እንጂ ስለ ፆታዊ ፍቅር በመዘፈኑ ፣በመቀንቀኑ ፣በመተወኑ ወዘተ ወዘተ… በመደረጉ ችግር የለብኝም ፈጽሞ፡፡ ነገር ግን እንደ ሀገርና እንደ ሕዝብ እንደመኖራችን መጠን ከዚህ ማለትም ከፆታዊ ፍቅር ከሚገኝ እርካታና ጥቅም በላይ የሆኑ ዋጋ ያላቸው ስንትና ስንት ነገሮች እንዳሉ ማወቅ ይኖርብናል፡፡ ለምሳሌ በሥራ የሚገኝ እርካታ፣በሀገር መውደድ ላይ ያለ ኃያል ፍቅር፣ በማኅበራዊ ሕይዎት ስላሉ አንፀባራቂ ማኅበራዊ መስተጋብሮች፣ በኅብረተሰባዊና ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ አንዱ ለሌላው በሚሠራው መልካም ሥራ ያለ የመንፈስና የሕሊና እርካታ ወዘተ…፡፡ ነገር ግን አሁን እያየነው ካለነው አንጻር ፆታዊ ፍቅር ልክ የነገሮች ሁሉ መቋጫ መጨረሻ የስኬቶች ሁሉ ዳርቻ እንደሆነ አድርገን ሌት ተቀን ስለ እሱ ብቻ ብናስብ በእሱ ላይ ብቻ ብናተኩር ይህ ያለንን የአመለካከት አድማስ ጥበትና የብስለት እንጭጭነት የሚያሳይ ካልሆነ በቀር በምንም ተአምር የምሉዕ እና የበሳል ሰብእና መገለጫ ሊሆን አይችልም፡፡ እንደማኅበረሰብ እንዲህ ብለን እያሰብን ከሆነ የትም ልንደርስ እንደማንችል ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡ አይ አይደለም እንዲህ አናስብም የምትሉኝ ከሆነ ደግሞ በሏ የትኩረት አቅጣጫችንን እናስተካክል፡፡
ከዚያ እላቹህ ይህንን የሰጠኋቸውን ዘፈን በተመለከተ ከሬዲዮ (ከነጋሪተወግ) ጣቢያዎችና ከመዝናኛ ዝግጅት አዘጋጆች የገጠመኝ ምላሽ ግን ፈጽሞ በዚህ ደረጃ ይሆናል ብዬ ያልጠበኩትና አስደንጋጭም ሆነ፡፡ አንዳንድ የነጋሪተወግ የመዝናኛ ዝግጅት አዘጋጆች በዘፈኑና በመልዕክቱ እንደተደሰቱና እንደተገረሙ ገልጸውልኝ ዘፈኑን ወይም ሙዚቃውን ለመጋበዝ ሲሞክሩ ግን በየነጋሪተወግ ጣቢያዎች አሠራር ለአየር የሚቀርቡ ዘፈኖችን ለአየር ከመብቃታቸው በፊት በሚገመግሙ ኃላፊዎች ተከለከሉ፡፡ አንዳንዶቹ የዘፈኑን መልእክት ከግል ሰብእናቸው አንጻር ሲያዩት ግጭት የፈጠረባቸው ደግሞ ዘፈኑን አይመጥንም፣ መጋጨት ነው የፈለከው? ይሄ በጓዳ እንጂ በአደባባይ የሚሰማ አይደለም የመሳሰሉትን በማለት ስሜቴንም ጭምር ለመንካት ወይም ለመጉዳት ቅስሜንም ለመስበር የሚገርም ሙከራ አደረጉ፡፡ እኔም በትዕግስትና በትሕትና እሺ ጥሩ እኔም የምፈልገው የተሸለ ሥራ ለመሥራት ያስቸለኛልና እንዲህ ደካማ ጎኔን የሚነግረኝን ነው አስተያየታችሁን እባካችሁ? ምኑ ላይ ምን ይጨመርበት? ምኑ ይስተካከል? ብዬ ስጠይቃቸው ቀድሞም ቢሆን የሰጡት ምክንያት የሐሰት እና ከሌላ መንፈስ የመነጨ ነውና የሚመልሱልኝን አንዲት ቃል እንኳ አጥተው ቀንዱን እንደተመታ በሬ ዞር በማለት ይሸሻሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ስለሴቶች እና ስለ ሕፃናት መደፈር ስለ ትውልዱና ስለ ሀገር ፈተናዎች ዘፈኖቻችን ስላላቸው የጭብጥ ውስንነት ጭምር ሲያወሩ ስትሰሙ አፋቹህን ሊያስከፍቷቹህ ሁሉ ይችላሉ፡፡ የእውነት ልባቸው የተነካና የሚያዝኑ ተቆርቋሪና ኃላፊነት የሚሰማቸው ነው መስለው የሚታዩት፡፡ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ቀርቤ ሳያቸው ግን ሰብእናቸው የነገረኝ ይሄንን አልሆነም፡፡
ስለ ሥራ ጥራት ያወራሉ የሥራ ጥራት አያውቁም፣ ስለ ሞራል(ቅስም) ድንጋጌዎች ያወራሉ የቅስም ወይም የግብረገብ ድንጋጌዎችን ግን አያውቁም፣ ስለ ሀገር ያወራሉ ሀገርን ግን አያውቁም፣ ስለ ቅንነት ያወራሉ ቅን ግን አይደሉም፣ ስለ መደጋገፍ መተባበር ያወራሉ እነሱ ግን አደናቃፊ ናቸው ወዘተ. ያለመታከት ስልክ በመደወል በአካል ለማግኘትና ለማናገር ሞከርኩ አንዳቸውም እንኳ ሊጨበጡኝ አልቻሉም፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ዘፈኑ ምንም እንኳን ከተለመደው ውጪ በርከት ባሉ ስንኞች ጥርትና ግልጽ ባለ መልኩ ጠንካራ መልእክቱን ያስተላለፈ ቢሆንም የዘፈኑ መልእክት ምን እንደሆነ በቅጡ መረዳትና መገንዘብ የተሳናቸውና የረቀቀባቸው ወይም በክፉ የምቀኝነት መንፈስ የተመረዙ በመሆናቸው አሊያም ደግሞ ዓላማቸው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም ተፃራሪ በመሆኑና ሕዝብን የመበከል ሥውር የባንዳነት ዓላማ ስላላቸው በእነሱ አገላለጽ ዘፈኑን “ምንም እርባና የሌለው” ሲሉ አጣጣሉ፡፡ በርግጥ ዘፈኑ ምንም እንኳ ግጥሙ የአመክንዮ (የሎጂክ)፣ የማንነት (የአይደንቲቲ)፣ የኃላፊነት (የሪስፖንሲቢሊቲ)፣ የግብረገብ (የሞራል) ጥያቄዎችን በማንሣት የአደጋ ሥጋቱን ከሀገር ጥቅም ጋር በሚገባ አሰላስሎ የያዘ በመሆኑ የተዋጣለት ነው ለማለት እንደምደፍረው ሁሉ ዜማው እና የእኔም አዚያዚያም ቅንብሩም እንደዛው የግጥሙን ያህል የተዋጣለት ነው ለማለት አልደፍርም፡፡ አስተያየቱን ካገኘሁ በኋላ እንደተረዳሁት ከአቀናባሪው ማንነት አንፃር ይመስለኛል ዘፈኑ የሆነ የፕሮቴስታንቶችን(የተቃዋሚዎችን) መዝሙር የመምሰል ነገር አለው፡፡
ከዚህ ውጭ ግን እንደመጀመሪያ ሥራ ሲታይ ግን እንዲያውም ከብዙዎች ዘፈኖቻችን የማይተናነስ ነው፡፡በነገራችን ላይ ዘፈኑ ይሄን ያህልም እንኳ ተሠርቶ መውጣቱ እራሱ ለእኔ በጣም የሚደንቀኝና ይሄንንም አገኛለሁ የሚል እምነት አልነበረኝም ምክንያቱም አቀናባሪው ግማሽ ክፍያ ወስዶ ሥራ ከጀመርን በኋላ ምን እንደነካው ሳላውቅ ተለዋውጦብኝ የነበረን መልካም ግንኙነት በለየለት ግጭትና አለመግባባት የተሞላ ዛቻና ሽምግልና የተፈራረቁበት ስለነበረ ነው፡፡ በኋላ ላይ ግን በአንድ አጋጣሚ ልጁ ሳይፈልግ ከጀርባው ሆኖ ይሄንን እንዲያደርግ የሚያስገድደው አካል እንደነበረ ስለተረዳሁ እሱ ላይ የነበረኝን ቅሬታ ለመተው ተገደድኩ፡፡ ባጠቃላይ ያሳለፍኩት ፈተና ስሜቴን የጎዳ ሕሊናየን ያቆሰለ ነበር፡፡ ከእነዚህ ከእነዚህ ነገሮች አንፃር ነው ዘፈኑ ለእኔ አሁን ባለበት ሁኔታ በጣም ጥሩ ነው ለማለት የምደፍረው፡፡
አንዳንዶቹ የመዝናኛ ዝግጅት አዘጋጆች ደግሞ እነዚህኞቹን ግን በእውነት እንደ ላይኞቹ ሳይሸፍጡና ሳይቀጥፉ እውነቱን ስለነገሩኝ ሳላመሰግናቸው እና ሳላደንቃቸው አላልፍም፡፡ ለግልጽነታቸው በጣም አመሰግናለሁ፡፡ እናም እነኚህ ሰዎች ምን አሉኝ? ግማሾቹ ዘፈኑ ሴትን ስለሚገስጽ እንዲህ ዓይነቱን ዘፈን እንዳናስተላልፍ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ሕግ ይከለክለናል በተደጋጋሚም ደርሶብናል ሲሉ የተቀሩት ደግሞ አይ የእኛ አድማጮች ሴቶችና ሕፃናት ናቸው፡፡ ይሄንን ዘፈን ለቀን ወይም አጫውተን አድማጮችን ማስከፋትና ማጣት አንፈልግም በማለት ምክንያታቸው ምንም ይሁን በግልጽ ግን ሳይደብቁ ስለነገሩኝ በጣም አመሰግናቸዋለሁ፡፡
አንዱ ደፈር ያለ የመዝናኛ ዝግጅት አስተናጋጅ ደግሞ እነኝህን ሁሉ ማነቆዎች ጥሶ ዘፈኑን ሲለቀው ወይም ሲያጫውተው የዝግጅት ወይም የፕሮግራም ተቆጣጣሪዎቹ ዘፈኑን እንዲያቆመው ወይም እንዲያቋርጠው ካደረጉ በኋላ ስላስቆሙበት ምክንያት ሲናገሩ ምን ይላሉ? ይሄ ሙዚቃ በሴቶች ጉዳይ ያስከስሰናል እንኳን ይሄ ሴትን የሚገስጽ ዘፈን በአለፈው ጊዜ አንድ ሩጫውን አቋርጦ የወጣን ሯጭ ወይም አትሌት ቃለ-መጠይቅ በሚደረግለት ጊዜ ለምን አቋርጦ እንደወጣ ሲጠየቅ ሰዓቴን ሳየው በጣም ዘግይቼ ስለነበር በሴት ሰዓት ከምገባ ብዬ አቋርጬ ወጣሁ በማለቱ ብቻ የሴትን መብት ተጋፍቷል ወይም ተዳፍሯል ብለው ከሰውታል እና ይሄን ሙዚቃ ሁለተኛ ለመልቀቅ እንዳትሞክር በማለት ከማስጠንቀቂያ ጋር ማሳሰቢያ ተሰጠው፡፡
እንደተባለው የሴቶች ጉዳይ ይሄንን ጉዳይ ፈጽሞት ከሆነ እስከዛሬ በጣም ካስገረሙኝ እና ካሳቁኝ ነገሮች የመጀመሪያውን ደረጃ ሊይዝ ነው፡፡ ምክንያቱም ሴቶች በጉልበት ከወንዶች ያነሱ መሆናቸው መጣቃዊ (ሳይንሳዊ) ማረጋገጫ ያለው ጉዳይ እንደሆነና በግልጽም የምናየው የምናውቀው ነገር ሆኖ ሳለ ሯጩ ወይም አትሌቱ ይህንን እውነታ በመናገሩ በምን መለኪያና ሕግ ታይቶ እንደወንጀል እንደቆጠሩበት እስከመከሰስም እንዳደረሱት ጨርሶ ሊገባኝ ስላልቻለ እና በእርግጥ ይህ መ/ቤት ይህንን አድርጎት ከሆነ ይህንን ያደረጉት ሰዎች ምን እንደሚሠሩ ያውቃሉ ብዬ ለማመን እጅግ ስለምቸገር፡፡ ምክንያቱም ያለቻቸውን በጣም ውስን አቅም ያለቦታው ወይም ያለአግባብ አባክነዋልና፡፡
ስንት የተገፉና መብታቸው የተረገጠባቸው የተጣሰባቸው ሴቶች የሚሟገትላቸውና መብታቸውን የሚያስከብርላቸው አይዟችሁ አለንላችሁ የሚላቸው አጥተው የፍትሕ ያለህ የመብት ያለህ እያሉ መራራ እንባ በሚያነቡበት ዘመን አዛኝ ቅቤ አንጓች እንዲሉ በየትኛውም መመዘኛ ቢታይ ሐሰት ባልሆነ ነገርና ያሉት እውነታዎችም የሚያሳዩት ይሄንኑ በሆነበት ሁኔታ እንዴት ብለው ለክስ እንደተነሣሡ በጣም ግራ ስለሚገባኝም ነው፡፡ ይህ ስሕተታቸው በብዙኃን መገናኛ አካባቢ ምን ዓይነት አግባብ ያልሆነ ተጽዕኖ እንዳሳደረና አጥፊና አፈንጋጮችን በዘፈንም ይሁን በሌላ የሥነ-ኪን ሥራ መምከር፣ መገሰጽና ማስተማር እንዳይቻል እንዳደረገ የእኔና የእኔን ዘፈን የመሰሉ ሥራዎች ያጋጠሟቸው ችግር ምስክሮች ወይም ማስረጃዎች ናቸው፡፡
እኔ ዝግጅቴ ሰፋ ያለ ነበር እንደ ዜጋ በሚጠበቅብኝ ደረጃ ኅብረተሰቡን ከማገልገል አኳያ እንዲህ በአንድ ዘፈን እሰናከላለሁ የሚል ግምት በዚህ የፈተና ደረጃ አልጠበኩም ነበር፡፡ በብዙ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ምርጥ ምርጥ ዘፈኖችን ጽፌ (ደርሸ) ነበር፡፡ ብዙዎቹ እንዲያውም እግዚአብሔር ይመስገንና ከዚህ በፊት በማንም ሰው በዚህ ደረጃና ጥራት ተደርሰው በማያውቁበት ልዩነት የተጻፉ ነበሩ፡፡ እንደገናም ከዚህ ቀደም በማንም ተጽፎባቸው በማያውቁ ነገር ግን ጠቃሚና አስፈላጊ በሆኑ ርእሰ ጉዳዮች(ቁምነገሮች) ላይ የጻፍኳቸው ድንቅ ድንቅ ዘፈኖችም ነበሩኝ፡፡ ነገር ግን ሁኔታው እንዲህ ከሆነ በየት በኩል ተገናኝተን? አዝናለሁ ቀረባችሁ፡፡
እግረመንገዴን ማለት የምፈልገው እኔ በግሌ የሴቶች ጉዳይ ወይም የሴቶች እንደዚህ የሚባሉ ሥያሜዎች አይመቹኝም፡፡ ምክንያቱም ሴቶችን የሚያጠቁ ወይም የሚበድሉ ባሎች ወይም ጓደኞች ወይም ወንድሞችን ስናይ ሴቶቻቸውን የሚያጠቋቸው ሴት ስለሆኑ ወይም ወንድ ስላልሆኑ አይደለምና፡፡ ሴት ስለሆነች ወይም ወንድ ስላልሆነች ብቻ ጥቃት የሚያደርስ ሰው ካለ እስካሁን ሰምቼ አላውቅም ይኖራል ብዬም አልገምትም አለ ከተባለ ግን ይህ ሰው ጤነኛ ባለመሆኑና ይህ ለየት ያለ (Exceptional) በመሆኑ ጉዳዩ መታየት ያለበት በተለየ ሁኔታና ቦታ እንበል ለምሳሌ በአእምሮ ሕሙማን ማዕከላት ዓይነት ቦታ ነው፡፡
ጉዳዩ ወይም ችግሩ ግን ፈጽሞ የማኅበረሰቡ ተደርጎ መታየት የለበትም፡፡ ይህንን ካደረግን ግን ማኅበረሰቡን መስደብና ማዋረዳችን ነው፡፡ በደል የተፈጸመባቸውን ሴቶች የበደል ዓይነቶች ያየን እንደሆነ እነዚያ የተፈጸሙ በደሎች ሁሉም በተመሳሳይ ሁኔታ በወንዶችም ላይ የሚፈጸሙ ናቸው፡፡ በመሆኑም በደሉ የተፈጸመባት ሴት ያ በደል የተፈጸመባት ሴት በመሆኗ አይደለም ማለት ነው፡፡ ታዲያ ምንድነው? ያልን እንደሆነ በጉልበትና በመሳሰሉት ነገሮች በደል ከሚያደርሰው ሰው ያነሰች ስለሆነች ነዋ፡፡ በማነሷም በጉልበት ከእሱ ማነሷን ምቹ ሁኔታ አድርጎ ከእሷ የሚፈልገውን ነገር ለማግኘት ወይም ለመበዝበዝ እንጂ፡፡ ወንዶች ያላቸውን ጉልበት የሴቶች ሴቶች ያላቸውን የአቅም ውሱንነት ለወንዶች አድርገን ብናስበው ይህ አሁን በሴቶች ላይ እየተፈጸመ ያለው ችግር ሁሉ የሚታሰብ ባልሆነም ነበር ፡፡በመሆኑም ጉዳዩ የጉልበተኞች እና የአቅመ ውስኖች ጉዳይ እንጂ በፍጹም የጾታ ጉዳይ ወይም ሴት እና ወንድ የመሆን ጉዳይ አይደለም ማለት ነው፡፡ በወንዶችም ላይ የሚፈጸመው ይሄው ነውና፡፡ ጉልበተኛው አቅመ ቢሱን ወይም ደከም ያለውን ሲጎዳው ሲያጠቃው ሲበድለው ሲበዘብዘው እንደሚታየው ሁሉ ማለት ነው፡፡ ሕፃናት ወንዶች ለመግለጽ የሚቀፍ የጥቃት ሰለባ በሆኑበት ሁኔታ የጥቃት ዓይነቶችን በፆታ ወስነን እንዴት ነው የሴቶች እንደዚህ ልንል የምንችለው? ፆታ የለየ ጥቃት ከሌለስ እንዴት ነው ጥቃትንና ፆታን ልናያይዝ የምንችለው ?
በዚህም ምክንያት የሴቶች ምንትስ የሴቶች እንደዚህ አሁንም የሴቶች ቅብርጥስ የሚባሉ ነገሮች ሁሉ ችግሩንና ጉዳዩን በትክክል ማይት መግለጽ መወከል ካለመቻላቸው የተነሣ ሥያሜዎቹ ፈጽሞ አይመቹኝም፡፡ ይሄ እንዲያውም የፖለቲከኞች ቁማር ይመስለኛል፡፡ ማኅበረሰባቸውን በተገቢው መንገድ ማስተዳደር ሲያቅታቸው ወይም ከማኅበረሰቡ ለሚሰነዘሩ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ሲሳናቸው የማኅበረሰቡን ትኩረት ማስቀየሻ እና ከእነሱ ላይ ዞር ማድረጊያ ለዚያ ማኅበረሰብ እዚያው ባለበት የሚይዙላቸው ፆታን እና የመሳሰሉትን ርእሰ ጉዳዮች መሠረት ያደረጉ የተለያዩ የቤት ሥራዎችን ሆን ብለው ይፈጥራሉ፡፡ ይሄም እንግዲህ ከቤት ሥራዎቹ አንዱ መሆኑ ነው፡፡ ይህን ስል ግን ለተገፉ ወይም ለተጠቁ ሰዎች ጥብቅና አይቆም ይረሱ ይገለሉ ማለቴ እንዳልሆነ መረዳት የሚችል ጭንቅላት ያለው ሰው ሁሉ ይረዳኛል ብዬ እገምታለሁ፡፡
ነገር ግን ዓላማችን የተገፉትን ወይም የተጠቁትን ሰዎች መብት ማስከበር ወይም ማስጠበቅ ከሆነ አቅምን አይቶ ወይም ገምቶ በአቅም ውስንነት ምክንያት በተወሰኑ የማኅበረሰብ ክፍል ላይ ብቻ አትኩሮ መሥራት ካስፈለገ ወይም ግድ ካለ በተሳሳተ ሚዛን ጾታን መሠረት ባደረገ ሥያሜ በጅምላ የእንትን መብት በማለት ሳይሆን የተጠቂ ሴቶች ጉዳይ ወይም የግፉአን ማለትም የተገፉ ሴቶች መብት ተከራካሪ ወይም አስጠባቂ ቢባል ትክክለኛ ሥያሜ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም የማይጠቁና ያልተጠቁ ሴቶች አሉና፣ ያልተገፉና የማይገፉ ሴቶች አሉና፣የተከበሩ እና የሚከበሩ ሴቶች አሉና አብሶ ለእኛ ለሐበሾች ይሄ ሊነገረንና በዚህ ልንታማ ጨርሶ የሚገባ ጉዳይ አልነበረም፡፡ ከተሞከረም ድፍረት ነው፡፡ ማንም ነጭ ለእኛ ለሐበሾች አፍ አለኝ ብሎ እና ደፍሮ በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ ሐበሻን እንደ ሐበሻ ሊነቅፍ ወይም ሊኮንን የሚችልበት የሞራል (የግብረገብ) ብቃትና ነፃነት ከቶውንም አይኖረው፡፡ በታሪኩ የሴት መሪ አይቶ ወይም አግኝቶ ወይም አብቅቶ የማያውቅ ድኩም ኅብረተሰብ ከቀዳማዊት ሳባ (ከዛሬ 4380-4370 ለ10 ዓመታት የነገሠች) ጀምሮ እስከ ዘውዲቱ ከ ሃያ በላይ ገናና ብልህ አስተዋይ ብቁ ሴቶችን ያፈራንና ያበቃን ሕዝብ እና ሀገር ሊነቅፍ ሊመክር ሊኮንን ሊተች የሚችልበት ኧረ በየትኛው ሒሳብ ይሆን? እንደ አለመታደል ሆኖ በዚህ ዘመን ካለን ሐበሾች ጥቂት የማንባለው አፈር ያብላንና ለነገሩ በልተናል ከዚህ በላይ አፈር መብላት የት አለና፡፡
እናም ክብራችንን ዋጋችንን(ቫሊዩአችንን) ባለማወቅ የዚያ ችግር ባለቤት ወይም ተጠቂ የሆኑ የበርካታ ምዕራባዊያን ሀገሮች ጩኸት ሴቶችን ለመሪነት ማብቃት አይደለም ለሴቶች እንደ ሰው የሰውነት መብት ከሰጡ እንኳን ከአንድ የእድሜ ባለጸጋ አረጋዊ እድሜ የማያልፉትን፣ የሴቶችን ሰብአዊ መብቶች በተጻፉ ሕጎቻቸው ሳይቀር በይፋ የደፈለቁትን ኅብረተሰቦች ወይም ሀገሮች ጩኸት የሴቶችና የወንዶች የሚል ልዩነት ሳታደርግ እስከ የመጨረሻው የሥልጣን ደረጃ አብቅታ ባረጋገጠች ሀገር፣ ሴት ልጅ ክብሯን ለመጠበቅ ካልሆነ በቀር ጾታዋን እንደበደል በመቁጠር ምንም ዓይነት ገደብ አድርጎ በማያውቅ ኅብረተሰብና ሀገር ኢትዮጵያ ውስጥ በእኛው በሐበሾች አፍ ስንጮኸው ጉዳዩ ምን ያህል አሳዛኝና ልብ የሚሠብር እንደሆነና በዚህ ዘመን ያለነውን ሐበሾች ያለንበትን የሞራል (የንቃተ ወኔ) ዝለት፣ ኪሳራና ዝቅጠት የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡ ምንአልባት አንዳንድ የሚመስሉና የሚታዩ ነገሮች ካሉ ወይም ቢኖሩ እነኚህ የድህነት ገጽታችን የፈጠራቸው ሳንኮች የድሀነታችን መገለጫዎች እንጂ በፍጹም እንደ ሐበሻ የባሕላችን አካል ወይም የአስተሳሰባችን ደረጃ ሆነው አይደለም፡፡ አስተዋይ ልቡና ያለው ማንኛውም ሰው ይህንን በሚገባ ይረዳል፡፡
ለማንኛውም ወደ ቀደመው ነገራችን እንመለስ እና እንግዲህ የጻፍኩት ዘፈን መልእክቱ ለማኅበረሰቡ ሳይደርስ መቅረቱ እጅግ ቢያሳዝነኝ ለጊዜው በፍኖተ እናንት /YouTube/ እና በፌስ ቡክ /በመጽሐፈ ገጽ/ ድረ ገጾች ላይ በመጫን በYouTube (Fashion Amsalu Gebrekidan) በfaceBook ደግሞ Amsalug1 ብሎ በመግባት ዘፈኑን ማድመጥ እና መመልከት እንዲቻል አደረኩ ዘፈኑ ትዕይንተ ኩነት (video) ስላልተሠራለት ምሥለ አካል (ፎቶ) ለመለጠፍ ተገድጃለሁ፡፡ የዘፈኑ ግጥምም የሚከተለውን ይመስላል
ፋሽን (ዘመንኛ)
Tadias guys listen up please?
This music called fashion
Dedicated to you all
Come on.
ፋሽን የውበት ፍካት፣ገብቶ ከተዘራ
በጣም ተዘንግቷል፤ ትምህርትእና ሥራ
እራፊ ጣል አርገው፤የመዘዋወር ጣጣ
ጆሮ የማይችለውን፤ ጉድ ጎትቶ አመጣ
አንችን መንገድ ላይ አይቶ፤ የጦዘ ስሜት
ሄዶ የሚበርደው፤ ከጮርቃ ሕፃናት
ለጥቃት ተጋላጭ፤ ሆነው ከሚኖሩት
ክፉ ይመጣል ብለው፤ ከማይጠረጥሩት
አንችንማ ከየት፤አግኝቶ ያጠቃሻል
ያየሽ ከአደባባይ፣ ከብዙ ሰው መሀል
ለዚያች ምስኪን ሕፃን፤ ለገዛ እኅትሽ ብለሽ
አደብ ሥርዓት ያዥ፤ እኅቴ እባክሽ
ክቡር እራቁትሽን፤ የማየት መብት ያለው
በአካላትሽ ውበት፣ ደስታ የሚገባው
አንዱ ያንቺው ብቻ አንጂ፤ ለምን ማንም ሰው ይይ
ይሄ እማ ከሆነ፤ዘማ አልሆንሽም ወይ
አቤት የውበት ዓይነት፤ የቆንጆው መብዛት
እንዴት ጥሩ ነበር፤ ባይሆን ለጥፋት
በፋሽን ፉክክር፤ ለማማር በቦዲ
ሚሚንም አስበላት ፤ በእነ ሹገር ዳዲ
የአጭር ጊዜ ምቾት፤ የዕለት ተድላ ደስታ
ለአንቺ ሕይወት ማለት፣ ይሔ ነው እፎይታ
የሕይወት ትርጉሟ፤ እኅቴ ጠፍቶሻል
ሳሩን ብቻ ስታይ፤ ገደሉ ይውጥሻል
የራስሽን ይዘሽ፤ ፍቅርም አለን ካልሽ
ከአንተ ሌላ አልሻም፤ ብለሽ ቃል ከገባሽ
ምን ለመሆን ነው ታዲያ፤ መዞር በእራቁት
ሌላን ለመማረክ፤ ካልሆነ ለመወስለት
በዚህስ ሁኔታሽ፤ በዚህ አለባበስሽ
ሚስት ትሁነኝ ብሎ፤ ማነው የሚመርጥሽ
እንዳሻሽ እንድትሆኝ፤ ግድ ቢልሽም ስሜት
ቀይደሽ እሰሪው፤ በግብረገብ ሥርዓት
ስሜትማ እንዲያዝሽ፤ ወዳሻው እንዲጋልብሽ
ሥልጣን ከሰጠሽው፤ ካነገስሽው ፈቅደሽ
እንደሰከረ ሰው፤ ብዙ ጠጥቶ አረቂ
ምን እንዳረግሽ አታውቂም፤ በርዶልሽ ስትነቂ
እኅቴ አንችም ሰው ነሽ፤ ምን ያቅትሽና
ሠርተሽ ተለወጪ እንጂ፤ተጋትረሽ ፈተና
ሸቀጥ አይደለሽም፤ የሌለሽ ሰብእና
ተገምተሽ ተገዥ፤ በመልክ በቁመና
ከምንም ምን በላይ፤ ከወንድም ትከሻ
ሀገር ትጠብቃለች፤ እኅቴ ያንችን ድርሻ
ጠብቀሽ አክብረሽ፤ እምነት ባሕልሽን
ሠርተሸ አደራ ተወጭ፤ የዜግነትሽን
ጀግናን የምትፈጥሪው፤ ሆነሽ የወኔ ስንቅ
ጉልበቱ እኮ አንችው ነሽ፤ ስኬት ላገኘም ሊቅ
የአንች እጅ ሳይገባበት፤ ምን ግቡን ሲመታ
ሀገር የምትሞተው፤ አንችን ያጣች ለታ
e…h… what do you think?
You know that is the serious problem
It is really looks like a pornography
So we have to do what we should have to do
bye-bye.
(amsalugkidan@gmail.com)
Leave a Reply